የኢትዮጵያ ግብርና የዝናብ ጥገኛ ሆኖ ነው የኖረው:: ይህ ዓይነቱ የግብርና ልማት ግብርናው የሚጠበቅበትን እንዲወጣ እንደማያስችለው እየተጠቀሰ ሲተች ኖሯል:: በተለይ ድርቅ በመጣ ቁጥር በግብርና ላይ የሚደርሰው ጥፋት ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎትም ኖሯል:: በዚህ ዓይነት ሁኔታ በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የግብርና ምርቶች ፍላጎት መሟላት አይቻልም የሚሉ ሀሳቦችም ሲንሸራሸሩ ቆይተዋል:: መንግሥት የግብርናው ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን እያደነቀ፣ ከግብርናው ከሚጠበቀው አኳያ ምርትና ምርታማነቱ ብዙም እንዳልሆነም ሁሌም ሲያስገነዝብ እንደነበር ይታወቃል::
በተለይ ደግሞ የውሃ ማማ በመባል ለምትታወቀው ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ በእጅጉ የሚያም ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችም መንግሥትም በቁጭት ሲያነሱት ኖረዋል:: ክረምት ከበጋ የሚፈሱና ለልማት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ ወንዞችና ጅረቶች ያሏት አገር በመስኖ ልማት ስሟ ሳይጠራ ኖራለች::
ባለፉት ጥቂት አመታት ግን በመንግሥት ቁርጠኝነት የተሞላበት አሠራር እነዚህ ሁኔታዎች እየተቀየሩ መጥተዋል:: እንደ አገር ኢኮኖሚን ሊያሳድጉ የሚችሉ ዘርፎችን በመምረጥ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሠራባቸው ካሉት መካከል የግብርናው ዘርፍ አንዱ ሆኗል::
በዚህም ቅድሚያ ሰጥቶ እየተሠራበት ያለው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ነው:: እንደ አገርም ከውጭ በግዥ የሚገባን ስንዴ ለማስቀረት በአገር ውስጥ ስንዴ በብዛት ማምረት የሚል አቋም ተይዞ ወደ ሥራ ከተገባ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል::
ይህን ተከትሎም የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችን መሠረት በማድረግ በአገር ደረጃ ላለፉት ሦስት አመታት በተከናወነው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ውጤት እየተገኘ ነው:: ለእዚህም በተለይ ባለፈው አመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው ውጤትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተለያየ ጊዜ ተዘዋውረው የጎበኙዋቸው በሰፊ ማሳዎች ላይ የተካሄዱ የስንዴ ልማት ሥራዎች ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው::
በመስኖ ስንዴ ልማቱም ባለፈው አመት ከ600 ሺ ሄክታር በላይ በዘር በመሸፈን 26 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማግኘት ተችሏል:: ዘንድሮ ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል:: አንዳንድ አካባቢዎች የመኸር አዝመራ ሰብስበው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ጀምረዋል::
አሁን በስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብቻ አይደለም የሚሠራው:: ያን ማድረግ ተችሏል፤ አገሪቱ በስንዴ ላይ በመኸርም በበጋ መስኖም ባከናወነችው ተግባር እንደ ቀደሙት ጊዜያት ባለፈው በጀት አመት ስንዴ ከውጭ አላስገባችም:: ዘንድሮ ደግሞ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር ለውጭ ገበያ ስንዴ ለማቅረብ አቅዳ እየሠራች ትገኛለች::
በበጋ መስኖ በተከናወነው ተግባር የተገኘው ምርትም ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሱም በመንግሥት ይፋ ሆኗል:: በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ዙሪያ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳይያስ ለማ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል::
የሦስት አመታት የበጋ ስንዴ ልማት
እንቅስቃሴዎች
እንደ አቶ ኢሳይያስ ገለጻ፤ የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ከተጀመረ ወደ አራተኛ አመት ተሸጋግሯል:: ልማቱ በቆላማ ስምጥሸለቆ አካባቢዎች የተጀመረ ሲሆን፣ በዋናነትም አፋር፣ ከፊል ኦሮሚያ፣ሶማሌ እና ደቡብ ክልሎች ውስጥ ነው:: በመጀመሪያው ዙር በተከናወኑት ሥራዎችም በአፋርና ከፊል ኦሮሚያ ላይ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል:: ከአገራዊ የልማት መርሃ ግብሩ (ፕሮግራም) አንጻር አፈጻፀማቸው በንጽጽር ሲቀርብ ልዩነት ይኑረው እንጂ ልማቱ በተከናወነበት በሶማሌ ክልልም የተገኘው ውጤት አበረታች ነው::
በመጀመሪያው ዙር በቆላማው አካባቢ የተከናወነውን የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት መሠረት በማድረግ በሁለተኛው ዙር የልማት እቅድ አማራጮች ታይተዋል:: ውሃ ገብ ሆነው ነገር ግን በበጋ የማያመርቱ ደጋና ወይና ደጋ አካባቢዎችን በማካተት የልማት ፕሮግራሙን የማስፋት ሥራ ነው የተከናወነው:: በዚሁ መሠረትም አማራ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያና አፋር ክልሎችን ያካተተ ልማት ማከናወን ተችሏል::
በደቡብ ክልል በመጀመሪያው ዙር ደቡብ ኦሞ ላይ ነበር የተጀመረው:: በሁለተኛው ማስፋፊያ ግን መካከለኛው የደቡብ አካባቢዎችን በማካተት ሥራው ተከናውኗል:: እንደ አጠቃላይ የልማቱ ሥራ ሲገመገም በተለይም በማስፋፋቱ ሂደት ከክልሎቹ በልማቱ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ኦሮሚያ ክልል ነው:: እንደ አገር በመስኖ ከለማው ከ450ሺ ሄከታር መሬት እንዲሁም በበልግ ወቅት ወደ 255ሺ ሄክታር መሬት ከለማው ውስጥ ኦሮሚያ ከፍተኛውን የልማት ድርሻ ይዟል::
በአጠቃላይ በበልግና በመስኖ እንደ አገር ከለማው ወደ 625ሺ ሄክታር መሬት ኦሮሚያ ክልል ወደ አምስት መቶ ሺ ሄክታር በማልማት ከአጠቃላዩ ብልጫውን ይዟል:: በመቀጠል አማራ ሲሆን፣የተቀሩት በቅደም ተከተል ላይ ይገኛሉ::
በዚህ መልኩ የሦስቱ አመታት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ነበሩ::በተያዘው በጀት አመት ደግሞ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር ለማልማት በእቅድ የተያዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ኦሮሚያ አንድ ሚሊዮን ሄክታር፣ አማራ 250ሺ ሄክታር፣ ቀሪውን ሌሎች ክልሎች የሚጠቀሙ ይሆናል:: ይህም የሆነው ክልሎቹ ባላቸው ስፋት፣ የመስኖ አቅም (ፖቴንሻል) እንዲሁም ባላቸው የማልማት ተሞክሮ ነው::
ለውጤቱ መመዝገብ የተከናወነው ሥራ
እንደ አቶ ኢሳይያስ ገለጻ፤ ወደ ልማቱ ከመግባቱ በፊት መንግሥት ግብ አስቀምጧል:: ወይንም ቅድመ እቅድ አድርጓል:: የበጋ መስኖ ልማት ዋና አላማ በአገር ውስጥ የስንዴ ልማትን በስፋት በማከናወን በግዥ ከውጭ የሚገባ ስንዴን ማስቀረት ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ማግኘት ነው::
መንግሥት በግብርናው ክፍለኢኮኖሚ ላይ ባስቀመጠው የአስር አመት መሪ እቅዱ በሦስት የሰብል ዓይነቶች ላይ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቷል፤ ቅድሚያ ልማቱ ውስጥ የገባው ስንዴ ሲሆን፣ ሁለተኛው የቅባት እህል ነው:: ከቅባት እህሎችም በዋናነት አኩሪ አተር ሲሆን፣ ሱፍና ለውዝ ይገኙበታል:: በሦስተኛ ደረጃ ትኩረት የተሰጠው የሩዝ ልማት ነው::
መንግሥት ትኩረት የሰጣቸው እነዚህ የሰብል ዓይነቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ለፍጆታ ወደ አገር የሚያስገባቸው በመሆናቸው ነው:: እነዚህ የተጠቃሚውን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው አቅርቦቱ በአገር ውስጥ እንዲሆን ለማስቻል ነው:: እንዲመረቱ የተመረጡት የሰብል ዓይነቶችም የኅብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል ነው::
የልማት ተነሳሽነቱ በስንዴ ቢጀመርም ሌሎቹም በእቅዳቸው መሠረት ይከናወናሉ:: ከቅባት ሰብሎች የአኩሪ አተር ልማት ባለፈው አመት አማራ፣ በከፊል ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ላይ ተጀምሯል::በአኩሪ አተር ልማት ሥራ ደግሞ አማራ ክልል ብዙ ድርሻ ይኖረዋል::
መንግሥት በገበያ አዋጭነቱ፣ በምርታማነቱ፣ በየትኛውም የአየር ፀባይ መልማት በመቻሉ፣በተጠቃሚው የመግዛት አቅምና የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ማዕከል በማድረግ በልዩ ትኩረት በእቅድ ይዞ ከሚንቀሳቀስባቸውና ልማቱም እንዲፋጠን እየሠራባቸው ከሚገኙ የቅባት ሰብሎች የአኩሪ አተር ተረፈ ምርት ለእንስሳት መኖነት በመዋል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው:: በመደበኛው የልማት ሥራ የሚቀጥሉት ኑግ፣ ተልባ የመሳሰሉት የቅባት ሰብሎች በዋናነት ለውጭ ገበያ የሚውሉ ቢሆንም በአገር ውስጥም አቅርቦታቸው እንደተጠበቀ ነው::
በልማት እቅድ ውስጥ የተካተተው የሩዝ ልማትም በስፋት የሚከናወን ሲሆን፣ ልማቱ የሚከናወንባቸው ሰባት የሚሆኑ አካባቢዎች ተለይተዋል:: ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው አማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ፎገራ ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ወደ አምስት ወረዳዎች ይሸፍናል::ቤኒሻንጉልጉሙዝ፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ ክልሎች ልማቱን ለማከናወን ታቅዷል:: በስንዴ ልማቱ ላይ የተከናወኑትን ተግባራት በተመሳሳይ በመፈጸም በፍጥነት ልማቱ ተከናውኖ ውጤታማ እንዲሆን ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው::
የስንዴ ልማቱና ቀድሞ የተያዘው ግብ
እየተከናወነ ባለው የልማት ሥራ የተገኘው ውጤት አያጠራጥርም:: በቅድመ እቅድ ላይ የምርት መጠን ተቀምጧል:: ሆኖም ግን ውጤቱን በቁጥር ብቻ መለካት ስህተት ነው:: እንደ አገር የተያዘው ግብ በግዥ ወደ አገር የሚገባን ስንዴ በማስቀረት በምርት ራስን መቻል ነው::
የስንዴ ፍላጎት በየአመቱ በሦስት በመቶ ያድጋል:: በየአመቱ አገራዊ የስንዴ ምርት ፍላጎት ወይንም ፍጆታ ወደ 97 ሚሊዮን ኩንታል እያደገ ይሄዳል:: እንዲህ እያደገ ላለው ፍላጎት ምላሽ እየሰጡ መሄድ ያስፈልጋል:: በየአመቱ የሚያድገውን ፍላጎት ለማሟላት ምርቱን እያሳደጉ መሄድ ይጠይቃል::
እንደ አገር በተያዘው በጀት አመት ከአንድ መቶ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ይመረታል ተብሎ ይጠበቃል:: ስለዚህ አገራዊ ፍላጎትን በማሳካት ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ተግባርም ይከናወናል:: የመኸሩ የሰብል ስብሰባ በመካሄድ ላይ በመሆኑ ከታኅሣሥ መጨረሻ በኋላ ነው አጠቃላይ የስንዴ ምርት የሚታወቀው:: አጠቃላይ የምርት ግምገማ ከተካሄደ በኋላ ነው መረጃዎችን ማውጣት የሚቻለው::
በበጋውና በመደበኛው በመኸሩ ከሚከናወነው የስንዴ ልማት መካከል ስላለው ግንዛቤ መያዝ አለበት ብለው አቶ ኢሳይያስ እንዳስረዱት፣ ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የመኸሩ ወይንም መደበኛው ልማት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል:: በመኸሩ የሚለማው መሬትም ሰፊ ነው:: የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጨማሪ ፕሮግራም፣ ጉልበትና አቅም የሚጠይቅ ሥራ ነው:: ሆኖም ግን የበጋ ስንዴ ልማቱ በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ፍላጎትንና ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድን ከማሳካት አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ አለው:: ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ በተያዘው አመት ይሳካል::
ልማቱን ለማፋጠን በቴክኖሎጂ የተደረገ እገዛ
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ አቶ ኢሳይያስ ያብራራሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ እንደ ማጨጃ መውቂያና ሌሎች ከእርሻ ጋር የተያያዙ መሣሪያዎች ወይንም ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መንግሥት አመቻችቷል:: በተለይም በማህበር ተደራጅተው መሣሪያውን ገዝተው ለገበሬው ለሚያቀርቡ ብድር ተመቻችቷል:: ባለሀብቶችም ከባንኮች ብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል::
እያንዳንዱ ገበሬ ትራክተር እንዲኖረው አይጠበቅም:: መሣሪያውን ከሚያቀርቡ አገልግሎት ሰጪዎች በመጠቀም ነው የግብርና ሥራውን እንዲያከናውን የሚጠበቀው:: በተለይ የህብረት ሥራ ማህበራት መሣሪያውን ገዝተው በተመጣጣኝ ዋጋ ገበሬውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ይበረታታሉ::
በአማራ ክልል ወጣቶች ተደራጅተው የስንዴ ማጨጃ መሣሪያ ገዝተው አገልግሎት በመስጠት እያከናወኑ ያሉት እንቅስቃሴም ተሞክሮ ይሆናል:: አንድና ሁለት ትራክተር የነበራቸው ባለሀብቶችም ተጨማሪ በመግዛት አገልግሎታቸውን በማስፋት ላይ ይገኛሉ:: ጠንካራ ማህበራት የሌሉባቸው፣ ተደራጅቶ ለመሥራት ፍላጎት ባላሳዩ፣ ባለሀብቱም ባለመንቃቱ ክፍተት ያለባቸው አካባቢዎች ይገኛሉ:: በነዚህ አካባቢዎች በትኩረት መሥራት ይጠይቃል::
በልማቱ የተስተዋሉ ጠንካራ ጎኖችና
ተግዳሮቶች
አቶ ኢሳይያስ ከአመራር ጀምሮ ያለውን ቁርጠኝነት በጥንካሬ ጠቅሰዋል፤ ሥራውን የራስ አድርጎ ማየት በአመራሩ ዘንድ እንደሚታይም ነው የገለጹት:: እንደርሳቸው ገለጻ፤ እቅዱ የእኔ ነው የሚል መንፈስ በፌዴራልም በክልል አመራሮች ዘንድ ይታያል:: የልማቱ ሥራ ውጤታማ የሆነውም ለዚህ ነው:: በስንዴ ልማቱ ላይ የተሻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተተግብሯል:: ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዲሁም ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች በመጠቀም የታየው ነገር አበረታች ነው:: በበጋ ስንዴ ላይ በሽታ አለመከሰቱም ሌላው መልካም ጎን ነው:: በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱም በጥንካሬ ይገለጻል::
አቶ ኢሳይያስ እንደ ተግዳሮት ካነሷቸው መካከል ደግሞ ሌላ ሰብል ከተነሳ በኋላ ወደ ሌላ ሰብል በመዞር እህል የሚበላ ወፍ ወይም ግሪሳ የሚባለው በአንዳንድ አካባቢዎች መኖሩ ይጠቀሳል:: በልማቱ ቀድሞ ልምድ ባላቸውና በጀማሪዎች መካከል የታየውን የልማት አለመመጣጠንን እንደ ክፍተት አንስተዋል:: ወደ አገልግሎት ያልገቡ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ቢገቡ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥሩም ሀሳብ ሰጥተዋል::
በአጠቃላይ በስንዴ ልማቱ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በርብርብ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል:: የዘር ብዜት በሁሉም ክልል እንዲከናወን መደረጉንም ገልጸዋል:: እንደ ማዳበሪያ ያለ የግብአት አቅርቦትን በተመለከተም ችግር እንዳያጋጥም ለበጋ መስኖ ልማቱ ከመኸሩና ከበልጉ ጋር አብሮ ታቅዶ ቀድሞ እንደሚዘጋጅም አስታውቀዋል::
እንደ አቶ ኢሳይያስ ማብራሪያ፤ አገራዊ የስንዴ መርሃግብር(ፕሮግራም)በመኸር የአነስተኛ አርሶ አደሮችና የባለሀብቶች መሬት ላይ የሚለማውን ጨምሮ በበጋ መስኖ የሚከናወነውን የሚያካትት ነው:: ልማቱም በክረምት፣ በበጋና በበልግ የሚከናወን ሲሆን፣ የእርሻ ሥራውም አካባቢዎቹ እንዳላቸው የአየር ፀባይ ይወሰናል:: የምርት አሰባሰቡም ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኀዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም