የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ቻምፒዮና አገር ሴኔጋል በኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫም 16ውስጥ የገባች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር በመሆን በእግር ኳስ ታሪኳ ወርቃማ ጊዜ እያሳለፈች ትገኛለች። ባለፉት ሃያ አመታት በተለያዩ ጊዜዎች በዓለም እግር ኳስ ብቅ እያለች የተለያዩ ኮከቦችንና ታሪኮችን ማሳየት የቻለችው ሴኔጋል የአፍሪካ ኩራት ስለመሆኗ ጥርጥር የለውም። በእነዚህ አመታት የቴራንጋ አንበሶች የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥም መዘንጋት የሌለበት አንድ ሰው ጎልቶ ይታያል። የአሁኑ የቴራንጋ አንበሶች መሪ አሰልጣኙ አሊው ሲሴ ሴኔጋል ብቻም ሳትሆን አፍሪካ በእግር ኳስ ታሪኳ ልዩ ቦታ የምትሰጠው ታሪካዊ ሰው ነው።
የሴኔጋልን ብሔራዊ ቡድን እኤአ ከ2015 ጀምሮ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው የ46 አመቱ ሰው ሲሴ የቴራንጋ አንበሶች በዓለም ዋንጫ ዓለምን ሲያነጋግሩ የቡድኑ አምበል ነበር። የቴራንጋ አንበሶችን መምራት ከጀመረ ወዲህም 2019 እና 2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ተፋላሚ አድርጎ ያለፈውን አፍሪካ ዋንጫ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነሳ ቁልፉ ሰው በመሆን ህያው ታሪክ ሰርቷል።
“ዝምተኛው አንበሳ” የሚል ስያሜን የደረበው ሲሴ የቴራንጋ አንበሶች ኩራት ነው። አሊዩ ሲሴ ሁሌም አገሩ በፈለገችው ጊዜ ከፊት የሚገኝ፣ በተጨዋችነትም በአሠልጣኝነትም ሌሎች ጎልተው እንዲወጡና አገሩ ደምቃ እንድትታይ በዝምታ ውስጥ ቁልፍ ሚናን የሚወጣ በጨለማ የሚያበራ ጥቁር አልማዝ ነው።
ሲሴ በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ምንም እንኳን የቡድኑ ኮከብ ሳዲዮ ማኔን በጉዳት አጥቶ ሁለት ጨዋታ በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለ የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡድንን በማሠልጠን ታሪክ ሠርቷል። የሴኔጋል ምልክት የሆነው አልዩ ሲሴ የቴራንጋ አንበሦች ብቻ ሣይሆን ለአፍሪካ አሠልጣኞችም ኩራት ሆኗል።
በአፍሪካ እግር ኳስ ገናና ስም ካላቸው አገራት መካከል ሴኔጋል አንዷ እንድትሆን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል። የቴራንጋ አንበሶቹ በተለይም ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ባፈሯቸው አስደናቂ ከዋክብት ተጫዋቾች በዓለም እግር ኳስ ላይ ጎልተው ሲጠሩና ሴኔጋልም በፊፋ የአገራት ወራዊ የእግር ኳስ ደረጃ በተለያየ ጊዜ የጎላ ለውጥ አምጥታ በትልቁ አህጉራዊ ውድድር ግን ጣፋጩን ድል አንዴም መጎንጨት አልቻለችም ነበር። የሚያሳዝነው የቴራንጋ አንበሶች እኤአ በ2002 የኮሪያና ጃፓን የዓለም ዋንጫ ጭምር ቅኝ ገዣቸው ፈረንሳይን ሳይቀር አሸንፈው እስከ ሩብ ፍጻሜ በነበራቸው አስደናቂ ጉዞ ወርቃማው የእግር ኳስ ትውልዳቸው የአፍሪካ ዋንጫን ለመሳም አለመታደሉ ነው።
በተለይም የቴራንጋ አንበሶች በ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ወርቃማው የእግር ኳስ ትውልዳቸው ለፍጻሜ ደርሶ ዋንጫውን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳም ተቃርበው በመጨረሻ ድሉን በካሜሩን ተነጥቀው እንባቸውን ያፈሰሱበት አጋጣሚ የሚዘነጋ አይደለም። ከዚያም በኋላ የቴራንጋ አንበሶች በአህጉሪቱ ታላቅ የእግር ኳስ መድረክ የሚታወሱበትን ድል ለማግኘት ብዙ ጠብቀዋል።
የያኔው የቴራንጋ አንበሶች ወርቃማ ትውልድ ከስሞ ሌላ አዲስ ወርቃማ ትውልድ ለመተካት ግን ሴኔጋል ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም ማለት ይቻላል። በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ተጽኗቸው የጎላ ከዋክብትን ማፍራት የቻለችው ሴኔጋል ሁሌም ወደምትጓጓለት የአፍሪካ ዋንጫ ድል በእጅጉ ለመቅረብ አልተሳናትም። በ2019 የአፍሪካ ዋንጫም ለፍጻሜ ቀርባ አዲሱ የቴራንጋ አንበሶች የከዋክብት ስብስብ በአልጄሪያ አንድ ለምንም ተረቶ ዳግም አንብቷል። ይህም የቴራንጋ አንበሶችን ሁለት የወርቃማ ዘመን የእግር ኳስ ትውልድ በአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ቀርቦ ዋንጫ የማንሳት እርግማን እንዳለበት በተጫዋቾቹም ጭምር እንዲታመን እስከማድረግ ደርሶ ነበር።
እኤአ 2002 ላይ የቴራንጋ አንበሶቹ ለፍጻሜ ደርሰው ዋንጫውን በካሜሩን ሲነጠቁ ተጫዋች የነበረው አሊው ሲሴ የሴኔጋል አሰልጣኝ በመሆን ይህን ታሪክ ሽሯል።
በተጫዋችነት ዘመኑ ለአገሩ ሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ለዓለም ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ መድረስ የቻለው የቡድኑ አሰልጣኝ አሊዩ ሲሴ ዋንጫውን ካነሰ ከቡድኑ ጋር ስሙ በወርቅ ጽፏል። ይህም ሲሴ “ጠንክረህና ጸንተህ ከሠራህ የምትፈልገውን እንደምታገኝ ያሳያል” ሲሉ በርካቶች ምሳሌ አድርገው እንዲጠቅሱት አድርጓቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም