የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ሲኖር ትግል ብቻም ሳይሆን ዕድል እንደሚያስፈልገው የሚጠቁሙ አጋጣሚዎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። አብዛኛው በትግል ጥቂቶች ደግሞ በዕድል ሲኖሩ የተመለከተ ሰው ዕድልን የህይወት አንዱ ገፅታ አድርጎ ቢያይ አይገርምም። በዕድል ተጠቃሚ ለመሆን የተወሰነ ሙከራንና ተስፋን ያለመቁረጥን እንደሚጠይቅ ከሎተሪ በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡
ሎተሪ ሳይገዛ የሎተሪ ዕድል አይገኝምና፡፡ ከዚህ አኳያ ዕድል ተዘጋጅተው ለሚጠብቁ ሰዎች ታደላለች የሚል አባባል ብንስማም አንዳንዴ ዕድል ሳይታሰብም ዘው የምትልበት አጋጣሚ ይከሰታል፡፡ ሰሞኑን በአሜሪካ የቨርጅኒያ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ኤልቪራ ሄንሪ በባሏ የቀድሞ የእግር ኳስ መለያ ቁጥር ሎተሪ ቆርጣ የአንድ መቶ ሺ ዶላር ዕጣ አሸናፊ መሆኗን ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ አስነብቧል፡፡
ቨርጅኒያ ሎተሪ በሚያዘጋጀው ካሽ ፋይፍ በተባለ የሎተሪ ጨዋታ ሚስስ ኤሊቬራ የባሏን የቀድሞ እግር ኳስ መጫወቻ መለያ ቁጥር 7-18-19-24-34 እንዲሆኑ በማድረግ በቅደም ተከተል በማቀናጀት የዕድል ቁጥሯን መርጣለች፡ ፡ በዚህ መሰረት በአምስት አኀዝ ተቀናጅተው የተመረጡት የሚስስ ሄንሪ ባል የቀድሞ የመለያ ቁጥሮች የአንድ መቶ ሺህ ዶላር አሸናፊ ሆኖ ከወጣው የ “ኤፕሪል ዘፉሉ” የቨርጅኒያ ሎተሪ ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ሆኗል፡፡
እናም ወይዘሮ ሄንሪ ፈረንጆቹ “የጅሎች ቀን” በሚል ከባባድ የጅል ቀልዶችን በመቀላለድና በመሸዋወድ በሚያከብሩት የሚያ ዝያ አንድ ምሽት ላይ በወጣው የቨርጅኒያ ሎተሪ የመጨረሻውን ትልቁን ዕጣ የአንድ መቶ ሺህ ዶላር አሸናፊ በመሆን በሽወዳ ፋንታ በሀብት ተንበሽብሸዋል፡፡
“ቁጥሮችን ስመርጣቸው እንደማሸንፍ ለባለቤቴ ነግሬው ነበር፡፡ አሁንም በእርግጥም የባሌ የመለያ ቁጥሮች ዕድለኛ ቁጥሮች መሆናቸውን በድጋሜ አረጋግጫለሁ” ብላለች አሸናፊዋ ሽልማቷን ከተቀበለች በኋላ ይህ አንድ መቶ ሺህ ዶላር የሚያስገኘው የቨርጅኒያ ሎተሪ ካሽ ፋይፍ የሎተሪ ጨዋታ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ በየቀኑ የሚወጣ ሲሆን ይህን ታላቅ የሎተሪ ሽልማት የማግኘት ዕድል ከ278 ሺህ 256 ሰዎች አንድ ያህል ነው፡፡
ታዲያ በባሏ የመለያ ቁጥር ይህን ጠባብ ዕድል ወደ እርሷ ያመጣችው ሚስስ ሄንሪ እውነት በዕድል ብቻ ወይስ በፍቅር ማግኔት በመሳብ? የምትወደው ባሏ የመለያ ቁጥር የዕድል ካባ አከናንቧታል፡፡ የባሏ መለያ ቁጥር የሎተሪ ዕጣ ውስጥ አሸናፊ የዕድል ቁጥር ሆኖ መገኘቱ አጋጣሚ ብቻ አይመስልም፡፡ የእነ በዛብህና ሰብለ ወንጌል “ፍቅር እስከ መቃብር” እንደሚባለው የእነ ሚስስ ሄንሪና የባሏ ፍቅር “ፍቅር እስከ ዕድል ቁጥር” ቢባል ያንስበት ይሆን?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በዳንኤል ዘነበ