የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ በተለይም ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊ ማዕቀፍ ላይ በተመሰረተ መልኩ እንዲሳተፉ በኢትዮጵያ በኩል በሩ ተከፍቷል። አዋጁም ጸድቋል። በዚሁ መሰረት (እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት) ስመ-ጥር ዓለም አቀፍ ባንኮች፣ በተለይም ምዕራብ ተኮር የሆኑቱ የአዋጭነት ጥናታቸውን በይፋ ከጀመሩ ሰንብተዋል።
በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የ“ይግቡ” በር በመከፈቱ ምክንያት ጉጉታቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ያስችላቸው ዘንድ በአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤታቸውን የከፈቱትና የአዋጭነት ጥናት እያደረጉ ካሉት መካከል በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ቁጥር አንድ የሆነውና ንብረትነቱ የህብረቱ አገራት የሆነው European Investment bank፤ በደቡብ አፍሪካ እውቅናን ያተረፈው ስመጥሩው Standard bank፤ የጀርመኑ ቱጃር Commerz bank፤ ኖይሮቢ ያለውና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይነቱ KCB bank ተጠቃሽ ናቸው።
ዋና መቀመጫውን ካዛብላንካ ያደረገውና በ18 የአፍሪካ አገራት ቅርንጫፎች ያሉት Bank of Africa (BOA)፤ በ1863 የተመሰረተው፣ 1ሺህ 773 ቅርንጫፎች ያሉትና ንብረትነቱ የቱርክ መንግስት የሆነው Ziraat Ban፤ አገራት በአክሲዮን ያቋቋሙትና መቀመጫውን ፍራንክፈርት ያደረገው Deutsche Bank፤ በ“Tier 1 capital” በ(capital + reserves + retained earnings + minority interests ላይ የተመሰረተ) መለኪያ ከምስራቅ አፍሪካ አንቱ የተባለውና የ$1.6 ቢሊዮን ካፒታል ባለቤት የሆነው Equity Bank Group ሌሎቹ ናቸው።
ለወጪ ንግድ በማበደር የሚታወቀውና የደቡብ ኮሪያ ንብረት የሆነው South Korean Exim Bank (Korea Eximbank በሚልም ይታወቃል)፤ የህንድን የወጪ ንግድ ይደግፍ ዘንድ በፓርላማው ፀድቆና በ1982 ተመስርቶ ወደ ስራ የገባው Export-import Bank of India እና የመሳሰሉትም ይጠቀሳሉ።
በምስራቅ አፍሪካ እየመሩ ያሉት ባንኮችም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር እስከ መምከር ድረስ መዝለቃቸው እየተሰማ ይገኛልና ተስፋችን ትልቅ ነው። የትልቅነቱ መለኪያ ድጋሚ ከዚህ በታች የምናወራው እውን ሲሆን ነው።
እንዳለመታደል ሆኖ እኛ አገር ሀብት ሲገኝ ያንን ሀብት ወደ ሌላ ሀብት የመቀየር፣ በተገኘው ሀብት ተጠቅሞ ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ነገር አልተለመደም፤ ወይም አይታወቅም። የግል ባንኮች (Domestic banks) ሳይቀሩ ሰኔ ግም ባለ ቁጥር ትርፋቸውን ሸንሽነው ከመከፋፈል ውጭ የውጪ ባንኮች (Foreign banks) ገብተው እንዳያሽመደምዱን ብለው ሲሰጉና ትርፋቸውን ወደ ካፒታላቸው ማሳደጊያነት ሲያዞሩ እንኳን ብዙም አይታዩም።
የሁሉም አጠቃላይ (ካፒታል) አቅም የንግድ ባንክን ሩብ ያህል ለመድረስ እንኳን አልደረሰም። በግል ቢዝነስ የተሰማሩትም ቢሆኑ ትርፍ ሲያገኙ ወደ “ቪ8” እና ከፍ ሲልም “ሀመር” ላይ ሲያፈሱት እንጂ እስኪ ለአንድ ለ50 ሰው እንኳን የስራ እድል ልፍጠር ብለው የጎጆ ኢንዱስትሪን የምታክል “ጎጆ” ሲያቋቁሙ አይታዩም። ዝርዝሩ ብዙ ነውና ወደ ጉዳያችን እንመለስ። ተመልሰንም የባንኮችን ሚናና የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንመልከት።
ባንኮች (የMicrofinance ባንኮቹ እንዳለ ሆኖ) ከተቋቋሙበት ዋና ዋና አላማዎች ባሻገር ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ሀላፊነትም ያለባቸው ሲሆን፤ አንዱም ከማበደር ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ነው።
ሰፋፊ የስራ እድሎችን የመፍጠር ግዴታ ያለባቸው ባንኮች፣ ይህ ሀላፊነት በራሳቸው ቋንቋ ሲገለፅ “Banks provides loans for skill development and contributes towards job opportunities.” በሚል ሲሆን፤ እዚህ ሲመጡ እንዳይረሱት እንጂ ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ግዴታ አለባቸው። ጉዳዩ በአገራቸው የተለመደ እንደ መሆኑ መጠንም እንደሚያደርጉት ጥርጥር የለም።
ማርች 2020 ይፋ በሆነ፣ በሰንጠረዥ የተደገፈና “Job creation scenario in the banking sector” በሚል ርእስ የቀረበ ጥናት እንደሚያሳየው ባንኮች በያሉበት የስራ እድል መፍጠር ተግባር ላይ የተሰማሩ ሲሆን በተለይም አስፈላጊ በሆኑ መስኮች በአውቶሜሽን፣ ምርትና ምርታማነትን በተመለከተ፣ በመቆጠብና ቁጠባን በማሳደግ፤ አመለካከትን በመቀየር፤ የመንግስት የስራ ፈጠራ ተግባራትን በማገዝ፤ ስልጠናዎችን በመስጠት፤ ክሂሎትን የማዳበር ስራዎችን በመስራት፤ የስራ ፈጠራ አቅምን በማጎልበት ወዘተርፈ ላይ ያሳዩት ተሳትፎና ያስገኙት ውጤት በስኬታማነታቸው ተመዝግቦላቸዋል።
በ2022ም 100 ሚሊዮን የስራ እድሎችን ይፈጥራሉ ተብሎ በእቅድ ተይዞ ያሳኩታል ተብለው እየተጠበቁ ሲሆን፤ አመቱ ተጠናቅቆ በ2023 የእቅድ አፈፃፀማቸው ይፋ ሲሆን የምንገነዘበው ይሆናል። ይህ ወደዚህ ከሚመጡትም ሆነ እየመጡ ካሉት ይጠበቃልና እኛም እድሉን ለመጠቀም፤ እነሱም እድሉን ለመፍጠር፤ ሁለታችንም መዘጋጀት አለብን ማለት ነው። (ይህ ባንኮች በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን፣ (ለምሳሌ የትምህርት፣ የጤና … ተቋማት ግንባታን፤ በባንኮቹ ውስጥ ቀጥረው የሚያሰሯቸውን … የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ የሚያደርጉትን እንደማያካትት ልብ ይሏል።)
በዚህ መስክ ተጠቃሽ ከሆኑት አገራትና የባንክ ኢንዱስትሪዎች መካከል (ያንን አድርጎ እንኳን “በቂ ነው” አልተባለለትም) አንዷ ባንግላዴሽ ስትሆን ባለፈው አመት ብቻ በግል ባንኮች ከ182ሺህ 610 በላይ የስራ እድል ለዜጎች የተፈጠረባት አገር ሆና ተመዝግባለች። ባንኩም “የስራ እድሎችን የፈጠረ …” ተብሎ ተይዞለታል።
በአመቱ ውጤታማ ከተባሉት ባንኮች መካከል የህንዶቹ (State Bank of India, Bank of Baroda, Punjab National Bank, IDBI Bank … እና የመሳሰሉት) የሚገኙበት ሲሆን ለዚህ ካበቋቸው ተግባራቶቻቸው መካከልም አንዱ ይኸው ለዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸው መሆኑን መዘንጋት አይገባም፤ ከመጪዎቹ እንግዶቻችን ባንኮችም ይህንን መጠበቅ የዋህነት አይደለም፤ የማይገባንም መሻት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም።
በአንፃሩ፣ መጪዎቹ ባንኮች ይህንን ወሳኝ ተግባር በእቅዶቻቸው ይዘው፤ የሰው ኃይልና በጀት መድበው ሊሰሩበት ነው የሚገባው። መንግሥትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም ባንኮቹን ሲመዝኑ መስፈርቶቻቸው እነዚህን ሊያካትቱ ይገባል።
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ መሰረት ባንኮች አገራት ከድህነት እንዲወጡ የማድረግ፣ የማገዝ … ከፍተኛ ሀላፊነት አለባቸው። በተለይም የዩኤንን ስትራተጂያዊ የልማት ግብ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ባንኮች ቁልፍ ሚና መጫወት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተገልፆ ይገኛል።
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ባንኮች ከአትራፊነት ተልእኳቸው በዘለለ ማህበራዊ አገልግሎት መስጠትና በአገራት የልማት ተግባራት ላይ መሳተፍ አንዱ ተግባራቸው መሆኑን ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ዜማና ግጥሙን ውሀ በላው ማለት ነው ፤ ይህ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም