“መሪ ከመሆንህ በፊት ስኬት ማለት ራስህን ለማሳደግ የምታከናውነው ማንኛውም ተግባር ነው፤ መሪ ከሆንክ በኋላ ደግሞ ስኬት የሚባለው ሌሎችን ለማሳደግ የምትሠራው ማንኛውም ሥራ ነው” ይህን የተናገረው በአንድ ወቅት የጀኔራል ኤሌክትሪክ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ታዋቂው አሜሪካዊ መሃንዲስ፣ ደራሲና የቢዝነስ ባለሙያ ጃክ ዌልች ነው።
ጃክ ዌልች ዝነኛውን ሞተር አምራች ኩባንያ ከ1981 እስከ 2001 ዝነኛውን የአሜሪካ ሞተር አምራች ኩባንያ ጀኔራል ኤሌክትሪክን በመራባቸው ሃያ ዓመት የኩባንያውን አጠቃላይ ገቢ በአራት ሺ እጥፍ እንዲጨምር ማድረግ ችሏል። በግሉም ጃክ ዌልች ከቢሊየነሮች ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን የሀብት መጠኑም እስከ አውሮፓውያኑ 2006 ድረስ 720 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ የነበረ መሆኑን ከዊኪፒዲያ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ትልቅ ደረጃ ላይ ከደረሱ ስኬታማ የዓላማችን መሪዎች መካከል አንዱ ሆኖ የሚጠቀሰው መሃንዲስ፤ ደራሲና የቢዝነስ ባለሙያው ጃክ ዌልች በጡረታ ከተሰናበተ በኋላም በታሪክ 417 ሚሊዮን ዶላር የጡረታ ክፍያ የተከፈለው ብቸኛው ሰው ሆኖ ተመዝግቧል። ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ እኛም የጃክ ዌልችን አባባል ለሐተታችን መግቢያ እንዲሆን መምረጣችን ያለ ምክንያት አይደለም – የጉዳያችን ጭብጥ አጥርቶና አጉልቶ የሚያሳይ የሃሳብ አጉሊ መነጽር ስለሆነልን እንጅ።
እንዴት ካላችሁ አብራችሁ ቆዩ። ሰሞኑን የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ከመላ አገሪቱ ለተውጣጡ የአገራችን ወጣቶች ተተኪ አመራሮችን ማፍራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አስር ቀናትን የፈጀ ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናው በስኬታማ መሪዎች ስብዕናዎች፣ ፈጠራ የታከለበት አመራር፣ የወጣቶች በጎ ፈቃደኝነት፣ ራስን ማሳደግ በሚሉ ንዑስ ርዕሶች ተከፋፍሎ የወጣቶችን ውሳኔ ሰጭነት ሚና ማሳደግ በሚቻልበትና የሃገር ተረካቢ የሆኑትን ወጣቶች ለአመራር ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያግዙ የዕውቀትና የክህሎት ትጥቆችን ለማስጨበጥ ያለመ ነበር። ታዲያ በስተመጨረሻ አሰልጣኙና ሰልጣኙ ዓላማቸውን ዕውን ለማድረግ “ከምንም
በላይ አንድ ነገር ያስፈልገናል” በማለት በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል – በቅድሚያ ራስን መለወጥ።
ስልጠናው ወደፊት ተተኪ ሊሆኑ የሚችሉ አመራሮችን ለማፍራትና የወጣቶችን አቅም
ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ያመላከቱት የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ፤ “ሆኖም ይህ ዓላማችን የሚሳካው ከሁሉ አስቀድሞ ራሳችንን ማሳደግና መለወጥ ስንችል ነው፤ ያኔ ነው አገርን በአግባቡ መምራት የምንችል፤ መሪ የምንሆነው” ይላሉ።
“መሪነት ከራስ ይጀምራል” የሚሉት ሚኒስትር ዲኤታዋ፤ ለዚህም ወጣቱ ራሱን በመልካም ሥነ ምግባር ማነፅ እንደሚገባው ይናገራሉ። ምክንያቱም ሃገርንና ህዝብን በሚጠቅም መንገድ መምራት የሚቻለው ራስን በአግባቡ በመምራትና መልካም ስብዕናን በመላበስ ነው። ይህም ትክክለኛው የመሪነት መንገድ ሲሆን መግቢያው ላይ አባባሉን የጠቀስንለት በበርካታ ዘርፎች ስኬትን የተጎናጸፈው ሁለገቡ መሪ ጃክ ዌልች የሚለውም ይህንኑ ነው።
ከዚህ አኳያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተተኪ ወጣት አመራሮችን ለማፍራት ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል። ይሁን እንጂ በመንግሥት የሚሠሩት ሥራዎች እንዳሉ ሆነው የሃገሪቱ ቀጣይ መሪ የሆነው ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ መንቀሳቀስ ይገባዋል። በራሱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራትና በሁሉም ነገር ላይ ብቁ ሆኖ መገኘት
ይጠበቅበታል ብለዋል።
ይህንን ሃሳብ ስልጠናውን የወሰዱ ወጣቶችም ደግፈውታል። ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አንዷ የሆነችውና በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን የሴት ወጣት አመራር ፎረም ሰብሳቢ ወጣት ማርታ ማሙዬ፤ “በእርግጥም መሪነት የሚጀምረው ከራስ ነው” ትላለች።
በስነልቦና፣ በሥራ ፈጠራና በሥራ አመራር ጠለቅ ያለ ዕውቀት ባላቸው ታዋቂ ምሁራን የተሳተፉበት በመሆኑ ከስልጠናው በጣም ጠቃሚ ዕውቀት መቅሰሟን የምትናገረው ወጣት ማርታ “ያገኘነው ዕውቀት ለእኛም ሆነ ለሌሎች ሊጠቅም የሚችለው ግን ቅድሚያ ራሳችን ስንጠቀምበትና ስንለወጥበት ነው” ትላለች።
በመሆኑም ስልጠናው የወጣቶችን የአመራር ጥበብና ክህሎትን የሚያሳድግና በአገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳይ ላይም ንቁ ተሳታፊና ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ የሚያግዝ በመሆኑ ያገኘችውን ዕውቀት በመጠቀም ራሷን የበለጠ ለመለወጥና ለመምራት ተዘጋጅታለች። ሌሎችንም ለማሳወቅና ራሳቸውን በአግባቡ እንዲመሩና ወደ አመራር እንዲመጡ ለማድረግ የበኩሏን ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክራ እንደምትሠራም ወጣት ማርታ ለራሷ ቃል ገብታለች።
ሌላኛው የስልጠናው ተሳታፊ ወጣት ፀጋዬ ሳሙኤል በበኩሉ፤ “መሪ ለመሆን ራስን በአግባቡ መምራት፤ ራስን በአግባቡ ለመምራት ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን ያስፈልጋል” ይላል። ወጣት ፀጋዬ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የወጣቶች ሪፎርም ዘርፍ ወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ሲሆን የተሰጠው ስልጠና ለወጣቱ በጣም የሚያስፈልገው ዓይነት መሆኑን ይናገራል።
“በተለይም አሁን ባለው የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ለመሪነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑት መልካም ስብዕናና ሥነ ምግባር በወጣቱ ዘንድ ቸል እየተባሉ ናቸው፤ ለዚህም ማሳያው እየተፈጠሩ ያሉት ኃላፊነት የማይሰማቸው ከሥነ ምግባር ያፈነገጡ የወጣት አደረጃጀቶች ናቸው” ይላል። ለሚፈጽመው ድርጊት ኃላፊነት የማይወስድ ወጣት ራሱን በአግባቡ መምራት የማይችል በመሆኑ ሌላውንም ሊመራ አይችልም።
ስለሆነም ወጣቱ ከምንም በላይ መልካም ስብዕናን በመላበስና ራሱን በመግዛት የሚረከባትን አገር በአግባቡ መምራት እንዲችል መንግሥትም ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ባለቤትና ተጠያቂነት የሌላቸው ሜዳ ላይ ያሉ የወጣት አደረጃጀቶችን ህግና ሥርዓት ተከትለው የሚንቀሳቀሱበትን አሠራር ማበጀት የሚገባው መሆኑንም ነው ወጣት ፀጋዬ አፅንኦት ሰጥቶ ያሳሰበው።
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ሥነ ሥርዓት ወቅት የማጠቃለያ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋዬም ስልጠናው ወጣቶች በሀገራቸው መጻኢ ዕድል ላይ ተስፋ እንዲታያቸው ለማድረግና ራሳቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ መሪዎች እንዲሆኑ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህም የነገዋ ኢትዮጵያ መሪና ሃገር ተረካቢ የሆነው ወጣት ወደ ራሱ እንዲመለከትና ራሱን በመልካም ሥነ ምግባር፣ ዕውቀትና ክህሎት እንዲገነባ ዕድል ይፈጥራል። በውጤቱም ከራሱ አልፎ ለሌላው የሚተርፍ፣ አገሩን በሰላምና በመግባባት የሚመራ ስልጡን ወጣት ይፈጠራል። ለዚህም ወጣቶች ሀገራችን የያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል በአግባቡ ተደራጅተውና የህግ የበላይነትን አክብረው በመንቀሳቀስ መልካም መሪነትን መለማመድ ይገባቸዋል። የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎችም በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ የወጣት አደረጃጀቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ራሳቸውን በማጠናከር ለሰላምና ለሀገራዊ አንድነት በጋራ መቆም የሚገባቸው መሆኑን ሚኒስትሯ ያመላክታሉ። ስለሆነም ወጣቱ መልካም ባህሪያትን በመላበስ ገንቢ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን በማዳበር ራሱን በአግባቡ መምራት ይኖርበታል። በዚህም ወጣቱ ከራሱ አልፎ ሃገሩንም በአግባቡ ለመምራት የሚችል፤ ሃገሩ የምትኮራበት እርሱም የሚኮራባት ታላቅ ሃገር መገንባት ይችላል።
በመጨረሻም ወጣትነት በስነ ምግባር ካልታነፀ እንኳንስ አገር ለመምራት ራስን ለመምራት ከፍተኛ ችግር እንደሆነ ዛሬ በገሃድ የምናየው የአገራችን ገሀድ የወጣ ሀቅ ነው። ለዚህ ነው በመጀመሪያ ወጣቱ ራሱን በስነ ምግባር አንጾ ራሱን መምራት አለበት። ይሕን ማድረግ የቻለ ወጣት የመጀመሪያውን ፈተና አለፈ ማለት ይቻላል።
ከዚህ በመቀጠል ወጣቱ ከሚኖርበት መንደር ጀምሮ አገሩ ምን መልክ እንዳላት ማወቅ፤ መብትና ግዴታውንም መለየት ይቀጥላል። በዚህ ሂደት ውስጥ ወጣቱ አገር ወዳድነትን ሊላበስ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ የአመራር ክህሎት በማዳበር አገርን ወደ መምራት አዲስ ምዕራፍ ሊሸጋገር ይችላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2011
በይበል ካሳ