ታሪካዊው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የአትሌቲክስ ክለብ ለጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ጥሩነሽ ዲባባ ልዩ የኒሻን ሽልማት አበረከተ። ክለቡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶቹም የማዕረግና የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማ ከሆኑ ታሪካዊ የስፖርት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው። ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ለአገራቸው በርካታ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብና አገራቸውን ማስጠራት የቻሉ አትሌቶችን አፍርቷል። ከእነዚህ መካከል ረዳት ኮሚሽነር ጀነራል ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ እና ጥሩነሽ ዲባባ ብቻ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በኦሊምፒክ መድረክ መሰብሰብ ችለዋል። ይህንን ተከትሎም ጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ጥሩነሽ ዲባባ የልዩ ኒሻን ተሸላሚ ልትሆን ችላለች። ሽልማቱ ከረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ ቀጥሎ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
አትሌቷ አገሯን በወከለችባቸው አራት ኦሊምፒኮች (አቴንስ፣ ቤጂንግ፣ ለንደን እና ሪዮ ኦሊምፒኮች) 3 የወርቅ እና 3 የነሃስ ሜዳሊዎችን አግኝታለች። ይህም በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በመድረኩ እንድትሆን አስችሏታል። ከረጅም ርቀት የምንጊዜም ስኬታማ የዓለም አትሌቶች አንዷ የሆነችው ጥሩነሽ ዲባባ ከኦሊምፒክ ባሻገር በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናም 5 የወርቅ እና 1 የነሃስ ሜዳሊያዎችን እንዲሁም በዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና እና የአፍሪካ ቻምፒዮናዎች 6 የወርቅና 3 የብር ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በአትሌቲክስ ሕይወት ወደር የሌለው ስኬት በመጎናፀፍ የአገሯን ባንዲራ አውለብልባለች። ይህንን ተከትሎም ክለቧ የክብር ሽልማቱን ሊያበረክትላት ችሏል። አትሌቷም በተሰጣት ሽልማት መደሰቷን ገልጻለች። በማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ ትንሽ ልጅ ሆና ተቀጥራ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ መብቃቷንም ነው ጥሩነሽ ያመላከተችው። ‹‹የማረሚያ ቤት ስፖርት ክለብ ወጣት አትሌቶች ጠንክረው እንዲሰሩ፣ እንዲበረታቱና የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ያደርጋል›› ያለችው አትሌቷ በተለያዩ የውድድር መስኮች ሁለት ወይንም ሶስት ወርቅ ከተገኘ አንዱ በማረሚያ ቤት አትሌት መሆኑን መግለጻንም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
በአራት የስፖርት ዓይነቶች አትሌቶችን የሚያሰለጥነው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ስፖርት ክለብ በየውድድር መስኩ ለብሄራዊ ቡድን ተመራጭ የሆኑ ስፖርተኞችን ያፈራና እያፈራም ያለ ስመጥር ክለብ ነው። ባለፉት ሶስት ዓመታትም 26 የወርቅ፣ 31 የብር እና 38 የነሃስ በድምሩ 95 ሜዳሊያዎችን በተጨማሪም 8 ዋንጫዎችን እና 47 ዲፕሎማዎችን በዓለም አቀፍ እና በአገር ውስጥ ውድድሮች ማግኘቱንም በሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጻል። ይህ ውጤት የተመዘገበውም በ78 የክለቡ አትሌቶች ሲሆን፤ ለ34 ስፖርተኞች ከረዳት ሳጅን እስከ ኮማንደር ድረስ የማዕረግ ዕድገት ሲሰጥ፤ ለ19 ስፖርተኞች የገንዘብ እና ለ13 ስፖርተኞች ደግሞ የእርከን ጭማሪና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በቅርቡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ለሚገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ የረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ማዕረግ መስጠቱ የሚታወስ ነው። ክለቡ በዚህ ወቅት በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ጾታዎች 105 አትሌቶችን እያሰለጠነ የሚገኝ ሲሆን፤ በኦሪጎኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል ሁለቱ የተገኙት በዚሁ ክለብ አትሌቶች እንደነበር ይታወሳል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/ 2015 ዓ.ም