ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀውና በሰሜኑ የአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት መቋጫ ያገኝ ዘንድ ከሰሞኑ በፌደራል መንግስቱና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል። ይህ ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ድጋፍ የተሰጠው ሲሆን በዲፕሎማሲው ረገድ እንደትልቅ ስኬት የተቆጠረ ነው። በተለይም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ስለመሆኑ ብዙ የዘርፉ ባለሙያዎች እማኝነታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁንን የዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳ›› አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- በፌደራል መንግስቱና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አንድምታ ምን እንደሚመስል ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አምባሳደር እሸቴ፡– የሰላም ድርድሩ ይጀመራል ሲባል ከተለያዩ አካላት በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ስለነበር ጥርጣሬዎች ነበሩ። በእርግጥ በፌደራል መንግስቱ በኩል የነበረው ግልፅ ነበር። ይኸውም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለመወያየት ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁ ነበር። በሕወሓት በኩል ደግሞ በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን ያዘለና በየጊዜው ደግሞ የሚለዋወጥ አይነት መልዕክት ይተላለፍ ስለነበር ማንም ሰው ላይ ጥርጣሬ ቢኖር የሚገርም አይደለም። ዋናው ነገር እንግዲህ አይነት ድርድሮች ሲካሄዱ ተደራዳሪ ወገኖች ለመገናኘት ያላቸው ፍላጎት፤ በድርድር ችግሩን ለመፍታት ያላቸው የመተባበር ፍቃደኝነት ነው። ሂደቶች ሲታዩም ወደ በጎ አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
በእኔ እምነት በፌደራል መንግስቱና በሕወሓት በኩል ከጀርባው ለውጥ ላለማምጣት የተዘጋጀ አይነት መንፈስ ቢኖር ኖሮ አሁን የምንገኘው ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም ነበር። እንዳውም ካነሳሁልሽ በተቃራኒ አንዱ የሌላውን ሁኔታ ለመረዳት የመፈለግ ነገር ይታያል። የድርድር ጉዳይ ዞሮ ዞሮ ሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በተወሰኑ ነገሮች ላይ መስማማት የሚቻለው ግትር አቋም በመያዝ አይደለም። እናም ይህንን መንፈስ ይዘውና ተዘጋጅተው በመሄዳቸው እስካሁን ባለው ሁኔታ አወንታዊ መንፈስ ነው የሚታየው።
ድርድሩ ምን ይዞ መጣ? ካልን ብዙነገሮችን ማንሳት ይችላል፤ ለምሳሌ ለአገራችን የዲፕሎማሲ ስኬት ነው ብለን መውሰድ አለብን። ማናቸውም ችግሮች በኃይል አይፈቱም፤ ለጊዜው በኃይል ግጭትን ማቆም ይቻላል፤ ሰላምንና የማህበራዊ ግንኙነት መሻከርን መልሶ ለማሻር ግን አይቻልም። እንደገና በግጭት ወይም በኃይል ብቻ መፍትሄ የሚያገኝ ሲሆን ጉዳት አለው። መጀመሪያ ማንኛውም ግጭት በተለይም እንደዚህ አይነቱ የከፋና ሰፊ ይዞታ ያለው ጦርነት የሰውን ህይወት ይበላል፤ የአገርን ሃብት ያወድማል፤ መሰረተ ልማቶችን ያጠፋል፤ ማህበራዊ ግኑኝነቶችን ያቃውሳል፤ በዲፕሎማሲ በንግግር በውይይት ሲፈታ እነዚህን ችግሮች ማስቀረት ይቻላል። ስለዚህ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ብዙ ጉዳት ከደረሰብን በኋላም ቢሆን ድርድሩ መካሄዱ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድል ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ደሴት አይደለችም፤ ከዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ጋር አካል ሆነን የምንኖር በመሆኑ የዓለም አቀፍ ህብረተሰቡ ይህ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ መከታተል አለብኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ያሳሳበኛል የሚል የተለያየ መልዕክት የተለያየ ተፅዕኖ ማሳደሪያ መንገዶችን ተግባርያዊ ማድረግ በተለይ እኔ በምከታተላቸው በምዕራቡ ዓለም አገራት ይሄ መንፈስ እንዳለ ይታወቃል። ያንን በእጅጉ የሚያቀል ነው። ተጨማሪ ስራዎችን ስንከውን ደግሞ የበለጠ ኢትዮጵያ ወደነበራት የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ደረጃ እንድትመለስ ያግዛታል። ስለዚህ የዲፕሎማሲ ስኬት አለው ብለን ማየት እንችላለን።
ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍላጎቶችን በኃይል፤ በተለይም በጦር መሳሪያ ኃይል ለማስፈፀም የማያስኬድ፣ የማያዋጣና አክሳሪ መሆኑን በየዘመኑ እያየነው መጥተናል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት የሚሰጥ ይመስለኛል። ወደ ድርድር ፖለቲካ፤ የሰለጠነ የፖለቲካ አስተሳሰብ የምንሸጋገርበትን ሁኔታ የሚያደላድል ነው ብዬ አምናለሁ። ለዚህም መላ ህብረተሰቡ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ሁላችንም ተረባርበን የጦርነትና የግጭት ታሪካችንን በቃ እንድንል እድል የሚፈጥር ይመስለኛል። ለዚያ ደግሞ ሁላችንም መስራት አለብን። ምክንያቱም ጥቅሙ ለራሳችን ነው። መላው ኢትዮጵያውያን አሸናፊ የሚሆኑት በዚህ ነው። ችግር አፈታት፤ አስቀድሜ ያነሳኋቸው የህይወት፤ የንብረት መውደም ሳያደርስ ተነጋግሮ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ የሚወስኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፤ እናም ለግጭቱ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመግባባት መፍታት ሲቻል በመሆኑ በዚህ ረገድ ድርድሩ መልካም ነገሮችን ይዞ መጥቷል የሚለው በጣም ሊሰመርበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አስቀድማም ይዛው ከነበረው የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት ከሚለው አቋሟ አኳያ ምን ያህል ተሳክቶላታል ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር እሸቴ፡- ስምምነቱ አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ያለጥርጥር ጥሩ ማሳያ ነው ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው ምዕራፍ ተወጥተነዋል፤ ቁጭ ብለን በንግግር ጉዳዩን ለመፍታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይዞ መገኘት ተችሏል። ይህ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ የማይታይና እየጎዳን ያለ ነው። እስካሁን በነበረው አካሄድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የጋበዘ ግጭቶች የተራዘመ ጊዜ እንዲፈጁ የሚያደርገውን ታሪክ እንዴት ለመለወጥ እንደሚቻል ሞዴል ሊሆን የሚችል ነው። ከአሁን በኋላም ይህንኑ አቅጣጫ ይከተላል ብዬ አስባለሁ። እንዳልኩሽ ይህ ድርድር የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ይዞ የተጀመረ ነው። በመቀጠልም በወታደራዊ መሪዎች መካከል ውይይት ተደርጓል። የሚቀረው የአፈፃፀም ጉዳይ ነው የሚሆነው።
የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ አንደኛ አፍሪካ ችግሮቿን በራስዋ ለመፍታት ያዘጋጀቻቸው በርካታ መዋቅሮች አሉ። ከዚያ ውስጥ አንዱ ምሰሶ ይሄ ነው። በንግግር፣ በውይይትና በድርድር ችግሮችን መፍታት ለዚህ ደግሞ አህጉሪቱ ያላትን ታላላቅ ሰዎች፣ አሸማጋዮች፣ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በመጠቀም ችግራችንን መፍታት እንችላለን ብለው መሪዎቹ ከተስማሙበትና ስራ ላይ እንዲውል ተቋማቱን ካደራጁ ቆይተዋል። ግን በስኬት የተቋጩ ግጭቶች ብዙ አይደሉም። የሚናቁ ደግሞም አይደሉም። ብዙ በድርድር መፍትሔ ያገኙ ግጭቶች እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ተቋማትና ለፓን አፍሪካኒዝም ካለብን ኃላፊነት አንፃር ውጤት እንዲያገኝና ማሳያ እንዲሆን ሁላችንም በርትተን መስራት አለብን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ምንአልባት ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ በህብረቱ ላይ ሙሉ እምነት ያለመኖር ነገር ይታያል፤ ከዚህ አንፃር የዚህ ድርድር መሬት መውረድና ከዳር መድረስ ይህንን አስተሳሰብ በመቀየር ረገድ ያለውን ፋይዳ ከዚሁ ጋር አያይዘው ቢመልሱልኝ?
አምባሳደር፡- አንቺም እንዳነሳሽው አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው ይፈታሉ፤ ህብረቱም የመፍታት አቅም አለው ወይ? የሚለው ነገር በብዙ አባላት ኀገራት ጥርጣሬ ነበር። እኛም ብንሆን ምንያህሎቻችን ነን የአፍሪካ ህብረት ያደራጃቸውን መዋቅሮች፣ ያሉትን የአሰራር ስርዓቶች እንዲሁም በጋራ መንግስታቱና የህብረቱ አባል ኀገራት ዜጎች እንዲተገብሩ የምንፈልጋቸውን ጉዳዮች የምናውቀው የሚለውን ነገር ጥያቄ አለ። ያ ማለት ማስተዋወቅ ላይ መንግስታትም፤ ምሁራንም፤ የሲቪል ማህበረሰብ ሁላችንም የምንወስደው የድክመት ድርሻ አለ። ያ ነው የጥርጣሬ መንፈስ እንዲኖር ያደረገው።
ሁለተኛው ከብቃት ጋር፣ ካነሳሽው ጋር ተያይዞ አፍሪካ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮቿን በአጋሮች ድጋፍ፤ ፋይናንስ የማድረጓ ነገር ነው። በተለይ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በሌላ ኃይል የምትደጎሚ ከሆነ ሁልጊዜም አብሮ እየተጎተተ የሚመጣ የድጋፍ አድራጊዎቹ ፍላጎት አለ። ከዚያ ለመላቀቅ የሰላም ፈንድ ተቋቁሞ እየተሰራበት ነው። ግን አህጉሪቱ ራሷን የምትችልበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ስራ ያስፈልጋታል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ከ25 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪ ለመሸፈንም አይችልም። ያውም አፍሪካ መር በመሆኑ እንደዚህ አሁን እንዳየነው ድርድር የሰላም መልዕክተኞች የመላክ አይነት ወጪያቸው እጅግ ያልተጋነነውን ብቻ ነው የመሸፈን አቅም ያላት። በነገራችን ላይ በዓለም ላይ ካሉት የሰላም ጥበቃ ስምሪቶች ከ60 እስከ 70 በመቶው አፍሪካ ነው ያለው። በየዓመቱ ለዚህ ዓላማ ከስድስት እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በጀት ይፈጃል። በአጠቃላይ አሁን ላይ አፍሪካ በራስዋ ተነሳሽነት የፈጠረቻቸው የሰላም ማስከበር ተቋማት በራሷ ለመደጎም በጭራሽ አልደረሰችም።
በዚህ ምክንያት የውጭ እጅ ስላለበት የአፍሪካ የግጭት አፈታት በጥርጣሬ ቢታይ የሚገርም አይደለም። ሆኖም እኛ እንደኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ ማድነቅና ከፍ አድርገን ማሳየት ያለብን አህጉሪቱ የራስዋን የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት፣ ኮሚሽኑ፣ የተደራጁ የተለያዩ መዋቅሮች፣ የፖለቲካ ዲፓርትመንቱ፣ የሚኒስትሮቹ ምክር ቤትም እንዲሁ ከዚያም ከፍ ስንል የመሪዎቹ ጉባኤ አለ። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አፍሪካ ችግሮቿን ለመፍታት አሁንም ቢሆን ብቃት አላት፤ የሂደት ጉዳይ ነው ብሎ ማመንና እዚያ ላይ ሁሉንም አቅም ማረባረብ ነው የሚገባን።
አዲስ ዘመን፡- የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መረጋጋትና ሰላም መስፈን ለምስራቅ አፍሪካ የሚኖረው አንድምታ ምንድን ነው ይላሉ?
አምባሳደር እሸቴ፡- ትክክል ነው፤ አንደኛ ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ያላትን ክብደት መረዳት ያስፈልጋል፤ በህዝብ ብዛታችን፣ ኢኮኖሚው ለማደግ ባለው ተስፋ፣ ህዝቡ ራሱን ችሎ ነጻነቱንና ክብሩን ለመጠበቅ ካለው ፍላጎት፣ ከታሪካችንና ሌሎች በርካታ ነገሮችን መዘርዘር ይቻላል። ከእነዚህ ዋና ዋና መለኪያዎች አንፃር በቀጠናው ላይ ከፍተኛ ሚና ያላት አገር ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት ከአሁን ቀደም የቆየውንና ለረጅም ጊዜ የምናውቀውን የግጭት ቀጠና ነው። ለዚህ ምክንያቶች አሉት፤ ከቀኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የመጣ ስትራቴጂካዊ የሆነ የመተላለፊያ ግንባር አካባቢ ነው። ተፎካካሪ የዓለም ኃያላን የሚፈልጉት አካባቢ ነው። ግጭቱ ሁልጊዜም ቢሆን በአካባቢው ላይ የሚያጠላው ነገር አለ።
ሌላው የሽብርተኝነት፣ የሃይማኖት ፅንፈኝነት ችግሮች አሉ። ዋናው ደግሞ የዚህ የአፍሪካ ቀንድ አገራት የመንግስታቱ አቅም፣ የሕዝብና የመንግስት ተቋማት የሚገኙበት ሁኔታ፣ የጎረቤት አገራት የንግድና የኢኮኖሚ ትስስራችን የተዳከመ መሆኑ ለግጭቶች ተጋላጭ አድርጎናል። እዚህ በጣም የሚያስተሳስሩን የጥቅም ጉዳዮች ጠንካራ ሲሆኑ እርስ በርስ መደጋገፍና ግጭትን ለመከላከል አመቺ ሁኔታን የመፍጠርና የመተባበር መንፈሱ እንዲበረታ ያደርጋል። ስደትም እንዲወገድ ያደርጋል፤ የአካባቢው አገራት ሙሉ ትኩረታቸውን ከህዝባቸው ጭምር ወደ ልማት፣ ረሃብን መዋጋት፤ ችግርን ማስወገድ እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል። እናም ይህ የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ ያለው አንድምታ ትልቅ ነው። ምንም ይሄ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡-አፍሪካውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት መቻላቸው የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴና በህብረቱ አባላት ጋር ያለውን ህብረት በማጠናከር ረገድ ምን አይነት ሚና ይኖረዋል?
አምባሳደር እሸቴ፡- ይሄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው። የፓን-አፍሪካኒዝም ዋናው መነሻው የአስተሳሰቡ ማዕቀፍ አፍሪካውያን የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መምራት እንችላለን የሚለው ነው። ሌላ ወገን መጥቶ ፍላጎቱን በእኛ ላይ መጫን የለበትም የሚል ነው። ይሄ ደግሞ ከአድዋ ድል በኋላ የመጣ አስተሳሰብ ነው። የማድረግና ክብርን የማስጠበቅ አቅም መፍጠር፤ እኩል ተደራዳሪና አቻ ሆኖ በዓለም አቀፍ መድረክ የመታየት፤ የአገር አጀንዳን የማጋራትና የጋራ አቋም ሆኖ እንዲወጣ የማድረግ ነገሮች አሉበት። ዋናው የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መምራት፣ ማስተዳደር አቅምም፣ ዝግጁነትም አለን የሚለው መንፈስ ውስጡ ያለ ነው።
ለዚህ መንግስታችን በቁርጠኝነት ሰርቷል። ከአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ አደራዳሪ ውጪ የጎንዮሽ ወይም ሌላ አማራጭ የድርድር መስመር አንቀበልም የሚለው በጣም ጠንካራ አቋም ነበር። ወደኋላ ላይ በዋና አደራዳሪው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች ሕወሓት ማቅረብ ሲጀምር የሚያሰጋ ሁኔታ መጥቶ ነበር። ግን ሌሎች ይታከሉበት የሚለው ሃሳብ ሲመጣ ያለ ቅድመ ሁኔታ ያልነው ነገር ተቀባይነት አገኘ። በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ያለውን መንግስት ቃሉን አክብሯል። ይህ ደግሞ በአፍሪካ ተቋምና በአፍሪካውያን ላይ እምነት ማሳደር ነው። ይሄኛው ደግሞ ከአፍሪካዊ ወንድማማችነት ጋር የሚያያዝ ሲሆን የፓን- አፍሪካ መንፈስንም ያስጠበቀ ነው።
ከዚህ አንፃር ለፓን-አፍሪካኒዝም መጠናከር ትልቅ ጥቅም አለው። በአፍሪካ ህብረት ተቋማት ላይ እምነት እንዲያድር ያደርጋል። ሌላው ደግሞ አፍሪካውያን በራሳችን ችግራችንን የመፍታት ብቃት አለን፤ መደራደር እኛም እናውቃለን የሚል መልዕክትም አለው። አፍሪካም ያለ ሌላ ወገን ተፅዕኖና ቅድመ ሁኔታ በራስዋ ዜጎቿ ተነጋግረው ችግራቸውን መፍታት ይችላሉ፣ በራሴ ነው የምቆመው የሚለውን መንፈስ የሚያንፀባርቅ የሆነ ትርጉም አለው ባይ ነኝ። ይልቁንም ስምምነቱ የህብረቱ ዋና መቀመጫ በሆነችው አገር ለፓን-አፍሪካኒዝም ፋናወጊ በሆነችና ሌሎችን አነሳስታ ለዚህ አስተሳሰብ መሪ ሚና የነበራት አገር ላይ የተቻለ መሆኑ ከፍተኛ ትርጉም አለው።
አዲስ ዘመን፡- ከስምምነቱ በኋላ የአለም አገራት ስሜት ምን ይመስላል? በተለይ በዚህች አገር ጉዳይ እጃቸውን ሲያስረዝሙ የነበሩ ኃያላን አገራት ይህንን ስምምነት የተቀበሉበት ሁኔታ እንዴት ይታያል?
አምባሳደር እሸቴ፡- አንዱ ሁልጊዜ ማወቅ ያለብን ማንኛውም በዓለም ላይ ያለ አገር ከሌሎች አገር ጋር በሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ሆነ የአጋርነት ማዕቀፍ ውስጥ ሁልጊዜ ተቀባዩ አገር ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከ አፍሪካም ሆነ ከአውሮፓ የምትፈልገው ነገር አላት፤ እነሱም እንደዚያው የሚፈልጉት ነገር አለ። የበለፀጉት አገራት ዋናው የሚፈልጉት የእነሱን እሴቶቻችን ብለው የሚያራምዱትን ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት ድጋፍ ጉዳይ፣ የመልካም አስተዳደር የመለኪያ መለያየት ካልሆነ በስተቀር እኛም ይህንን እንፈልጋለን። እነሱ 150 ዓመታት ሄደውበትና ዛሬ የደረሱበትን ደረጃ ‹‹ተቀብላችሁ ተግባራዊ አድርጉት›› ሲሉ ተቋማት፣ የማህበረሰብ ዝግጁነት የመሳሰሉት አስቻይ ሁኔታዎች ስለማይኖሩን እንደምንፈልገውና እነሱ ከሚያስቀምጡት መለኪያ አንጻር ለመራመድ አስቸጋሪ ነው። ይሄ ችግር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አፍሪካ አገሮች ላይ የሚታይ ነው። የተሻለ መዋቅርና መሰረት አላቸው የሚባሉት አገሮችም ቢሆኑ በምዕራባውያኑ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ፖለቲካል ኢኮኖሚያቸውን ለመምራት የሚሆን ነገር አይደለም።
ሁለተኛው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያሳድሩት ጫና እና በሚያራምዱት አቋም ኢትዮጵያ ልትከተላቸው ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ በታሪካችን እንደሚታወቀው ጉዳዮች ከብሔራዊ ጥቅማችን፣ ከነፃነታችን፣ ከእኩልነታችን መንፈስ ጋር የሚቃረን ከሆነ ለመስማማት በጣም እንቸገራለን። ይሄ አቋማችን ያስደስታችኋል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ይህም አስቀድሜ ካልኩት ጋር ግጭት አለው ማለት ነው። ስለዚህ ጉዳዮቻችን እነሱ በሚፈልጉት አቅጣጫ እንዲሄዱ የመሻት ስሜት ነበረ። ስምምነቱ ከተደረሰ በኋላ የመጣው ምላሽም ይህንኑ ከሞላ ጎደል የሚያንፀባርቅ ነው። እኔ እንደታዘብኩት ግን በጣም በአብዛኛው አዎንታዊ ነው። በተለይ ትልልቆቹና ተፅዕኖ አሳዳሪ የሆኑት አገራት በአዎንታ ተመልክተውታል። ለውጤታማነቱም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃላቸውን ሰጥተዋል። እርግጥ ቃል የመጠበቅ ጉዳይ በሂደት የሚታይ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ በዓለምአቀፍም ሆነ በአገራችን ውስጥ ለማሳደር ከሚፈልጉት ተፅዕኖ አንፃር የማሰለፍ ፍላጎት የሚኖር ነው። ስለዚህ ሁሌም አንፃራዊ ነው ማለት ነው። በአብዛኛው ድጋፍ አለ፤ በተለይ ከትልልቆቹ አገራት የሚለውን መውሰድ ያስፈልጋል። ሁለተኛዎቹ ደግሞ የሚያምኑት አይነት ነገሮች ነበሩ፤ ‹‹ይሄ ነገር ወታደራዊ መሪዎች ተቀምጠው እስከሚነጋገሩበት ድረስ ከባድ ነው፤ ትጥቅ ማስፈታት አይቻልም፤ ስለዚህ ጠብቀን እንይ›› በሚል በጥርጣሬ መንፈስ የሚያዩ አሉ። ይህም ቢሆን የሚገርም ነገር አይደለም፤ መልካሙ ነገር ግን አብዛኞቹ አለመሆናቸው ነው።
ሌሎች ደግሞ የተበሳጩ አሉ፤ ‹‹አሰላሳይና ፀሃፊ ነን የሚሉ፤ የአካባቢውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ በደንብ እናውቃለን የኛ ትንታኔ ብቻ እንደእውነት መወሰድ አለበት›› የሚሉ አሉ። እነዚህ ብዙዎቻችን እንደምናውቀው የግጭት ነጋዴዎች የምንላቸው ናቸው። ሌላው የተሳሳተ አቋም የያዙ ኢትዮጵውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን ማየት ተገቢ ነው። እነሱ የሚያስተላልፉትን መልዕክት አለማቀፉ ህብረተሰብ ይወስድና ‹‹ይሄው እነዚህ ሰዎች አልተስማሙም፤ አዝማሚያውም የመስማማት አይደለም፤ እንደገና ሌላ መታየት አለበት ነገር አለ›› የሚሉ የተወሰኑ ሊኖሩ ይችላሉ።
ያም ቢሆን ግን እኛ በውስጣችን የምንፈልገውና የምናየው ነገር ግጭቱ የጎዳቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ምንድን ነው የሚሰማቸው? በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ህይወታቸውን እየመሩ ያሉት? የሚለውን የፖለቲካ መሪዎቹ ተረድተው ለሰላም ቁርጠኛ ሆነዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ከዚያ በኋላ ያለው የድጋፍ ነገር ሆኖ ነው የሚቀጥለው። እስከተወሰነ ጊዜ መንገራገጭ፣ መጠራጠር፣ አንደኛውን ውጤት ስናገኝ ሌላ ነገር አለ ብሎ ጥያቄ ማቅረብ፣ ቅድም ባነሳኋቸው መሰረታዊ የተፅዕኖ ፍላጎቶች ምክንያት እስከተወሰነ ጊዜ አብሮ የሚቀጥል ነው የሚሆነው። እስካሁንም የሰብአዊ ድጋፍ በሚፈለገው መጠን እየደረሰ አይደለም፤ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተሟልተው አልቀረቡም፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አልተስተናገዱም የሚሉና ልክ በእለት የሚከናወን ይመስል ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ። ሆኖም ዲሞክራሲ በአንድ ጀንበር እንዳልተገነባው ሁሉ እዚህ ላይ በአንድ ጊዜ የሚከናወን ነገር የለም። ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ ሁሉንም በመታገስ ነው ወደፊት መሄድ ያለባት።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ሲያሳድሩ የነበሩ አገራትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሁን ላይ ድጋፋቸውን ማሳየታቸው እንደ ዲፕሎማሲ ስኬት ማየት አይቻልም?
አምባሳደር እሸቴ፡- መቼም በዚህ ድርጅት ምክንያት በታሪካችን ደርሶ ከነበሩ ተፅዕኖዎች ሁሉ የረቀቀና ጎጂ ተፅዕኖ ደርሶብናል ብሎ ማየት መልካም ነው። ይህንን ተፅዕኖ ያደረጉት በእርግጥ ለኢትዮጵያ አስበው ነው ወይ ? ችግሩስ አሁን በመፈታት ላይ ባለበት ሁኔታ የእነሱ ጉልህ ተፅዕኖና እጅ ሳይኖር እንዲፈታ ይፈልጉ ነበር ወይ? የሚለው ነገር ሁላችንም ልናሰላስለው የሚገባ ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል ጦርነቱ የሰብአዊ ድጋፍና የሰብአዊ መብት አድርሷል የሚል ክርክር አላቸው። በሌላ በኩል በርካታ ሴቶች እናቶች በአግዋ ማዕቀፍ ውስጥ ተቋቁሞ በነበሩ አምራች ድርጅት ውስጥ አሜሪካውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን ባቋቋማቸው የልማት ድርጅቶች ውስጥ ይሰሩ ነበር። ክልከላው እነዚያ ሰዎች ያለኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲቀሩ አድርጓል። ከሰብአዊ መብት ጉዳዮች አንዱ የኢኮኖሚና የህዝቦች የመልማት መብት ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በበለፀጉት አገራት ሁልጊዜ ሁለት አይነት መስፈርት የመጠቀም ነገር አለ። የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመልማት መብት ለድምፅ በሚቀርብበት ጊዜ ይቃወሙታል። በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር፣ መሞገት ያስፈልጋል። ሁልጊዜም የእኛ ተቋማት መሪዎች ዲፕሎማቶቻችን ዲያስፖራው የሚከራከሩት ይህንን ነው።
ሁለተኛው የልማት እርዳታንና ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በሚመለከት ነው። በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት በኩል የሚገኙ ብድሮችና ድጋፎችን የሚያስተጓጉል ተፅዕኖ ተደርጓል። እንግዲህ እንደአንድ መስፈርት አድርገው ለዚህ ሁሉ ተፅዕኖ ሲጠቀሙበት የነበረው ግጭቱ ይቁም ነው። ግጭት ባለበት ሁኔታ ሃብት ማፍሰስ በአገራት በተናጠል ደረጃ የተጠያቂነት ጉዳይ አለ። ‹‹ታክስ ከፋዮቻችን ይጠይቁናል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሃብቱ መባከን የለበትም›› የሚል ነገር ያነሳሉ። ይህ እንግዲህ ውስጡ እውነት ያለው ቢመስልም ከጀርባው የፖለቲካ አላማ ያለበት ነው። እሱ እየተፈታ ሲሄድ በእኛ በኩልም ባለድርሻ የሆኑትና ኃላፊነቱን የያዙት ተቋማት በሚያደርጉት ድርድር እየቀለለና እየተፈታ ይመጣል። ያለጥርጥር መንገድ ይከፍታል፤ አወንታዊ ምላሽ እንድናገኝ ያደርጋል የሚለውን መያዝ መልካም ይመስለኛል።
በአጠቃላይ ግን ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር የለውጥ መንፈስ አለ፤ አወንታዊ ድምፅ እየተሰማ ነው፤ ተግባራዊነቱ ግን የሂደት ጉዳይ ነው። ህዝባችንም እንዲሁ ሊያውቀው የሚገባው ጉዳይ ወዲያው በእለቱ የሚለወጥ አለመሆኑን ነው። በሂደት እየተለወጠ የሚመጣና ውሳኔውን በሚወስኑበት ጊዜ በራሳቸው ተቋማት አሰራር ውስጥ ያለፈ ነገር መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በመሆኑም የተወሰነ የጊዜ ክፍተት ይኖራል። ለዚህ ደግሞ ጥረት ያስፈልጋል፤ የዲፕሎማሲ ስራ ይጠይቃል፤ ይህ ደግሞ ለ24 ሰዓታት የሚቆም አይደለም፤ በዓለም ጥግ ሁሉ ባለን የዲፕሎማሲ መገኘት ሁሉንም ነገር እንከታተላን።
አዲስ ዘመን፡- ስምምነቱን ያልደገፉ አንዳንድ የትግራይ ዲያስፖራ አካላት በሚያደርጉት ተቃውሞ በመነሳት ድጋፋቸውን የሰጡ አገራት አቋም ይሸረሽራል ብሎ እንደስጋት ማንሳት ይቻላል?
አምባሳደር እሸቴ፡– በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ አይነት ፍላጎትና መንፈስ ያላቸው የትግራይ ዲያስፖራ አባላት በሙሉ አይደሉም። የተወሰኑ ናቸው፤ ይህንን ደግሞ መጀመሪያውኑ መረዳት ያለብን ይመስለኛል። በግጭቱም ሆነ በሰላሙም ጊዜ የተለያየ አይነት አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ የሰላሙን ጉዳይ ብንወስደው አንደኛ የድርድሩን አላማ አተኩሮ ያለማየት ሁኔታ አለ፤ ሁልጊዜ የምፈልገው ብቻ ነው መሆን ያለበት የሚል ምኞት ያላቸው አሉ። ሁለተኛ በግጭቱ ወቅት የነበረ ፍላጎትን ለማሟላት የተከፈለ ነገር ይኖራል። ለዚያ የሚጠበቅ ነገር አለ። ስለዚህ ባለብዙ ፈርጅ ፍላጎት ስላለ በተለይ የመጀመሪያው የስምምነቱ ምዕራፍ የተወዛገበ ነገር ቢኖር መገረም የለብንም።
ዋናውና ሁላችንም ኢትዮጵያውያን መረዳት ያለብን አዋኪዎቹ ማሸነፍ የለባቸውም። እነሱ የራሳቸውን ጥግ ይዘው ይቀጥላሉ። ጠርዝ መያዝ ሁልጊዜ ይኖራል። ታሪክ ዘግቦት የሚያልፍ ነውር የሆነ ነገር የሚያደርግ ይኖራል። እንደዚህ አይነቶችን የመመለሱ ጉዳይ አንዱ ጥረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። የበላይነት እንዳይኖረው የእነሱ አስተሳሰብ መታገል ያስፈልጋል። ጫጫታው ስምምነቱን ከመረበሽ አኳያ ትንሽ የመንፈስ መናጋት ሊያመጣ ይችላል። ግን የሚደራደር ኃይል ደግሞ ከዚህ የላቀ አጀንዳ ነው የሚይዘው። የሰው ህይወት ማዳን እኮ ነው፤ የሰው ህይወት በምን ሊተካ ይችላል? ህይወትንም ሆነ አገርን ማዳን በምንም ሊተካ አይችልም። ሉዓላዊነት፤ ሰላም መረጋጋትና አንድነት የሚባሉ ትልልቅ አጀንዳዎችን ቀስ በቀስ ደግሞ አብረን የመኖር መንፈሳችንን የማሻር፤ የዲሞክራሲና የለውጥ መንፈሱን ወደፊት የማስኬድ ነገር የሚሉ ትልልቅ ጉዳዮች አሉ።
ስለዚህ የሌሎችን የመናገርና የመንጫጫት መብት እየጠበቁ ዋናው አጀንዳችንን መሳት የለብንም። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ጫጫታዎች ሊረብሹ ይችላሉ፤ ግን ደግሞ ያንያህል ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ብዬ አላምንም። ደግሞም የፖለቲካ መሪዎቹ የጦር መሳሪያ ጩኸትን፤ የሰው ህይወት ማጣትንና ንብረት መውደምን አልፈው መጥተው እኮ ነው እንደራደራለን ያሉት። ስለሆነም ጫፍና ጫፍ የወጡ ጠርዞችን ትተን መሃሉ ላይ አብዛኞቻችን የምንፈልገው አውድ ላይ መረባረብ ነው የሚሻለው። በመሰረቱ እነዚህ ውስን አካላት የሚያደርጉት ረብሻ የዓለም መንግስታትን ቀልብ ይገዛል ብዬ አላምንም። እንዳልኩሽ የግጭት ነጋዴዎች መኖራቸውን አንስተውም። ሁለተኛ በተለያዩ ድብቅ ፍላጎቶች ምክንያት ይህንን እንደመነሻ አድርገው ‹‹ሁሉንም አያሳትፍም›› የሚሉ አሉ። በእኔ እምነት መንግስታትና ታላላቅ ተቋማት እንደዚህ አይነቱን ነገር ወስደው ወደ ፖሊሲያቸው ያስገቡታል፤ ይተረጉሙታል የሚል ስጋት የለኝም። በየጊዜው የሚታይም የሚሆንም ነገር አይደለም።
ስለዚህ የመተንፍስ፤ ብስጭትን የማውጣት ሁኔታዎችን እየታገሱ ማሳለፍ ይገባል። ሌላው እነዚህ ወገኖች መረዳት ያለባቸው አገር የሚለውን ነገር ከተቀበሉ በአንድ አገር ውስጥ ሰላምን የማስከበር፤ ፍትሕን የማስፈንና የመሰረታዊ ልማቶችን የማቅረብ ፍላጎቶችን የሚያሟላው መንግስት ነው። ሁሉም የሚሰጠውን አስተያየት ያለፍላጎት እጭናለሁ ካለ አገር የሚለው አረዳድ አይመጣም። በዲሲፕሊን መመራት የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ያደርጋል፤ ኢትዮጵያ ዳር ድንበሯ እንዲከበር፤ የውስጥ ሰላሟ እንዲረጋጋ፣ ዜጎች በችሎታቸውና በአቅማቸው በነጻነት እየኖሩ ሰርተው እንዲጠቀሙ፤ ከሁሉ በላይ የሰላም ስምምነቱ ማህበራዊ ግኑኙነታችን እንዲሽር የሚያደርግ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ይህንን ሁሉ መቃወም ለኢትዮጵያ በታሪክም አጉል ትዝብት ላይ የሚጥል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ይህ የሰላም ስምምነት ከዳር እንዲደርስ በዲፕሎማሲው ምን መሰራት እንዳለበት ይንገሩንና ውይይታችንን እናብቃ?
አምባሳደር እሸቴ፡– በዲፕሎማሲው ረገድ የምናስተላልፈው መልዕክት ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ አንደኛ ግጭቱ መፈታቱ ሰብአዊ እርዳታ ያለችግር እንዲቀርብ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያሉ እነሱ የሚወተውቱት ነገር እንዲታረምና ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ እድል ይፈጥራል። እኛ ደግሞ ወደ ብሔራዊ መግባባታችን ሄደን ኢትዮጵያ ሰላሟን አረጋግጣ ወደ እድገት እንድትሄድ አፈጻፀሙ ላይ እንዲረዱን ነው የምንጠይቀው። ብዙ የመልሶ ግንባታ ስራዎች ይኖሩናል፤ እሱ ላይ እንሰራለን። በመሰረቱ ዓለምአቀፉ ህብረተሰብ የውስጥ ጉዳያችን ወሳኝ አይደለም። ግን አወንታዊ ድጋፍ የማድረግና የማበረታት ኃላፊነት አለበት። የዲፕሎማሲ ስራ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም የተወሰኑ ዲፕሎማቶች ስራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሊሳተፍበትና ዘብ ሊቆምበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ሲያደርጉ እንደነበረው ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ጥረታቸውን መቀጠል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፤ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አምባሳደር እሸቴ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም