በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሲካሄድ በሰነበተው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) የቮሊቦል ውድድር ፍጻሜውን ሲያገኝ በሴቶች ጌታ ዘሩ በወንዶች ደግሞ ብሔራዊ አልኮል ሻምፒዮን በመሆን አጠናቀዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ከኅዳር 9/2015 ዓ.ም ጀምሮ ባዘጋጀው አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) የቮሊቦል ውድድር ለተከታታይ 10 ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል። በውድድሩ በሴቶች 4 ክለቦች በዙር ውድድር ያደረጉ ሲሆን ጌታ ዘሩ ክለብ ውድድሩን በበላይነት በማጠናቀቅ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆኗል። ፌዴራል ማረሚያ ቤት ሁለተኛ ብሔራዊ አልኮል ሦስተኛ በመሆን የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆኑ ክለቦች ናቸው።
ብርቱ ፉክክር በታየበትና 5 ክለቦች በተሳተፉበት የወንዶች የቮሊቦል ውድድር መቻልና ብሔራዊ አልኮል ለፍፃሜ የደረሱ ሲሆን ብሔራዊ አልኮል የስፖርት ክለብ 3ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድሩ ሻምፒዮን በመሆን የተዘጋጀለትን የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳልያ መውሰድ ሲችል መቻል ስፖርት ክለብ የብር፣ አዲስ አበባ ፖሊስ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።
በውድድሩ ፍፃሜ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ፣ “እንደነዚህ አይነት ውድድሮች መዘጋጀታቸው ክለቦች አቋማቸውን እንዲለኩበት ከማድረጉ ባሻገር የተቀዛቀዘውን የቮሊቦል ስፖርት እንዲነቃቃ ከማድረግ አኳያ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው” ብለዋል።
አቶ አብርሀም ቢሮው በከተማው የሚገኙ የስፖርት ማኅበራትን ለመደገፍ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለሀብቶች እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የከተማውን ስፖርት እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/ 2015 ዓ.ም