22ኛው የዓለም ዋንጫ ሊጀመር ሰባት ቀናት ብቻ ቀርተውታል። አውስትራሊያ መቶ ቢሊዮን ዶላር አፍስሳና አሉ የተባሉ ታዋቂ ሰዎቿን ቀስቃሽ አድርጋ ይህን የዓለም ዋንጫ የማስተናገድ እድል አላገኘችም። አሜሪካም ሃያልነቷን ተጠቅማ ይህን እድል የግሏ ማድረግ አልቻለችም። እንግሊዝም ባላት ታላቅ ሊግና የእግር ኳስ ባህል ተማምና አዘጋጅነቱ ከእጇ እንደማይወጣ እርግጠኛ ነበረች። ሞሮኮን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ለዚህ ታላቅ ዓለም አቀፍ ድግስ አዘጋጅነት ለመፎካከር ሞክረዋል።
እኤአ መስከረም 2/ 2010 የዚህ ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ አገር በሲውዘርላንድ ዙሪች ይፋ ተደርጓል። የፊፋ የቀድሞ ፕሬዘዳንት ጆሴፍ ሴፕ ብላተር የ2022 የዓለም ዋንጫን የምታስተናግደው አገር ኳታር መሆኗን በተዘጋጀው መድረክ አወጁ። በሼህ መሐመድ ቢን አልታኒ የሚመራው የኳታር ልኡክ የፊፋን አዋጅ እንደሰማ ተቃቅፎ ደስታውን ለመግለጽ ወደ አገሩ እስኪመለስ አልጠበቀም ነበር። ሼሁ በዚያ መድረክ ባሰሙት ንግግርም ‹‹ነገ ዝግጅታችንን እንጀምራለን›› አሉ። ጨዋታው ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ ነውና ኳታር አካሄዱን ስላወቀችበት ከፊፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የ22ቱን ድምጽ በማግኘት የዓለም ዋንጫን ድግስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ወሰደችው።
የዓለም ዋንጫ ለዘመናት የየአገራቱ ታላላቅ ሊጎች ሰኔ ላይ ሲጠናቀቁ ይካሄዳል። ይህን ኳታር ላይ ለመተግበር በአገሪቱ ያለው ከፍተኛ ሙቀት ስለማይፈቅድ ወደ ሕዳር ተዘዋወረ። በዚህ ምክንያት ‹‹ሊጋችን ይጎዳል፣ የመርሃግብር መዛባትና ኪሳራ ይገጥመናል›› ያሉ አገራትን ማንም ጆሮ አልሰጣቸውም። ትንሿና በነዳጅ ገንዘብ ኪሷ ያበጠው አገር የዓለም ዋንጫን የጊዜ ሰሌዳ አስቀየረች።
ኳታር ወግ አጥባቂነትና ሃይማኖተኝነት የተጫናት በመሆኗ የዓለም ዋንጫው ሁሉም ሰው የሚዝናናበት እንደማይሆን ብዙዎች ተችተዋል። የአገሪቱ ኤሚር ሼህ ሞሐመድ ቢን ታኒ ግን ከመላው ዓለም የሚመጣውን እንግዳ ካለምንም ልዩነት እንደምታስተናግድ ቃል ገብተው ሽር ጉዱን ጀመሩ። ለዚህም ስትል ኳታር በዓለም ዋንጫው ወቅት የአልኮል መጠጥን እስከ መፍቀድ ጨከነች።
ሩሲያ የ2018ቱን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት 11 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች። ብራዚሎች በ2014 ላዘጋጁት የዓለም ዋንጫ 15 ቢሊዮን ዶላር ነው ያፈሰሱት። ደቡብ አፍሪካም በ2010 የዓለም ዋንጫ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ነበር ያወጡት። ኳታር ግን እነዚህ አገራት ያወጡት ተደምሮ ካፈሰሱት መዋእለ ንዋይ በእጅጉ የበለጠ ለማውጣት አልሰሰተችም። 229 ቢሊዮን ዶላር መድባ በታሪክ ውዱን የዓለም ዋንጫ እውን አድርጋለች። የኳታር የዓለም ዋንጫ ሩሲያ ካወጣችው በአስራ ስድስት እጥፍ የላቀ ነው። አገራት ከአንድ ወር ለማይበልጥ የእግር ኳስ ድግስ ይህን ያህል ገንዘብ ለምን ያወጣሉ? የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን ያነጋግራል። ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ ያወጡትን ያህል ገቢ አላገኙም ተብለው የዓለም ዋንጫ አገራትን ለብክነትና ለኪሳራ የሚዳርግ መሆኑን የሚሞግቱ ብዙዎች ናቸው። አጠቃቀሙን ያወቁበት አገራት ግን በብዙ መንገድ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይታመናል።
እንደ ፊፋ ግምት የኳታሩን የዓለም ዋንጫ ከ5 ቢሊዮን በላይ የዓለም ሕዝብ በቴሌቪዥን መስኮት ይከታተለዋል። ኳታርም ከዚህ የአንድ ወር ድግስ በትንሹ 17 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ተሰልቷል። አገሪቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የውጭ አገር ዜጎችን ለማስተናገድ ስምንት ስቴድየሞችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን መገንባቷ በቀጣይ ዓመታት ቱሪዝምና አጠቃላይ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ይጠቅማታል ተብሎ ይጠበቃል። ኳታር ይህን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ስምንት ስቴድየሞችን ከመገንባትና ከማዘመን በተጨማሪ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን ዘርግታለች። ለስቴድየም ግንባታ ብቻ ወደ 6 ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች። 36 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ለመጓጓዣና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ፈሷል። የኳታር የሆቴል ኢንቨስትመንት ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል። ፐርል የተባለውን እጅግ ብዙ ሰው የሚስተናገድበትን ሆቴልም ገንብታለች። አገሪቱ በዓለም ዋንጫው ምክንያት ከስቴድየሞች አልፎ አዲስ ንኡስ ከተማም ቆርቁራለች። ሉሴል የተባለው አዲስ ንኡስ ከተማ 45 ቢሊዮን ዶላር ፈሶበት የለማ ስቴድየም፣ ዘመናዊ መኖሪያ፣ የገበያ ማዕከልና ሌላም የሕዝብ አገልግሎት የተሟላለት ነው፡፡ ይህም አገሪቱ ከዓለም ዋንጫው የምታተርፈው ቋሚ ሀብት ነው ተብሏል፡፡ የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ በነበረው ፉክክር ምራቅ የሚያስውጥ ገንዘብ ይዛ የቀረበችው ካታርን ፊፋ ለመግፋት ድፍረቱ አልነበረውም፡፡ ለዚህ ድምፃቸውን ከሰጡ 22 የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከል ግን 16ቱ በሙስናና በምዝበራ ቅሌት ተከሰዋል፡፡ ለዚህም ነው ካታር የዓለም ዋንጫውን ለማዘጋጀት በእግር ብቻ ሳይሆን በእጅም ጭምር ነው ወደ ዙሪች የሄደችው የሚባለው፡፡ የፊፋ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብላተር፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዚዳንት የነበረው ሚሼል ፕላቲኒና ሌሎችም ታላላቅ የፊፋ አመራሮች በመጨረሻም በዚሁ ቅሌት ተዘፍቀው ተገኝተዋል፡፡ ለፊፋ ንቅዘት ምክንያት የሆነውም ይሄው የካታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ይዞት የመጣው ጣጣ እንደሆነ ኋላ ላይ ተደርሶበታል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም