በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሌብነት መንግሥታዊ ሥርዓትን በመላበሱና አቅሙ በመደንደኑ የአገር ህልውና ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ዜጎች መብቶቻቸውንም ሆነ አገልግሎት ያለ ጉቦ ማግኘት ህልም እየሆነባቸው መምጣቱን ያነሳሉ፡፡ መንግሥትም ቢሆን ሌብነት በራሱ መዋቅር ውስጥ ከላይ እስከ ታች ሰንሰለት ፈጥሮ አላሰራ እንዳለው በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይደመጣል፤ ጥቂትም ቢሆኑ ሌቦችን ተጠያቂ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የችግሩን አሳሳቢነት፤ ለአገር ህልውና ስጋት እየሆነ ስለመምጣቱ ለአባላቱ አስረድተዋል፡፡ ይህንን የአገርና የሕዝብ እድገት ፀር የሆነ ክፉ ባህል መንቀል ያስችለው ዘንድ ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ አቋቁሞ በሌብነትና በሌቦች ላይ ሊዘመት እንደሆነ አብስረዋል፡፡ ለመሆኑ ይህ የመንግሥት እርምጃ እንዴት ከስኬት ይደርሳል? ምንስ ሊሠራ ይገባል? በሚሉ ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ የሕግ ባለሙያ፤ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ መስኡድ ገበየው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ስለመጣው ሌብነት ወይም ሙስና አጠቃላይ ገፅታ ምን እንደሚመስል ያብራሩልንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ መስኡድ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ሌብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረና በጣም ተቋማዊ በሚመስል ደረጃ ጎልብቶና የአገር ህልውና ስጋት ሆኖ ነው የሚታየው። ግለሰቦች ሳይቀሩ ምንም ዓይነት ተጠያቂነትን ባለመፍራትም ጭምር በአደባባይ የሚያደርጉት ነገር እየሆነ መጥቷል። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ይሄ ሪፎርም እንዲመጣ አንዱ መነሻ ምክንያት ሕዝቡ በመንግሥታዊ ሌብነት እጅግ በመማረሩና ያንን ለማስወገድ በተደረገ ትግል ነው። በተለይም በሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው እንደመሬት አስተዳደርና ገቢዎች አካባቢ ምንም ዓይነት አገልግሎት ለማግኘት ገንዘብ መክፈል ግዴታ የነበረበትና ያ ደግሞ ሕዝቡ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ መንግሥት ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሮ ወደ ተቃውሞ እንዲያመራ ምክንያት ሆኗል።
ለውጡ ከመጣ በኋላ የዶክተር ዐቢይ መንግሥት በተለይ ከባድና ቆራጥ እርምጃ እወስድባቸዋለሁ ብሎ ከጀመራቸው ሥራዎች አንዱ የሌብነቱ ጉዳይ ነው። እንደምናስታውሰውም ‹‹ሙስና እያሉ ማንቆለባበስ አያስፈልግም፤ ሌብነት ሌባ ብለን በስሙ ልንጠራው ይገባል›› በማለት በአደባባይ ሲናገሩ አድምጠናል። በዚህ ላይ መንግሥታቸው ምንም ዓይነት ርህራሄ የሌለው እንደሆነ ተናግረውም ነበር። ሆኖም ለውጡን ተከትሎ የነበረው አንዳንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው ግጭት የመንግሥትን ትኩረት በመሳቡ ሌብነት ላይ ለማድረግ ታቅዶ የነበረውም እርምጃ መሬት ላይ ሳይወርድ ቀርቶ ቆይቷል። ይህን ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሌቦች ከፍተኛ የሆነ ሰንሰለት በመፍጠር የተደራጁበት ሁኔታ ነው ያለው።
ይሄ እንግዲህ በሁሉም ዘርፎች ላይ ጎልቶ የሚታይ ከመሆኑም በላይ በጣም ስር የሰደደ ሰዎች በሌብነት ሀብት ማፍራትን፤ ገንዘብ ማግኘትን፤ ገንዘብ ያገኙ ሰዎችን ወደ ድህነት መቀየር ሳይቀር በዚህ ደረጃ በጣም ተንሰራፍቶ በተለይ በአንዳንድ ተቋማት ጥቅሙ በገሃድ ማንም ሰው ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ሲያደርግ ነበር። ለምሳሌ ይሄ መሬት አስተዳደር፤ በጉምሩክ አካባቢዎች ጎልቶ ይታያል። ለዚህም ነው ከኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ይሄን ያክል ሚሊዮን ዕቃ በቁጥጥር ስር ዋለ ሲባል የምንሰማው። ሆኖም እነዚህ እንቅስቃሴዎች አልፎ አልፎ የሚደረጉ ናቸው። በየጊዜው ምንያክል የሕዝብ ሀብት እንደሚባክን፣ እንደሚበዘበዝ፤ አላግባብ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዕቃዎች እንደሚገቡ መገመት የሚቻል ነው። ስለዚህ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት አሁን ላይ መንግሥትም በከባድ ሁኔታ እየተፈተነበት ያለ መሆኑ እሙን ነው።
ለዚህም ነው በቅርቡ ሁላችንም እንደሰማነው መንግሥት ይህንን ልዩ ራሱን የቻለ ሁኔታ የሚመራ ግብረኃይል አቋቁሞ የነፃ የስልክ መስመር ከመዘርጋት ጀምሮ፤ ግብረኃይሉ ወደ ተግባር ገብቶ ውጤት ማምጣት እንዲችል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ያደረገው። በዚህ አጋጣሚም እያንዳንዱ ሰው በማናቸውም መልኩ ጥቆማቸውን በመስጠት፤ መረጃን በማጋራት፤ ሌሎችንም ከሕዝብ የሚፈለጉ ማናቸውንም ትብብሮች በማድረግ ይህንን የፀረ-ሌብነትን ዘመቻ ሁሉም ሰው እንዲያግዝ ጥሪ አቅርቧል። እንግዲህ እኛም የሲቪል ሶሳይቲ ማህበራት ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ አንዱም የምንሠራበት የትኩረት አቅጣጫችን በመሆኑ ሌብነት ባለበት ሰብአዊ መብት አይከበርም፤ ሰላም አይመጣም ብለን ነው የምናምነው። ምክንያቱም ሌቦች ሰላም በተፈጠረ፤ አገር በተረጋጋና ሥርዓት በተዘረጋ ጊዜ ቦታ ስለማያገኙ አይመቻቸውም። ሌብነት በራሱ ሥርዓት አልበኝነት ስለሆነ የእነሱ መጠቀሚያቸው ሰላም እንዲመጣ አይፈልጉም።
አንዳንዴም ግጭቶችንም በማባባስ፤ ስፖንሰርም በማድረግም ጭምር ለሌብነት እንዲመቻቸው ሲያደርጉ ይስተዋላል። የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው በዚህ ዓይነት መልኩ እኛ በተለያየ ጉዳዮች ላይ በምናተኩርበት ጊዜ እነሱ ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአገርን ክብር በሚያዋርድ መልኩ በሌብነት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰማርተው ይገኛሉ። አሁን ላይ ሌቦቹ በጣም ከባድ የሆኑ ሰንሰለቶችን በመፍጠር ሕዝብና አገርን እንደሚበዘብዙ በቅርብ የወጣው የመንግሥት መግለጫ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምክር ቤት ቀርበው ያስረዱት ይህንኑ ነው። ስለዚህ ይሄ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ጥሩና ይበል የሚያሰኝ ነው ባይ ነኝ። ምክንያቱም እኛ ሁሌም የምንወተውተውና መንግሥት ይሄንን የሌብነት ጉዳይ ትኩረት አልሰጠውም የምንለው ነገር በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ባለው ሂደት መንግሥት ሌብነትን ለመዋጋት የተለያዩ ሥራዎችን ቢሠራም ለውጥ ሊመጣ ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ? ጥቂት ሰዎችን ብቻ ማዕከል ያደረገ እርምጃስ ምን ያህል አስተማሪ ነው?
