የደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ጥብቅ ደንና በዞኑ ከይርጋ ጨፌ ከተማ ወደ ገጠር ወጣ ብሎ የሚገኘውን የጌዲኦ ብሄረሰብን ጥምር ግብርናን፣ ትክል ድንጋዮችንና የተለያዩ የብሄረሰቡን ባህላዊ ሥርዓቶች በመጎብኘት ጅማሬውን ያደረገው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ፣ የቱሪዝም ጋዜጠኞችና አስጎብኚዎች ቡድን፣ በከንባታ ጠንባሮ ዞን የአምበርቾ ተራራን፣ የዞኑን የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች ጎብኝቶ፣ እነዚህን የሀገር ሀብቶች የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አዳምጦና ተመልክቶ ፣ የሌላ ጉብኝቱን መዳረሻ ደግሞ ጋሞ ዞን ላይ አድርጓል::
ለእዚህም አርባ ምንጭ ከተማ ገብቶ አዳሩንም በዚህች ውብ ከተማ አርጓል:: በሙዟ፣ በአሳዋ፣ በአባያና ጫሞ ሀይቆቿ፣ በአርባ ምንጮቿ፣ በደን ሀብቷ፣ በአዞዎቿ፣ በነጭ ሳር ቤሄራዊ ፓርክና በውስጡ ባሉ የዱር እንስሳት፣ የሰላም ተምሳሌት በሆኑት ጋሞዎች በእጅጉ የምትታወቀው የአርባ ምንጭ ከተማ ተቀብላናለች::
ሆቴሎቿ በሰፋፊ ይዞታ ላይ ያረፉና ውብ ናቸው:: መንገዶቿ ያማምራሉ፤ ምሽት ላይ ዝናብ የሰማሁ ቢመስለኝም፣ ብርድ ብሎ ነገር ግን አልተሰማኝም፤ ጧት ላይም ከተማዋ ዝናብ አየሁ ያለች አልነበረችም፤ መንገዶቿ ያምምራሉና በሚገባ የተነቡም በመሆናቸው ጭቃ ብሎ ነገር አላስተዋልኩም::
ቁርሳችን በላልተን የእለቱ ጉብኝት መዳረሻችን ወደሆነችው የጋሞ ዞኗ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዘይሴ ዲንቢሌ ቀበሌ መጓዝ ጀምረናል:: አርባምንጭ ከተማን ወደኋዋላ ትተን ወደ ኮንሶ የሚወስደውን መንገድ ይዘናል:: ከተማዋን ለቀን ስንወጣ ከሶዶ ወደ ከተማዋ ስንመጣ የተመለከትነውን ሰፋፊ የሙዝ እርሻ በዚህ የጉዞ መስመርም መመልከት ጀምረናል:: መሀል አገር ላይ የአርባ ምንጭ በጣእሙ በእጅጉ ይታወቃል:: የጫሞ ሀይቅን ፊት ለፊት እያየን የሙዝ እርሻውን በግራም በቀኝም እየተመለከትን በኮስትራችን እየበረርን ነው::
ወደ ኮንሶ የሚወስደውን ዋናውን መንገድ ትተን በስተቀኝ ጥቂት እንደተጓዝን እንዲት መንደር አገኘን፤ መንደሯን መሀል ለመሀል ሰንጥቀን ጉዟችንን ቀጠልን:: ጠንካራዋ ኮስትራችንንና አሽከርካሪዋ ወደ ጌዲኦ ጥብቅ ደን ስንጓዝ ያን ቁልቁለትና ዳገት ስንወጣና ስንወርድ፣ ከዱራሜ ወደ አምበሪቾ ስንሄድ ያን ዳገት ስንመለስም ያን ቁልቁልት የወጣችው የወረደችው ኮስትር መኪናችን ጉዞውን ተያይዘዋለች::
አካባቢው እህል የሚመረትበት ነው፤ በየደጁ ጎተራ ይታያል:: የሆነ አዝመራ ተነስቶ ሌላ አዝመራ የተከተለ የሚመስል ሁኔታ በማሳዎች ይታያል:: አንዳንድ ቦታ ላይ የደረቀ የበቆሎ አገዳ ክምር፤ በሌላ ቦታ ደግሞ ቡቃያ ይታያል፤ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ::
