የኦሮሚያ ፖሊስ ስፖርት ክለብ የ18ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ(ዱላ ቅብብል) ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ18 ጊዜ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድሩን በአፋር ክልላዊ መንግሥት ሠመራ ከተማ ባለፈው እሁድ ሲያካሂድ ከማራቶን ሪሌ ውድድሩ ጎን ለጎን የ5 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርም ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነውን የማራቶን ሪሌ ውድድር ሲሆን የበረሀ ገነት በሆነችው አፋር ሰመራ ከተማ በሁለቱም ፆታዎች የድብልቅ ሪሌ ውድድሩን አከናውኖ በተሳካ ሁኔታ አጠናቋል። በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ክልሉ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ ተቀዛቅዞ የቆየውን የስፖርት ዘርፍ እንዲነቃቃ ለማድረግ ውድድሩ መካሄዱ ተጠቁሟል።
በውድድሩ ላይ ከሦስት ክልሎች፣ አንድ ከተማ አስተዳደር እና 12 ክለቦች የተወጣጡ 96 አትሌቶች ተካፋይ ነበሩ። በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ ፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ
አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሁመድና ሌሎች አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል።
በዚህም መሠረት በአትሌቶች መካከል በተካሄደው ውድድር የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ የወርቅ ሜዳሊያና የገንዘብ ተሸላሚ ሆኗል። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ የብርና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። ሽልማቱንም የክልልና ከተማ አስተዳደር አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶችና የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በጋራ አበርክተዋል።
የአጠቃላይ አሸናፊ የዋንጫ ሽልማቱት ባለቤት የሆነው የኦሮሚያ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብም ከእለቱ የክብር እንግዳ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ ተረክበዋል። በሕዝባዊ ሩጫው ደግሞ አብዲሳ አብደታ፣ ጀማል አብደላ እና መሐመድ ሄላም አሸንፈዋል።
ፌዴሬሽኑ ውድድሮች በተለያዩ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ አፋር ላይ እንደተካሄደ፤ የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ ገልጿል። ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ሙቀት ባለበት በአፋር ሰመራ ይደረግ እንጂ በውድድሩ ወቅት የነበረው የአየር ሁኔታ አመቺ ነበር። በመሆኑም ይህን መሰል ውድድሮች ማዘጋጀት ለአትሌቶች የውድድር ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለክልሉና በዙሪያው ላሉ ፌዴሬሽኖችም ማበረታቻ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ውድድሩ በአካባቢው ያለውን የአትሌቲክስ አቅም ለመመልከት እንዲሁም የክልል መንግሥታትም ለስፖርቱ ትኩረት እንዲሰጡ መልዕክት እንዲተላለፍበት ታስቦ እንደተከናወነ ታውቋል። ውድድሩ የክልል ፌዴሬሽኖችን ለማቋቋም ቢያንስ አምስት ክለቦች መኖር አለባቸው ከሚለው ሀገር አቀፍ ደንብ ጋር ተያይዞ ክለቦችን ለማበረታታት እንደተካሄደም ተጠቁሟል።
ብርሀን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/ 2015 ዓ.ም