አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ ህብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ከክልል ከተሞች በተለየ ሁኔታ ሞቅና ደመቅ ትላለች። በመሰረተ ልማቶቿም የተሻለችና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማ ናት።
ለኑሮ ምቹ ሁኔታዎች ያሏት፣ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ስራ ፍለጋ፣ ሌሎች ደግሞ በከተማዋ ካለው አንጻራዊ ሰላም ጋር በተያያዘ የዜጎች ምርጫ እየሆነች የምትገኘው ይህች መዲና፣ በሰላም አጦትና በመሳሰለው የተቸገሩ የጎረቤት አልፎም ተርፎ የሩቅ አገሮች ስደተኞች ምርጫም ሆናለች። ከተማዋ የእነዚህን ሁሉ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ለመመለስ እየተውተረተረች ትገኛለች።
የብዙሃኑ መኖሪያ የሆነችው አዲስ አበባ አሁን አሁን ግን በኑሮ ውድነት ያዳከማት ትመስላለች። በአራቱም አቅጣጫ በየጊዜው እየፈለሰ ወደ ጉያዋ ለሚተመው ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቱን ልታሟላለት አቅም አጥታለች። የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የጤና፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ማዳረስ ፈተና ሆኖባታል። ከሁሉም በላይ መቆሚያ ባልተገኘለት የኑሮ ውድነት በእጅጉ እየተፈተነች ትገኛለች።
ከተማዋ የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ የተለያዩ ተግባሮችን ስታከናውን ቆይታለች። መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በሸማቾች ማህበራት በኩል ለህዝቡ ለማቅረብ በትኩረት መስራቷን ቀጥላለች። ህገወጦችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየሰራ ይገኛል። በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የከተማዋ አስተዳደር የፋይናንስ አቅርቦት በማድረግ ጭምር እየሰራ ነው። የህብረት ስራ ማህበራት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየሰሩ ናቸው።
ችግሩ እየተቃለለ ይመጣል ሲባል እየተባባሰ መጥቷል። የሸቀጦች የዋጋ ንረት ህዝቡን ሰቅዞ የያዘው ቀዳሚ ችግር ነው። ማህበረሰቡ እየተፈተነበት ያለው የኑሮ ውድነት በእጅጉ እያሳሰበው መምጣቱን የሚገልጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ፣ በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍትሔውን ለማፈላለግ እየሰራ መሆኑን ይገልጻል።
ቢሮው ሰሞኑን ባዘጋጀው መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነት እየከፋ ሊመጣ የቻለው በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን በጥናት ማረጋጋጡን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው የህዝብ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ንረት እያስከተለ መሆኑንም በጥናቱ ማረጋጋጥ እንደተቻለ አመላክቷል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በከተማው የሚስተዋለውን የንግድ እንቅስቃሴ ጤናማ ለማድረግና የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የተለያዩ ዘዴዎች ቀይሶ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ፤ የኑሮ ውድነቱን መነሻ በማድረግ በመሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርትና አቅርቦት ላይ ለሚስተዋለው ችግር መፍትሔ ለመስጠት ጥናቱ መደረጉን አስታውቀዋል።
በጥናቱም የተለያዩ አካላት ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን፤ የጥናቱ ውጤትም የምግብ ሸቀጦችን የዋጋ ንረት ገታ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ በመድረኩ ተጠቁሟል።
አቶ አደም እንዳብራሩት፤ ቢሮው ተነሳሽነቱን ወስዶ ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት አዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ለከፍተኛ የምግብ ዋጋ ንረት ተጋላጭ መሆኗን ማረጋገጥ አስችሏል። ከተማ አስተዳደሩም የምግብ ዋጋ ንረትን ተከትሎ የሚመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በጊዜያዊነትና በዘላቂነት መፍትሔ ያመጣሉ ያላቸውን የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ እየሠራ ነው።
የገበያ ማዕከላትን በመገንባትና በማስፋፋት፣ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦትን ማሻሻል፣ የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶች በፍትሃዊነት ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በንግድ ስርዓቱ ላይ ቁጥጥር በማካሄድ የዋጋ ንረትንና የምርት ቅሸባን መከላከል ላይ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የገበያ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ሥራ ላይ በማዋል፣ በከተማው ህገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በከተማው ፍትሃዊ፣ ዘመናዊና በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥርዓት ለማስፈን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ኃላፊው አብራርተዋል።
በመሰረታዊ የፍጆታ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጥናቱን መሰረት በማድረግ እንደሚሰራም ተጠቁሟል። ጥናቱ ለመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ትልቁ መንስኤ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን መሆኑን ማመልከቱን አቶ አደም ተናግረዋል። በተመሳሳይ መልኩ የንግድ ሥርዓቱ ክትትልና ቁጥጥር መላላት፣ ምርትን የመደበቅ እና በግብይት ሰንሰለቱ የበርካታ ተዋናዮች ጣልቃገብነት እንዲሁም የጸጥታ ችግር ለዋጋ ንረቱ ሌላኛዎቹ ምክንያቶች መሆናቸውን በጥናቱ መለየት እንደተቻለ ነው ያስረዱት።
የጥናቱ ቡድን መሪ አቶ እንዳለ ተገኝ እንዳብራሩት፤ የጥናቱ ዋና ዓላማ የአዲስ አበባ ከተማ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት፣ የመፍትሔ አመላካቾችን ማቅረብም ነው። ጥናቱ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ እየተስተዋለ ለሚገኘው የዋጋ ንረት ከመላ ምት ያለፈ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ያስችላል።
አምስት ዓላማዎችን ይዞ ጥናቱ መካሄዱን ጠቅሰው፣ በቀዳሚነት መሰረታዊ የምግብ ምርቶች በጥናት መለያታቸውን፤ ፍላጎቱ ምን ይመስላል፣ አቅርቦቱስ ምን ያህል ነው፣ ክፍተቱ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚሉትን መመለስ የቻለ ጥናት እንደሆነም አስታውቀዋል፤ የከተማዋ የምግብ ምርት አቅራቢ ቦታዎችንም መለየት እንደሚያስችል አብራርተዋል።
እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ በመዲናዋ የሚዘወተሩት የምግብ ምርት አይነቶች 23 መሆናቸውን በጥናቱ መለየት ተችሏል፤ እነዚህም ጥራጥሬ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በሚል ይመደባሉ። በጥናቱ መሠረት፣ በአሁኑ ጊዜ የመዲናዋ ሕዝብ ብዛት አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ደርሷል፤ ከሕዝቡ አጠቃላይ ወጪ 52 በመቶው ለምግብ ፍጆታ ይውላል።
ከእነዚህ ወጪዎች መካከልም ጤፍ 57 ነጥብ 7 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ደረጃን የሚይዝ ሲሆን፤ ስንዴ፣ ቀይ ሽንኩርት እና ድንች በቅደም ተከተል ከ2ኛ እስከ 4ኛ ደረጃን ይይዛሉ። በርበሬ፣ ወተት፣ ዘይት፣ ሥጋ፣ እንቁላል እና ስኳርም በመዲናዋ በጣም ተፈላጊ የምግብ ሸቀጦች ናቸው።
ከምግብ ምርቶቹ ምንጭ አንጻር የመዲናው ሕዝብ በብዛት የሚጠቀማቸው የምርት አይነቶች፤ ከጤፍ የአደዓ፣ ከስንዴ የአቡሴራ፣ ከቀይ ሽንኩርት የሸዋሮቢት፣ ከዳልጋ ከብት የሐረር፣ ከምግብ ዘይት የማሌዥያ፣ ከስኳር የሕንድ ቀዳሚ ደረጃ ላይ መሆናቸውን አቶ እንዳለ አብራርተዋል። ለዋጋ ንረቱ እንደ ምክንያት የተጠቀሱትን ችግሮች በመግታት ያሉትን ምርቶች በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ካልተቻለ አሁን እየታየ ያለው እጥረት በእጥፍ እንደሚጨምር በጥናቱ ተለይቷል ይላሉ።
ጥናቱ የከተማዋ ህዝብ የምግብ ምርቶችን ከመጠቀም አንጻር የሰብል ምርቶች 48 በመቶ፣ አትክልትና ፍራፍሬ 29 በመቶ፣ እንስሳት 7 በመቶ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች 16 በመቶ እንደሆኑ አመላክቷል። ጥናቱ በዋናነት በመዲናዋ የሚዘወተሩ የምግብ ፍጆታዎች መጠንና አቅርቦትን እንዲሁም የምግብ ፍጆታዎቹን ምንጮች በውል በመለየት የምግብ አቅርቦቱ የሚጨምርበትን የመፍትሔ ሀሳብ ያመላከተ መሆኑንም አቶ እንዳለ አንስተዋል።
አልጣጣም ያለውን የምግብ ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም እንዲሁም እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ያለመው የትንበያ ጥናት ከ2015 እስከ 2025 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚዳስስ መሆኑን አቶ አደም ይናገራሉ፤ ጥናቱ የህዝቡን ችግር ከመፍታት አንጻር አይነተኛ ሚና የሚኖረው መሆኑን ሲያስረዱ፤ በከተማ ውስጥም ሆነ በአገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የምግብ ዋጋ ጭማሪ እየታየ ገልጸው፣ በአገር ውስጥ ብሎም በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ላለው የምግብ ዋጋ ጭማሪ መነሻውን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥናት መካሄዱ ጠቃሚ መሆኑን አስታውቀዋል። ጥናቱ አንጻራዊ በሆነ መንገድ የምግብ ዋጋ ንረትን፣ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምን ለመቆጣጠር ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
አሁን ላለው የዋጋ ንረት የምርት እጥረት ችግር ብቻ ምክንያት እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ የአገሪቱ ምርቶች ወደ ከተማዋ ገበያ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ መግባት እንዳልቻለም ተናግረዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም በሰላምና ጸጥታ መደፍረስ እንዲሁም ረዘም ያለ የግብይት ሰንሰለትም በምርት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ይገልጻሉ።
አቶ አደም ከአዲስ አበባ ከተማ በአራቱም አቅጣጫዎች የሚመጣው ምርት በቀጥታና ጤናማ በሆነ መንገድ ወደ ከተማዋ መግባት እንደሚኖርበት ጠቅሰው፣ ምርቱም ባጠረ የግብይት ሰንሰለት መግባት እንዲችል በህገወጥ ደላሎችና በሌሎችም የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የንግድ ስርዓቱን ቀልጣፋ በማድረግ ቁጥጥሩንም ጠንካራ ማድረግ የግድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የንግድ ስርዓትን ቀልጣፋ፣ ቁጥጥሩንም ጠንካራ ከማድረግ ባለፈ ቢሮው የዋጋ ንረቱን ለመቀልበስ በዩኒዬኖችና በሸማቾች አማካኝነት ለሸማቹ ማኅበረሰብ የሚያቀርባቸውን ምርቶች አጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ተጠቁሟል። አቅርቦቱን ለመጨመርም ከአምራቾች ጋር እየሠራ እንደሆነና ወደ ማምረት የመግባት እቅድ እንዳለውም አቶ አደም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ጥናቱ አንዲካሄድ በተነሳሽነት የተሳተፈ ቢሆንም በጥናቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ስትራቴጂክ ቡድንና የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ባለስልጣን መሳተፋቸውንም አቶ አደም ገልጸዋል። ጥናቱ በዋናነት የምርት አቅርቦት እንዲበረታታ እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ ለተግባራዊነቱም የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር እንቅፋት እንዳይሆን መደገፍ የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥናቱ የተመላከቱት መፍትሔዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ፈጻሚዎች በቅንጅት መሥራትና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አቶ አደም ይገልጻሉ፤ ለዚህም ጊዜ፣ እውቀት፣ ከፍተኛ ልፋትና ብቃት ላለው አመራር መስጠትን ይጠይቃል። ለጥናቱ ተግባራዊነት ሁላችንም በቅንጅት መነሳት የግድ ይለናል ያሉት አቶ አደም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ ተቆጥረው የተሰጡትን ኃላፊነቶች የማስተባበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ይረባረባል ሲሉ ተናግረዋል። መንግሥት የምግብ ዋጋ ንረትን ለመከላከል የሚሰራቸው ሥራዎች እንዲሳኩ የከተማዋ ነዋሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መንግሥት የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎች ለመፈጸም የበኩላቸውን ኃላፊነቶች መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/ 2015 ዓ.ም