ኮስትራችን አንድ ቦታ ላይ ከጭቃ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረ ስጋት በስተቀር ምንም አልተቸገረችም፤ መንገዱን ላስ አድርጋዋለች:: ከፊት ለፊታችን የተሰበሰበ ሕዝብና የቆሙ መኪኖች ተመለከትን:: መኪኖቹ ከኛው ጋር የነበሩና ቀድመውን የደረሱ ናቸው:: ከአርባ ምንጭ ከተማ ወደ 72 ኪሎ ሜትር ተጉዘነው ቦታው ላይ የደረስነው:: ከዚህ ርቀት 13ቱን ኪሎሜትር በፒስታ መንገድ ተጉዘናል::
ታዳጊዎች፣ ወጣቶች፣ አባቶች እናቶች የመንገዱን ዳርዳር ይዘው ቆመው ሌሎች በመንገዱ መሀል ሆነው ይዘፍናሉ፤ የብሄረሰቡን የባህል አልባሳት የለበሱ የዘይሴ ብሄረሰብ አባላት ለብቻቸው እያዜሙ እየተወዛወዙ ናቸው:: ዘይሴ ዲንቢሌ ቀበሌ መድረሳችንን በአካባቢው ከተሰቀለ ማስታወቂያ ተረዳሁ:: ጭፈራና ውዝዋዜው እንዲቆም ተደርጎ የሐገር ሽማግሌዎች ንግግር ቀጠለ::
ይህን ሥነሥርዓት አንድ የስራ ሃላፊ ተረጎሙልን:: ‹‹እንኳን በሰላም መጣችሁ እያሉ መሆናቸውን ነገሩን:: የብሄረሰቡ አባቶች ‹‹የተከበራችሁ እንግዶቻችን ክበሩ፤ ክበሩ ፤ እንኳን በደህና መጣችሁ ፤ ዓመቱ የምንረዳዳበት ይሁንልን ፤ አሁንም ክበሩ፤ ክበሩ ነው የምንለው›› ማለታቸውን ሃላፊው እየተረጎሙ አብራሩልን::
እኚህ ሃላፊ አቶ ገመቹ ቡልቡላ ይባላሉ:: የጋሞ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻዎችና አገልግሎቶች ምርት ቡድን መሪ ናቸው:: ቀጥሎ ‹‹ሞጎ ቃቃ›› በመባል የሚታወቀውን ውብ ስፍራ እንደምንጎበኝ አቶ ገመቹ ጠቅሰው፣ ስፍራው የበሬ ሻኛ እንደሚመስል፣ ባለ ቀለምና ሰንሰላታማ ማራኪ ስፍራ መሆኑን አብራሩልን፤ ለቱሪስት መስህብነት ሊያገልግል ይችላል፤ አካባቢውን ማስተዋወቅ ያስፈለገውም ለእዚሁ ነው ሲሉ ገለጹልን::
የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሀረጓ ጴጥሮስ ‹‹ሞጎ ቃቃ›› በመባል የሚታወቀው የመስህብ ስፍራ ወደ ቱሪስት ግብይት እንዲገባ እንፈልጋለን ሲሉ ይገልጻሉ:: እንደ ሞጎ ቃቃ ያሉትንና ሌሎች ሰው ሰራሽ ካቦችን እንዴት ነው ወደ ገበያ ውስጥ ማስገባት የሚቻለው በሚለው ላይ ጽህፈት ቤቱ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ:: የሀገር ውስጥም የውጭ ቱሪስቶችም ወደ እዚህ አካባቢ መጥተው እንዲጎበኙ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ገልጸዋል::
ቀጣዩ ጉዞ በእግር ተጀመረ:: ለቱሪስት መስህብነት ወደ ታጨው ሞጎ ቃቃ:: ከፍታ ቦታ ላይ ነን፤ ቆም ብዬ ከርቀት ስመለከት ስፍራው በጨዋታ ብዛት የተመለጠ የእግር ኳስ ሜዳ ይመስላል፤ ቀድመውን በስፍራው የደረሱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አካባቢው ላይ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ:: ስፍራው የሹሮ መልክ አለው::
ቁልቁል መውረዱን ተያይዘነዋል:: አስቸጋሪ መንገድ ነው፤ ጠባብ፣ አንሸራታች፣ ቁጥቋጦ የበዛበት:: በመኪና ላይ ሆነን እያለ ከሩቅ ያዩሁት ስፍራ ነው::
በዘዴ እየተጓዝን በስፍራው ደርሰናል፤ ገባ ወጣ ይበዛዋል፤ በላዩ ላይ ለመራመድ ያስፈራል:: የበሬ ሻኛ ይመስላል የተባለው እውነት ነው፤ ለዚያውም ብዙ የበሬ ሻኛ:: በመሀል በመሀል ቦዮች ይታያሉ:: በአናቱ ላይ ለመንቀሳቀስ ቢያስፈራም መንቀሳቀስ ግን የግድ ነው:: በቦዮቹ ውስጥ ግን መንቀሳቀስ ያስቸግራል:: እናቶቹ ጠባብ ስለሆኑ መተላለፍ አያስችሉም፤ ለአንድም ሰው ቢሆን እንደልብ የሚያስረግጥ ቦታ የለም::
ጎልማሶቹም ሽማግሌዎቹም በላዩ ላይ ለመሄድ ሲቸገሩ አይታዩም:: የአካባቢው ወጣቶች፣ ታዳጊዎች ህጻናት ከአንዱ ጉብታ ወደሌላው እየዘለሉ ይሮጣሉ:: እኛም በዘዴ ስንሻገር ቆይተን ሁላ ላይ ግን ተለማምድነው::
የአሸዋ ክምር ቢመስልም ሲወጡበት ግን አያንሸራትትም፤ የሚፈረፈሩ ነገሮች ከመኖራቸው በስተቀር አይናድም፤ አያንሸራትትም ፤ ጎን ለጎን መሄድም መተላለፍም ያስቸግራል:: የጉብታዎቹ ላይ ጉዞ የገመድ ላይ ጎዞ የሚመስልበት ሁኔታም አለ::
አንዳንዶች ስፍራውን ሰሀራ በረሃ ውስጥ ያለን የአሸዋ ክምር ይመስላል ሲሉ ገልጸውታል፤ በእርግጥም ከአንዳንድ አረብ ሀገሮችና የሰሀራ በረሃ አካባቢ ሀገሮች አካባቢዎች ምስሎች ጋር ሲተያይ በንፋስ ሃይል የተጠራቀመ የአሸዋ ክምር ይመስላል::
የሚገርመው ደግሞ አቅራቢያው አረንጓዴ ሆኖ ያ ስፍራ ግን ምንም አይነት ሳር ዛፍና ሌሎች ተክሎች የማይታዩበት መሆኑ ነው:: ጎንበስ ብዬ ያን ምጥን ሹሮ መሳይ ተፈጥሮ አፈስ ላደርገው ሞከርኩ:: እንደ አሸዋ የሚታፈስ አይደለም፤ የሆነ የሚፈረፈር ነገር ነው:: ለግንባታ ግርፍ በሚል የሚዘጋጀውን የተፈጨ ጠጠር ይመስላል::
ስፍራውን ቆመው በአርምሞ የሚመለከቱ በርካታ ናቸው::ጋዜጠኞች ፎቶ ያነሱታል፤ እነሱም አብረው ይነሳሉ:: ቃለ መጠይቅ ያደርጋሉ፤ የዞኑና የወረዳው የባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎችና ባለሙያዎች መረጃዎችን እየሰጡ ናቸው::
የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ባህል ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቱሪስት መስህብ ልማት ባለሙያ አቶ ሙሉቀን ጎበና ሞጎ ቃቃ አናት ላይ ቆመን አነጋገርኳቸው፤ እሳቸው እንደሚሉት ፤ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልሉ የጋሞ ዞን ሶስት ብሄረሰቦች የሚገኙበት ነው:: እነሱም ጊዲቾ ብሄረሰቦች ዘይሴ ናቸው:: የዘይሴ ብሄረሰብ የሚኖረው ይህ መስህብ ባለበት አርባምንጭ ዙሪያ ነው::
አቶ ሙሉቀን የዘይሴ ብሄረሰብ እስከ አጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ድረስ የራሱ የአስተዳደር ሥርዓት ነበረው ሲሉ ያስታውሳሉ:: በንጉሳዊ አስተዳደር ይመራ እንደነበር ይገልጻሉ:: ንጉሱ የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚውና ማህበራዊው አስተዳደር ማእከል /ኒውክለስ. ነበር ይላሉ::
እሳቸው እንዳሉት ፤ የሕዝቡ ብዛት ወደ 60 ሺ ይጠጋል:: ዘይሲቴ የሚሰኝ ቋንቋም አለው፤ ይህ ቋንቋ ከኦሞቲክ የቋንቋ ዘር ግንድ ውስጥ ይመደባል:: ዘይሴ ብሄረሰብ የራሱ የኀዘን፣ የደስታ፣ የእርቅና የመሳሰሉት ባህላዊ ሥርዓቶችም አሉት::
ሞጎ ቃቃ ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺ 760 ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚገኝና 40 ሄክታር መሬት ይሸፍናል:: ሞጎ ቃቃ አፍርም አሸዋም አይደለም፤ ለየት ያለ ተፈጥሮ ነው:: ሞጎ ማለት ጥንት አካባቢውን ወይም ቀበሌውን ያስተዳድር የነበረ መሪ ስም ሲሆን፣ ቃቃ ማለት ደግሞ በዘይሲኛ ድንጋይም አፈርም ያልሆነ ጠንካራ ተፈጥሮ ማለት ነው::
ሞጎ ቃቃ ከበርካታ ዓመታት በፊት በእሳተ ገሞራ ምክንያት የተፈጠረ ስለ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ ሲሉ አቶ ሙሉቀን ይናገራሉ:: ከላይ የነበረው የአፈር ክፍል ተሸርሽሮ አልቆ ይህ ሹሮ የሚመስለው ክፍል ብቻውን እንደቀረ ይገልጻሉ::
አቶ ሙሉ ቀን እንደምታዩት በባህር ዳርቻዎች አካባቢ የሚታይ የአሸዋ ቁልል ይመስላል ሲሉ ስፍራውን በእጃቸው እያመለከቱ ገልጸውታል፤ አካባቢው ላይ ሎጆችና ሪዞርቶች ቢገነቡ ሌሎች የቱሪስት ፋሲሊቲዎች ቢዘጋጁ ለአካባቢውም ለዞኑም ለሀገሪቱም ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ሊሆን የሚችል ነው ይላሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ አካባቢው ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል፤ ቦታውን አስመልክቶ እስከ አሁን የተሰራ የለም ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዩቲዩበሮችን፣ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ወጣቶችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል:: ከክልልም ከፌዴራልም ሰዎች እየመጡ አካባቢውን እየተመለከቱ ናቸው:: ለማልማትም እቅድ እየወጣ ነው::
የጋሞ ዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻዎችና አገልግሎቶች ምርት ቡድን መሪ አቶ ገመቹ ቡልቡላ እንደሚሉት፤ ብሄረሰቡ የራሱ የምግብ አሰራር፣ የሰርግ ፣ የለቅሶ፣ ወዘተ ባህሎች ባለቤት ነው፤ የተለያዩ ሰብሎችን፣ ሙዝ፣ አቦካዶ፣ ጥጥ፣ ማር፣ ያመርታል፤ ከብት ያረባል:: የብሄረሰቡን ባህል ለማስተዋወቅ በብሮሸሮች፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ ወዘተ እየተሰራ ነው::
አቶ ገመቹም ሞጎ ቃቃ ምንም አይነት ጥናት እንዳልተካሄደበት ይገልጻሉ:: የእድሜ ባለጸጋዎች በ1965 አካባቢ በንጉሡ ዘመን አካባቢው ላይ ሄሊኮፕተር ወርዶ አፈሩን ይዞ መሄዱን ሲናገሩ እንደሚሰማ ጠቅሰው፣ ስፍራው ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ ህብረተሰቡም ከእዚህ አካባቢ ተጠቃሚ ሳይሆን መቅረቱን ይናገራሉ::
እንደ አቶ ገመቹ ገለጻ፤ ስፍራው ለቱሪዝም መስህብነት በትኩረት ቢሰራበት አዋጭ ሲሆን፣ የአካባቢው ማህበረሰቦችም ከዚህ ሊጠቀሙ ይችላሉ:: ወቅቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት እየተሰጠ ያለበት ነው፤ ከዚህ አኳያ ቦታው ለቱሪስት መስህብነት ሊውል ይችላል በሚል ተወስዶ በወረዳም በዞንም በክልል ደረጃም እየተሰራበት ነው:: በተለይ የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ ይገኛል::
ከዋናው አስፋልት መንገድ አንስቶ እስከ ዘይሴ ዲንቢሌ ያለው መንገድ በወረዳው መሰራቱን የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደ መስህቡ የሚያስገባ መንገድ ቢሰራ ደግሞ መስህቡ ይበልጥ የመጎብኘት እድል እንደሚኖረው ይናገራሉ:: ወረዳው በዚህ ላይ ከቀበሌ አመራሮች ጋር አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዞንና ከክልል አመራሮች ጋርም መሰራት እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ::
አንድ መስህብ የቱሪዝም መዳረሻ ከተደረገ መከለልና መጠበቅ እንዳለበት አቶ ገመቹ ጠቅሰው፣ ስፍራው በቀጣይ ለወጣቶች የስራ እድል እንደሚያስገኝና ለማስጠበቅና ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል::
የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የባህል ታሪክና ቅርስ ጥናትና ልማት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ጮሞም ይህን የተፈጥሮ መስህብ ለማስተዋወቅ እንዳልተሰራ ይናገራሉ:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እኛ ውስጥ መነሳሳት በእነሱ ውስጥ መነሳሳት መፈጠሩን ይገልጻሉ::
በየትምህርት ቤቶቹ ያደራጀናቸው የአገርህን እወቅ እንዲሁም ባህልና ቅርስ ክበባት አሉ የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ ከዚህ በኋላ ይህን መስህብ የበለጠ በማስተዋወቅ ከነበረበት ቦታ አንድ ደረጃ ከፍ አርገን ለማሳየት እንሰራለን ብለዋል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በክበባት እየሆኑ መስህቡን ለመጎብኘት በስፍራው እየተገኙ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ:: የመስህቡና አካባቢው አለመልማት በጣም እንዳስቆጫቸው ተናግረው፣ መስራት እየተቻለ ነው እስከ አሁን የተቀመጥነው የሚሉ አሰተያየቶች ከተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች እንደሚሰነዘሩም አስታውቀዋል::
ሞጎ ቃቃን ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት ሊበረታታ ይገባዋል:: የጋሞ አካባቢ የበርካታ ቱሪስት መስህቦች አካባቢ እንደመሆኑ ቱሪስቶችን ለማቆየት ምቹ ስፍራ ነው:: ሞጎ ቃቃ አጩ የቱሪስት መስህብ ነው:: ይህ መስህብ ቢተዋወቅና ወደ ቱሪስት ገበያው እንዲቀላቀል ቢደረግ የአካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማስፋትና ቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም እንዲሁም አካባቢውን ይበልጥ ለማስተዋወቅና ለማልማት ፋይዳው ከፍተኛ ነው::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም