በረጅም ርቀት ሩጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሆኑት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በዓለም የጸረ አበረታች ቅመሞች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በልዩ ዓይን የሚታዩ መሆኑ ይታወቃል። በእርግጥም በቀጣናው ንጹህ ስፖርትን የሚተገብሩ እንዳሉ ሁሉ በማጭበርበር የተካኑና በአቋራጭ መንገድ ውጤታማ ለመሆን የሚተጉም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በተለይ ጎረቤት አገር ኬንያ በዚህ ቅሌት ሳቢያ አትሌቶቿ በተደጋጋሚ የሚወቀሱባት አገር ሆናለች። ለማሳያ ያህልም በዚህ የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ ከ50 በላይ አትሌቶች በዚህ ምክንያት ለእገዳ ተዳርገዋል።
ይህ ሁኔታ በአትሌቲክሱ ዓለም አዳዲስ ታሪኮችን ያስመዘገቡ ጠንካራ አትሌቶች ያላትን አገረ ኬንያን ስም ከማጉደፍ ባለፈ እንደ ሩሲያ ከየትኛውም ውድድር ውጪ ልትሆን የምትችልበትን አጋጣሚ ያሳድጋል። አለፍ ሲልም ዓለም አቀፉ ተቋም በቀጣናው ያለውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያጠናክር ምክንያት ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዓለም አቀፉ ተቋም በቅርበት ክትትል የሚደረግባት ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ማወቅም አስፈላጊ ነው። በእርግጥ የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ባከናወናቸው በርካታ ተግባራት ጥሩ አፈጻጸም አስመዝግቧል። ከሚያቀርባቸው ሪፖርቶችም እንደ ኬንያ የከፋ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚ አትሌቶች አለመኖራቸውንም መረዳት ይቻላል።
በአንጻሩ ከአትሌቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ባለሙያዎች አሁን በአትሌቶች ዘንድ ያለው ዝንባሌ እንደ ጎረቤት አገር ኬንያ ብቻም ሳይሆን እንደ ሩሲያ ከስፖርቱ ውጪ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ነው የሚጠቁሙት። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አያሌው ጥላሁን፤ ኅብረተሰቡ የስፖርት አበረታች ንጥረነገሮች ተጠቃሚነት ከታዋቂ አትሌቶች ጋር የሚያያዝ አድርጎ እንደሚያስብ ይገልጻሉ። ነገር ግን 11 የሚሆኑ አትሌቶች ተጠቃሚ መሆናቸው የተረጋገጠው ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ላይ ነው። ይህም የሚያሳየው ደግሞ በትልልቅና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ብቻም ሳይሆን በአገር ውስጥ ውድድሮች ላይም ጀማሪ የሚባሉ አትሌቶች እየተጠቀሙት ስለመሆኑ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ይህ ሁኔታ ነገ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚለውን አመላካች ከመሆኑም ባለፈ ዓለም አቀፉ ተቋም ኢትዮጵያ የስጋት ቀጣና ከመሆን እንዳትላቀቅ ያደርጋታል። ነገሩን ይበልጥ አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ በጀማሪ አትሌቶች ዘንድ መለመዱ ሲሆን፤ ለዚህም በማናጀሮች መመራት አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነው ዶክተር አያሌው የሚያብራሩት። የተጠናከረ አሠራር እንዲሁም ህግ ባለመኖሩ የውጭ ዜጎች የፈለጉትን ንጥረነገር ይዘው ወደ አገር በመግባት በተለያየ መንገድ አትሌቶቹ ጋር ሊደርሱ ይችላሉ። በአገር ውስጥ ያሉ የመድኃኒት መደብሮችም ቢሆኑ በቀላሉ መድኃኒቶችን ስለሚሸጡ አትሌቱ ሳይቸገር የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን የማግኘት ዕድሉ የሰፋ ነው።
ሌላው እንደ ወረርሽኝ በአትሌቱ ዘንድ እየተስፋፋ ያለው ጉዳይ ደግሞ የተለያዩ ቫይታሚኖችን መጠቀም መሆኑን ዶክተር አያሌው ያመላክታሉ። ይህም በጊዜ ሂደት እየተጠናከረ በመሄድ አትሌቶችን ወደ አበረታች ንጥረነገር ተጠቃሚነት ሊያደርሳቸው ይችላል። በመሆኑም ከዓመታት በፊት በስፋት የተካሄደው አገር አቀፍ ንቅናቄ በድጋሚ መጀመር አለበት። መንግሥታዊ ተቋማቱም ቢሆኑ በጉዳዩ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ባለሙያው ያሳስባሉ።
የአትሌቲክስ ስፖርትን የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነበት በፕሬዚዳንቷ ረዳት ኮሚሽነር ጀኔራል ደራርቱ ቱሉ በኩል አሳውቋል። ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉት መካከል ሲሆን፤ ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቷል። ነገር ግን በመሃል በመቋረጡ ምክንያት ጋብ ያለው ሁኔታ በድጋሚ እየተባባሰ መሆኑ ታውቋል። በግለሰቦች ጉዳይ አገሪቷ በዚህ መልክ ስሟ መነሳቱ ፌዴሬሽኑም ስጋት ላይ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ጉዳዩን የፌዴሬሽኑ ብቻም ሳይሆን የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚፈልግ ነው። ሁኔታው ካልተቀረፈ ግን አትሌቶችንና አሰልጣኞችን ከውድድሮች ማገድ ብቻም ሳይሆን የአገርን ጥቅምን በመንካት በህጉ መሠረት እንዲጠየቁ ማድረግ የግድ ነው።
የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን አበረታች ሥራ እያከናወነ መሆኑን የምትጠቁመው ፕሬዚዳንቷ፤ ችግሩ ግን አሁንም ድረስ ሊቀረፍ አልቻለም። አንጋፋዋ አትሌት ደራርቱ በሩጫ ዘመኗ የምታውቀው ንጹህ ስፖርት ነበር፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የአትሌት ተወካዮች ወይም ማናጀሮች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አትሌቶች በማይገነዘቡበት ሁኔታ ቫይታሚን አሊያም ሌላ መድኃኒት ነው በማለት ስለሚሰጧቸው ነው። ዓለም አቀፉ ተቋም ክልክል የሆኑ መድኃኒቶችን ዝርዝር በግልጽ ያስቀመጠውን በመመልከት አሊያም የፌዴሬሽኑን የህክምና ባለሙያዎች በማማከር መውሰድ ይገባቸዋል። ካልሆነ ግን በፍትሃ ብሔር እንዲጠየቁ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ እየሠራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ አሳስባለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም