በኢትዮጵያ ትልልቅ ስቴድየሞችን መገንባት ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሐዋሳ፣ ባህርዳር፣ ነቀምት፣ ሐረር፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ ጋምቤላና ሌሎችም ከተሞች ትልልቅ ስቴድየሞች ግንባታቸው ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን መጠናቀቅ
አልቻሉም፡፡ የአብዛኞቹ ስቴድየሞች ግንባታም ኮንክሪት ከማቆም የዘለለ ዓለም አቀፍ ስቴድየሞች የሚጠይቁትን መስፈርት ማማላት ሳይችሉ በቁም ቀርተዋል፡፡ የሐዋሳና የባህርዳር ስቴድየሞች ከሌሎቹ በተሻለ ውስን መሰረተ ልማቶችን አማልተው ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ ቢችሉም ግንባታቸው በተጀመረው ፍጥነት መጋዝ አልቻለም፡፡ እንዲያውም ከዓመታ በፊት የነበራቸው መሰረተ ልማት እየተዳከመ በመሄዱና ማሻሻያ ማድረግ ባለመቻሉ ያስተናግዱ ከነበረው ዓለም አቀፍ ጨዋታ ሊታገዱ በቅተዋል፡፡ የባህርዳር ስቴድየም ባለው የተሻለ ይዞታና መሰረተ ልማት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ብቸኛው ዓለም አቀፍ ጨዋታ የሚካሄድበት
ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስቴድየም በካፍና በፊፋ እንዲያሻሽል በተሰጠው ግብረመልስ መሰረት ስራዎችን ባለማከናወኑ ከዓመት በፊት ሊታገድ ችላል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን የሚያደርጋቸውን ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በሌሎች አገራት እንዲያካሂድ አስገድዶታል፡፡ በዚህም የስፖርት ቤተሰቡ የተጀመሩ ስቴድየሞች በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም እነዚህን በጅምር የቀሩ ስቴድየሞች ለማጠናቀቅ አብዛኞቹ ክልሎች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም፡፡
የባህርዳር ስታዲየም ሌሎች ክልሎች ካሉት በተለየ በክልሉ መንግሥት ተነሳሽነት የሁለተኛውን ዙር ቀሪ ሥራ ግንባታ ለማስጀመር ተወስኖ ወደ ስራ ተገብታል፡፡ የዚህን ስቴድየም የሁለተኛ ዙር ቀሪ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃግብርም ከቀናት በፊት ተካሂዷል፡፡
የባህርዳር ስታዲየም ከጣራ ውጪ ያሉ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና የካፍን 16 መሠረታዊ መስፈርቶች ለማሟላት የግንባታ ሥራው በይፋ የተጀመረ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅም ታስቧል፡፡
ኅዳር 2002 ላይ በ780 ሚሊዮን ብር በጀት 52 ሺ ተመልካቾችን እንዲይዝ ታስቦ ወደ ግንባታ የገባው የባህርዳር ስታዲየም፣ ለግንባታው ማስጀመሪያ 389 ሚሊዮን ብር ተፈርሞ የነበር ሲሆን እስካሁንም 758 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ታውቋል፡፡
በ MH ኢንጀነሪንግ አማካሪነት እና በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ለሚደረገው ግንባታ 1 ቢሊዮን 74 ሚሊዮን የተሰበሰበ ሲሆን ከጣራ ውጪ ያሉትን ሙሉ ሥራዎች የሚያጠቃልል እና በአንድ ዓመት የሚጠናቀቅ ይሆናል።
የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ ከሁሉ ስታዲየሞች በፊት ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ፍላጎት በማሳየት ድምጻቸውን ለማሰማት ባህርዳር እንደተገኙ ተናግረዋል፡፡ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፣ ብሔራዊ ቡድናችን በስታዲየም ዕጥረት ምክንያት ተሰዶ መጫወቱን ኮንነው ድርጅታቸው ስታዲየም ግንባታዎች በመሥራት እንደሚታወቅ በማስታወስ ለባህርዳር ስታዲየምም ከተበጀተው 740 ሚሊዮን ብር ላይ 300 ሚሊዮን ብር ጨምረው ግንባታውን እንደሚያሳልጡ አሳውቀዋል።
የክልሉ ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ ፕሮጀክቱ የሀገራችንን ስፖርት አንድ እርምጃ የሚያስኬድ መሆኑን ጠቁመው ግባቸው ግንባታውን ማስጀመር ሳይሆን ማጠናቀቅ እንደሆነ ገልጸዋል። ስታዲየሙን ብቻ ሳይሆን ከውጭ ያሉትን ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች አሻሽሎ በመሥራት ለወጣቶች ምቹ መዝናኛ ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም “ሀገራችን ውስጥ ግንባታ ይጀመራል እንጂ አይጨረስም” የሚሉ የሕዝብ አስተያየቶችን በማስተካከል ግንባታውን ለመጨረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ግንባታው 16 የካፍ መስፈርቶችን ለማሟላት የሚደረግ ሲሆን በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና የአማራ ክልል ወጣት እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዕርዚቅ ኢሳ መካከል የስምምነት ፊርማ ተደርጓል።
በግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተጨማሪ፣ የኢፌዴሪ መረጃ እና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ፣ የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ፣ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ፣ አትሌት ሞስነት ገረመው፣ የክልሉ ባለሀብቶች እና ሌሎች በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም