ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ኳታርን ለዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት የመረጣት ከ12 ዓመታት በፊት ነው። ይህን ውሳኔውን ግን መላው ዓለም በፀጋ የተቀበለው አልነበረም። በተለያዩ መንገዶች የኳታርን መስተንግዶ የሚያጣጥሉና የሚያወግዙ ትችቶች ሲሰራጩ ቆይተዋል። የመጀመሪያው ንትርከ የፊፋ አስተዳደርና አባል አገራቱ አዘጋጅነቱን ለኳታር ለመስጠት ሲወስኑ በሙስና ተደልለዋል የሚለው ነው። የኳታር ንጉሳዊ መንግስት ለአዘጋጅነት በተካሄደው ምርጫ የድጋፍ ድምፆችን ለማግኘት እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር በተለይ ለአፍሪካ አገራት ፌደሬሽኖች ማከፋፈሉን ያወሱ ዘገባዎች ነበሩ። ይሁንና ሁሉም አሉባልታዎች በትክክለኛ መረጃዎች ዛሬም ድረስ አልተረጋገጡም።
አንዳንድ የኤስያ አገራትና በተለይ ደግሞ አሜሪካ የዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው መሰል ዘገባዎች ተሰራጭተዋል። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በ2010 እኤአ ላይ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ 21ኛውን የዓለም ዋንጫ እንድታስተናግድ ከመረጠ በኋላ በ2022 እኤአ ላይ ደግሞ ኳታር 22ኛውን ዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ወስኗል።በተለይ ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ አሜሪካ፤ አውስትራሊያ፤ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ ለመስተንግዶው ፉክክር አድርገው አልተሳካላቸውም። ፊፋና የዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ኳታር በውድድሩ ታሪክ ዘላቂ የስፖርት ልማቶች በመገንባት፤ ከካርቦን ልቀት የነፃ መስተንግዶ በማካሄድ፤ በዘመናዊ ዝግጅት የተሟላ እንደሚሆን እምነት ማሳደራቸው የሙስናውን ወሬ አደብዝዞታል።
በሌላ በኩል የዓለም ዋንጫው በሚካሄድበት ወቅት ከተለመደው መርሃ ግብር እንዲቀየር መደረጉንም ያማረሩ አልጠፉም። ኳታር በሙቀታማ አየር ንብረቷ ሳቢያ ዓለም ዋንጫው የፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ባለው ወር እንዲካሄድ አድርጋለች። በመደበኛው የዓለም ዋንጫ ወቅት የአየሩ ሙቀት ከ50 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ ይሆናል። አዲስ በታቀደው የዓለም ዋንጫ ወር ግን የኳታር አየር ንብረት እስከ 29 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መውረዱ ውሳኔውን አፅንቶታል። ኳታር የዓለም ዋንጫን የሚያስተናግዱ ስምንት ስታድዬሞች ከሙቀቱ ጋር ለማመጣጠን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመስራት ከአየቅጣጫው የመጡትን ትችቶች አብርዳለች። የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር ካደረገ በኋላ በተጨዋቾች፤ በደጋፊዎች እና በአጠቃላይ በስታድዬም ውስጥ ቀዝቃዛ አየር የሚያነፍስ ዘመናዊ የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ በመፍጠር ተግባራዊነቱን አረጋግጧል። አስደናቂዎቹ የዓለም ዋንጫ ስምንት ስታድዬሞች በዚህ ረገድ ስኬታማ ውድድር ለማስተናገድ እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖባቸዋል።
ሌላው ትችት ኳታር የዓለም ዋንጫን የመስተንግዶ ደረጃ በታሪክ ከፍተኛውን በጀት በማውጣት ሰቅላዋለች በሚል የተናፈሰው ነው። በአረቡ ዓለም በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከ229 ቢሊዮን ዶላር በኳታር መንግስት መውጣቱ በቀጣይ ዓለም ዋንጫዎች በብቸኝነት ውድድሩን ለማስተናገድ የሚችል አገር ማሳጣቱ ነው የተሰጋው። ከኳታር በፊት ራሽያ ለ21ኛው የዓለም ዋን 14.6 ቢሊዮን ዶላር ብራዚል ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ 11 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጡ የሚታወስ ሲሆን የኳታር በጀት ከ10 እጥፍ በላይ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። በ2026 እኤአ ላይ 23ኛውን የዓለም ዋንጫ አሜሪካ፤ ካናዳና ሜክሲኮ ለሶስትዮሽ ለማስተናገድ ያቀዱት በነፍስ ወከፍ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማውጣት በማቀድ ነው።
ኳታር አስደናቂውን የአለም ዋንጫ መክፈቻ ስነስርአት ካሳካች በኋላም በተለይም በምእራባውያን መገናኛ ብዙሃኖች መብጠልጠሏ አልቀረም። በእነዚህ መገናኛ ብዙሃኖች አሁንም ድረስ ከኳታር የአለም ዋንጫ በጎ ነገሮች ይልቅ ጸጉር እየሰነጠቁ አሉታዊ ዘገባዎችን ማቅረብ ስራዬ ብለው ይዘውታል። ያም ሆኖ ኳታር ዝግጅቷ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል እንከን እንደማይወጣለት በተግባር ለአለም ማሳየቷን ቀጥላበታለች። አገሪቱ ለአለም ዋንጫው ዝግጁ ያደረገቻቸው ስምንት ስታዲየሞች ከዶሃ እምብርት በ33.8 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የተገነቡና በመሰረተ ልማት እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውም ተመልካቾች በአንድ ቀን በርካታ ጨዋታ እንዲመለከቱ በማድረግ የኳታር ድግስ ሞቅ ደመቅ ብሎ እንዲቀጥል አስችሎታል።
በኳታር የአለም ዋንጫ ስጋት የነበረውና ምናልባትም ውድድሩን ማዘጋጀቷ ስህተት መሆኑን ያሳያል ተብሎ የታሰበው የሙቀት ጉዳይ ነበር። ኳታር ስቴድየሞቿን በቴክኖሎጂ ታግዛ ይህን ትችት ለማስቀረት በራስ መተማመን የነበራት ቢሆንም ቴክኖሎጂዎቹ ያን ያህል ውጤት አያመጡም ብለው የጠበቁ ጥቂት አይደሉም። በዚህም የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃኖች የሰላ ትችታቸውን ለመሰንዘር ቢዘጋጁም አልተሳካላቸውም። የሙቀት ጉዳይም በየጨዋታዎቹ አሳሳቢ ችግር ሆኖ ሊታይ አልቻለም። ለዚህም እያንዳንዱ ስታዲየም በጸሃይ ብርሃን ሃይል የሚሰራ ራሱን የቻለ የሃይል ምንጭ ያለው መሆኑ ሙቀቱን ለመቀነስ የሚያግዙ የተዋጣላቸው የማቀዝቀዣ ሲስተሞች ስራቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ኳታር ውድድሩ ከሰኔ መጨረሻ ወደ ህዳር እንዲመጣ መርሃግብሩን ቀደም ብላ ማስቀየሯ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። አሁን ውድድሩ የሚከናወነው በኳታር በንጽጽር ቀዝቃዛ በሆነው የዓመቱ ክፍል በመሆኑ ምናልባትም የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂዎቹ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆኑ የሚጠቁሙ ዘገባዎችም ወጥተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/ 2015 ዓ.ም