ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርቱ እንዴት እያደረጋችሁ ነው? ትምህርት ከጀመራችሁ ሦስት ወር ሞልቷችኋልና ፈተና እየወሰዳችሁ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ታዲያ ፈተናው እንዴት ነው? በእርግጥ እናንተ በጣም ጎበዝ ልጆች ስለሆናችሁ ይህ ነገር ያሳስባችኋል ብዬ አላምንም፡፡ የምታነቡት ደግሞ ፈተናን ለማለፍ ብቻ ሳይሆን ለእውቀት ጭምር በመሆኑ ፈተናው እንደማይከብዳችሁ ግልጽ ነው፡፡
እውቀት ፈላጊ ልጅ መሆን ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዋናነት መድረስ የሚፈልግበት ላይ ለመድረስ ያስችላል፡፡ ለሚጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም ያግዛል፡፡ በተለይ ደግሞ በመምህራን፣ በተማሪዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር ተወዳጅና መፍትሄ አፈላላጊ ልጅ ያደርጋል፡፡ ታዲያ ይህንን ዓይነት ልጅ መሆን አትፈልጉም? እንፈልጋለን የሚል ምላሽ ሰጥታችኋል አይደል? አዎ ሁሌ በትምህርት ሂደታችሁ ላይ እውቀት ፈላጊ ልጅ ሁኑ፡፡
ልጆች ዛሬም እንደባለፈው ሳምንት ልምዱንና ተሞክሮውን የሚያካፍለንን ጎበዝ ተማሪ ይዤላችሁ ቀርቤያለሁ፡፡ ልጁ ብሩክ ሚኪያስ ይባላል፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ በራይሲ ሪች ኢንተርናሽናል ሴንተር ኦፍ ኢዲኩዌሽን በሚባል ትምህርት ቤት ይማራል፡፡ በትምህርቱ ደግሞ የደረጃ ተማሪ ነው፡፡ ለዚህ ያበቃው ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ቴክኖሎጂን ለትምህርቱ በሚመቸው ልክ መገልገሉና አዳዲስ እድሎችን መጠቀም መቻሉ ነው፡፡
ብሩክ በአይቲ ቤተሙከራ ውስጥ ከተማሩ ተማሪዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ትምህርትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን እንዲያመጣጥን አድርጎታል፡፡ በዚያ ላይ በሒሳብ ትምህርት የተሻለ እውቀት እንዲያካብት ሆኗል፡፡ አሁን በሒሳብ ትምህርት ጎበዝ ሆኗል፡፡
ልጆች ለመሆኑ የአይቲ ቤተ ሙከራ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ተንቀሳቃሽና ብዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የያዘ ማሰልጠኛና ማስተማሪያ ክፍል ነው፡፡ በተለይም ለኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን መማሪያነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን የሚይዝ ሲሆን፤ ተማሪዎች ከሳይንሱ ጋር እንዲቀራረቡ የሚደረግበት ቤተ ሙከራ ነው፡፡ ለአብነት ኮንፒውተር፣ ሮቦቶችና መሰል የአይቲ ቁሳቁሶችን ለተማሪዎች በማሳየትና አጠቃቀሙን በማሰልጠንና በማስተማር ከቴክኖሎጂው ጋር እንዲቀራረቡ የሚያደርግ የሙከራ ክፍል ነው፡፡
እንደምታውቁት ብዙዎቹ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ተማሪዎች ኮንፒውተር ምንድነው፣ ማውዝስ ብትሏቸው ምንም ሊነግሯችሁ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም እጥረት ስላለ ብዙ ገጠር ውስጥ አልገባም፡፡ በመሆኑም እነርሱ የሚያዉቄት የንድፈ ሀሳቡን ትምህርት እንጂ ቁሱን አይደለም፡፡ ስለዚህም ይህ ቤተሙከራ እነርሱን ከማሳወቅ አንጻር ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በዚያ ላይ ልጆች ቤተሙከራው በጸሐይ ብርሃን የሚሰራ በመሆኑ መብራት ጠፋ ውጡ አይባል በትም። መብራት የሌለበት ቦታ ላይም አትሂዱ የሚለው ክልከላ አይኖርም። ስለዚህም ዘና እያላችሁ የምትማሩበት ነውና ደስተኛ ያደርጋችኋል፡፡ በተጨማሪም ተገ ቢውን እውቀት እንድትቀስሙ ያስችላችኋል፡፡
ብሩክ በዚህ የስልጠና እና የመማሪያ ክፍል ውስጥ በመማሩ በርካታ እውቀቶችን አግኝቷል፡፡ ለአብነት የተበላሹ ነገሮችን በቤት ውስጥ መጠገንና ወደነበሩበት መመለስ የቻለው ከዚያ በአገኘው እውቀት ነው፡፡ እነርሱ ቤት ዋይ ፋይ ሲበላሽ ከባድና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተያያዘ ችግር ካልሆነ በስተቀር ሰሪ አይጠራም፡፡ ብሩክ በተማረው ትምህርት መሰረት ያስተካክለዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ጥገናዎችንም ያደርጋል፡፡
በአይሲቲ ቤተሙከራ ውስጥ ተምሮ ማወቁ ለትምህርቱ ጭምር በብዙ ነገር እንደጠቀመው የነገረን ብሩክ፤ ቀድሞ ማንበብ እንዲችል፣ ተጨማሪ ነገሮችን እንዲመረምር፣ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችን እንዲያመነጭና አብዛኞቹን ትምህርቶች በቀላሉ እንዲሰራ አግዞታል፡፡ ለሌሎችን የትምህርት ቤት ጓደኞቹን ማገዝ ችሏል፡፡ መምህሩ ሲያስረዳው ቀድሞ ከአነበበው ጋር ሲያገናኘው ትምህርቱን ግልጽ ስለሚያደርግለት መምህሩ ጭምር ሲሳሳት እንደያርመውም አስችሎታል ፡፡
ልጆች ብሩክ የሚፈልገው በቴክኖሎጂው ዘርፍ አገሩን የሚያስጠራ ተማሪ መሆን ነው፡፡ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በማምጣት ማህበረሰቡን ከችግሩ ማውጣት ይፈልጋል። ራሱንም ታዋቂ ማድረግ ይሻል፡፡ ለዚህም በመማር ማስተማሩ ሂደት ውስጥ ለፍላጎቱ ወደሚቀርበው ትምህርት አዘንብሏል። የተለያዩ እውቀቶችን ለመቅሰም ከኢንተርኔት ጋር ጥብቅ ቁርኝት የፈጠረውም ለዚህ ነው፡፡ ይህንን ስኬቱን ለማግኘት አባቱና እናቱ እያገዙት እንደሆነ ነግሮኛል። እገዛቸው ተንቀሳቀሽ ሸረሪት ለመስራት እንዳስቻለውም አጫውቶኛል፡፡
ከዚህና ሌሎች ነገሮች ጋር ተያይዞ ብሩክ ለተማሪዎች ‹‹ትምህርታችሁን ከሁሉም በላይ አስቀድሙ፤ ለሕልማችሁ ሁልጊዜ ሥሩ የሚል መልክት አስተላልፎላችኋል፡፡አገር ወዳድና አገራችሁን የምታውቁ ሁኑም ብላችኋል። አትችሉም የሚሏችሁን ሰዎች አትስሟቸው ይልቁንም ችላችሁ በማሳየት አሳምኗቸውም ይላል፡፡
የተማሪው ሌላው ምክረሀሳብ የሚመጡ ዕድሎችን መጠቀም መቻል አለባችሁ የሚለው ነው፡፡ ዕድሎችን ስንጠቀም አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦች ወደ አዕምሯችን ይመጣሉ፤ አገር ቀያሪ ተግባርን እንድንከውን እንሆናለን፡፡ ለምንሰራቸው ሥራዎች ኃይል እናገኛለን፤ ለሌሎች መድረስና አገርን ከፍ ለማድረግ እንችላለን ይላል፡፡ ምክንያቱም ለእርሱ እንዲህ አይነት ተማሪ ለመሆን ምስጢሩ በአንድ አጋጣሚ ባገኘው እድል መጠቀሙ ነው፡፡ እናም አሁን በዘጠኝ ከተሞች ላይ ቴክኖሎጂ የማግኘት እድሉ ስለተመቻችላችሁ ፈጥናችሁ ተጠቀሙበት በማለት ከአለው ልምድ በመነሳት መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
ልጆች ብሩክን እንዴት አገኛችሁት ፤ ጎበዝ ነው አይደል? ብዙ ቁምነገር አስጨበጧችኋል አይደል? ግን የመከራችሁን ካልተገበራችሁ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህም ምክሩን ተግብሩት? ምክንያቱም ጎበዝ ልጅ ለመሆን ከፈለጋችሁ የሚሰጧችሁን መልካም ዕድሎች ሁሉ መጠቀም አለባችሁ፡፡ በሉ ለዛሬ በዚህ ሀሳቤን ልቋጭ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም ሰንበት እመኝላችኋለሁ!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/ 2015 ዓ.ም