ሰውና አመሉን አስባችሁት ታውቃላችሁ? አመል በድንቅ ተፈጥሯችን መሀል ሰርጎ የገባ ሰውኛ ነውር ነው ። የእለት ተእለት ኑሯችንን የሚያውክ፣ በእኛው የተፈጠረ ሰው ሰራሽ እንከን ነው ። ሰው የፈጣሪ የመጨረሻው ድንቅ ተፈጥሮ ነው ። ከሰው ያማረ፣ ከሰው የሰመረ ድንቅ ነገር ዓለም የላትም ። ተፈጥሮ እንከን አልባ ነው ። ሙሉ ሆነን ነው ወደዚህ ዓለም የመጣነው ።
ግን እግራችንን በገዛ እጃችን የምናውክ ነን ። የምናየውና የምንሰማው ነገር ካለን የተሻለ እየመሰለን በውብ ተፈጥሯችን ላይ ሌላ የማይጠቅም ነገር እናክላለን። ቀና እየመሰለን ባልተገባ መንገድ ላይ የቆምን ብዙዎች ነን። ከእኛ የተሻለ ሌላ ተፈጥሮ ያለ እየመሰለን ተፈጥሯችንን በአርቴፊሻል ነገር እያበላሸን ነን ።
አብዛኛው መከራችን ተፈጥሮን ከመቃወም የሚመነጭ ነው ። አጠገባችን ካለ ነገር የተሻለ ሌላ ነገር ያለ የሚመስለን ብዙዎች ነን ። አጠገቡ ያለን ነገር ማየት ያልቻለ በምንም ምክንያት ሩቅ ያለን ውብ እድል ማየት አይችልም ። ከፍታዎቻችን ሁሉ በቅርባችን የሚገኙ ናቸው ።
አብዛኞቻችን አጠገባችንን ትተን ሩቅ የምናይ ነን። ዛሬን ረስተን ነገን የምንናፍቅ ነን ። ከእኛ ውድ ነገር ይልቅ የሌሎች ርካሽ ነገር የሚያስቀናንም ነን ። ተፈጥሮ በእያንዳንዳችን ውስጥ እውነትና ሚዛናዊ ሆና ናት ። ከዚህ እውነት ስንወጣ ነው ለነውርና ለአልተገባ ሰውኛ አመሎች የምንጋለጠው ። ከዚህ እውነት ስንርቅ ነው ለሞትና ለጉስቁልና ለመከራም የምንበቃው ። አምላክ በውስጣችን ያስቀመጠውን ዘለዓለማዊ እውነት ብናውቅ ኖሮ በዚህ ልክ ራሳችንን ተበላሽተን አናገኘውም ነበር እላለሁ ።
አንድ ሴት ለአንድ ወንድ፣ አንድ ወንድ ለአንድ ሴት ተብለን ታዘን ደስታችንን ግን ከብዙ ርቃን ውስጥ የምንፈልግ ነን ። አትስረቅ፣ አታመንዝር፣ በሀሰት አትመስክር ተብለን ታዘን የምንሰርቅ የምናመነዝርና በሀሰት የምንመሰክር ነን ። ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ ተብለን ታዘን እኛ ግን በጥላቻና በመገፋፋት የቆምን ነን ።
ፍቅር የህግ ፍጻሜ ነው፣ የሚምሩ ይማራሉ፣ “ልበ ንጹሃን እግዚአብሔርን ያዩታል” ተብሎ ተነግሮን እኛ ግን ከዚህ በተቃራኒ የቆምን ነውረኞች ነን ። የዛሬ አመሎቻችን ከዚህ የተወለዱ ናቸው ። የዛሬ ሞታችን የዛሬ አንበሳችን ከዚህ እውነት መራቃችን የፈጠራቸው ናቸው ።
አመሎቻችንን መግደል አለብን ። አመሎቻችን ይዘውን የሚጠፉ የሀጢአት ውጤቶቻችን ናቸው ። አመሎቻችን ነገን እንዳናይ የሚያደርጉን ወጥመዶቻችን ናቸው ። አመሎቻችን አጥፊዎቻችን ናቸው ። በዚህ ዘመን ላይ በተፈጥሮው ኮርቶ ከነውር ርቆ እንደተፈጠረ የሚኖር እርሱ አዋቂ ነው ።
ራስን እንደመግዛት ራስን እንደመቆጣጠር ምን እውቀት ምን ማስተዋልስ አለ? ከአመል የጸዳ ሰውነት ያስፈልገናል ። ከጉጂ ልማዶች የራቀ ማህበራዊ ሕይወት ግድ ይለናል ። በህሊናችን እንገዛ እንጂ በልማዶቻችን አንገዛ ። አሁን ላይ ብዙዎቻችን የሚያስብ አእምሮ እያለን በሚገርም ሁኔታ ለልማዶቻችን እጅ ሰጥተን ባሪያ ሆነን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው ።
ለምንም ነገር ስሜቶቻችንን የምናስቀድም ነን። ለምንም ነገር አሳማኝ ምክንያት የሌለን ነው ። በአእምሯችን የበላይነት ስሜቶቻችንን ብንገድል አሁን ከሆነው በላይ የብዙ በረከቶች ባለቤት እንሆን ነበር ። ከልማዶቻችን በላይ ምክንያታዊ እሳቤን የእኛ ብናደርግ አሁን ከሆነው በላይ ሌላ እንሆን ነበር ።
ከእውነት በላይ የሆነ አንድ ነገር ታውቃላችሁ? ከታሪክም ከቁስም የላቀ..ከሁለንተናዊው ዓለም የተለቀ አንድ ነገር ምን ታውቃላችሁ? ከአእምሮ በላይ፣ ከስልጣኔ በላይ፣ ካለፈው ከሚመጣውም የማይወዳደር ድንቅ እውነት ታውቃላችሁ? አያችሁ አታውቁም..እኔም አላውቅም ያ ነው ሰውነት..ያ ነው ሰው መሆን ።
ያ ነን እኛ ። አመል ይሄን ታላቅና ድንቅ እውነታችንን የሚያጠይም የሰው ልጅ ጉድፍ ነው ። አመል ሳናውቃቸው በምናደርጋቸው ነገሮች የሚመጣ የድግግሞሽ ውጤት ነው ። በትላንትና በዛሬ ውስጥ አልፎ ሌላ ስምና ባህሪን የሚያላብሰን ክፉ አባዜ ነው ። ልማድ ጎልቶ ሲወጣ የአንድ ሰው ጠቅላላ መገለጫው ሊሆን ይችላል ። አንዳንድ ሰዎችን አታውቁም ስም እያላቸው በሰዎች ዘንድ በሚታወቁበት ክፉ ልማድ ሲጠሩ? እኔ ግን አውቃለሁ ። አመል ስር ከሰደደ እጅግ አደገኛ ነው ።
አባቶች ሲተርቱ “ከሰይጣን አመልን ፍራ” ይላሉ። ሰይጣን በግዝት ይሸሻል ። አመል ግን በስመ አብ ብለነው ገዝተነውም የሚተወን አይደለም ። ልማድ በጊዜ ካልተቆጣጠርነው አጠቃላይ ታሪካችንን የሚያበላሽ አውዳሚ መሳሪያ ነው ። እንተወው ብንል እንኳን የማይቻለን የነገ አበሳ ነው ። በውስጣችን ሆኖ ህልማችንን የሚበላ ነጋችንን የሚያጨልም ሰይጣናዊ ሀይልም ነው ።
ይሄን ሀይል በጊዜ መዋጋት ይኖርብናል ። “ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚባለው መጥፎ ልማድም ወደ ሕይወታችሁ የሚገባው እንደቀልድ ነው ። አብዛኞቹን ሱሰኞች እንዴት ለሱስ እንደተጋለጡ ብትጠይቋቸው የሚያስቅ መልስ ነው የሚሰጧችሁ ። በቃ እንደቀልድ ሳላስበው ነው የጀመርኩት.. ጓደኞቼን አይቼ..እስኪ ልሞክረው ብዬ… ሲሉ ቀላል የሚመስል ነገር ግን አደገኛ መልስ ነው የሚሰጧችሁ ።
ሁሉም አደገኛ ነገር መጀመሪያ ላይ ቀላል የሚመስል ነው ። ራሳችሁንን መቆጣጠር ካልቻልን የምንበላሽባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ ። አእምሯችንን ከስሜቶቻችን በላይ ማጠንከር ካልቻልን እጅ የምንሰጥባቸው በርካታ አጉል ነውሮች ይፈጠሩብናል ። እንደ ማህበራዊ ሕይወታችን ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን ከታላላቆቻችን የምንወስዳቸው ብዙ አዎንታዊና አሉታዊ ልማዶች ይኖራሉ ።
ከእኛ የሚጠበቀው ጥሩዎቹን እየወሰድን መጥፎዎቹን እየጣልን ወደፊት መሄድ ነው ። እንደዚሁም ደግሞ እኛው የፈጠርናቸው ብዙ አመሎችም ይኖሩናል ። ሳናውቀውና ሳናስበው እንደ ቀልድ ሞክረናቸው ላይወጡ ወደ ሕይወታችን የገቡ ማለት ነው ።
ከቀላል ጉዳት ሕይወት እስከማጥፋት የሚደርስ ሀይል ያላቸው አንዳንድ አመሎች እንዳሉ ታውቃላችሁ? ትዳር የሚያፈርሱ፣ ታሪክ የሚያበላሹ፣ ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያላሉ ግላዊ ልማዶች ስለመኖራቸው ስንቶቻችሁ ታውቁ ይሆን? የመጠጥና የሲጋራ ሱሶች ሕይወት ሲቀጥፉ አላያችሁም? ጠጥተው በማሽከርከር ሕይወት ያጠፉ፣ ንብረት ያወደሙ ሀላፊነት የጎደላቸውን ሰዎች አታውቁም?።
ስር በሰደደ የገንዘብ ፍቅር ጉቦ ሲሰጡና ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው የታሰሩ እንዳሉስ አታውቁም? ልክ በሌለው ሴሰኝነት በሚስቶቻቸውና በባሎቻቸው ላይ ሲማግጡ ሕይወታቸውን በበሽታ ያጡ የሉም? ትዳራቸው የፈረሰባቸውን አታውቁም? ሲሰርቁ ተይዘው የታሰሩ፣ ሲዋሹ ተይዘው ከስራቸውና ከማህበራዊ ሕይወታቸው የተገለሉ እንዳሉስ አታውቁም ? እኔ ግን ብዙ አውቃለሁ ።
እንዳውም በየሚዲያው ላይ የዜና አርዕስት ሆነው በየቀኑ የምሰማቸው እኚህን ግለሰቦች ከነመጥፎ አመላቸውና ከነመጥፎ ፍጻሜአቸው ጋር ነው ። በዚያው ልክ ደግሞ ከመጥፎ አመሎቻቸው ጋር ተስማምተው በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ሳያደርሱ የሚኖሩም አሉ ። እንደተፈጠረ በንጽህና የሚኖር ማንም የለም ። ሁላችንም ከመጥፎ አመሎቻችን ጋር የምንኖር ድውይ መጻጉ ነን ።
ዓለም ራሱ ውጥንቅጧ የወጣው ከተፈጥሮ በወጡ ድውያን ነው ። ጉዳት አልባ የሚመስሉን ትንንሽ ልማዶች እንኳን በሕይወታችን ላይ የሆነ ቦታ ላይ ይጎዱናል ። አልተው ያለኝን የኔን አመል ብነግራችሁ እንኳን እጄን መላስ እወዳለሁ ። ምግብ በልቼ ከመታጠቤ በፊት እጄን የማጸዳው በምላሴ ነው ። በልቼ የጠገብኩ የሚመስለኝ እጄን ስልስ ነው ። እጄን ካላስኩ የረካሁ አይመስለኝም። ምግቡን እጣቴ ላይ ሳየው ያሳዝነኛል ። እጄን ሳልስ ከታጠብኩ ጡር የሰራሁ ይመስለኛል ። ታዲያ ይሄ መጥፎ አመል አይደለም ትላላችሁ?
አመል በሰውነት ላይ የበቀለ እንከን ነው ። ከትላንት እስከዛሬ የሰው ልጅ ከአመል ተለይቶ አያውቅም ። ሁላችንም ከነጉድፋችን ወጥተን የምንገባ ነን ። ቤት ውስጥ ከቤት ውጪ የምንሆናቸውና የምናሳያቸው ባህሪዎቻችን መገለጫችን ሆነው አብረውን ይኖራሉ ። ለምሳሌ ታክሲ ውስጥ ሲገባ ጭቅጭቅ የሚያምረው፣ መልስ አልሰጠህኝም በሚል የባጥ የቆጡን የሚቀባጥር፣ መውረጃዬን አሳለፍከኝ በሚል የሚራገም ብዙ ነው ።
ከአንደበታችን መልካም ቃል እንዳይወጣ የተገዘትን ይመስል ታክሲ ውስጥ ስንገባ አመላችንም የሚቀየር ጥቂቶች አይደለንም ። ትንሽ ነገር እየፈለግን የምንሳደብ፣ የምንነታረክ ሞልተናል ። በዚህ ተማረው ይመስለኛ የታክሲ ሾፌሮች “የቤቶን አመል እዛው” ሲሉ ጥቅስ የሚለጥፉት ።
ሰሞኑን ታክሲ ውስጥ ምን አየሁ መሰላችሁ አንድ ትልቅ ሰውዬ ናቸው አጠገባቸው የተቀመጠውን ወጣት የመማታት ያክል እየነኩ ያወሩታል ። ወጣቱ በጨዋታ መሀል የሚደልቀውን የሽማግሌውን እጅ እየተከላከለ በዝምታና በትዝብት ያዳምጣቸዋል ። ከወሬያቸው ይልቅ ሁኔታቸው እንዳስገረመው ያስታውቅበት ነበር ። ተዉ እንዳይላቸው ትልቅ ሰው ሆኑበት..እየተደለቀ ዝም ።
ድንገት ወራጅ አለ ሲሉ ሰማሁ..እንደማይተዋወቁ ያረጋገጥኩት መሀል ላይ ደህና ዋል ብለውት ሲወርዱ ነበር ። ያኔ እኔ ብቻ አልነበርኩም ረዳቱን ጨምሮ የታክሲው ግማሽ ተሳፋሪ ተገርሞ ነበር ። «አትተዋወቁም ማለት ነው?» ስል በተገረመ ፊት ወጣቱን ጠየኩት ።
ከግርምት ያላባራ ፊቱን ወደፊቴ መልሶ ‹አዎ ሲል መለሰልኝ ። ላያቸው እኮ አባትና ልጅ ነው የሚመስሉት። ላያቸው እኮ ለረጅም አመታት የሚተዋወቁ ባልንጀሮች ነበር የሚመስሉት ። በልቤ ስንት አይነት ሰው አለ እያልኩ እየተገረምኩ ከታክሲ ወርጄ ወደ ጉዳዬ ሄድኩ ። አቤት የሰው ልጅ አመል..መኖር ስንቱን ያሳየናል ።
አንድ ጓደኛ አለኝ እየሄደ፣ እየተማረ በማንኛውም ቦታና ሁኔታ ላይ ጸጉሩን የሚቆነድድ ። ሲበላ እንኳን እጁ ከጭንቅላቱ ላይ አይወርድም ። በአንድ እጁ እንጀራ እየቆረሰ በአንድ እጁ ጸጉሩን የሚያፍተለትል ነው ። ግራ እጁ ስራ ፈቶ አያውቅም ። አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ መመረቂያ ጽሁፍ ሊያቀርብ መምህራኖቹ ፊት ቆሞ ገለጻ ሲያደርግ አንድ እጁ አናቱ ላይ ነበር ። እስኪ አስቡት የመጨረሻ ቀን ነው፣ ለመመረቅ ያቺ ቀን የመጨረሻው ናት ። ሱፍ ለብሶ ከረቫት አድርጎ ጥሩ የሚባል ጫማ ተጫምቶ አንድ እጁ ብላክ ቦርድ ላይ አንድ እጁ ደግሞ አናቱ ላይ ።
መቁጠር አልቻልኩም እንጂ ለጆሮ የሚሰለቹ እጅህን ከራስክ ላይ አውርድ የሚሉ ብዙ የቁጣ ድምጾችን ከመምህራኖቹ ሰምቼ ነበር ። አመል አይደል! እሺ ባለ በማግስቱ እጁን ራሱ ላይ ያገኘዋል ። ወዲያው ቁጣ.. ወዲያው እሺ..እጁ ግን ከአናቱ ላይ መሸሽ አልቻለም ከተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ በኋላ ራሱን አስተካክሎ ጽሁፉን በድጋሚ እንዲያቀርብ ለሳምንት አዞሩበት። በመጨረሻ ምን ሆነ መሰላችሁ..እኛ ስንመረቅ እሱ የመመረቂያ ጽሁፉን ያቀርብ ነበር ። አመል ክፉ ነው ። አመላችን ሳይቀይረን አሁኑኑ አመላችንን እንቀይር ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 25/ 2015 ዓ.ም