ጠዋት ከእንቅልፉ ተነስቶ ፊቱን መታጠብን እንደ ትልቅ ውሳኔ ቆጥሮ የሚቸገር ሰው አጋጥሟችሁ አያውቅም? ይቅርታ ጉዳዬን በጥያቄ ጀመርኩ እኔን እንደዚህ ለውሳኔ የሚቸገር ሰው ስለሚያበሳጨኝ ነው። ውሳኔ የሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አካል መሆኑን አምናለሁ።
በእርግጥ አንዳንዶች በየዕለቱ የሚከናወኑ ድርጊቶች ልማዳዊ ተግባሮች እንጂ ውሳኔዎች ሊባሉ አይገባም ይላሉ። ነገር ግን በልማዳዊ ድርጊት ውስጥ ውሳኔ አለ። እናም ሰዎች በፍጥነት አስበው በጥበብ ሊወስኑ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በእርግጥ እኔም ብሆን በተለይ ትልልቅ ጉዳዮች በደንብ ጊዜ ተወስዶ ታስበውባቸው ውሳኔ ሊያገኙ እንደሚገባ እምነቴ ነው። ነገር ግን ማሰብ በሚል ሰበብ መጎተት እና አሰልቺ የሆነ መወላወል በጣም ያስቀይማል፤ ያስቀይማል ብቻ አይደለም እንደውም ያስጠላል። ይህን ለማለት ያስገደደኝ ሰሞኑን ያስተዋልኩት አንድ ጉዳይ ነው።
ሰዎቹ ዘመዶቼ ናቸው። ለመጋባት እንደአገራችን ባህል ሽማግሌ ልከው እጮኛሞች መሆናቸው ከታወቀ ሁለት ዓመት ተቆጠረ። ሆኖም አልተጋቡም፤ አብረው እየኖሩም አይደለም። በዚህኛው ዓመት በኅዳር እንጋባለን ብለው ብዙም ሳይቆዩ የሠርጉን ቀን ወደ ጥር፣ ሲሉ ወደ ሚያዝያ እያሉ ሁለት ዓመት አለፈ። ብዙዎቻችን በተለይ ቀረብ ያልነው ዘመዶች ግራ ተጋብተን ነበር።
ራቅ ያሉ እና ሽምግልናውን የሰሙ ሰዎች ደግሞ ጭራሽ ሠርጉ የተሰረዘ መስሏቸዋል። ጉዳዩ ሚስት ስትስማማ ባል ለመወሰን ሲቸገር፤ ባል ሲስማማ ደግሞ ሚስት ለመወሰን ስትቸገር እንደቀልድ ዓመታት ተቆጠሩ ይኸው ሦስተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። በዘንድሮ ሚያዝያ ካልተጋቡ እኛም ጉድ ለማለት ተዘጋጅተናል። ነገሩን እስከማውቀው ድረስ ችግራቸው መወሰን አለመቻል ነው።
የሴቷ ወገን ነኝ እና ለመወሰን ለምን እንደተቸገሩ ጠየቅኳት፤ ሁለቱም መሰረግ ፈልገዋል ፍላጎታቸው ደግሞ ድንቅ የተባለለትን የሠርግ ሥነሥርዓት ማካሄድ ነው። ነገር ግን አቅም ገድቧቸዋል። ጊዜው በገፋ ቁጥር ደግሞ የሚያስፈልገው ወጪ ከመቶ እጥፍ በላይ እየጨመረ ጭራሽ መጠነኛ እና አስደሳች ሠርግ ለመደገስ እንኳ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ስለዚህ አሁንም አልሰረጉም፤ አልተጋቡም፤ አቦ! አቅምን አይቶ እንደሁኔታው መወሰንማ ወሳኝ ጉዳይ
ነው፤ ወደ ኋላ መሸሽም ከሆነ ወስኖ ማቆም ሲቻል ልብላ አልብላ፤ ልልበስ ይቅርብኝ፤ ልነሳ ልቀመጥ፤ ልጠይቅ ይቅርብኝ እያሉ ማመንታት ኧረ እንደውም ማመንታት አይደለም መወላወል እና ማወላዳት አስቀያሚ ነገር ነው።
ሕፃናት ተወልደው የእናታቸውን ጡት ከመጥባት ጀምረው ከመተኛት ወደ መቀመጥ ደረጃ ይደርሳሉ፤ ቀስ በቀስ ተለማምደው እየተንደረደሩ መራመድ ይችላሉ። በደንብ መራመድ የሚችሉት አቅም ስላላቸው ብቻ ሳይሆን ለመራመድ ስለወሰኑም ጭምር ነው። ውሳኔያቸው በሕይወታቸው ውስጥ የሚያመጣው ለውጥ ትልቅ ይሆናል። ከሰው እቅፍ ወጥተው በራሳቸው የፈለጉትን ያነሳሉ፤ የፈለጉትን ይነካሉ። ትልልቅ ሰዎችም የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በሕይወታቸው ላይ ትልልቅ ለውጦችን ያመጣሉ። ሆኖም ውሳኔ በጥበብ ሊሆን ይገባል።
አንድ ሰው የሦስት ልጆች አባት ነው። ሥራው ብዙም የማያስጨንቀው ሲሆን፤ በጊዜ ወደ ቤቱ በመግባት ልጆቹን ያስጠናል ይንከባከባል። ቅዳሜ እና እሁድ ልጆቹን ያዝናናል፤ በሚፈልገው መንገድ ልጆቹ እንዲያድጉለት ምክር ይሰጣል፤ ዘመዶቹንም ይጠይቃል። አንድ ቀን ሥራውን ለመቀየር ፈልጎ ወደ አንድ ተቋም አመለከተ። ለሥራው ተወዳድሮ አለፈ። ደመወዙ ከፍተኛ ልዩነት ያለው በመሆኑ የቤተሰቡ ገቢ መጨመር ሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አስቦ እጅግ ተደስቷል።
ሆኖም ሥራው እንደቀደመው በጊዜ ወደ ቤት የሚያስብል እና ቅዳሜና እሁድን እረፍት የሚሰጥ አልነበረም። ሰውዬው ገቢውን ማግኘት እጅግ በጣም ፈልጓል፤ ከዘመዶቹ በተለይም ከልጆቹ ጋር ያለው ግንኙነት እንዳይቀንስበት ተጨንቋል። አስቦ አሰላስሎ የእርሱ ክትትል እና ድጋፍ ልጆቹ ላይ የሚያመጣውን ውጤት ግምት ውስጥ አስገብቶ የልጆቹን የወደፊት ሕይወት ተስፋ አድርጎ አዲሱን ሥራ ለመተው ወሰነ። ውሳኔው ጊዜያዊ ውስን ገንዘብ ከማግኘት ይልቅ የልጆቹን የነገ ማንነት የመገንባት ጉዳይ ዋነኛ መሆንን መሠረት ያደረገ ነበር።
በእርግጥም ነገን እና የተሻለውን አስቦ በጥበብ መወሰን ይገባል። እናም በተለይ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች፣ ባለሞያዎች እና አገልግሎት ሰጪዎች ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ሥራዎቻቸውን አስበው በአግባቡ ውሳኔ ሊሰጡበት ሲገባ፤ ይዋል ይደር እያሉ ለውሳኔ ማመንታታቸው የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ወሳኝ መሆን ይገባል እንላለን ደህና ሰንብቱ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በምህረት ሞገስ