ኢትዮጵያ ታዋቂ በሆነችበት የአትሌቲክስ ስፖርት ስኬት የተመዘገበባቸው ጥቂት ርቀቶች ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት በርካታ ስመ ጥር አትሌቶችን ካፈሩ አካባቢዎች ባሻገር የአጭር ርቀት አትሌቲክስ እና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ስኬታማ የመሆን እድል እንዳላትም ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ከአየር ሁኔታው፣ ከቦታ አቀማመጡ እንዲሁም ከማህበራዊ አኗኗር ጋር ተያይዞ ያልተሰራባቸው ዕምቅ አቅሞች እንዳሉ ይታመናል።
በዚህ ረገድ ትኩረት ካልተሰጣቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የአፋር ክልል ነው፡፡ ይህ ክልል እንደሌሎቹ ሁሉ በተለያዩ ስፖርቶች ፕሮጀክቶችን መስርቶ ለማንቀሳቀስ ሙከራ ቢደረግም ውጤታማ አልነበረም፡፡ በቅርቡ በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ደግሞ የነበሩት ጥቂት ፕሮጀክቶችም መፍረስ እጣ ፋንታቸው ሆኗል። ክልሉ በስፖርቱ ውጤታማ ላለመሆኑ እንደ ምክንያት የሚነሳው በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፈና የክልሉ አቅም በየትኛው ስፖርት ላይ ነው በሚል ጥናት ላይ የተመሰረተ ስላልነበረ ነው፡፡ አሁን ግን ክልሉ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን ጋር በመሆን ባካሄደው ጥናት በተለይ በአጭር ርቀት አትሌቲክስ እንዲሁም በእግር ኳስ ስፖርቶች ላይ ክለብ በማቋቋም በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የአፋር ክልል የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡመር ኢብራሂም፤ በክልሉ የነበረው የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ውስን እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡ በክልሉ የነበረው ፕሮጀክትም በሃገሪቷ ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት ፈርሷል፤ ክለቦችም የሉትም፡፡ አሁን ግን ክልሉ የሚጠራበትን ክለብ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በማቋቋም ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ባለሙያዎችም የተመለከቱት ሲሆን፤ ለምስረታው አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች እና መሰረተ ልማቶች ተዘጋጅተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በብዛት የሚወከለው በረጃጅም ርቀቶች ነው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ይህ ሁኔታ እየቀነሰ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፌዴሬሽኑን ‹‹የአትሌቲክስ›› እንደማያሰኘውና ስሙን ሙሉ ለማድረግ አጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራትን አካታች መሆን እንደሚገባው ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡ በእነዚህ ስፖርቶች ላይ ውጤታማ ለመሆን ደግሞ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከአየር ንብረቱ ባሻገር የህዝቡ አኗኗር አብዛኛውን ጊዜ ለሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ ስፖርቶች ምቹ እንደሆነ ይታመናል። በሰመራ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች አካላት በተደረገ ጥናትም በእነዚህ ስፖርቶች የተሻለ ስኬት ሊመነዘገብ እንደሚችል ተጠቁሟል። በመሆኑም ይህ ከግምት ገብቶ እና በሳይንሳዊ ዘዴ ታግዞ ኢትዮጵያ በሁሉም የአትሌቲክስ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትወከል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኃላፊው ተናግረዋል።
አቶ ተመስገን አስናቀ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የእግር ኳስ ክለቡ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በአፋር ክልል ከዚህ ቀደም ከዳባ የሚባል የእግር ኳስ ቡድን ቢኖርም አሁን ግን መፍረሱን ያስታውሳሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2014ዓም ወጣቶችን ወደ ስፖርት የመመለስ ፕሮግራም መቅረጹን ተከትሎ የክለብ ምስረታው ይሁንታን ለማግኘት ቻለ፡፡ ክለቡ ከተመሰረተ በኋላም አምና ሃዋሳ ላይ በተካሄደው የክልል ክለቦች ቻምፒዮና ሁለተኛ ቡድኑን በማሳተፍ በተያዘው ዓመት ደግሞ በብሄራዊ ሊግ ለመካፈል ምዝገባውን አጠናቋል፡፡
ይህ ፕሮግራም የተቀረጸበት ዋነኛ ምክንያትም ክልሉ ከሌሎች አንጻር በስፖርት ያነሰ ተሳትፎ ያለው በመሆኑ ዘርፉን ለማነቃቃት እንዲሁም በፕሮጀክት የታቀፉ ታዳጊዎችን የሚቀበልና ራዕይ የሚሆናቸው ክለብ በማስፈለጉ ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከእግር ኳሱ ጎን ለጎን በአትሌቲክስ (ከረጅም ርቀት ውጪ) እና በውሃ ስፖርቶች ክለቦች የሚቋቋሙ እንደሚሆንም አቶ ተመስገን ይገልጻሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች በተደረገ ሳይንሳዊ ምርምር በክልሉ የሚዘወተሩ የባህል ስፖርቶች ፈጣን እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረቱ እንደመሆናቸው በአጭር ርቀት ሩጫ ክልሉ ውጤታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ከውሃ ዋና ጋር ተያይዞም የአዋሽ ወንዝ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን የተለያዩ ቴክኒኮችን በማሰልጠን ብቻ ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ከክለቦቹ ምስረታ ጎን ለጎንም በስፖርት መሰረተ ልማት ላይ አስቀድሞ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በስፖርት አካዳሚ ደረጃ ጂምናዚየም እና የውሃ ገንዳ ለማስገንባት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በታቀደው ልክ በተጠቀሱት ስፖርቶች ውጤታማ መሆን ሲቻል፤ በቀጣዩ ዓመት (2016ዓ.ም) ደግሞ ክልሉም የራሱ የሆነ ሌላ ክለብ ይመሰርታል በሚል እንደሚጠበቅ አቶ ተመስገን ጠቁመዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 16/ 2015 ዓ.ም