የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ውድድር በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም እየተካሄደ ነው። አስራ ስድስትና ከዚያ በታች እድሜ ላይ በሚገኙ ተማሪዎች መካከል በሁለቱም ጾታ በሚካሄደው ውድድር ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ በርካታ ትምህርት ቤቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ውድድሩ ከትናንት በስቲያ ሲጀመር በስፍራው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ውድድሩ ፓንአፍሪካኒዝምን ለማጠናከር የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፣ በእያንዳንዱ ክልል መሰል ውድድሮች ተካሂደው በአገር አቀፍ ውድድር ከተለዩ በኋላ ዩጋንዳ ላይ በሚካሄደው የፓንአፍሪካኒዝም ውድድር ላይ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ይህን ውድድር ሲያካሂድ ዋንጫ ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የፓንአፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ በተማሪዎች ውስጥ በደንብ እንዲሰርጽ ለማድረግ ታስቦ ነው እየተካሄደ የሚገኘው። በቀጣይ አህጉሪቱን የሚመሩት ተማሪዎች እንደመሆናቸው አፍሪካ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ባህልና ሌሎችም ዘርፎች ጠንክራ እንድትወጣ ተማሪዎች ላይ መስራት ያስፈልጋል። መሰል ውድድሮችም ለዚህ አስተዋጿቸው ትልቅ በመሆኑ በስፋት እየተሰራባቸው ይገኛል። “ተማሪዎች የነገ አገር ተረካቢና ገንቢዎች ናቸው፣ አባቶቻችን የተጠናከረች አፍሪካን ለመገንባት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፣ ይህን ታሪክ ተማሪዎች አጠናክረው እንዲቀጥሉና ኃላፊነት ለመውሰድ እንዲዘጋጁ ማሳሰብ እፈልጋለሁ” ያሉት ኃላፊው ይህ የፓንአፍሪካኒዝም ውድድር እግር ኳስ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ቢሆንም በቀጣይ በሌሎች ስፖርቶችም ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህም ትምህርት ቢሮው ከክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ እንደሚፈራረም ተናግረዋል። የዚህ ስምምነት አላማም ስፖርትን ከትምህርት ቤቶች ለመጀመር የሚያስችል ነው። በዚህም በሃያ የስፖርት አይነቶች በሁሉም ትምህርት ቤቶች ውድድሮችን ለማካሄድ ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ከዚህ ዓመት ጀምሮ በዘላቂነት እንደሚቀጥል ኃላፊው አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ አብደላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት፣ ከአመት በፊት የፓን አፍሪካኒዝም የእግር ኳስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈ ትምህርት ቤት ከኦሮሚያ ክልል መመረጡን አስታውሰዋል። ዘንድሮም በአገር አቀፍ ውድድር ላይ ክልሉን የሚወክል ትምህርት ቤት ለመምረጥ በአዳማ ውድድር እየተካሄደ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመው ይህም በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክል ትምህርት ቤት ዳግም ከዚሁ ክልል ለማስመረጥ የሚደረገው ጥረት አንድ አካል መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት ለረጅም ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃም እንደ ክልልም የትምህርት ቤቶች ውድድር ሲካሄድ መቆየቱን የጠቆሙት ኃላፊዋ፣ በ2011 ዓ.ም አገር አቀፉ የትምህርት ቤቶች ውድድር መቀሌ ላይ ከተካሄደ በኋላ 2013 ላይ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ መከሰት ሳይካሄድ መቅረቱን ጠቅሰዋል። ዘንድሮ ግን በአዲስ መልክ ቢሮው ሰነድ አዘጋጅቶ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ውድድሩን ማካሄድ ችሏል። “በስፖርት ትልቁ ተስፋ የሚገኘው ታዳጊዎች ላይ ነው፣ ታዳጊዎችን ለማግኘት ደግሞ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርገናል” ያሉት ወይዘሮ ጠይባ በክልሉ ከስር ጀምሮ በእያንዳንዱ የመዋቅር ደረጃ ውድድሮች በስፋት እንደሚካሄዱ አስረድተዋል። ለዚህም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሰነድ ከትናንት በስቲያ ተፈርሟል።
የፓን አፍሪካኒዝም የእግር ኳስ ውድድር ከዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮንጎ ሲካሄድ ኦሮሚያ ክልል የአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያን ወክሎ እንዲወዳደር ማስመረጥ ችሏል። በዚያም ውድድር ክልሉ ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን አራተኛ ደረጃን ይዞ ከማጠናቀቅ ባለፈ ጥሩ ልምድ ይዞ መመለሱን ኃላፊዋ ተናግረዋል። በፊፋም ሰዎች በተለይም ከእድሜ ተገቢነት አኳያ አድናቆት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። “የኦሮሚያ ክልል በሁሉም ስፖርቶች እምቅ አቅም አለው፣ ከእኛ የሚጠበቀው ይህን እምቅ አቅም አውጥቶ መጠቀም ነው” ያሉት ኃላፊዋ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚወክሉ ታዳጊዎችን ለማፍራት ቢሮው ሰፊ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፣ ትምህርት ቤቶች ሲመሰረቱ የስፖርት ሜዳዎች አላቸው፣ እነዚህን የስፖርት ሜዳዎች ተማሪዎች ከትምህርት ቀን ውጪም ክፍት ሆነው በነፃነት እንዲጠቀሙባቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቶቹ የሚገኙ የስፖርት ባለሙያዎችም እውቀታቸውን እንዲያካፍሉና ስፖርትን እንዲያስፋፉ ይፈለጋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ቢሮው የማህበረሰብ ስፖርትን የማስፋት ፍላጎት አለው፣ ለዚህም ተማሪዎች ልምዱን እንዲያዳብሩ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ከትምህርት ቢሮው ጋር እንደተፈረመ ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/ 2015 ዓ.ም