አቶ መስኡድ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁንም ትልቁ ችግር ሌብነት ተቋማዊ መሆኑ ነው። ይህ በመንግሥታዊ መዋቅር ሁሉ ስር የሰደደውን ሌብነት አንድን አመራር ፍርድ ቤት በማቅረብ፤ ተጠያቂ በማድረግ የሚፈታ አይደለም። እርግጥ ነው የሥራ ኃላፊዎች ተቋሙን በሚመሩ ጊዜ በግዴለሽነት ወይም ደግሞ አውቀው እንዲህ ዓይነት ነገሮች እንዳይፈፀሙ ለማድረግና አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር ሊጠየቁ ይችላሉ፤ ይገባልም። ጥያቄው ግን ሌብነት የሚባለው ጉዳይ ሥርዓታዊ በሆነ በራሱ የሌብነት ሰንሰለት ተዘርግቶ ልክ ከከፍተኛ አመራሮች ጭምር እየተሠራ ያለበት ጉዳይ መሆኑ ነው። እርግጥ የመንግሥት ሰዎች ይህንን አያውቁም፤ ወይ ደግሞ ከእነሱ ትኩረት የተሰወረ ነው ልንል አንችልም። ምክንያቱም አሁንም በመንግሥት መዋቅር ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እየተመዘበረ ነው ያለው።
ስለዚህ የፀረ-ሌብነት እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ ውጤት እንዳያመጣ ምክንያት የሆነው ባህል ሆኖ እንደመብት የተቆጠረበት ደረጃ በመድረሱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አንዳንድ አመራሮች ስለሚሳተፉበት ራሳቸውን አጋልጠው የማይሰጡ በመሆኑም ጭምር ነው። እንዲሁም አሁን ያለውን የፖለቲካ ችግር እንደሽፋን በመጠቀም ሰዎች ዘርፈው፤ ሰርቀውና አጭበርብረው ሲጠየቁ ‹‹የዚህ ብሔር አባል ስለሆንኩኝ ነው፤ የዚህ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆንኩኝ ነው›› በማለት ነገሩ ተድበስብሶ እንዲያልፍ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። በተጨማሪም ትልልቅ የወንጀል ክሶች ቀርበው ሰዎች ሲከሰሱ የፖለቲካ ምህዳርን ለማስፋት በሚል የሚለቀቁ ሰዎች መኖራቸው በራሱ ወንጀሉ እንዲበረታታ አድርጎታል ባይ ነኝ። ለምሳሌ የሜቴክ ጉዳይን ማንሳት ይቻላል፤ ክሱ በመቋረጡ መንግሥት በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት አጥቶበታል።
በአጠቃላይ ባለፉት አራት ዓመታት ሌብነትን ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ይሄነው የሚባል ለውጥ አልመጣም። ለዚህ ደግሞ በዋናነት መንግሥት በተለያየ ጊዜ ጫና ላይ ሲሆን እዚያ ላይ በማተኮሩ ለዚያ ለገባበት ጫና እንደማስተንፈሻ ተጠቅመውበታል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ ባሻገር በሌብነት ላይ የተሳተፉ ሰዎችንም በሚገባ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ያለመቻሉም ችግሩን አባብሶታል ባይ ነኝ። እርግጥ ነው በተለይ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክሶችን የማቋረጥ ስልጣን አለው፤ እሱም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ የሕዝብ ጥቅምን አደጋ ላይ የጣሉ ሰዎችን በዚህኛው ቀዳዳ እንዲያመልጡ ዕድል የፈጠረ ነው ብዬ አምናለሁ።
በሌላ በኩል ሌቦችን የሚያጋልጡ ሰዎች ደህንነታቸውን የሚያስጠብቅ ሕግና ተቋምም አለመኖሩ ለሌብነቱም ሆነ ለሌቦቹ መስፋፋት አንዱ ችግር ነው። እርግጥ ነው የምስክሮች ጥበቃ የሚባል አዋጅ አለ፤ ግን ብዙ ጊዜ በይፋ ክስ ተመስርቶ ፍርድ ቤት ለሚቀርቡ ጉዳዮች እንጂ ለሚሰጡ ጥቆማዎች እምብዛም የሉም። በአገሪቱ ይህንን የሚያደርግ የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ የለም። ስለዚህ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ እንዲሁም በተቋም ደረጃ የፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ቢሆን ጠንካራ ያለመሆኑ በራሱ ሌቦች እንዲበረታቱ ምክንያት ሆኗል። በተለይም ይህ ተቋም ከሶ፤ ተከራክሮ ተጠያቂ የማድረጉ ስልጣን ወደ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ መሄዱ በራሱ የፈጠረው ችግር አለ። ይህ መሆኑ በመርህ ደረጃ ችግር ባይኖረውም ግን ደግሞ ኮሚሽኑ ራሱ መርምሮና አጣርቶ ሰዎቹን ለፍትሕ አቅርቦ የሚያስወስንበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ጎን ለጎንም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ሊሠራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ መንግሥት ሌብነትን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማምጣት ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ ማቋቋሙ ምን ያህል ችግሩን ይፈታዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ መስኡድ፡- አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ በራሱ የሚበረታታና መንግሥት ተጠያቂነት ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኑን ማሳያ ነው። ይሁንና አሁን ላይ ሌብነት በራሱ ሥርዓት ዘርግቶ እየተፈፀመ ያለ ወንጀል ስለሆነ በኮሚቴ ደረጃ ብቻ ሥራ ተሠርቶ ለውጥ ይመጣበታል ብዬ አላምንም። ከዚያ በተጨማሪ እዚህ ላይ ኃላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመ ተቋም ኃላፊነቱን አስፍቶ የበለጠ አቅሙን በማሳደግ ፀረ-ሌብነት ትግሉን በበላይነት እንዲመራው መደረግ ነው የሚገባው። አሁን ባለው ሁኔታ ካልተሳሳትኩት የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይመስለኛል። ከዚህ ይልቅ የሕዝብ አድርጎ ከሕዝብ ጋር ቅርበት ፈጥሮ እንዲሠራ ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
በተጨማሪም ሌቦችን የሚያጋልጡ ሰዎችን በመሸለምም፤ ጥበቃ በማድረግም ሊያበረታታ ይገባል። በሌብነት ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎችን ደግሞ በማናቸውም ሁኔታ ክሳቸው የማይቋረጥበት፤ ለፖለቲካው ምህዳር መስፋት ወይም በሌላ ብዙም አጥጋቢ ባልሆነ ምክንያት እንዳይፈጠር ተደርጎ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት በሕግ አግባብ ተጠያቂነትን ማምጣት ያስፈልጋል። በተለይም ለእንደዚህ ዓይነት ተግባር የበለጠ ተጋላጭ ናቸው የሚባሉ ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይገባል። ለምሳሌ ግዢ ኤጀንሲ ጋር ተያይዞ ብዙ የሚቀርቡ ቅሬታዎች አሉ፤ ገቢዎች አካባቢም ታክስ በመሰወር የሚታዩ ወንጀሎች ላይ በጣም ጠንካራ የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት እርምጃ መውሰድ ይገባል። ጎን ለጎንም ከሃይማኖት ተቋማት፤ ከሲቪል ማህበራት ጋር በመሆን ግንዛቤ በማስጨበጥ ሌብነትን የሚፀየፍ ዜጋ የማፍራቱ ሂደት መጠናከር አለበት።
ይህንንም በተከታታይ በመተግበር ባህል ካላደረግነው አሁንም ቢሆን ስጋቴ የተጀመረው ዘመቻ የአጭር ጊዜ ሆኖ ከዚያ በኋላ የሚረሳ እንዳይሆን ነው። ይህ መሆን ካልተቻለ እንዲያውም ሌቦችን በጣም በረቀቀ መንገድ ስርቆት እንዲፈፅሙ የሚያበረታታ ስለሚሆን እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው የማምነው። ሌብነት ላይ በሚዲያ ከሚነገረው በተጨማሪ መሬት ላይ ደግሞ የሚታይ የሚጨበጥ እርምጃን መውሰድ ይገባል። ምክንያቱም ሕዝቡ መንግሥትን ማገዝ የሚችለው የሚጨበጥ እርምጃ ሲያይ ነው። በተጨማሪም የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት፣ይህን ደግሞ ከጸረ- ሙስና ኮሚሽንና ለዚህ ከተቋቋመው ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ ጋር በማገናኘት ከሲቪል ሶሳይቲ ከአካባቢ ተቋማት ጋርም የግንዛቤ ማስጨበጡን ሥራ መሠራት አለበት። ሌብነትን የሚጸየፍ ማኅበረሰብ የመፍጠር ሂደት፤ በተወሰነ ጊዜ የዘመቻ ሥራ ሊሆን አይገባም። በተቋም ደረጃ ሀብት መድቦ ሰፊ ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት ካልተቻለ እንዲያውም ሌቦችን በጣም በረቀቀ ዘዴ ሌብነትን እንዲፈጽሙ ስለሚያደርግ ጥንቃቄ ማድረግ እና በብዙሃን መገናኛ ጉዳዩ ትኩረት የተሰጠው አድርጎ ማቅረብ ያስፈልጋል።
መሬት ላይ ደግሞ የሚታይ ርምጃ እየወሰዱ ማኅበረሰቡ መንግሥት እያደረገ ያለውን ተግባር እያደነቀና ድጋፍ እየሰጠ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል። ማኅበረሰቡ የሚጨበጥ ነገር ማየት ይፈልጋል። ስለዚህ በተግባር መሬት ላይ በሌብነት የተሰማሩ ሰዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በሌብነት የተገኘ ሀብትንም መልሶ የሕዝብ በማድረግ ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማድረግ፣ እንዲህ ዓይነት ክሶችን ደግሞ በአፋጣኝ መልስ በመስጠት ማሳየት ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ነገሮችን በአፋጣኝ ልስ መስጠት የግድ የሚል ነው። ምክንያቱም በተራዘመ ቁጥር ከተጠያቂነት የሚያመልጡበት መንገድ ይሰፋል። በአጠቃላይ መከላከሉ ላይ አተኩሮ መሥራት በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባሁ።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ በራሱ ብቻውን ችግሩን በዘላቂነት አይፈታውም እያሉ ነው?
አቶ መስኡድ፡- ይህንን ስል ልብ እንድትዪልኝ የምፈልገው ነገር ብሔራዊ የጸረሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ ተገቢ አይደለም እያልኩ አለመሆኑን ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽም የሚበረታታና የመንግሥትን ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያ ነው። ግን ደግሞ ተቋም እየገነቡ መሄድ እንጂ በተቋም ላይ ሌላ ተቋም መፍጠር አስፈላጊ አይደለም። እርግጥ ነው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ከሰባቱ የኮሚቴ አባላት አንዱ ናቸው። በመርህ ደረጃ ብዙ ችግር ያለው አይደለም። ግን አሁንም በአገር ውስጥ በሪፎርሙ የሚቀርበው ትችት ተቋማዊ አልሆነም በሚል ነው። ደግሞም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ጉዳዮች ላይ በጣም ተጨናንቀው ከአቅማቸው በላይ እንዲሠራ ያደርጋሉ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ግን የተቋቋሙበትን ዓላማ በአግባቡ እየፈጸሙ አይደለም። ያለመፈጸማቸውም ሪፎርሙ ወደ መሬት ባለመውረዱ፤ ወደ ክልል፣ ወደ ዞንና ወረዳ ስንመጣ ችግሩ በጣም የተንሰራፋ ሆኖ በመገኘቱ ነው። በእኔ እምነት ሪፎርሙ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደረገው ተቋማዊ ችግር ከሆነ የስልጣን ከሆነ ስልጣኑን ማሻሻል፣ የመፈጸም አቅም ከሆነ የመፈጸም አቅሙን ጥናት አድርጎ ማሻሻል ነው የሚገባው።
እንደሚታወቀው ተቋሙ በአዋጅ የተቋቋመ ነው፤ ግብረ-ኃይል ወይም ኮሚቴ መቋቋሙ ደግሞ ከአዋጅ ባነሰ መመሪያ የኮሚሽኑን ስልጣን ለሌላ አሳልፎ እንደመስጠት ሆኖ ነው የሚታየኝ። በርግጥ ሃሳቡ ጥሩ ነው የሚበረታታ ነው፣ ሁኔታውንም እገነዘበዋለሁ። ግን ደግሞ ተቋማትን እየገነባን፣ ሥርዓት እየፈጠርን መቀጠል ጥሩ ነው። የሕግ-ማዕቀፍ ከሆነ ሕግን ማሻሻል፣ የማሻሻል አቅም ከሆነ የአቅም ማሻሻያ ሥራ መሥራት ተገቢ ነው። የአመለካከት ባህል ማሳደጉ ላይ ነው ብዙ ሥራ መሠራት ያለበት። ምክንያቱም ሰዎች ሌብነትን ቀላል እያደረጉት የመጡት ሰርቆ መለወጥ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል፤ ሰርቆ ምንም ችግር አይመጣም የሚለው ልምምድ የፈጠሩት የተጠያቂነት ሥርዓቱ ደካማ በመሆኑ ነው። ሌብነትን የሚጠየፍ ባህል ለመፍጠር ደግሞ ከታች ጀምሮ ሥነ- ምግባር ላይ መሥራት፣ የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የሃይማኖት ተቋማትና ከሲቪል ሶሳይቲ እና ከብዙኃን መገናኛ ጋር መሥራት፣ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማበረታታትና እውቅና በመስጠት በምክረ ሃሳቦች መሠረት መሥራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከሀብት ምዝገባ ጋር ተያይዞ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ምዝገባ ተካሂዷል፣ አሁንም እየተካሄደ ይገኛል ።ነገር ግን ምንም ውጤት አይታይበትም። ለመሆኑ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ መስኡድ፡- አንቺም እንዳልሽው ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ለዓመታት ሲሠራ የቆየው ይህንኑ ነው። ከሆነ ደረጃ በላይ ያሉ ወይም ደግሞ በባህሪያቸው ለሌብነት ተጋላጭ ናቸው ተብሎ የሚገመቱ ተቋማት ላይ የሚሠሩ ሰዎች ያላቸውን ሀብት እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል። ከመጀመሪያውም ቢሆን የሰረቀ ሰው የሰረቀውን በራሱ ስም አያስመዘግብም፤ ይሄንን ማንም ተራ ሰው ሊሠራው የሚችለው ስሌት ነው። ስለዚህ ያስመዘገብከው ሀብት ይሄ ነው፤ አሁን ግን ካስመዘገብክ በኋላ እንዲህ ዓይነት ሀብት በስምህ ተገኝቷልና ትጠየቃለህ ብሎ መሄድ በራሱ ስሜት አይሰጠኝም። ሌባ የሰረቀውን ንብረት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት እንደተናገሩት የሰረቁ ሰዎች የሰረቁትን ገንዘብ ወደ ገበያው አያስገቡም፤ ምክንያቱም ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ገንዘብ ያገኘ ሰው በሕጋዊ መልኩ ግብይት አያደርግም።
በመሆኑም በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ በሕጋዊ መልኩ ገበያ ውስጥ ስለማይገባ የሕገ ወጥ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬ በጥቁር ገበያ እና በመሳሰሉት ሕገ ወጥ መንገዶች ነው ገንዘቡ ዝውውር የሚያደርገው። ወይንም ከአገር ውጪ ወጥቶ ነው የሚቀመጠው። ይህ ደግሞ ለአገር ኢኮኖሚ ፋይዳ አይሰጥም። ይሁን እንጂ ሌብነት የሚበረታታ ጉዳይ ባይሆንም ሰርቆ ሆቴል ገንብቶ የሆቴል አገልግሎት ቢሰጥ ይህም አንድ ነገር ነው። ግን ደግሞ የተሰረቀ ገንዘብ ወደ ሕጋዊ ሂደቱ ሲገባ ‹‹ከየት መጣ?›› የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ስለሚችል ሰው ይህንን አይመርጥም። በሩቅ ዘመድ ወይንም በሽርክና አብሮ ከሚሠራ ሰው ጋር፣ በሕገ ወጥ መንገድ በዘረጓቸው ኔትወርኮች ነው የሚፈፅሙት።
ለምሳሌ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጠቅላይ ላይ ሚኒስትሩ ሲያነሱ አዲስ አበባ ውስጥ ኦዲት ሲደረግ በርካታ ትላልቅ ባለቤት የሌላቸው ሕንፃዎች ተገኝተዋል። ሕንፃ ድንገት አይበቅልም። ሕንፃ እንደጨረቃ ቤት በአንድ ጀምበር አይገነባም። ለሕንፃ ሲገነባ ብዙ የሚያስፈልጉ ግብቶች ሊሟሉለት ይገባል፤ ደግሞም በሆነ ሰው ስም ካልተመዘገበ ሊጀመር አይችልም። በአጠቃላይ የሀብት ምዝገባ ሂደቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን ንብረትን መርምሮ ከዚህ በላይ ያለው ንብረት ካንተ ገቢ ጋር አይጣጣምም ማለት በራሱ ቀልድ ነው የሚመስለኝ። ደግሞም ከልብ ለውጥ ያመጣል ብዬ አልገምትም። ሰዎች ሰርቃችኋል ተብለው ሲጠረጠሩ ንጽህናቸውን ለማወጅ ይህንን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ያስመዘገብኩት የራሴ ነው ማለት ይችላሉ።
በተለያየ ጊዜ ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ንጹህ የሆኑ ባለስልጣናትም ሲከሰሱ፣ ሲታሰሩና ሲጠየቁ እናያለን። ይሄ በፖለቲካው ውስጥ ሲፈጠሩ የምናያቸው ችግሮች ናቸው። ግን ይሄ ብዙ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም። ወደ ትክክለኛ መንገዱ ወደ ገበያው ስለማይገባ ማለት ነው። በዋናነት አሁንም በዚህ ላይ የመንግሥትን ቁርጠኝነት እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድ፣ ከተጠያቂነት ጋር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ጠንክሮ በመሥራት ለውጥ ይመጣ የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በአ ንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግ ናለሁ።
አቶ መስኡድ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 17/ 2015 ዓ.ም