42ኛው የቫሌንሲያ ማራቶን እሁድ ይካሄዳል። በስፔን ከሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሁሉ ተወዳጅ የሆነው ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ ከከተማዋ የቦታ አቀማመጥ ጋር በተያያዘ ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ምቹ በመሆኑ በአትሌቶች ዘንድ ተመራጭ ነው። በማራቶን ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በ10 ኪሎ ሜትር በሚካሄደው ህዝባዊ ሩጫ ደግሞ 30ሺ ሰው ተሳታፊ እንደሚሆንም ታውቋል።
በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ የሩጫ ውድድር ላይም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የርቀቱ ዝነኛ አትሌቶች እንደሚፎካከሩ አረጋግጠዋል። በአትሌቲክስ ቤተሰቡ በተሰጠው ቅድመ ግምት መሰረትም ውድድሩ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ይጠናቀቃል በሚል የሚጠበቅ ሆኗል። በተለይ በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ወጣት አትሌት ለተሰንበት ግደይ ተሳታፊነቷን ማሳወቋ በውድድሩ አዲስ ነገር እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል።
በ5 ሺ እና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በ15 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ለተሰንበት አሁን ደግሞ ከምትታወቅበት የመም ውድድር ወደ ማራቶን ፊቷን ያዞረችበት ውድድር ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጎዳና ላይ ውድድሮች የታየችው አትሌቷ ባለፈው ዓመት በዚሁ የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ሮጣ 1:02:52 በሆነ ሰዓት በመግባት የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በእጇ አስገብታለች። አሁን ደግሞ በረጅሙ ርቀት ማራቶን ልትወዳደር መዘጋጀቷን ግሎባል ስፖርት ኮሚዩኒኬሽን የተሰኘው የስልጠና ቡድኗ አስቀድሞ ነበር ያሳወቀው። ይህንን ተከትሎም የአትሌቷ አሰልጣኝ ኃይሌ እያሱ ከለተሰንበት ጋር ከዓመታት በፊት በ5ሺ ሜትር እና 10ሺ ሜትር እስከ ማራቶን የዓለምን ክብረወሰን መስበር የሚል እቅድ እንደነበራቸው ገልጾ ነበር። በዚህ መሰረት አትሌቷ አሁን በደረሰችበት ማራቶን አዲስ ነገር ልታስመለክት ትችላለች በሚል ትጠበቃለች።
ለተሰንበት ዝግጅቷን አስመልክታም በስልጠና ቡድኗ በኩል አስተያየቷን ገልጻለች። ዝግጅቷን በአዲስ አበባ ስታደርግ ቆይታ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በሳምንት ለአንድ ቀን 30ኪሎ ሜትር በመሮጥ ርቀቱን እንደተላመደችውም ጠቅሳለች። አሰልጣኟም ማራቶንን መሮጥ እንደምትችል አረጋግጦላታል። የመጀመሪያውን የዓለም ክብረወሰን በ5ሺ የሰበረችው በቫሌንሲያ በመሆኑ በቦታው የተለየ ትውስታ ያላት አትሌቷ ሌላኛውን ህልሟን ለማሳካትም ደግም በተመሳሳይ ከተማ ማራቶን ትሮጣለች።
በቫሌንሲያ ማራቶን የሴቶች ሩጫ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የሚሆኑ አትሌቶች አሸናፊ ሊሆኑ ችለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የበላይነቱን የያዙት ኬንያዊያን አትሌቶች ሲሆኑ፤ የቦታው ፈጣን ሰዓትም እአአ በ2020 ፔሬስ ጄፕቺርቺር 2:17:16 የተመዘገበ ነው። በዚህ ውድድም ለመጀመሪያ ጊዜ ተካፋይ የምትሆነውና ክብረወሰን በመስበር ልምድ ያላት ብርቱዋ አትሌት ለተሰንበት አዲስ ሰዓት ታስመዘግባለች በሚል ትጠበቃለች። ሱቱሜ ከበደ፣ ቲኪ ገላና፣ ትዕግስት ግርማ፣ እታገኝ ወልዱ፣ አማኔ ሻንቁሌ፣ ታደለች በቀለ እና ብሩክታይት እሸቱ ደግሞ ከለተሰንበት ጋር የሚሮጡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በወንዶች በኩል ደግሞ ርቀቱን ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች የሮጡ ሰባት ያህል አትሌቶች ተካፋይ ይሆናሉ። በውድድሩ ተሳታፊ ከሆኑ አትሌቶች ፈጣን ሰዓት ያለው አትሌት ጌታነህ ሞላ ሲሆን፤ በርቀቱ ያስመዘገበው 2:03:34 የሆነ ሰዓት ቀዳሚው ነው። በአምስት ሰከንዶች ብቻ ከእሱ ያነሰ ሰዓት ያለው ታምራት ቶላም ተጠባቂ አትሌት ነው። የኦሪጎኑ የዓለም ማራቶን ቻምፒዮና የሆነው አትሌቱ በማራቶን ከፍተኛ ልምድ አለው። በዚህ ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶንም ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ውድድሩን ያጠናቀቀው። 2:04:27 የሆነ ሰዓት ያለው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዳዊት ወልዴ ደግሞ ሶስተኛው ባለፈጣን ሰዓት ነው።
በአምስት ሰከንዶች ብቻ በመዘግየት አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አትሌት ደግሞ ጆናታን ኮሪር ነው። አትሌቱ ለኢትዮጵያውያኑ ፈተና እንደሚሆን ቢገመትም፤ ህዝቄል ተወልደ፣ ጫሉ ዴሶ እና ወርቅነህ ታደሰን የመሳሰሉ አትሌቶች ግን በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አይሆኑም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም