ትናንት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ በየጥጋ ጥጉ ተጎሳቁለው ስናያቸው የነበሩ ባህላዊ ቁሳቁሶች ዛሬ አምረውና ደምቀው በአደባባይ መታየት ጀምረዋል። ለወትሮው በዘመናዊ የመኖሪያ ህንጻዎች የውስጥና የውጭ ግድግዳዎች ላይ የምናስተውላቸው ዘመናዊ ጌጣጌጦችም ኢትዮጵያዊ ባህል በሆኑ በእነዚሁ የስፌት ሥራዎች ተተክተዋል። እነዚህ የስፌት ሥራዎች በልዩ ልዩ ዲዛይንና ከዘመኑ ጋር በዘመነ መንገድ በእጅ ተሰርተው ለተለያየ አገልግሎት መዋል እየቻሉ ነው። በዚህም የበርካቶችን ቀልብ መያዝ ችለዋል።
አሁን አሁን እየተለመደ የመጣውና የበርካቶችን ቀልብ መግዛት የቻለው የስፌት ሥራን ኢትዮጰያዊ ከሆኑ እናቶቻችን በተጨማሪ በዘመናዊ መንገድ እያሳመሩ ወደ አደባባይ የሚያወጡት ወጣቶች ናቸው። የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችንም ኢትዮጵያዊ የሆነውን ቱባ ባህል በድንግዝግዝ ሳይሆን በግልጽ የተረዳች ወጣት ናት። ወጣቷ ስንደዶን ከመርፌ፣ ከክርና ከወርቀዘቦ እያዋሃደች ኢትዮጵያዊ መገለጫ የሆኑ ቁሳቁሶችን በአይነት በአይነቱ ሰፍታ ለገበያ ታቀርባለች።
የእጅ ሥራን በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ከሚኖሩ እናቶች እግር ሥር ተቀምጣ ነው የተማረችው። ያኔ ታድያ ሙያውን ለመቅሰም ስታስብ የደራውን ገበያ አስባ አልነበረም። “እንዲያው አለ አይደል!” ውስጣዊ ፍላጎቷን ለማሟላት እንጂ። ታዲያ ከጥልቅ መሻት የመጣው መነሳሳት የስፌት ሥራን እንዲሁም ጥጥ መፍተልን አቀላጥፋ መሥራት እንድትችል አገዛት። ይህ ደግሞ የስፌት ሥራዋን በዘመናዊ መንገድ ለማሳደግ በር ከፈተላት። ዛሬ ከአገር ውስጥ አልፋ በውጭው ዓለም ሳይቀር ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሥራዎቿን ታቀርባለች። በተለያዩ ውድድሮች ላይም ትሳተፋለች። እየደበዘዘ የመጣውን ኢትዮጵያዊ ቱባ ባህል እየተረተረች ከአገር አልፋ ለዓለም ማሳየት የቻለችው ወጣት አርክቴክት አራራት ታምራት “የቱባ ባይ አራራት” መስራችና ባለቤት ናት።
ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ መሀል አራት ኪሎ ነው። ከልጅነት ዕደሜዋ ጀምራ ለእጅ ሥራዎች ትኩረት ትሰጣለች፤ መሥራት ያስደስታታል። በተለይም በቤታቸው የነበሩ የተለያዩ የስፌት አይነቶች ትኩረቷን ይወስዱት እንደነበርም አትዘነጋም። ውስጣዊ ፍላጎቷ የሆነውን የእጅ ሥራ ለመልመድና ለመሥራት የተነሳሳችውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ መሆኑን አጫውታናለች።
አራራት በሙያዋ አርክቴክት ብትሆንም ለሥራዬ ያግዘኛል ያለችውን አካውንቲንግና ማኔጅመንትን ጨምሮ የተለያዩ ኮርሶችን ወስዳለች። ‹‹ከልብ ካለቀሱ እምባ አይገድም›› እንዲሉ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በምትማርበት ጊዜ ውስጣዊ ፍላጎቷ የሆነውን የእጅ ሥራ በቀላሉ መልመድ ችላለች። የለመደችበት መንገድም በጎንደር ገበያ ጥጥ የሚፈትሉ፣ የስፌት ሥራና ሌሎች የእጅ ሥራዎችን ከሚሠሩ ሰዎች ጋር በመወዳጀት ነው። አሠራሩን ጠይቃ በመረዳት የተረዳችውንም በተግባር በማዋል ዛሬ የስፌት ሥራዎችን በተለያየ ዲዛይን እያሳመረች ለገበየ ታቀርባለች።
የእጅ ሥራዎቿም አይነ ግቡ የሆኑ፣ ቀልብን የሚስቡና እጹብ ድንቅ ናቸው። እንደዘበት የተረሳውን፣ ኢትዮጵያዊ መገለጫ የሆነውን ቱባ ባህሎች ማስታወስ የሚያስችሉም ናቸው። አገርኛ ቀለም የያዙ ቱባ ባህሎችም ዛሬ ከወዳደቁበት ተነስተው አቧራቸው በመራገፉ ከራስ አልፈው በውጭው ዓለም መታወቅ ጀምረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመናዊ መንገድ በመሰራታቸው ትኩረት ያገኙት የእጅ ሥራዎቹ ከቤት ውስጥ መገልገያነት ባለፈ የቤት ውስጥ ማስዋቢያና ጌጥ ሆነው በትላልቅ ሆቴሎች፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ መታየት ጀምረዋል። የስፌት ሥራዎቹ ዛሬ ላይ ለመድረሳቸው ኢትዮጵያዊ እናቶች ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም በተለይም የስፌት ሥራዎቹ ከዘመኑ ጋር ዘምነው ከአገር አልፈው በውጭው ዓለም ለመቅረባቸው ግን እንደ አራራት አይነት ወጣቶች ጉልህ ድርሻ አላቸው።
የእጅ ሥራ ሞያን ከውስጧ በመነጨ ፍላጎት መማር የቻለችው አራራት፤ ለሙያው ፍላጎት ቢኖራትም ቁሳቁሶቹን ከመገልገያነት ውጭ በቤት ውስጥ ሲሰራ ያየችው ሰው አልነበረም። ያም ቢሆን ግን ሙያውን የመልመድ ጥሩ አጋጣሚ አግኝታለች። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ በለመደችው የስፌት ሥራ ገቢ ከማግኘቷ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊ የሆነውን ቱባ ባህል በዘመናዊ መንገድ ለጌጣ ጌጥና ለመገልገያ መዋል እንዲችል ማድረጓ በእጅጉ እያስደሰታት የመጣ ጉዳይ መሆኑን ትናገራለች።
‹‹የስፌት ሥራ ኢትዮጵያዊ ባህላችንን ከሚያንጸባርቁት እንደ ሸክላና እንደ ሽመና ሁሉ ማንነታችንን የሚገልጽ የጥበብ ሥራ ነው›› የምትለው አራራት፤ በጎንደር ቆይታዋ ከትምህርቷ ጎን ለጎን የስፌት ሥራን በቀላሉ መልመድ ችላለች። እርሷ ይህን የጥበብ ሥራን ለመማር ዝግጁ እንደነበረችው ሁሉ የጎንደር እናቶችም ሙያውን ለማስተማር ፍጹም ፈቃደኞች እንደነበሩ በማስታወስ፤ ከመግዛት ባሻገር ሰዎች ባህላቸው ሲታወቅላቸው የሚያስደስታቸው እንደሆነ ነው የተረዳቸው።
የአርክቴክት ትምህረቷን አጠናቅቃ፤ የስፌት ሙያንም ለምዳ ወደ ሥራ የገባችበት ወቅት የኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን የመጡበት ወቅት መሆኑ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላት ታስታውሳለች። በወቅቱ በርካታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የውስጥ ዲዛይን ሥራን በመሥራት የተዋቡ ቢሮዎች እንዲኖራቸው ተደርጓል።በመሆኑም ለወትሮው ምንም አይነት ውበት ያልነበራቸውና የእቃ ማጠራቀሚያ ይመስሉ የነበሩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ የውስጥ ዲዛይን አሰርተዋል። በዚህ ወቅት ታድያ የአርክቴክት ሙያዋን ተጠቅማ ወደ ሥራው የመግባት ዕድል ያገኘችው አራራት፤ የብዙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ቢሮ የውስጥ ዲዛይን ሥራ መሥራቷም በእጅጉ ጠቅሟታል።
ከውስጥ ዲዛይን ሥራዋ ጎን ለጎንም ታስብ የነበረው ባህላዊ ቁሳቁሶችን ዘመናዊ በማድረግ ወደ ፊት ማምጣት ነበር። በወቅቱም መሰል ሥራዎች ገና አልተጀመሩም። ይሁን እንጂ እርሷ እንደ አርክቴክት የተለያዩ ንድፎችን ባልተለመደ ቀለምና ፓተርን ተመሳሳይ የሆኑ ቁሳቁሶችን በኮምፒውተር ታዘጋጅ ነበር። በውስጥ ዲዛይን ሥራዋ ወቅት ያስተዋለችውን ክፍተትም ባዘጋጀቻቸው ዲዛይኖች ለመሙላት ወስና ወደ ሥራው ገባች። ወደ ሥራው ስትገባ ታድያ እንደዋዛ አምስት ሺ ብር በመያዝ ስንደዶ፣ ሰበዝና ክር በመግዛት ነበር።
በቤቷ ውስጥ ተቀምጣ ከጀመረችው ሥራዎቿ መካከል በስፌትና በክር የተሠሩ የአበባ ማስቀመጫ ገንቦዎች ቀዳሚዎች ነበሩ። ገንቦዎቹን ለደንበኞቿ ማቅረብ ጀመረች። ሥራዎቿ ተቀባይነት እያገኙ ቀስ በቀስ እያደገ መምጣት ሲጀምርም ሥራዋን በማስፋት አንድ ሁለት በማለት ሠራተኞችን በመቅጠር ቱባ ባይ አራራት በሚል ስያሜ ድርጅቷን ማቋቋም ቻለች። በአምስት ሺ ብር እንደቀልድ የተጀመረው የስፌት ስራም አሁን ላይ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በስፌት ሥራዎቿ የተለያዩ የቤት ውስጥና የቢሮ ጌጣ ጌጦችን እና የመገልገያ ቁሳቁሶችን በመሥራት ለገበያ እያቀረበች የምትገኘው አራራት፤ ሥራዎቿን በሒልተን ሆቴል፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በተለያዩ ሎጆች ውስጥ የሚገኙ እንደሆነ አንስታለች። ከምትሠራቸው የሥፌት ሥራዎች መካከል አንደኛው እርቦ የሚባለው ሰፌድ ሲሆን ሰፌዶቹ የተለያየ አይነትና መጠን ያላቸውና ለግድግዳ ጌጥ መሆን የሚችሉ ናቸው።
ከሰፌዶቹ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የአበባ ማስቀመጫ ገንቦዎችንም እንዲሁ በዲዛይንና መቀለማቸው በማመሳሰል የምትሠራ ሲሆን በሽመና የሚሠሩ የሶፋ ትራሶች፣ ከምንጣፍና ከመጋረጃዎች ጋር በማመሳሰል እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በዲዛይንና በቀለም አመሳስላ ትሠራለች። የስፌቱም ሆነ የሽመና ሥራው አርት ነው የምትለው አራራት፤ የዲዛይንና የቀለም ሥራው ኮምፒዩተር ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰዎች እጅ የሚሠራ እንደሆነም አስረድታለች።
ሥራው በእጅ የሚሠራ እንደመሆኑ በአሁን ወቅት ለሥራው ንቁና ብቁ ለሆኑ 40 ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሴቶችም የቤት እመቤት የሆኑና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ የጎንደር ሴቶች እንደሆኑ ትናገራለች። ከእግራቸው ስር ተቀምጣ የስፌትና ጥጥ የመፍተል ሞያን የተማረችው አራራት፤ የሥራ ዕድሉንም ለእነዚሁ ሴቶች ሰጥታለች። ሴቶቹ ለቤታቸው አገልግሎት የሚውል እንዲሁም ትናንሽ ወጪያቸውን ለመሸፈን ያስችላል በሚል የተሰማሩበት የስፌት ሥራ በቋሚነት ገቢ እንዲያገኙበት አድርጓቸዋል።
ሥራውን የሚሠሩት ሴቶች በተለያየ ምክንያት ሙሉ ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ የሚያሳልፉ እናቶች እንደሆኑ ያነሳችው አራራት፤ በተለይም የስፌት ሥራ ሙያው እያላቸው ነገር ግን ሥራውን ገቢ ማግኛ ያላደረጉና በተለያዩ ጫናዎች ከቤት መውጣት ያልቻሉ እናቶች ከቤት ሳይወጡ ሠርተው ገቢ ማግኘት የቻሉበት መንገድ በመፈጠሩ እጅግ ደስተኛ እንደሆነች ትናገራለች። ሥራውን ለመሥራት የሚያስችሉ ስንደዶ፣ ሰበዝ፣ የተለያዩ ክሮች፣ መስፊያና ሌሎች ግብዓቶች ጭምር ባሉበት የሚቀርብላቸው ሲሆን በኮምፒዩተር የተዘጋጀው ዲዛይንም በወረቀት ይቀርብላቸውና ዲዛይኑን መሠረት አድርገው ይሠራሉ።
የስፌት ሥራዎቹ በአገሪቱ የተለያ አካባቢዎች የተለመዱ ቢሆንም እንደየ አካባቢውና አሰራሩ የሚለያይ እንደሆነ ያስረዳችው አራራት፤ በተለይም በሀረርጌና በጉራጌ ማህበረሰብ በስፋት የሚታወቁ ስለመሆናቸው ታነሳለች። ሙያውን የለመደችው በሰሜኑ የአገሪቱ አካባቢ እንደመሆኑ በአካባቢው የተለመደውን በክር የሚሠራውን ስፌት ትሠራለች። የስፌት ሥራውም በስንደዶው ላይ የተለያዩ ቀለማት ያላቸው ክሮች በተቀመጠው ዲዛይን መሰረት የተጠለፉ እጅግ የተንቆጠቆጡ የስፌት እና የአበባ ማስቀመጫ ገንቦዎች ናቸው። ከአካባቢው ባገኘችው ልምድና ዕውቀት በመነሳት ወደ ሥራ የገባቸው አራራት፤ ቁሳቁሶቹን የምታሠራው በጎንደርና ባህርዳር አካባቢ ነው።
ለስፌት ሙያና ለጥጥ መፍተል ባላት ተነሳሽነት ሙያውን ተምራ ወደ ሥራ መቀየር የቻለችው አራራት፤ ተዘንግቶ የቆየውን ቱባ ባህል በዘመነ መንገድ ከማስተዋወቅ ባለፈ ምርቶቿን ለውጭ ገበያ በማቅረብም የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራች ትገኛለች። ኢትዮጵያዊ ማንነትን አንጸባርቆ የሚያሳይ ስዕል በመፍጠር ሰዎች ወደ ቱባ ባህላቸው መመለስ እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈም የስፌት ሥራ ዓለም አቀፍ እንዲሆን እያደረገች ትገኛለች።
“ባህላዊ የሆነን ማንኛውም ነገር ከዘመኑ ጋር አቆራኝቶ ማቅረብ ሲቻል የራስ የሆነ እሴትን ማቆየትና ለትውልድ ማስተላለፍ ይቻላል” የምትለው አራራት፤ ከዚህ ቀደም እናቶች ብቻ ይለብሱት የነበረው የሀገር ባህል አልባሳት አሁን ላይ ባለስልጣናቱን ጨምሮ ወንዱም፣ ሴቱም፣ ህጻናቱም በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚዋቡበት ትገልፃለች። ይህ የሆነውም አልባሳቱ በዲዛይነሮች አማካኝነት እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ መቅረብ በመቻሉ እንደሆነ ትናገራለች። እርሷም በስፌት ሥራዎቿ በተለይም ወጣቱ ላይ ትኩረት በማድረግ እየደበዘዘ የመጣውን ባህል በጥሩ ጎኑ እንዲነሳና በስፋት እንዲተዋወቅ እያደረገች መሆኑን ነው የገለፀችልን።
እየደበዘዘ የመጣውን ኢትዮጵያዊ ቱባ ባህል ከማስታወስ ባለፈ በውጭው ዓለም እንዲተዋወቅ እያደረገች የምትገኘው አራራት በስፌት ሥራዎቿ ተወዳድራ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ አገራት ተጉዛለች። በቅርቡ ኔዘርላንድ ኤምባሲ ባዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳትፋ አሸናፊ በመሆን ወደ ኔዘርላንድ በመሄድ የእጅ ሥራዎቿን አቅርባለች። በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩ በርካታ አገራት ጋር የመገናኘት ዕድል የገጠማት ሲሆን፤ ብዙ አፍሪካ አገራት በዘርፉ ሩቅ እንደተጓዙና ኢትዮጵያ ደግሞ ወደኋላ እንደቀረች መታዘብ ችላለች።
“የገበያ ክፍተት አለ ማንም ውስጣዊ ፍላጎት ያለው ሰው ገብቶ ቢሰራበት ተጠቃሚ ይሆናል” የምትለው አራራት፤ ትላልቅ በሚባሉ ሁነቶች ላይ መሳተፍ በመቻሏ በውጭው ዓለም የመታወቅ እድል ፈጥሮላታል። ለአብነትም እንደ አፍሪካ ህብረት የመሳሰሉ ጉባኤዎች ላይ በመሳተፍ የስፌት ሥራዎቿን ታቀርባለች። በዚህ አጋጣሚም ከአፍሪካ ሚዲያዎች ጋር የመተዋወቅ እድል አግኝታ ደቡብ አፍሪካ በሚገኝ Lioness of Africa በተሰኘ መጽሔት ምርጥ ሥራ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊ ወጣት በሚል በፊት ገጽ ወጥታለች።
በአሁን ወቅት ወጣቱ የተዘነጋውን ቱባ ባህል በዘመናዊ መንገድ ሠርቶ ለዓለም የማቅረብ ሰፊ ዕድል ያለው መሆኑን ያነሳችው አራራት፤ ለዚህም በቂ የሰው ኃይልና አስፈላጊው ግብዓት መኖሩን በመጥቀስ የዓለም አገራት በቴክኖሎጂው መድረስ የሚገባቸው ደረጃ ደርሰዋል። በአሁን ወቅት ደግሞ ትኩረታቸውን እየሳበ ያለው ባህላዊ ቁሳቁሶች ናቸው። በመሆኑም ወደ ኋላ በመመለስ ባህሉ ላይ ትኩረት እያደረጉ ነውና ይህን ዕድል በመጠቀም ኢትዮጵያዊ ባህሎቻችንን ማውጣት ይኖርብናል ትላለች።
በቀጣይም ሥራዋን በማስፋት ለበርካታ ሴቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ ያላት አራራት፤ ቀደም ባሉት ግዜያት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ሰፋፊ እቅድ የነበራትና በዚያም መሰረት ሥራውን ጀምራ የነበረ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት መበላሸቱን ታስታውሳለች። አሁን ሰላም ከሰፈነ ወደ አካባቢው በመሄድ የስፌት ሥራውን በስፋት ለመጀመር በአካባቢው ለሚገኙ ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር እቅድ እንዳላት ነግራናለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም