የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የዘርፉን የገበያ ልማት፣ፕሮሞሽንና ልማት ስራዎች በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመስራት እንዲያስችልም “የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን” ተቋቁሟል። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ዘርፉን ለማነቃቃት ልዩ ልዩ ስራዎች ተግባሮችን እያከናወነ ይገኛል።
ቢሮው በቅርቡ የዓለም የቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ “ምስራቅ ሐረርጌን የቱሪስት መዳረሻ እናደርጋለን” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ አካላትን ያካተተ የጉብኝት መርሀ ግብር አካሂዷል። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን መነሻ አድርጎ በክልሉ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ እየተሰሩ ባሉ ስራዎችና በመጡ ለውጦች እንዲሁም በሌሎች ተያየዥ ጉዳዮች ላይ ከቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፦ ወደ ምስራቅ ሐረርጌ ጉዞ አድርጋችሁ ነበር። የጉዞው ዋንኛ አላማ እና ግብ ምን ነበር?
አቶ ሁንዴ፦ እንደሚታወቀው የዓለም የቱሪዝም ቀን በየዓመቱ የዓለም የቱሪዝም ድርጅት በሚያወጣው መሪ ሃሳብ መሰረት ይከበራል። አገራችንም የድርጅቱ አባል እንደመሆኗ መጠን በተመሳሳይ መንገድ ይከበራል። እንደ አገር በመስከረም ወር ላይ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ቀኑ ተከብሯል። ከዚያ ወዲህም ክልሎች በየራሳቸው ቀኑን እያከበሩት ይገኛሉ።
እንደ ኦሮሚያም በክልል ከማክበራችን በፊት በሁሉም የከተማ መስተዳደሮችና በሁሉም ዞኖች ቀኑ ተከብሯል። በክልል ደረጃ ደግሞ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በሐረር ከተማ እንደዚሁም ደግሞ ሁለት ትልልቅ የቱሪዝም መዳረሻ የሚገኝባቸው ወረዳዎችን በመምረጥ አክብረናል።
የመጀመሪያው ባቢሌ አካባቢ ሲሆን፣ ይህ አካባቢ የኢትዮጵያ ዝሆኖች መጠለያ የሚገኝበት ትልቅ ወረዳ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እድሜ ጠገብ የሆኑ የቱሪዝም ሃብቶችንም እንዲጎበኙ ሆነዋል። ሁለተኛውን በሃሮማያ ወረዳ ላይ ነው ያከበርነው። በዚህም ደርቆ የነበረው የሃሮማያ ሃይቅ ከ18 ዓመታት በኋላ ዳግም ተመልሶ ይገኛል። ይህንን የቱሪዝም ሃብት ከመጠበቅ ከመንከባከብ አንፃር የተሰሩ ስራዎችን ተመልክተናል። እንደ አጠቃላይ ደግሞ በሐረር ከተማ ደግሞ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። መድረኩ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በተለይ ደግሞ ምስራቅ ሐረርጌን መዳረሻ ለማድረግ ምክክር ተደርጓል።
ዋናው ዓላማችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቱሪዝም ዘርፉ በመንግስት የተሰጠው ልዩ ትኩረት መሬት ላይ መውረድ አለበት የሚል ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ሰፊው ማህበረሰብ ጋር መድረስ አለበት። እኛም ይህንን በዓል ምክንያት በማድረግ ከሰፊው የማህበረሰባችን ክፍል ጋር የቱሪዝም ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ ነው። በዋናነትም የመዳረሻ ስፍራዎችን በመንከባከብ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ረገድ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲደርስ አጋጣሚውን ተጠቅመን የግንዛቤ ስራ ለመፍጠር እየሰራን ነው። በዚህ አጋጣሚም በቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ ያሉ ተዋናዮችን ይዘን ሄደናል። አገራችን ውስጥ ያሉ ቱር ኦፕሬተሮች፣ ከ15 በላይ የሚሆኑ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች አካላትም ተሳትፈውበታል።
አዲስ ዘመን፦ በምስራቅ ሐረርጌ ውስጥ የሚገኘው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ስጋት የተጋረጠበት እንደሆነ ይነገራል፤ ይህን ከመፍታት አንፃር ምን ያህል ርቀት ሄዳችኋል?
አቶ ሁንዴ፦ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር እኛ የክልሉን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ነው የምንመራው። በዋናነት የምንሰራውም የማስተዋወቅ ስራ ነው። ለምሳሌ ፓርኮችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ነው። እንደ ባህልና ቱሪዝም የምናስተዳድራቸው መዳረሻዎች ውስን ናቸው። ለምሳሌ እንደነ ሶፉመር ዋሻ አይነት ይኖራሉ። ከተፈጥሮ አንፃር የኛ ተፅእኖ ፈጣሪነት በእጅጉ ውስን ነው። እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በጋራ ተባብረን እየሰራን እንገኛለን። ከባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ጋር ተያይዞ ያነሳህው ጥያቄ ትክክል ነው። በጥብቅ ስፍራው ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲደርሱ እየተመለከትን ነው። ይህ ደግሞ ለዱር እንስሳቱ የመጥፋት ስጋት ደቅኗል።
የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በሶማሌ ክልላዊ መንግስት እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መካከል ይገኛል። ስለዚህ ጥብቅ ስፍራውን የመንከባከብና ለቱሪዝም መዳረሻነት የሚያገለግለውን ይህን አካባቢ በዘላቂነት እንዲጠበቅ የማድረጉ ስራ በጋራ ሊሰራ የሚገባና የሁለቱም ክልሎች ኃላፊነት ነው። በጉዳዩ ላይ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። ከኦሮሚያ ክልል አንፃር እዛ አካባቢ ያሉ ሰፋሪዎችን እስከማንሳት የደረሰ እርምጃ ሲወሰድ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም። አንደኛ እዚያ አካባቢ ባለው ማህበረሰብ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎችን ሰፋ አድርገን መስራት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን። ይህ ጥብቅ ስፍራ ሲኖር ማህበረሰቡ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆን መገንዘብ አለበት። የተፈጥሮ ሃብትንና ሰውን ለያይቶ ማየት አይቻልም። ሰው ከተፈጥሮ ሃብት ጋር ብዙ ፍላጎቶች ስላሉት በዚያ አካባቢ የመኖርና ከዚያ የመጠቀም አዝማሚያ አለው። ስለዚህ ይህን ትስስር ሙሉ ለሙሉ መገደብ አይቻልም። የቱሪዝም መስህብ የሆኑ ስፍራዎች ሳይጎዱ ከህብረተሰቡ ጋር የሚተሳሰሩበትን መንገድ መፈለግ ላይ መሰራት አለበት። ከዚህ አንፃር በርካታ ነገሮች ይጠበቃሉ። በባቢሌ ብቻ ሳይሆን በክልላችን የሚገኙ ሌሎች ፓርኮችም ላይ መሰል ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ እቅድ አውጥቶ መስራት ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ። እኛም እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ከባህልና ቱሪዝም የሚጠበቀውን ስራ ለመስራት ዝግጁ ነን። ከዚህ በፊትም እዛ አካባቢ ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገናል። ከሁሉም በላይ ግን ከመንግስት ብቻ መጠበቅ ሳይሆን ተፈጥሮን መንከባከብና በውስጡ የሚገኙ ሃብቶች እንዳይጠፉ የማድረግ አቅም ያለው ማህበረሰቡ በእኔነት መንፈስ ሃብቱን መጠበቅ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ የሃሮማያ ሃይቅ ለ18 ዓመት ከጠፋ በኋላ ዳግም ተመልሷል። ይህ ችግር መልሶ እንዳያጋጥም ሃብቱም የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሁንዴ፦ ይሄ የተፈጥሮ ሃብት ለበርካታ ዓመታት ጠፍቶ መቆየቱ ይታወቃል። የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ ባልሆንም ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተል እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ሃብቱ ጠፍቶ የነበረው ተፈጥሮውን መንከባከብ ስላልቻልን እንደሆነ አስባለሁ። አሁን ግን በተሰራው ስራና የእግዚአብሔር ርዳታ ተጨምሮበት ሃብቱ ሊመለስ ችሏል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የደረቀውን ሃይቅ ለመመለስ ልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውነዋል። የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ እና የወረዳው ማህበረሰብና የተለያዩ አካላት ሃብቱን ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በቀጣይነትም ውሃው እንዲበዛና ዳግም ችግሩ እንዳይከሰት የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ መሰራት እንዳለበት አምናለሁ።
ውሃው በመመለሱ በጥቂት አመታት ውስጥ የአካባቢው ማህበረሰቦች የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ጀልባ ሲያንቀሳቅሱ፣ አሳ ሲያጠምዱና መሰል የቱሪዝምና ሌሎች ስራዎችን ሲያከናውኑ መመልከት ችለናል። በዚህ ምክንያት ስፍራው ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ እየሆነ ነው። ይሁን እንጂ እንቅስቃሴ እየበዛበት በመጣ ቁጥር ሃይቁ ላይ ተፅእኖ እንዳይኖር ዘዴዎችን ተጠቅሞ መስራት ተገቢ ነው። የክልላችን ባህልና ቱሪዝም ቢሮም እንደ አንድ ባለድርሻ አካልና ተጠቃሚ ይህንን የሚከታተል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ከማስተዋወቅ፣ የገበያ ስራ ከመስራት እንዲሁም የመዳረሻ ስፍራዎችን ከመለየት አኳያ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ሁንዴ፦ የመጀመሪያው ስራ መሆን የሚገባው በክልላችን የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን መለየት ነው። ምን አይነት ሃብቶች እንዳሉ በተገቢው መንገድ መለየትና ማጥናት ያስፈልጋል። ይህን ማወቅ ካልተቻለ የማስተዋወቅ፣ የሽያጭና እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን በአግባቡ ማቀድና መስራት አይቻልም።
እንደ ኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአራትና አምስት ዓመታት በፊት በቀጣይ አስር ዓመታት “ከየት ተነስተን የት እንደርሳለን” የሚል እቅድ ሰርቷል።ይህንንም በድጋሚ ከልሰናል። በዚህ እቅድ ላይ በየትኛው አካባቢ ምን አይነት የቱሪዝም ሃብት እንዳለ ተለይቷል። በተለይ ከባህል፣ ከተፈጥሮ ቅርሶችና መሰል ሃብቶች አንፃር ያሉ ሃብቶች በሚገባ ማወቅ ተችሏል። ይሄ ለኛ ትልቅ አጋጣሚ ነው። ይህንን ተመርኩዘን የት ቦታ ምን መስራትና እንዴት የቱሪዝም ገበያን መፍጠር እንዳለብን አውቀናል። ለምሳሌ ቢሾፍቱና አዳማ ከተማን ብንወስድ “ለማይስ ቱሪዝም” የተመቹ ናቸው። በዚህ አካባቢ ከተፈጥሮ ቱሪዝም ይልቅ ወደ ማይስ ቱሪዝም እናተኩራለን። ሌሎች አካባቢው እንዳላቸው ሃብትና አቅም ልክ የተለያዩ ስልቶችን እንከተላለን።
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በዘርፉ ምን የተለዩ ስራዎችን አከናወናችሁ ምን ውጤቶችን አስመዘገባችሁ?
አቶ ሁንዴ፦ እንደ ኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ትላልቅ ኃላፊነቶችን ወስደን ዘርፉን ለማነቃቃት እና ውጤት ለማምጣት ሰርተናል። ለምሳሌ የክልሉን የቱሪዝም ኮሚሽን ያቋቋምነው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ በመሆኑ ሃብቶችን በመለየት፣ ከማስተዋወቅና ገበያ ከማፈላለግ አንፃር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። እንደ አገርም በነዚህ ዓመታት አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶች እየተሰሩ ተጨማሪ የዘርፉ ሃብቶች እየሆኑ ነው። በዚህ ላይም እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ተሳታፊ በመሆን እንሰራልን። እንደ ክልልም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ እየሰራን እንገኛለን። ለእዚህም በሪፍትቫሊና ወንጪ አካባቢ ያሉ ስራዎችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀምና ስራዎችን የተቀላጠፈ ከማድረግ እንዲሁም ከዲጂታል ቱሪዝም አንፃር ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሁንዴ፦ ቱሪዝምና ቴክኖሎጂ ተለያይተው የሚታዩ ዘርፎ አይደሉም። አሁን ባለንበት ደረጃ ለቱሪዝሙ የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ስራዎች መስራት ይገባል። ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በስካይ ላይት ሆቴል የቴክኖሎጂ ሳምንት በማዘጋጀት ለዘርፉ የሚጠቅሙ በርካታ የቴክኖሎጂ ተሞክሮዎችን አሳይቶናል። በዚህም አበረታችና ጠቃሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማየት ችለናል። ይህ ደግሞ የቱሪዝሙን ኢንዱስትሪ እንደሚደግፍ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ከዚህም በላይ መስራት ይጠበቅብናል። በተለይ ዘርፉን መደገፍ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ አካላትን ማበረታታትና መደገፍ ይኖርብናል። ጅማሮው ጥሩ ይሁን እንጂ በቂ የሚባልበት ደረጃ ላይ ግን እንዳልሆንን አምናለሁ።
አንዱ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያለ ችግር የመረጃ ነው። በተለይ የቱሪስት ፍሰትን፣ የቱሪዝም ገቢንና ሌሎች መሰል መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ከዚህ አንፃር የቱሪዝም ዘርፉን የመረጃ አያያዝና መሰል ጉዳዮችን የሚደግፉ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ስራ ይጠበቅብናል። ከዚህ ባሻገር ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂዎች ማላመድና እኩል መራመድም ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ ካልቻልን ዘርፉን በሚጠበቀው ልክ ማሳደግ እንደማንችል መገንዘብ ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፦ ለቱሪዝም እድገት ሰላም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በክልሉ ይህን ከማስጠበቅና ምቹ መደላድል ከመፍጠር አኳያ ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ሁንዴ፦ ትክክል ነው። ሰላም ለቱሪዝም ዘርፍ እጅግ ጠቃሚና ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይሄ ለድርድርም ሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ ነገር አይደለም። ቱሪስት ወደ መስህብ ስፍራዎችና መዳረሻ ቦታዎች የሚመጣው ሰላም ሲኖር ነው። ይህ ከሌለ የቱሪዝም እድገትንም ሆነ ስለ ቱሪዝም ፍሰት መጨመር ማንሳት አንችልም።
ከዚህ አንፃር በሰሜኑ ክፍል የነበረው ጦርነት በኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ ማየት ይቻላል። የሰሜኑ ጦርነት በአገር ገፅታ ላይ ካሳደረው ተፅእኖ ባሻገር በክልላችን ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ የሽብር ቡድን አለ። ይህም በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች መንቀሳቀስን አስቸጋሪ የሚያደርግበት ሁኔታ ሲፈጠር ቆይቷል። በተለይ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች በመሄድ ለመጎብኘት አስቸጋሪ ሆኗል።
የሰላም ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ይህንን ማስተካከል ካልቻልን በወደፊት የቱሪዝም ስራዎቻችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል። ከዚህ አንፃር እንደ ክልላችን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፀጥታው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። እውነቱን ለመናገር ይሄ ከአገራዊ ጉዳይ ጋርም በቀጥታ ይገናኛል። ክልላችንም ይህንን ቡድን ለማጥፋት የማያደርገው ጥረት የለም። ከዚህ አንፃር ሰላማችንን የሚያውኩ ለእድገትና ልማት እንቅፋት የሆኑና የቱሪዝም ዘርፉ እንዲቀዛቀዝ የሚያደርጉ ሽብርተኛ ቡድኖች እንደሚወገዱ ምንም ጥርጥር የለኝም። ይህንን ተከትሎም የቱሪዝም ዘርፉ ወደ ቀድሞው ቦታው እንደሚመለስ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር እናመሰግናለን።
አቶ ሁንዴ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም