ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ አዲስ አበባ ላይ የሚያካሂደው እውቅ የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። አርባ ሺ ህዝብ የሚሳተፍበት ይህ እንደ ስሙ ታላቅ የሆነ የጎዳና ላይ ውድድር መካሄድ ከጀመረም ዛሬ ሃያ ሁለተኛ ዓመቱን ደፍኗል።
የውድድሩ አዘጋጆችም ይህንን አስመልክተው ትናንት የቅድመ ውድድር መግለጫ የሰጡ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ምሽትም በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ውድድሩ ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 22ኛ ዓመቱን አስመልክቶ ባዘጋጀው የእውቅና መርሐግብር ለአትሌቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሲሰጥ “ኢትዮጵያዊነቴ ያኮራኛል” በሚል መሪ ሀሳብ ደምቆ አምሽቷል።
በእውቅና መርሃ ግብሩ በወንዶች አትሌት ፀጋዬ ከበደ፣ ኮማንደር አትሌት ሞስነት ገረመው እና አትሌት ታምራት ቶላ ፤በሴቶች ውዴ አያሌው፣ አሰለፈች መርጊያ እና ያለምዘርፍ የኋላው የእውቅና ሽልማት የተሰጣቸው አትሌቶች ናቸው።
አትሌቶቹ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለስኬታቸው መነሻ እንደሆናቸውና ከአትሌቲክሱ ማህበረሰብ ጋር እንዲተዋወቁ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ከአትሌቶቹ በተጨማሪ የቱሪዝም ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የእውቅና ሽልማት ያገኙ ተቋማት ናቸው።
በእውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ታዋቂ አትሌቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የእውቅና ሽልማቱ ከተበረከተላቸው ተቋማት መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሲሆን የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ ታደሰ ጫፎ እጅ ሽልማቱን ተቀብለዋል።
በ1993 ዓ.ም በጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ አንድ ብሎ የጀመረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ከሩጫ ውድድርነቱ በዘለለ የማህበረሰብ ጤናን በመጠበቅ እና እንደ ፌስቲቫል በማገልገል በበርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች እየተዘወተረ የሚገኝ ውድድር መሆኑ ይታወቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ታላቁ ሩጫ ለከተማዋ ገጽታ ግንባታ እና የቱሪዝም ምንጭ መሆኑን ተከትሎ በጋራ ለመስራት የሁለትዮሽ ስምምነት ከተፈራረመ ጀምሮ ለውድድሩ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ እና አብሮ በመስራቱ እውቅናውን እንዳገኘ በመድረኩ ተገልጿል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአስር ኪሎ ሜትር ውድድሩ እንደተለመደው ታላላቅ የአለማችንን አትሌቶች በውድድሩ እንዲታደሙ የሚጋብዝ ሲሆን በዛሬውም ውድድር የኬንያ ታዋቂ አትሌቶች በክብር እንግድነት ይገኛሉ::
ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ የ2015 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ በክብር እንግድነት የሚታደሙ ይሆናል።
ውድድሩ ዛሬ ማለዳ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ሲካሄድ ፔሬስ ጄፕቺርቺር በውድድሩ ላይ ለመታደም ከነቤተሰቧ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ መግባቷ ይታወቃል።
ከኬንያውያን በተጨማሪ ሁለት የዩጋንዳ አትሌቶች በዛሬው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ለውድድሩ ሽፋን ለመስጠትም የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ወደ አዲስ አበባ እንደመጡም ተነግሯል።
ፒሬስ ጄፕቺርቺር የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ማሪ ኬይታኒ አርአያ በማድረግ ወደ አትሌቲክሱ የገባች ኮከብ ስትሆን፣ እ.አ.አ በ2013 ጎዳና ላይ ሩጫ ነበር መወዳደር የጀመረችው፡፡ እ.አ.አ. 2021 በቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር እንዲሁም በኒውዮርክ ማራቶን ማሸነፍ እንደቻለችም ይታወቃል፡፡ እ.አ.አ. በ2022 ደግሞ የቦስተን ማራቶንን አሸንፋለች።
ፔሬስ እ.አ.አ. በ2016 እና 2020 ሁለት ጊዜ የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊም ሆናለች። ሌላኛው የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ በዛሬው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ላይ የሚገኝ ኮከብ ሲሆን፣ ይህ የ57 ዓመት አትሌት በ1993 በጀርመን ስቱትጋርት በተካሄደው አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ10 ሺ ሜትር ውድድር አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተከትሎ ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል። ሞሰስ ታኑይ በኬንያ ኤልዶሬት ከተማ የሚካሄደው የማራቶን ውድድር ዋና አዘጋጅ መሆኑም ይታወቃል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም