ወጣትነት ፍቅር ነው፤ ወጣትነት ኃይል ነው፤ ወጣትነት ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን በተስፋ የሚጠበቅበት ነው። ለመለወጥና ለመሻሻል ስንቅ የሚቋጠርበት፣ ለመልካም ጊዜና ለተሻለ ሕይወት ውጥን የሚጀመርበት፣ የሚንቀለቀል ትኩስ ስሜትን በውስጡ አምቆ የሚይዝበት የእድሜ ወሰን ነው – ወጣትነት።
የተለያዩ እውቀትንና ክህሎትን ለማሳደግ፣ ከእኩዮቻቸው ጋር መምከር፣ መሞገት፣ ግራና ቀኙን አገናዝቦ ትክክለኛ ግንዛቤ መያዝን ባህል አድርጎ መንቀሳቀስ በዚህ እድሜ የሚጠበቅ ነው። የተስተካከለና ቀና የሆነ አመለካከት መያዝ ሌላው ከወጣትነት ዓለም የሚጠበቅ ሲሆን ይህ ጉዳይ የተዛባ አመለካከትን ከመታገል ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ አልችልም ባይነትን፣ ጠባቂነትን፣ ጀምሮ መተውን፣ የፅናት መጓደልን፣ የአመለካከት ክፍተቶችን በማስወገድ ያቀዱትንና የወጠኑትን በታታሪነትና በቁርጠኝነት በመፈፀም የራስን አቅምና ጉልበት ማጎልበት ይገባል።
ወጣትነት የአፍላ ዕድሜ ነው። ረጅሙ የወደፊት ሕይወት መጀመሪያ፡፡ በመሆኑም ለወደፊቱ የግል ሕይወታቸው መሻሻል ሆነ ለአገር ግንባታ የሚሆን እውቀትና ክህሎትን መጨበጥ ይጠይቃል፡፡ እውቀት ሲባል ያሰቡትንና የተመኙትን የማቀድ፣ ያቀዱትን ከግብ ማድረስ ለተሰማሩበት መስክ የሚሆን እውቀት እና ክህሎትን መጨበጥ ነው።
ክህሎትን የጨበጠ በሀገሩ ሰርቶ ማደግን የመረጠ ወጣት እንዳለ ሁሉ የሰው መንጠቅ መዝረፍ የሰውን ሀቅ ለራስ ማድረግን እንደ ጀብዱ የቆጠረ የሌላውን ፍለጋ ሲሄድ በርካታ ጥፋቶችን የሚያጠፋው የወጣት ክፍልም ይሄው ፍቅር ነው ከምንለው ወጣትነት የወጣ ነው። ይህን ጉዳይ ልናነሳ የወደድነው ሁለት ወጣቶች አንዱ ታታሪ ሰራተኛ ሌላው ደግሞ የሰው ገንዘብ ቀማኛ ስለሆኑ ወጣቶች ታሪክ ልንነግራችሁ ስለወደደን ነው።
በሰው ላብ ማደግን እንደ ምርጫ
ወጣት ወዳጄ ልንገርህ አንለይ ከተወለደባት ከተማ የወጣው በልጅነት እድሜው ነበር። በህፃንነቱ ወላጆቹን በማጣቱ የተነሳ ባገኘው የጭነት መኪና ተንጠልጥሎ በመዲናዋ አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ አደገ። ወጣቱ ራሱን የመለወጥ ፍላጎት ስለነበረው፤ አንዴ ጋራዥ ውስጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ በመኪና ማጠቢያ በመላላክና በመስራት ቀኖቹን ይገፋ ጀመር።
ቀን ቀንን እየጨመረ አመታት ቢቆጠሩም የዚህ ወጣት ሕይወት ሊቀየር አልቻለም ነበር። ምንም ፊደል ያልቆጠረው ወጣት ከጉልበት ስራ በሻገር የተሻለ ደመወዝ የሚያገኝበትን ስራ ማግኘት አልቻለም። እድሜው እየጨመረ የእለት ከእለት ኑሮው ከመሻሻል ይልቅ ከደጡ ወደ ማጡ እየሆነ ሲሄድ ሌላ አማራጭ ሌላ የተሻለ ገቢ ሊያገኝበት የሚችለውን ነገር ማሰብ ማሰላሰል ቀጠለ። ከመስራት ይልቅ መንጠቅን። ለፍቶ ጥሮ ግሮ ከማግኘት ይልቅ መቀማትን እንደ አማራጭ ቆጠረ።
የተለያዩ የስራ አማራጮች ወደ አእምሮው ቢመጡም እሱ የፈለገውን ገንዘብ ያህል ሊያስገኙ እንደማይችሉ በማሰብ ውድቅ ሲያደርጋቸው ቆየ። ከእለታት በአንዱ ቀን አንድ የባስ ፌርማታ ላይ ቁጭ ብሎ ምን ባድርግ ይሻላል በማለት ያወጣል፤ ያወርዳል። ድንገት አንድ አውቶቡስ መጥታ ከፊቱ ትቀማለች። የቆመው ህዝብ ወደ አውቶቡሷ ለመግባት የፈጠርው ትርምስ ትኩረቱን ስቦት ወደ ህዝቡ አይኑን ጣል ያደርጋል። ያኔ ከሚጋፉት ሰዎች መካከል በጣም እየተገፋ በየሰው ቦርሳና ኪስ በመግባት የሚፈትሽ ሰው ተመለከተ። የሌባው ሁኔታ ትኩረቱን የሳበው ወጣት አይኑን ሳይነቅል ይከተለው ጀመር።
ትኬት እየቆረጠ ወደ አውቶቡሷ ውስጥ ሰው ቀስ በቀስ ሲገባ ሌባው የያዘውን ይዞ ወደ ፌርማታው መለስ አለ። ምን ባደረግ ምን ብሰራ ይሳካልኛል ብሎ በማሰብ ከራሱ ጋር ትንሽ ስብሰባ ላይ የነበረው ወጣት ያየውን ወጣት ልምድ ልቡ ውስጥ ከቶ ከሌብነት የተሻለ አማራጭ የለም በማለት ውሳኔው ያደርጋል።
በዚህ መልኩ የስራ ምርጫውን ካደረገ በኋላ ለስራው ምቹ የሆኑ ቁሳቁሶችን ማሟላት ይጀምራል። ለስራው የሚያስፈልገውን ትጥቅ አሟልቶ ቀኑ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ጨለምለም ያለ ቦታን በመምረጥ ሰዎችን በማጥቃት የያዙትን መዝረፍ ጀመረ። በየእለቱ ከስራው ጋር እየተለማመደ ደስ እያለው የሄደው ወጣት አካባቢ በመቀያየር ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ መዝረፉን ተያየዘው። በየእለቱ ተመሳሳይ አይነት ወንጀል በተለያየ ቦታ እየተፈፀመ እንደሆነ መረጃው የደረሰው ፖሊስ ክትትል ቢያደርግም ወንጀለኛው ወጣት ግን ቦታውንና ዘዴውን በመቀያየር አልያዝ አልጨበጥ ይላል። በስርቆት የሚያገኘው ገንዘብ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ አግኝቶት የማያውቀው በመሆኑ ወንጀል መሆኑን ረስቶ እንደ ምርጥ ስራ አጠናክሮ ቀጠለ።
ጥሮ ግሮ በላቡ አዳሪው ወጣት
ወጣት ነው። በአፍላነቱ የስራ ጥቅም የገባው ለፍቶ፣ ጥሮና ግሮ አዳሪ። የእንጨት ስራ ትምህርትን ከአንድ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሰልጥኖ ከወጣ በኋላ ለተወሰኑ አመታት ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቶ የራሱን አነስተኛ ድርጀት በመክፈት መንቀሳቀስ ጀመረ። በሙያው የተመሰገነ የሰራው ሁሉ የሚያምርለት ብናየው ጋሻው አንዱ የአንዱን ስራ እየተመለከተ በርካታ ትእዛዞችን መቀበል ከጀመረ ሰነባብቷል።
በአናት በአናቱ የሚመጣውን ስራ የሚረዱት ሰራተኞች ቀጥሮ የሚያሰራው ይህ ወጣት ለታዘዘው ቁም ሳጥን መስሪያ የሚሆን እንጨት ለመግዛት ገንዘብ ከባንክ አውጥቶ ማልዶ ወደ ገበያ ለመሄድ ያቀዳል። የነገ ስራውን አቅዶ ጨርሶ ወርክ ሾፑን ዘግቶ ወደ ቤቱ ለመግባት ሲጣደፍ ነው እንግዲህ ያላሰበው ዱብዳ የገጠመው።
አሰቃቂው ትንቅንቅ
ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ገደማ ነው። ቀኑ ጨልሟል፤ ባጋጣሚ እሱ በሚሄድበት መንገድ አካባቢ የመንገድ መብራቶች የሉም ነበር። ጨለማው ከብድ ያለ በመሆኑ ወጣት ብናየው ጀርባውን ገልመጥ ገልመጥ እያለ ወደቤቱ ለመግባት ይጣደፋል። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ቀጠና 01 አካባቢ ወደቤቱ በመሄድ ላይ የነበረውን ወጣት መንገድ ላይ ጠብቆ ለእኩይ ተግባሩ ማስፈፀሚያ ያደርገዋል።
ወትሮም ሌብነትን ከጥቃት ጋር አስተባብሮ መፈፀም የለመደው ወንጀለኛ ከተደበቀበት በመውጣት የግራ ጭንቅላቱን በድንጋይ ደጋግሞ በመምታትና በጩቤ ግራ ዓይኑ በመውጋት የግራ ዓይኑ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ያደርገዋል። ተከታታይ የዱላ ውርጅብኝ የደረሰበት በስራ የዛለው ወጣት መከላከል በማይችልበት ሁኔታ መሬት ላይ ይወድቃል። ይህን የተመለከተው አጥቂ ራሱን እንዳይከላከል አድርጎ ጥቃት ካደረሰበት በኋላ የግል ተበዳይ ይዞት የነበረውን ሳምሰንግ ሞባይል የዋጋ ግምቱ 8,000/ስምንት ሺህ/ ብር የሚገመት ቀምቶ ይዞ መሮጥ ይጀምራል።
የጩኸት ድምፅ እንደተሰማ የሰፈሩ ነዋሪዎች በራቸውን ከፍተው ዱላና ባትሪ በመያዝ ጩኸት ወደ ሰሙበት አቅጣጫ ተመሙ። ወንጀለኛው በርከት ያለ የእግር ኮቴ ሲሰማ የያዘውን ይዞ እግሬ አውጪኝ ብሎ መሮጥ ጀመረ። ብዙም ሳይርቅ በመሮጥ ላይ እያለ በአካባቢው ሰዎች ደርሰው ያዙት።
የተያዘው ወንጀለኛ የፈፀመው ወንጀል ከባድ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ይዘው ለህግ አስረከቡት። ተጎጂውንም ወደ ህክምና ተቋም አደረሱ። ተጎጂው የደረሰበት አደጋ እጅግ ከባድ በመሆኑ የተነሳ ሁለቱን የዓይኑን ብርሃን መመለስ ሳይቻል ቀረ።
የሰው ሀቅ ለመፈለግ ሰርቶ ማግኘት የሚችለውን ገንዘብ ለማግኘት ሲል ታታሪውን በርካታ ተስፋ ያለውን ወጣት የዓይን ብርሃኑን አጠፋው፤ በእጆቹ ጥበብ ተጠቦ የእለት ጉርሱን ከማግኘት ባሻገር ቤተሰቡን የሚያስተዳድረውን ወጣት አካል ጉዳተኛ አድርጎ አስቀመጠው። ከራሱ አልፎ ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረውን እጀ ወርቅ ወጣት ተስፋ አጨለመው።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጠርጣሪው እጁ ከገባ ሰዓት ጀምሮ የዓይን ምስክሮችን የህክምና ማስረጃና የግል ተበዳይን ቃል በመቀበል ምርመራውን አጠናክሮ ወደ ዓቃቤ ህግ ይልካል። ዓቃቤ ህግም የተፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል መሆኑን ያረጋግጣል።
በመቀጠልም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ወዳጀ ልንገርህ አንለይ በተባለው ተከሳሽ ላይ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 671/2/ ስር የተመለከተውን ተላልፏል ሲል በከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ መስርቶበት ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ውሳኔ
የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ቀጠና 01 አካባቢ የግል ተበዳይ ብናየው ጋሻው ወደቤቱ በመሄድ ላይ እያለ መንገድ ላይ ጠብቆ ጭንቅላቱን በድንጋይ ደጋግሞ በመምታትና በጩቤ ግራ አይኑ በመውጋት የግራ ዓይኑ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ በማድረግ እንዳይከላከል ጥቃት ካደረሰበት በኋላ የግል ተበዳይ ይዞት የነበረውን ሳምሰንግ ሞባይል የዋጋ ግምቱ 8,000/ስምንት ሺህ/ ብር የሚገመት ቀምቶ ይዞ በመሮጥ ላይ እያለ በአካባቢው ሰዎች የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የውንብድና ወንጀል ተከሷል፡፡
ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ “እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም” ሲል ክዶ የተከራከረ ሲሆን ዓቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር የምስክሮች ቃል እና የሰነድ ማስረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ የዓቃቤ ህግን ክስ እና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።
በዚህም መሰረት ተከሳሽ ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት መሆኑን ጨምሮ ሰባት የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለት በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም