ኢትዮጵያውያን ጀግንነታችንን፣ አትንኩኝ ባይነታችንና ለነጻነት የምንሰጠው የላቀ ዋጋና ይህንኑም ለማረጋገጥ የከፈልነውን ውድ መስዋዕነትት ዓለም ሁሉ የሚያደንቀው መልካም ዕሴታችን ነው። አሁን አሁን እየተሸረሸረ መጣ እንጂ ሃቀኝነታችን፣ እንግዳ ተቀባይነታችንና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ማህበራዊ ኑሯችን በዓለም ላይ የሚያስከብሩንና የሚያኮሩን ውድ ባህሎቻችን ናቸው። በአንጻሩ እኛ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ከምንተችባቸውና ከምንታማባቸው ነገሮች መካከል ደካማ የንባብ ባህላችን ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል።
ሃሜት ብቻም ሳይሆን ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ አንድ ጥናት የንባብ ባህላችንን በእጅጉ ደካማ መሆኑን አመላክቷል። ዋና ከተሞቻቸውን እንደማሳያ በመውሰድ የዓለም አገራትን የንባብ ባህል የገመገመው ጥናት እንደ ጃፓንና ጀርመን የመሳሰሉትን አገራት በማንበብ ባህላቸው ከፍተኛ ደረጃ መድረሳቸውን የጠቆመ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ያለው የንባብ ባህል ግን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሷል። የዓለም አገራት ዋና ዋና ከተሞችን የንባብ ባህል “ከፍተኛ”፣ “መካከለኛ” እና “ዝቅተኛ” በሚል በሦስት ምድብ ውስጥ በቅደም ተከተል ስማቸውን ያስቀመጠው ጥናቱ የእኛዋን አዲስ አበባ ግን ዝቅተኛም ቢሆን ከነጭራሹ ደረጃ ውስጥ ሳያስገባት “የማታነብ ከተማ” በማለት ተሳልቆባት አልፏል።
የንባብ ባህላችንን በሚመለከት የተሠራው ጥናት ውጤቱ ቢመረንም ሃቁ ግን ይኸው ነው። የማያነብ ሕዝብ ደግሞ የብልጽግና ትንሳኤው ሩቅ ነውና ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ የንባብ ባህላችን ለማሻሻል እንደዜጋ እያንዳንዳችን የበኩላችን መወጣት ይጠበቅብናል። የዛሬው ትዝብቴ በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል። በነገራችን ላይ የንባብ ባህል ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም። ጀርመናውያን በአንድ ወቅት “በመጸዳጃ ቤቶቻችን የምናነበው ነገር ይቀመጥልን” በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው መንግሥታቸውን መጠየቃቸውን ታሪክ ይነግረናል።
እናም ታሪክ ጥራዝ ነጠቆች እንደሚሉት ፋይዳ የሌለው ባዶ ተረት ተረት አይደለምና፤ ሰዎች በተግባር አድርገው ለትውልድ ያስተላለፉት ሰርቶ ማሳያ ቅርስ ነውና እኛም ከዚህ ታሪክ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር አለ። ይህም ጀርመናውያኑ እንዲህ ዓይነቱን ድንቅ የንባብ ባህል እንዴት አዳበሩት?፣ እኛስ የንባብ ባህላችንን ለማሻሻልና እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን እንድናጤን ዕድል የሚፈጥር ነው።
ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ትልቅ ቁም ነገር ጀርመናውያኑ መጸዳጃ ቤት ውስጥም ሆነው ማንበብ ይፈልጋሉ ማለት እጅግ የሚደነቅ ከፍተኛ የሆነ የንባብ ባህል አላቸው ማለት ነው። ለመሆኑ ጀርመናውያኑን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሳይቀር እንዲያነቡ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድነው? እንዲህ ዓይነቱን አንባቢነትስ “የንባብ ባህል” የሚለው ብቻ ይገልጸዋልን? ደካማውን የንባብ ባህላችንን ለማሻሻል እነዚህን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመርመርና መመለስ ይገባል። ምክንያቱም የንባብ ባህላችን ለማሻሻል ትልቁ ምስጢር ያለው በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ነውና።
አዎ፣ የዳበረ የንባብ ባህልን ለመፍጠር በቅድሚያ “የንባብ ፍቅር” ሊኖረን ይገባል። አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር፤ እንደ አገር የዳበረ የንባብ ባህል ባለቤት ለመሆን መፍትሄውም ይኸው ነው-መጽሐፍትን ማፍቀር፣ ንባብን ማፍቀር! ምክንያቱም አንድን ነገር ሳንፈልገው ወይንም ሳንወደው እንዴት እንዲኖረን እናደርገዋለን? በምንፈልገው ነገር ላይ ጥሩ ችሎታ እንዲኖረን ከፈለግን ደግሞ ከሁሉም በፊት ለዚያ ነገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል። ከላይ የተገለጸው የጀርመናውያኑ ታሪክም የሚያሳየን ይህንኑ ነው። እነሱ አይደለምና በመደበኛው ጊዜያቸው በዚያች የደቂቃ የመጸዳጃ ቤት ቆይታቸውም የሚነበብ ነገር ማጣት አይፈልጉም።
ለምን ቢሉ ንባብን ያፈቅሯታልና! ከማንበብ ፍቅር ይዟቸዋልና! ይህም የንባብ ፍቅራቸው በከፍተኛ ደረጃ የዳበረና የበለጸገ የንባብ ባህልን ፈጠረላቸው። የእኛም አገር ችግር የንባብ ባህል አለማደግ ሳይሆን የንባብ ፍቅር አለማደግ ይመስለኛል። ለመሆኑ ማንበብ እንወዳለን? ስንቶቻችን ነን ለመደበኛ ትምህርት ወይም የሆነ አስገዳጅ ነገር ተፈጥሮብን ካልሆነ በስተቀር ለንባብ ፍላጎት ኖሮን፣ ፍቅሩ ኖሮን የምናነበው? ማንበብን የምናስበውስ እንዴት ነው? እንደአንድ አስጨናቂ ሥራ ወይስ እንደ አዝናኝ የአዕምሮ ምግብ? መልሱን ለእያንዳንዳችን ልተወው።
ከዚሁ ከንባብ ፍቅር ጋር በተያያዘ አንድ ወዳጄ ያወራኝን ቀልድ የምትመስል ዕውነት ነግሬያችሁ ወደ ቀጣዩ ሃሳቤ ልለፍ። “ልጆች ያስቀመጥከውን ብር እያነሱ ካስቸገሩህ መጽሐፍ ውስጥ ደብቀው፣ ሌባ ይወስድብኛል የሚል ስጋት ካለህም ይህ ዘዴ ግሩም መፍትሄ ይሆንልሃል”። አይገርምም? በእኛ አገር መጽሐፍት የሚፈለጉና የሚፈቀሩ ሳይሆኑ የሚያስፈሩና የሚያስጠሉ ናቸው ማለት ነው? ታዲያ እውነት መጽሐፍትን እየፈራናቸውና እየጠላናቸው፤ እንዲህ እየሰለቸናቸው ከሆነ እንዴት ነው የንባብ ባህላችን የሚያድገው?
ይሁን እንጂ በተለያዩ መስኮች የዓለማችንን ስልጣኔ ከፊት ሆነው በፊታውራሪነት የመሩ ሁሉም ታላላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብዕናዎች ለንባብና ለመጻሕፍት ልዩ ፍቅር ያላቸው ናቸው። በአንድ ወቅት መላ አውሮፓን ጠቅልሎ ከገዛው ታላቁ ንጉስ ናፖሊዮን ቦናፖርቲ፣ ከአንድ ሺ በላይ ፈጠራዎችን እስካበረከተው ቁንጮ ሳይንቲስት ቶማስ ኤዲሰን፤ ከባለቅኔው ሸክስፔር እስከ ፈላስፋው ሶረን ኪርክጋርድ ሁሉም ስለመጻሕፍት ያልተቀኘ የለም።
“የታላቅ አገር መሠረቱ የሕዝብ አንድነት ነው” በሚል ፍልስፍናቸው የሚታወቁትና በግለኝነት አስተሳሰብ በዘቀጡ ዘመነ መሳፍንታውያን ተከፋፍላ የተዳከመችውን ኢትዮጵያን ሕይወታቸውን ጭምር በመክፈል ወደ ቀድሞ አንድነቷ የመለሷት፤ ለታላቅነቷ ታላቅ ራዕይን ይዘው ሕይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ የታገሉላት፣ የጀግንነትና የታላቅ ስብዕና ምልክት የሆኑት ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሠት አፄ ቴዎድሮስም ለመጽሐፍ ልዩ ፍቅር ነበራቸው። በዚህም ንጉሡ በሕይወት ዘመናቸው ልዩ ልዩ ዕውቀትና ጥበብ የያዙ እስከ አንድ ሺ የሚደርሱ መጽሐፍትን በመቅደላ ጊዜያዊ ቤተ መንግሥታቸው ሰብሰበው እንደነበር የአገር ውስጥና የውጭ የታሪክ ምሁራን ጽፈዋል።
እናም ብሒላችን እንደሚለው “ከመጠምጠም ማወቅ ይቅደም”። የንባብ ባህላችን እንዲዳብር ከፈለግን በቅድሚያ ለመጻሕፍት ያለን ፍቅር እናሳድግ። የንባብ ባህላችን እንዲዳብር መጻሕፍትን እንደእናትና አባቶቻችን፣ እንደምንወዳቸው ፍቅረኞቻችንና የትዳር አጋሮቻችን፣ እንደምንሳሳላቸው ልጆቻችን ከልባችን ልንወዳቸውና ልናፈቅራቸው ይገባናል።
ውሃን ከጥሩ ቢጠጡት፣ ነገርን ከሥሩ ቢሰሙት መልካም ነውና፤ ስለንባብ ፍቅር የዓላማችን ታላላቅ ሰዎች በተናገሩትና በተግባር በኖሩበት አባባሎቻቸው የዛሬውን ትዝብቴን ላጠቃልል።
“ሁልጊዜም ትንሿን ልጄ ስለማስደሰቴ ሐሴት ይሰማኛል-እርሷ መጽሐፍትን የመውደዷን ያህል ደግሞ የሚያስደስተኝ ምንም ነገር የለም። ምክንያቱም እንደ እኔ እድሜዋ ሲገፋ መጽሐፍት ከየትኛውም ኬክ፣ አሻንጉሊትና ከማንኛውም ጨዋታና ትዕይንት ሁሉ የተሻሉ መሆናቸውን ትገነዘባለች።
ማንም እስከ ዛሬ ከኖሩት ነገስታት ሁሉ ታላቁ እንዲሁም ባለ ቤተ መንግሥትና ባለ አትክልት ሥፍራ ቢያደርገኝ፣ የተመረጠ የእራት ግብዣ ከወይን መጠጥ ጋር የሚቀርብልኝ ንጉሥ ሊያደርገኝ ቢፈልግ እንኳ መጽሐፍትን የማነብበት ዕድል ከሌለኝ ንጉሥ መሆንን ነፍሴ አትቀበለውም። ማንበብን የማያፈቅር ንጉሥ ከመሆን ከበርካታ መጽሐፍቴ ጋር በአንዲት ትንሽ ክፍል ብታጎር እመርጣለሁ።”
ሎርድ ማክዋሌ፣ ብሪታኒያዊ ታሪክ ጸሐፊ፣ ሃያሲና ፖለቲከኛ
“የመጽሐፍት ፍቅር በየዕለቱና በየሰዓቱ ገደብ የለሽ የሆነ በማንም ጥገኛ ያልሆነ አግባብነት ያለውን የፍስሐ ምንጭ ይከፍትልናል። እናም ከቀኑ የተወሰኑ ሰዓቶቹን በክፍሉ ውስጥ ሆኖ በመጽሐፍት ውስጥ ከሚኖሩ ከበሬታን የሚያላብሱ ታላላቅ ሰዎች ጋር ከማያሳልፍ ሰው ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ዋጋ ያለውን አንዳች ነገር ተስፋ ማድረግ አያስፈልንም።”
ፍሪዴሪክ ፉበር
“የመጽሐፍት ፍቅር ብዙ ጠባብ ነፍሳትን አስፍቷል፤ ብዙ የተዘጉ፣ የተገደቡ፣ መስኮት አልባ ልቦችን በተራራማ አየርና የፀሐይ ብርሃን ሞልቷል፤ ለመለኮትም ሆነ ለስብዕና አስቀድሞ ክፍል ያልነበራቸው ቤቶችን አስለቅቆላቸዋል።”
ይበል ከሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም