ክትባት አካል እራሱን ከበሽታ መከላከል እንዲችልና የበሽታ የመከላከል አቅሙ እንዲ ጨምር የቫይረስ፣ ባክቴሪያ እና ፕሮቶዞኣ ህዋሶችን፣ በሽታ አምጭ ህዋሳቸውን በሽታ እንዳይፈጥሩ ወይም በሽታ እንዳያስተላልፉ ከተገደሉ ወይም ከተዳከሙ በኋላ ከተለያዩ ኬሚካሎች ጋር ተዋህዶ የሰውነትን የመከላከል አቅም እንዲጨምር የሚያደርጉ ውህዶች ናቸው፡፡ በጥሩ የክትባት ዘዴዎችና ግኝቶች የሰው ፈንጣጣና የቀንድ ከብቶች የደስታ በሽታን ከእዚህ ዓለም ማጥፋት ተችሏል። እንዲሁም በዓለማችን በተለያዩ ጊዜና ቦታ የተከሰቱ አያሌ ወረርሽኞችና በሽታዎችን በክትባት መቆጣጠር ተችሏል።
በአገራችንም መልቲሶዳ በሚባል ባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ የፎውል ኮሌራ (Fowl cholera) የዶሮ በሽታ ክትባትና በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ኢንፌክሽየስ በርሳል (Infectious Bursal Disease) የሚባል የዶሮ በሽታ ክትባትን አዲስና ዘመናዊ በሆነ መንገድ በአካባቢ በቀላሉ የሚገኙ የቫይረስና የባክቴሪያ ህዋሶችን በማዳከምና በማላመድ በአገር ውስጥ ክትባቱን ማልማትና ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል።
እነዚህ ክትባቶችም በዶክተር ሞላልኝ ቢተው ዋና ተመራማሪነት (Principal Investigator) የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን (Ethiopian Biotechnology Institute) በመወከልና ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት (National veterinary Institute) የሚሰሩ ሌሎች ተመራማሪዎችን በመጨመር፤ ከድሮው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአሁኑ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተገኘ የ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲካሄድ የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰና የፕሮ ጀክቱ አገራዊ ፋይዳው ምን እንደሚመስል ጥናቱን በበላይነት ከሚያከናውኑት በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የጤና ባዮቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ከዶክተር ሞላልኝ ቢተው ጋር ቆይታ አድርገናል።
ክትባቶቹን በአገር ውስጥ ለማምረት የመነሻ መንስኤዎች
ምንም እንኳን የፎውል ኮሌራ የዶሮ በሽታ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የዶሮ እርባታ ቦታዎች የሚገኙ የዶሮ ዝርያዎችን የሚያጠቃ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ክትባቱ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ካለመሆኑም ባሻገር
በአገር ውስጥም እየተመረተ አልነበረም፡፡ በሽታው በብዙ ዶሮዎች ላይ ባይስተዋልም የአመጋገብ ሥርዓታቸው ሲዛባና እንክብካቤ ባነሳቸው ወቅት ቫይረሱ አጋጣሚውን በመጠቀም ዶሮዎችን ከ70 እስከ 80 በመቶ ለበሽታ የሚያጋልጥና እስከ 50 በመቶ ለሞት የሚዳርግ ነው።
የኢንፌክሽየስ በርሳል የዶሮ በሽታ በሀገራችን ውስጥ ያልነበረ ቫይረስ ሲሆን፤ የዶሮ ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ ሲሄድ ከአውሮፓ ወደ አገራችን እንደገባ ይነገራል። ቫይረሱም በአገራችን ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ዶሮዎችን ለሞት የሚዳርግ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜ ከሦስት ሳምንት እስከ አራት ሳምንት ዕድሜ ውስጥ ያሉ ጫጩቶችን የሚያጠቃ በመሆኑ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ቫይረሱም ከፍተኛ የሆነ ስርጭት ያለው ሲሆን፤ ዶሮዎችን ከ70 እስከ 80 በመቶ ለህመም የሚያገልጥና 50 በመቶ ለሞት የሚዳርግ ነው። የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ በመሆኑ በተካሄደው ጥናት በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እስከ 90 በመቶ ድረስ በበሽታው የተጠቁ ዶሮዎች ተገኝተዋል።
በአጠቃላይ እነዚህ የዶሮ በሽታዎች የዶሮዎችን ምርትና ምርታማነት የሚቀንስና የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳጡ በመሆኑ ኅብረተሰቡን ለችግር እያጋለጠ ዶሮዎችን ለሞት እየዳረገ ይገኛል። ይሄን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ጀምሮ በእነዚህ በሽታዎች ላይ የተለያዩ ሙከራዎችንና ጥናትና ምርምሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
ኢንስቲትዩቱም ጥናትና ምርምር በማድረግ ለበሽታዎቹ እልባት ለመስጠት የተለያዩ ክትባቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡ ነገር ግን የአመራረት ሂደቱ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሲሆን፤ የሚገኘው ምርትም ከፍላጎቱ ጋር የማይጣጣም እና የአመራረት መንገዱም ውድ ነው፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱን ለማሳደግና ክትባቱን ለማምረት ከበካይ ተዋህሲያን ነፃ የሆነ እንቁላል (Specific Pathogen free egg) ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሬ የሚገዛ ሆኖ የመዳበር ሁኔታውም እስከ 40 በመቶ የወረደ ነው፡፡ ማለትም አንድ ከበካይ ተዋህሲያን ነፃ የሆነ እንቁላል በ17 ዶላር ተገዝቶ በአገር ውስጥ ሲዳብር ከመቶ እንቁላል ውስጥ አርባው ብቻነው ዳበሮ ለክትባት የሚውለው።
ከውጭ የሚገባው ከበካይ ተዋህሲያን ነፃ የሆነ እንቁላል ውድና ክትባቱን ለማምረት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፤ በቀላል መንገድ ቫይረሱን ወደ ካንሰርነት የተቀየሩ ህዋሳትን (Vero cells) በማላመድና በማባዛት ወጪና ጊዜን በቆጠበ መልኩ በብዛትና በጥራት በማምረት ክትባቱን በተፈለገው መጠን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ እንዲያስችል የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከብሔራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እነዚህን ክትባቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት ተችሏል።
የፎውል ኮሌራ ባክቴሪያ ክትባት
የበሽታው ምልክት ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተመሳሳይ እና ዝርያው ብዙ ዓይነት በመሆኑ በአገር ደረጃ ብዙ ጊዜ በሽታውን የመለየት ችግር ነበር። በመሆኑም ክትባቱ በሌላው ዓለም የነበረ ቢሆንም በአገሪቱ ግን ያልነበረ በመሆኑ፤ በአለፉት 12 ዓመታት በመላ አገሪቱ ጥናትና ምርምር በማድረግ የትኛው የፎውል ኮሌራ ባክቴሪያ ዓይነት ነው የሚለውን ለመለየት ተችሏል። በአገሪቱ ያለው የቫይረስ ዝርያ «ኤ ዋን» የተባለው የቫይረስ ዝርያ መሆኑ ታውቆ ለቫይረሱም ፍቱን ክትባት በሀገር ውስጥ ለማዘጋጀት ተችሏል።
ነገር ግን ክትባቱ ተሰርቶ በሦስት በተለያዩ የዶሮ እርባታ ቦታዎች ላይ ባሉ ዶሮዎች ላይ ሲሞከር የነበርው ምላሽ የተለያየ ነበር። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሲሰራ የነበረው ማቀዝቀዣ (ፍሪጂ) ላይ የቆየውን ባክቴሪያ ለዶሮዎች በሚሰጥበት ወቅት ባክቴሪያው ትኩስ ስለማይሆን ዶሮዎችን አይገላቸውም ነበር። በዚህም ባክቴሪያው ከእንስሳት ወደ እንስሳት መተላለፍ ካልቻለ ዶሮዎችን መግደል እንደማይችል የተረጋገጠ ሲሆን፤ ይሄን ችግር ለመፍታት ባክቴሪያውን በቤተ ሙከራ ዶሮዎች ላይ በማሳለፍ ከቤተሙከራ ዶሮዎቹ በቀጥታ በመውሰድ ክትባት ተደርጎ ለሌሎች ዶሮዎች መሰጠት አለበት በማለት ትልቅ ግኝት ማግኘት ተችሏል።
ስለዚህ ቫይረሱን ከማቀዝቀዣ (ከፍሪጅ) በቀጥታ ተወስዶ ተግባራዊ ቢደረግ በፍጥነት በሽታ ስለማይፈጥርና የማዳን አቅሙ ጠንካራ ስለማይሆን ክትባቱ የማዳን አቅሙና በሽታ የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ እንዲሆን በቀጥታ በቤተሙከራ እንስሳት አልፎ እንዲሰጥ ተደርጓል። በአጠቃላይ ክትባቱን ከሀገር ውስጥ ከተሰበሰቡ ፓስቹሬላ መልቶሲዳ (Pasteurella multocida) የተባሉ ባክቴሪያዎችን በመጠቀም የፎውል ኮሌራ ባክቴሪያ ክትባትን ማምረት ተችሏል። ክትባቱንም በቤተሙከራ እንስሳት እና በግለሰቦች የእንስሳት እርባታ ጣቢያዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል፡ ፡ ክትባቱ ለፓን አፍሪካ የክትባት ቁጥጥር ማዕከል (PANVAC) ተልኮ ውጤታማነቱን በማረጋገጥ ለገበያ መቅረብ የሚችል መሆኑን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት የተገኘ በመሆኑ፤ ክትባቱ ለገበያ ቀርቦ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እየሆነ ይገኛል፡፡
የኢንፌክሽየስ በርሳል ቫይረስ ክትባት
የኢንፌክሽየስ በርሳል ቫይረስ ክትባት ከአሁን በፊት በሀገር ውስጥ ክትባቱ የነበረ ቢሆንም፤ በሽታው በሚከሰትበት ቦታ ሲረጋገጥ ክትባቱ የማዳን አቅሙ ዝቅ ያለ ነው። ስለዚህ ችግሩን በመለየት በአገሪቱ ያሉ የዶሮ ዝርያን መሠረት በማድረግ፤ ከአሁን በፊት ክትባቱ ሲመረትበት ከነበረው ጥሬ ዕቃ የተለየ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም በሽታውን የማዳን አቅሙ አስተማማኝ የሆነ ክትባት በአገር ውስጥ ተሰርቶ ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነው።
ከአሁን በፊት ይሄን ክትባት በአገር ውስጥ ለማምረት ከበካይ ተዋህስያን ነፃ የሆነ እንቁላል (Specific Pathogen free egg) ከጀርመን ሀገር አንዷን እንቁላል በ17 ዶላር ዋጋ የሚገዛ ሲሆን፤ እንቁላሉን በመፈልፈያ ማሽን ሲዳብር ከ100 እንቁላል ውስጥ 40 በመቶው ብቻ ነው ውጤታማ ሆኖ የተፈለፈለው። ስለዚህ ይህን ክትባት በአገር ውስጥ ለማምረት የምንጠቀምበት ሂደት በጣም አዋጭ ያልሆነ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ችግር የሚያጋልጥ፣ እረጅም ጊዜ የሚወስድ እና ለብክነት የሚያጋልጥ መንገድ ነበር። በመሆኑም ይሄን መንገድ በመተው የኢንፌክሽየስ በርሳል በሽታ አምጪ ቫይረስን በካንሰር ህዋስ ላይ በማላመድ በአዲስ መልክ በአገር ውስጥ ክትባቱን መስራት ተችሏል።
እነዚህ የካንሰር ህዋስን ለማበልጸግ ግብአት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች በእርካሽ ዋጋ በሀገር ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጪን ቆጥቦ ፍቱን የሆነ ክትባት ለማምረትና ለማባዛት የሚያስችል ሳይንሳዊ የክትባት ዘዴ ነው።
ይህን ክትባት ለመስራት መነሻ የሆነው አንድ የፓኪስታን የምርምር ወረቀት ሲሆን፤ ክትባቱን በመስራት በሰውና በእንስሳት ላይ የጎንዮሽ ችግሮችን እንዳያስከትል ቫይረሱ የተዳከመ መሆኑንና አለመሆኑን በቤተሙከራ እንስሳት ላይ በመሞከር ሌሎች ተያያዥ ሙከራዎች እየተካሄዱ ይገኛል።ይህ ሂደት እንዳለቀ ክትባቱን በጥራትና በብዛት ለገበያ በማቅረብ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይሆናል።
ክትባቶቹ ለአገር ኢኮኖሚ ያላቸው ጠቀሜታ
የክትባት ሳይንስ የተጀመረው የዛሬ 200 ዓመት ገደማ በሊዊስ ፓስተር አማካኝነት በፓስተር ኢንስቲትዩት ሲሆን በዓለማችን የተከሰቱ አያሌ በሽታዎችን ክትባትን በመጠቀም ምድርን ምድረበዳ ከማድረጋቸው በፊት መቆጣጠር ተችሏል።
በአገራችንም የእንስሳት ክትባት ከተጀመረ 60 ዓመታትን አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት በሙሉ ብዙ የእንስሳት በሽታዎችን መከላከል ተችሏል። አንዳንዶቹን በሽታዎች ከአገራችን ያጠፋንባቸው ሁኔታዎች አለ። ለአብነት የከብቶች ደስታ በሽታ ከሀገራችን በመጥፋቱ ማህበረሰቡ ከእንስሳቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያገኘ ይገኛል። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ኢንፌክሽየስ በርሳል የተባለው በሽታ አምጭ ቫይረስና ፓስቹሬላ መልቶሲዳ የተባለው በሽታ አምጭ ባክቴሪያ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የዶሮ እርባታ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ በማሳደር ላይ ይገኛል፡፡ የስርጭት መጠናቸውም በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ስለዚህ እነዚህን በሽታዎች መከላከል የሚችል ክትባት ማምረቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ክትባቱ በዶሮ እርባታ የሥራ ዕድልን ያስፋፋል፣ የአመጋገብ ሁኔታን ያሻሽላል፣ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍልም የመቀንጨር ችግርን ለመቀነስ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል፣ እንስሳት በመሞታቸው የሚታጣው ኢኮኖሚና ለህክምና የሚወጣ ወጪ ይቀንሳል። እንዲሁም ለክትባት ግብአት የሚሆኑ ከውጭ የሚገቡ ጥሬ ዕቃዎችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል ያስችላል።
በተጨማሪም ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት እነዚህን ክትባቶች ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ የምናገኝበት መንገድ ይፈጠራል። በአጠቃላይ አገሪቱ ደህንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ ከፍተኛ የእንቁላልና የስጋ ምርት በጥራትና በብዛት በማምረት ለዓለም ገበያ የምትልክበትን ዕድል ይፈጠራል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4/2011
በሶሎሞን በየነ