ድርሳነ ወንዝ”፤
“ሕዝብ በታላቅ ወንዝ ይመሰላል” – ይህን አባባል የብዙ አገራት ቋንቋዎች ይጋሩታል። የወንዝ አቅምና ጉልበት “ታላቅ” ለመባል ክብር የሚበቃው ከመነጨበት አንድ ምንጭ በሚያገኘው የውሃ ፀጋ ሞልቶና ተትረፍርፎ ስለሚፈስ ብቻ አይደለም። በጉዞው ሂደት ብዙ ወንዞች ወይንም ተፋሰሶች እየተቀላቀሉት የፍሰቱን መጠን ከፍ በማድረግ ስለሚዋሃዱት ጭምር ነው።
ከተለያዩ ምንጮች ከሚፈሱት አነስተኞቹም ሆነ ከፍተኞቹ ወንዞች መካከል ውሃቸው እየተጨለፈ ይኼኛው የውሃ ዓይነት ከዚያኛው ምንጭ የፈለቀ ነው፣ ያኛው የውሃ ዓይነት ደግሞ እንቶኔ ከሚባለው ምንጭ የተገኘ ነው፣ የማዶው ከወዲያኛው ገባር ወንዝ የተቀላቀለ ነው ወዘተ. እየተባለ ሊለይ ከቶውንም የሚቻል አይደለም። እንኳን ምንጫቸውን አንጥሮ ለመለየት ቀርቶ ከእነ አባባሉም “አንድን ፈረሰኛ ወንዝ ሁለቴ መሻገር አለመቻሉንም” በተለመደ ብሂል ሲነገር ማድመጣችን አልቀረም።
ያ “ታላቅ” የተሰኘው አንድ ወንዝ ከሌሎች የጋራ ወንዞች ጋር ተቀላቅሎ ቁልቁል የሚምዘገዘገው ስሙ በየአካባቢው ቋንቋና ዐውድ እየተለዋወጠ መሆኑን ልብ ይሏል። ለምሳሌ፡– ዐባይ፣ ዋቢሸበሌ፣ ተከዜ፣ ኦሞ፣ አዋሽ፣ አንገረብ፣ ገናሌ፣ ዠማ፣ ባሮ፣ አኮቦ ወዘተ. ወንዞቻችን በሚያልፉባቸው አካባቢዎችና አገራት የሚታወቁባቸውን ተለዋጭ ስያሜዎች ማስታወሱ ብቻ ይበቃል።
እነዚህ ወንዞች በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ሲፈሱ እከሌ ከሚባለው “ምንጭ” ብቻ የተገኙ ናቸው ተብለው አይሞካሹም። ያጎለበቷቸው የተጨማሪ ወንዞች ስምም አብሮ መጠቀሱ ግድ ይሆናል። ዐባይ ወንዛችንም ሆነ ሌሎች ወደ ባዕድ አገር የመውጣት ጉልበት ያላቸው ወንዞቻችን ከአገራቸው ውጭ ምን ስያሜ እንደተሰጣቸው የሚታወቅ ስለሆነ ዝርዝሩን መተንተን እጅግም የሚያስፈልግ አይመስለንም።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የእኛው ጥቁር ዐባይና ከጎረቤት አገራት የሚመነጨው ነጩ የዐባይ ወንድም በመሃል ካርቱም ከተማ ተገናኝተው በፍቅር ሲሳሳሙ በተመለከተበት አጋጣሚ የተሰማውን ስሜት በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል። ያባባል፣ ያስደስታል፣ ያስቆጫልም። ከነጩ መንትያው ጋር የተገናኘው ድፍርሱና ደለል የታጠቀው የአገሬ ታላቅ ወንዝ “ነጩን ወንደሙን” በማቀፍ ሰላም የሚለው ልክ እንደተከፋ ብሶተኛ “በደለሉ ሜክ አፕ” ፊቱን አጨፍግጎ ነው።
የካርቱምን የሁለት ወንዞች ግንኙነት ለጊዜው ትተን በምስር (ግብጽ) ዋና ከተማ ካይሮ እየተገማሸረ ከሚያልፈው ውህዱ ናይል የትኛው ውሃ የጦቢያ የትኛው ደግሞ ከነጩ እንደሆነ ለመለየት ፍጹም አዳጋች ነው። ይህ ጸሐፊ ስሙ በናይል የተተካውን የራሱን አገር ወንዝና የነጩን ወንዝ ምሥጢር በጥልቅ ለመፈተሽ ዕድሉን ያገኘው በተከታታይ ጉዞዎች ግብጽን፣ ሱዳንንና ዩጋንዳን ለመጎብኘት በቻለባቸው አጋጣሚዎች ነበር። ሰበበ ምክንያቱ ደግሞ ሌላ ሳይሆን ይኼው የአገሬ ጥቁር ዐባይ ለተጠቀሱት አገራት የጋራ በረከት እንጂ የጠብ ምክንያት እንደማይሆን ለየመንግሥታቱ መሪዎች ማረጋገጫ ለመስጠት በተጓዘው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ውስጥ አባል ስለነበር ነው።
ሕዝብ በወንዝ ፍሰትና ውህደት መመሰሉን በሌላ አንድ ተጨማሪ ማሳያም ጠንከር አድርጎ ማጎላመስ ይቻላል። አንዳንድ ወንዞች በአገራቸው “ሥራ ፈት ሆነው” ሲፈሱ ውለው ሲፈሱ ያድራሉ። ወደ ሌላው አገር ሲደርሱ ደግሞ ስማቸውም ሆነ ግብራቸው ተለውጦ በረከት ያሳፍሳሉ። የእኛው “ታላቁ” ዐባይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ (አሁን እንኳን ሃሜቱ ቀርቶለታል) ለራሱ ሕዝብ “እራትም መብራትም” መሆን ተስኖት ዘመናት እንዳሸበተ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። ለጎረቤት አገራት ግን ከእራትም ሆነ ከመብራት የላቀ የብልጽግናቸው፣ የታሪካቸውና የባህላቸው መሠረትና ዐምድ ሆኖ መኖሩ ከእኛም ሆነ ከእነርሱ የተሰወረ አይደለም።
በእኛ ስንፍና ምክንያት ለዘመናት አስከፍተነው የኖርነውን ግዮን ወንዛችንን ጎረቤቶቻችን ከወንድሙ ከነጮ ጋር ሲገናኝ ቄጤማ ጎዝጉዘውና “ቤት ለእምቦሳ” በማለት እንደምን በዕልልታ አጅበው ሲቀበሉት እንደኖሩት በዐይናቸው ያዩ እማኞችና ታሪክ ምሥክሮች ናቸው። ለዘመናት ሲተረክና ሲወራ የኖረውን ይህን ያረጀ ተረክ እንደ አዲስ መቀስቀሱ “የዐዋጁን በጓዳ” እንዳይሆን ስለሰጋን ትንታኔውን ገታ በማድረግ ወደ ዋናው መነሻችን መዝለቁን መርጠናል።
ኢትዮጵያ ሆይ!
ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ሲቀላቀልና ሲዋሃድ የኖረው ሥርዓተ መንግሥታት ወይንም የየዘመኑ ዝንጉርጉር የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ፈቃድ ስለሰጡ ወይንም በአዋጅ ስላዘዙና ስላስፈራሩ አይደለም። አንደኛው ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ሲቀራረብ፣ ሲዛመድና ሲዋሃድ የኖረው ተፈጥሯዊ ግዴታ ስለሆነ ብቻ ነው። የደም ትሥሥር፣ የጋብቻ ውል፣ በኢኮኖሚ መደጋገፍ፤ የባህል፣ የቋንቋ፣ የእምነትና የሃይማኖት መወራረስ እንደ ድርና ማግ አጋምዶ ስለሚያደበላልቃቸው ጭምር።
ሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት ብቻም ሳይሆን ጦርነት፣ ፍልሰት፣ ስደትና መከራን የመሳሰሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችም ሕዝብን ከሕዝብ የማቀላቀል መግነጢሳዊ አቅማቸው እጅግ ከፍ ያለ ነው። የዓለማችን በርካታ ታሪኮች ለዚህ በቂ ማሳያዎች ስለሆኑ ዋቢ ሰነዶችን ማመሳከር ይቻላል። “የታላቅነቷን ትዕቢት” እንደ ባቢሎን ግንብ ሽቅብ እየገነባች ያለችው የዛሬዋ አሜሪካ ይሏት አገር ለዚህ እውነታ በጥሩ አብነት ትጠቀሳለች።
“በረከተ መርገም” እንዲሉ ይህቺ ለመሰደጃነት፣ ለእርዳታና ተራድኦ፣ ለጣልቃ ገብነትና ሌሎችም ማንም አገር እንዲቀድመኝ አልፈልግም የምትለው አገረ አሜሪካ ሕዝቧን የምትጠራው “Melting Pot” እያለች ሲሆን፤ ትርጉሙም የዓለማችን ሕዝበ አዳም እንደ “ለማኝ አኩፋዳ” የልመና ጥራጥሬ ተቀላቅሎና ተደበላልቆ የሚኖርባት አገር እንደ ማለት ነው።
“ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ተደርጎ አይቆጠርና የኢትዮጵያ ሕዝብ የጥንተ ሥሪት ታሪክ ድንቅ አሰኝቶ የሚያስደምም ነው። ውቢት ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ብሔረሰቦቿን አፋቅራና አስተቃቅፋ የኖረችው በታላቅ ጥበብና እውቀት ነው። ከደቡብ የተገኘው ወገን ወደ ምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ተጉዞ ከነዋሪው ጋር “ቤትህ እንደ ቤቴ” በማለት መቀላቀል የጀመረው ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ እምነቱንና ሃይማኖቱን እንደያዘ ነው። የምዕራቡ ወደ ሰሜን፣ የሰሜኑ ወደ ደቡብ፣ የምሥራቁ ወደ ምዕራብ፣ የምዕራቡ ወደ ደቡብ ሲጓዝና ሲደበላለቅ የኖረው “ይህ ልኩ” በሚባል መጠን ያለመሆኑን ብዙ የታሪክ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይችላል።
ይህንን ሰፊና ጥልቅ ፍልስፍና በደንብ የሚገልጽልን “ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ” በሚል ርዕስ በተከበረው ነፍሰ ሄር መምህራችን ገጣሚ ደበበ ሰይፉ የተጻፈው ግጥም ነው። መጽሐፉ ተፈልጎ ቢነበብ ይጠቅማል። የረጅሙን ተራኪ ግጥም ዋና ጭብጥ ጠቅለል አድርገው የያዙትን የተወሰኑ ስንኞች እንደሚከተለው እናስታውስ።
“እኔና ወንድሞቼ ሁላችን ሁላችን፣
ከባዶ አቁማዳ ነው እሚዛቅ ፍቅራችን።
ይህ ነው አንድነታችን፣
ይህ ነው ባህላችን፣
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን።”
ሕዝብ ያለ ሌላኛው ሕዝብ አስተዋጽኦ በታሪኩ፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ መስተጋብሩም ሆነ በባህሉና በሃይማኖቱ ወዘተ. ኑሮው ፍቺ አልባ ዕንቆቅልሽ እንደሚሆን መገመቱ አይከብድም። በጀብደኞች አካኪ ዘራፍ ወይንም በፖለቲከኞች “የተረት ተረት” ትርክት የሕዝቦች ወንድማማችነትና አህትማማችነት በፍጹም የሚቋረጥ ዥረት አይደለም። ሊሆንም አይችልም።
ሕዝብ ከሕዝብ እንዳይገናኝ በአዋጅም ሆነ በድንበር ጠባቂ ዘብ መግታትም የሚሞከርም አይደለም። የእገታው ዘዴ ከአሁን በፊትም ሆነ ዛሬ በፍጹም ሠርቶ አያውቅም። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከአንዱ ወንዝ ውስጥ የአንዱን ውሃ ከአንዱ ለይቶ ማውጣት እንደማይቻል ሁሉ በጋብቻና በመዋለድ የተቀላቀለውን የሕዝቦች ደምም የአንዱን ከሌላኛው አንጥሮ ለማውጣት መሞከር በተፈጥሮ ብርታትም ሆነ በሰው ልጅ ጥበብ የሚቻል አይደለም።
ኢኮኖሚያዊ ትሥሥሩን፣ ሃይማኖታዊ ኅብረቱን፣ ባህላዊ መስተጋብሩን፣ ማሕበራዊ ቁርኝቱንና ከሁሉም በላይ የደም ትሥሥሩን ለማላላት ይሞከር ካልሆነ በስተቀር የመሸመኛውን ድርና ማግ እበጣጥሳለሁ ብሎ መፎከርም ሆነ ማላዘኑ እርባና ቢስነት ነው። ሃሳቡን ከቀዳሚው ምሳሌያችን ጋር እናቆራኘውና፤ አንድን ታላቅ ወንዝ ለተወሰነ ዓላማ መገደብ ይቻል ካልሆነ በስተቀር የወንዙን ፍሰት ሙሉ ለሙሉ አቆማለሁ ማለት ከቶውንም አይሞከረም፤ ሊተገበርም አይችልም።
የሕዝብን የመፈላለግና የመሳሳብ ተፈጥሯዊ ባህርይ የጠብታ ያህልም ቢሆን ሊያመላክት ስለሚችል የዚህን ጸሐፊ አንድ የግል ገጠመኝ እዚህ ቦታ ማስታወሱ ተገቢ ይመስለናል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁሉም የአፍሪካ አገራት የተወከሉበት አንድ ታላቅ የባህል ፌስቲቫል በአልጄሪያ ዋና ከተማ በአልጀርስ ተካሂዶ ነበር። ይህ ታላቅ አህጉራዊ የአደባባይ ትእይንት የተካሄደው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በተጠናቀቀበት ማግሥት ስለነበር በሁለቱ አገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረው ቁርሾ እጅግ መራር ነበር።
በዚያ ወቅት የየአገራቱ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ለማራራቅና ለማለያየት ይፈጽሙት የነበረው የተጋጋለ ዘመቻና ቅስቀሳ በፍጹም የሚረሳ አልነበረም። ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች፣ ኤርትራውያንንም እንዲሁ ከኢትዮጵያ ነፍስያ ለመንጠቅ ሲሰራ የነበረውን የረቀቀ ሴራና ተንኮል ዕድሜውን ያደለን ዜጎች አንዘነጋውም።
ለማንኛውም በአልጀርሱ የባህል ፌስቲቫል ወቅት ለአፍሪካ አገራት የባህል ልዑካን የተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ የማረፊያ መንደር የየአገራቱን የጉርብትና ቅርበት መሠረት ያደረገ ስለነበር የኢትዮጵያና የኤርትራ የልዑካን ቡድን ያረፉት በተንጣለለ ሰፊና ሰማይ ጠቀስ የአፓርትመንት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነበር።
አመሻሽቶ አልጀርስ የገባውን የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ያስተባብሩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ማደሪያቸውን አደላድለው ሲያበቁ በአንድ ጉዳይ ላይ መመካከር ጀመሩ። አጀንዳውም “በሌሊት ተነስተን የኤርትራን የባህል ቡድን ለማግኘት ለምን አንሞክረም?” የሚል። በምክክሩ መሠረትም አምስት ያህል የሚሆኑት አስተባባሪዎች በማለዳ ነቅተው የኤርትራ ልዑካን ያረፉበትን አካባቢ እያፈላለጉ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ለካንስ ኤርትራውያን ወንድምና እህቶችም ልክ እንደ ኢትዮጵያውያኑ ተመካክረው ኖሮ ሁለቱም ሲፈላለጉ መሃል መንገድ ላይ ተገናኙ።
ያን ግንኙነት ማስታወሱ ስሜት ውስጥ ቢከትም አጋጣሚውን ለአንባቢያን ማስታወሱ ግን ይጠቅም ይመስለናል። የተገናኙት የሁለቱ ወንድማማች አገራት የቀድሞ ጓደኞች ገና በሩቁ ሲተያዩ ልክ ዘመድ እንደተረዳ ቤተሰብ በእንባ እየተራጩ ሮጠው ሲተቃቀፉ ላስተዋለ ሰው ግርምት የሚፈጥር ብቻ ሳይሆን ድንጋጤን የሚፈጥር ጭምር ነበር። ከተቃቀፉም በኋላ አንዱን ከአንዱ ለማላቀቅ በእጅጉ አስቸግሮ ነበር።
ለካንስ እነዚህ የሁለቱ አገራት የባህልና የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች በደጉ ዘመን፤ አገራቱ ለሁለት ሳይከፈሉ በፊት፤ ወይ አዲስ አበባ ብሔራዊ ቲያትርና ሌሎች ቲያትር ቤቶች አለያም አስመራ ከተማ ውስጥ በሚገኙ መሰል የቲያትር ቤቶችና የባህል ማዕከላት ውስጥ አብረው ሠርተዋል፣ አብረው ደስታና ሀዘን ተጋርተዋል፣ አብረውም አገር ወክለው ወደ ተለያዩ ዓለማት በመጓጓዝ ትዝታና ታሪክ የነበራቸው ነበሩ።
ከቁርኝታቸው ጥብቀት የተነሳ የወቅቱ የፖለቲካ ጭጋግ ፍቅራቸውን አላቀዘቀዘም። የፕሮፓጋንዳው ጥላም አላራራቃቸውም። በከንቱ የተለኮሰው የጦርነት ጥፋትም በመካከላቸው ቂምና ቁርሾ አልተከለም። በአንጻሩ ሲጨዋወቱ የነበረው የዚያን መልካም ጊዜ ትዝታና ገጠመኝ እንጂ ከጥቂት ወራት በፊት የተጠናቀቀው ጦርነትና ያልተቋጨው የድንበርና የወሰን ጉዳይ አልነበረም። በቆይታቸውም አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በፍጹም ፍቅር ተቀራርበው ሲጨዋወቱ ማየት በእጅጉ ይደንቅ ነበር። ይህ ገጠመኝ ለዛሬው ዐውዳችን አንዳች ትርጉም ሳይሰጥ ይቀራል?
የትግራይና የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተቆራኘው ክፉ ወቅት በሚበጣጥሰውና በሸረሪት ድር በሚመስል ግንኙነት አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ደም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ውስጥ ተደባልቆ ለአገራችን ውበት ሆኗታል። የተቀሩት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ደምም ከትግራይ ሕዝብ ደም ጋር ተቀላቅሎ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የመሠረት ማጥበቂያ ሆኖ ሥር ሰዷል። ይህ መስተጋብር የተፈጠረው ትናንት ወይንም ከትናንት ወዲያ ሳይሆን ቅድመ ታሪክና ድኅረ ታሪክ ሊባል በሚችል የዘመን ርዝመት ውስጥ ነው። ስለዚህም ነው “ሕዝብ ያለ ሕዝብ ኑሮው እንቆቅልሽ ነው” የሚባለው። ይህን ቁርኝት በፕሮፓጋንዳም ሆነ በፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ገፍትሮ ለመናድና ለማፈራረስ መሞከር እብደት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊኖረው ከቶም አይችልም። ልብ ያለው ልብ ይበል! የመልዕክታችን ማጠንጠኛ ነው። ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም