በሀገራችን የፋሽን ዘርፍ በመድረክ ቀርቦ ሲታይ እንጂ በዘርፉ ባለሙያዎች ሥልጠናዎች በስፋት ሲሰጡ ብዙም አይታይም፡፡ በዘርፉ አዲስ አበባ ላይ ሥልጠና ከሚሰጡት ተቋማት አንዱ የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ ይጠቀሳል፡፡
ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ የተመሠረተው በ1998 ዓ.ም ነው፡፡ የተመሰረተበት ዓላማም ሴቶችን በሙያው ማብቃት ላይ መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ኮሌጁ ሲመሠረት ‹‹አንድን ሴት መደገፍ የአንድ ቤተሰብን አባላት ሁሉ መደገፍ ነው›› እና ‹‹ ሴቶች የማኅበረሰቡ የጀርባ አጥንት ናቸው›› የሚል መርህ አንግቦ ነው፡፡
የኔክስት ፋሽን ኮሌጅ በሙያው ከተሰማራ 17 ዓመት እንደሆነው የሚናገሩት የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን አቶ አየለ እሸቴ፤ አልባሳት ወቅትን በዋጀ መልኩ ገጽታን የሚፈጥሩ፣ የሰው ልጅን መንፈስ የሚቀይሩ፣ ደስታን ውበትን የሚጭሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይህም የሚሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲዛይን ተደርገው ሲሠሩ ነው፡፡ ሀገራዊ አልባሳትም ገጽታን ከመቀየር በተጨማሪ ለባሹን፣ አልባሹንና ተመልካቹን እንዲስቡ በማድረግ፤ወይም የሰዎችን ፍላጐቶች በማየት ዲዛይን እንደሚደረጉ ይናገራሉ፡፡
በኮሌጁ የአልባሳት ፋሽንና ዲዛይን ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅቶ ከደረጃ አንድ እስከ አራት ባሉ ተዋረዶችም ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም በዲግሪ ደረጃ ሥልጠናው እንደሚሰጥ የኮሌጁ አካዳሚክ ዲን ያስረዳሉ፡፡
ፋሽን ገጽታን መቀየር፣ ማስዋብ፣ ማሰማመር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ነው፡፡ በኮሌጁ ፋሽን ለመማር ፍላጎት ያላቸው ይመጣሉ፡፡ ተቋሙ ይመጥናሉ የሚላቸውን ተቀብሎ ያስተምራል፡፡ የራሣቸው ሥራ ያላቸው፣ ዲግሪ እና ዶክትሬት ያላቸውም ጭምር ይህን ስልጠና ይወስዳሉ፡፡ በፋሽን ኮሌጁ የራሳቸውን ንግድ ለመሥራት፣ አውቀው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ለመሥራት የሚማሩና በሙያው ተቀጥረው ለመሥራት የሚማሩም አሉ፡፡ በኮሌጁ ከተማሩ መካከል ዕውቅና ያላቸው እንደሚገኙና በሥልጠናው አዎንታዊ ግብረ መልሶች እንዳሉ በተለያዩ ቦታዎች ከሚቀርቡ ፋሽን ተኮር ዐውደ ርዕዮችና የብዙሃንና መገናኛ ፕሮግራሞች እንደተመለከቱ አቶ አየለ ይናገራሉ፡፡
በፋሽን ዲዛይን ኮሌጁ ውስጥ የክርኤቲቭ ዲዛይን መምህር አርቲስት (ሰዓሊ) ቃልኪዳን ሾቤ ፤ ‹‹ፋሽን ማለት በጊዜው ይሁንታን ያገኘ እና ያሸነፈ ወይም የብዙውን ሰው ቀልብ የገዛ እና ተከታይ ያለው ስልት (ስታይል) የተካተተበት ስፌት ወይም አልባሳት ነው›› ይላል፡፡ ፋሽን ትምህርት ቤትም ከጊዜው ጋር አብረው የሚሄዱ በዲዛይን የሚያሸንፉ አልባሳት የሚሠሩ ተማሪዎች ወይም ሰልጣኞች የሚፈልቁበት ቦታ መሆኑንም ያስረዳል፡፡
ኮሌጁ በመደበኛነት ሦስት የትምህርት ክፍሎች አሉት፡፡ ስፌት፣ ቅድና ስኬች ወይም አርት ተማሪዎች ሀሳባቸውን የሚነድፉበት የፈጠራ ተሰጥኦዋቸውን ፣ አስተሳሰባቸውን የሚያዳብሩበት ክፍል ነው፡፡ ኮሌጁ መንግሥት በየዓመቱ በሚያወጣው ውጤትና መስፈርት መሠረት ነው ሥልጠና የሚሰጠው፡፡
ለጊዜው በኮቪድ-19 ተፅዕኖና እና በተለያዩ ምክንያቶች ሥልጠናዎችን በአንድ ቅርንጫፍ ተገድበው እየተሰጡ እንደሚገኙ የሚናገረው አርቲስት ቃልኪዳን፣ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ አራት ቅርንጫፎች ስልጠናዎች ይሰጡ እንደነበረ ያስታውሳል፡፡ የፋሽን ኮሌጁ ዋናው ዓላማ የኢትዮጵያን የፋሽን ኢንዱስትሪን ማንቀሳቀስ ነው፡፡ ከሥልጠናው ጎን ታዋቂ ዲዛይነሮችን አወዳድሮ ማውጣት፣ መሸለም፣ አዲስ አበባ ውስጥ ዓመታዊ የፋሽን ሾው ውድድር እንደሚያዘጋጁም አርቲስት ቃልኪዳን ይናገራል፡፡ ኮሌጁ በኢትዮጵያ ፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎችን በየዓመቱ ይሸልማል። የፋሽን ሥራውና ሥልጠናው ውስጥ በጥልቀት ገብቶም እየሠራ ስለመሆኑ አርቲስቱ ያክላል፡፡
ከተማሞች ውስጥ እንደ ጥበብ የመሳሰሉትን ባህላዊ አልባሳትን ዲዛይን እያደረጉ በፋሽን መልክ ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች በብዛት ኮሌጁ ያፈራቸው ናቸው፡፡ ‹‹ድሬዳዋም ሔደን ከአካባቢው የአየር ፀባይ እና ሙቀት ጋር አልባሳት እንዲሄዱና ከባህላቸው ጋር እንዲጣጣሙ በማድረግ በፋሽን መልክ አቅርበን አሳይተናል፤ ከራት ልብስ ጋር፣ ከዘመናዊ ልብስ ጋር እንዴት መሄድ ይችላሉ የሚለውን በደንብ ሠርተንበታል፣ ተማሪዎቻችንም እየሠሩበት ነው›› ሲልም አርቲስቱ ያስረዳል፡፡
ኮሌጁ ተማሪዎቹን ለፋሽን ሥራዎች ማብቃት፣ ገበያው ላይ እንዲወዳደሩ ማድረግን ዓላማው አድርጎ እየሠራ ይገኛል የሚለው አርቲስት ቃልኪዳን ፤ ትኩረታቸው በዘርፉ ሊሠለጥኑ የሚፈልጉ ሰዎችን ማብቃት እንጂ ኮሌጁ ተነጥሎ ገበያው ላይ ተሠማርቶ ፋሽን መሥራት ዓላማው አለመሆኑን ይገልፃል፡፡
‹‹ፋሽንና ሚዲያዎች አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው›› የሚለው አርቲስት ቃልኪዳን፣ በተለይም በዲጂታል ማርኬቲንግ ውስጥ ሚዲያዎች ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ባይ ነው፡፡
እንደ አርቲስቱ ገለፃ፣ በባህላዊ አልባሳት አብዛኛው ሽያጭና ጥሩ ገበያ ያለው በኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በኩል ነው፡፡ በእርግጥ በሀገር ውስጥም የገበያው ፍላጎት አለ፣ ነገር ግን አብዛኛው ውጭ አገር ያለ ኢትዮጵያዊ ልዩ ዝግጅትና በዓል ሲኖረው ለየት ብሎ ለመታየት ባህላዊ አልባሳትን ምርጫው ያደርጋል፡፡ ይህ ሀገርም ከማስተዋወቅ ፣ ከግብይትም አንፃር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለሀገርም የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል፣ ለቱሪዝምም መስህብ ሆኖ ያገለግላል፡፡
አንዳንድ ሀገሮች ባህላዊ ፌስቲቫል ወይም ካርኒቫል አላቸው፡፡ ባህላቸውን ልምዳቸውን ያዳብሩበታል። ለሰው ያሳዩበታል፤ በኢትዮጵያም በተወሰነ መልኩ አለ፣ ነገር ግን የኢትዮጵያዊ ባህላዊ ልብሶች ካርኒቫል ቢኖር ፋሽን ባህሎችን ለማዳበርና ለማጎልበት ብሎም ቱሪስቶችን ለመሳብ እንዲረዳ ብዙ መሰራት አለበት፡፡ የአደባባይ በዓላት ላይ ሰው ሁሉ ባህሌ የሚለውን ለብሶ የሚወጣበት፣ ማንነቱን የሚሳይበት እንደመሆኑ የተለያያ አልባሳት የመታየትና የፋሽን ዘርፉም የመዳበር እድል እንደሚኖረው አርቲስት ቃልኪዳን ይናገራል፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2015