የዳግማዊ አጼ ምኒልክ አባት ናቸው፡፡ የልጃቸው ስም ከእርሳቸው በላይ ስለገነነ የአባትየው ንጉሥነት ያን ያህልም አልተዘመረለትም፡፡ እንዲያውም ከታሪክ ሩቅ የሆኑ ሰዎች በስም ራሱ ላያውቋቸው ይችላሉ፡፡ ልጅየውን (ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ማለት ነው) ግን ማንም ያውቃቸዋል፡፡ በእርግጥ አባትየው ንጉሥ ሲሆኑ ልጅየው ግን ንጉሠ ነገሥት (የንጉሶች ሁሉ ንጉስ ማለት ነው) ስለሆኑ ጭምር ነው፡፡
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የሸዋ ንጉሥ እና የዳግማዊ አጼ ምኒልክ አባት የነበሩትን ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴን 167 ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን እናስታውሳለን፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በዚህ ሳምንት ጥቅምት 30 ቀን 1848 ዓ.ም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ዓመት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንትን አንኮታኩተው፣ ኢትዮጵያን አንድ አድርገው በነገሱ በሁለተኛው ዓመት ነው፡፡ ወደ ንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ታሪክ እንሂድ፡፡
የታሪክ ፀሐፊው ፍስሐ ያዜ ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ ከኖህ እስከ ኢህአዴግ›› በሚለው ቅጽ 1 መጽሐፉ በ81ኛው ምዕራፍ ላይ እንዲህ ይለናል፡፡
‹‹… ልጅ ምኒልክ የአጼ ልብነ ድንግል ልጅ ከሆኑት ከአጼ ያዕቆብ ትውልድ 13ኛ የዘር ሐረግ ላይ
ይቀመጣሉ፡፡ አያታቸው ሳህለሥላሴ የሸዋውን ንጉሥ ኃይለመለኮትን ይወልዳሉ…..›› እያለ ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ንጉሥ ኃይለመለኮት ከአፄ ልብነ ድንግል ዘር 12ኛ የዘር ሐረግ ላይ ይቀመጣሉ፡፡
ንጉሥ ሣህለሥላሴ (የንጉሥ ኃይለመለኮት አባት) ለ33 ዓመታት ከ 5 ወራት ያህል ሸዋንና በሸዋ ዙሪያ ያለውን ቦታ ሲያስተዳድሩ ቆይተው ጥቅምት 12 ቀን 1840 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ ዙፋኑን የወረሱት ልጃቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት ናቸው፡፡
ንጉሥ ኃይለመለኮት በሰውነታቸው ግዝፈትና ጥንካሬ እንዲሁም በልባቸው ቀናነት በሸዋ ዘንድ የታወቁና የተወደዱ ንጉሥ ነበሩ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚለው መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን፤ ንጉሥ ኃይለመለኮት ከጥንካሬያቸው የተነሳ ዒላማ ተኩስ በሚተኩሱ ጊዜ መሳሪያውን አጠንክረው በመያዛቸው ምክንያት ጥይቱ ሲወጣ ጠመንጃቸው ለሁለት ተሰብሮ እጃቸው ላይ ቀርቶ ያውቃል።
ንጉሥ ኃይለመለኮት ሸዋን ለ8 ዓመታት ያህል አስተዳድረዋል። በሥልጣን ላይ ሳሉም ተቀናቃኝ ሊሆኑባቸው የሚችሉትን ወገኖቻቸውን እንዲያስሯቸውና እንዲያስወግዷቸው ሰዎች ሲመክሯቸው፣ ‹‹ተዉ! ይሄን አላደርገውም! እግዚአብሔር የወደደውን ነው የሚያነግሰውና የሚያስገዛው›› የሚሉ ቀና ሰው እንደነበሩ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በመጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።
በመጨረሻም ዳግማዊ ዐጼ ቴዎድሮስ በሀገሪቱ በየቦታው ያለውን የተከፋፈለ አገዛዝ ወደ አንድ አስተዳደር በማምጣት በማዕከላዊ መንግሥት ስር የምትተዳር አንዲት ሀገር ለመመስረት አስበው ከየመሳፍንቱ ጋር በሚዋጉበት ጊዜ ‹‹ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሸዋም ሊመጡ ነው›› የሚል ወሬ ተሰምቶ ንጉሥ ኃይለመለኮትም ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ሆኖም ግን ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ንጉሥ ኃይለመለኮት ታመው ነበርና እርሳቸው በጦርነቱ ሳይካፈሉ፣ ጥቅምት 30 ቀን 1848 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የንጉሥ ኃይለመለኮት ሞት አሳዝኗቸው ነበርና አስክሬናቸው እንደገና ወጥቶ በንጉሣዊ የቀብር ሥርዓት እንዲቀበሩ አድርገዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እና የልጃቸው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ነው፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም