ተወልደው ያደጉት በቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሐገር ሆሮ ጉድሩ ነው፡፡ ወላጅ አባታቸው የቄስ ትምህርት አጠናክረው እንዲቀጥሉና ፣ ግዕዝ ተምረው፣ ዳዊት ደግመው፣ ቄስ እንዲሆኑ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ እርሳቸው ግን ለንግድ ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ገና በታዳጊነት ዕድሜያቸው ጀምረው ያስቡትን የንግድ ሥራ ለማሳካት ያወጡና ያወርዱ ጀመር፡፡
በልጅነት ዕድሜያቸው ‹‹ነጋዴ መሆን አለብኝ›› በማለት በ 14 ዓመታቸው የንግድ ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ ጠና ከበደ ናቸው፡፡ በ14 ዓመታቸው ከወላጅ እናታቸው አንድ ጠገራ ብር ተበድረው በዶሮ ንግድ የንግድ ሥራን የተቀላቀሉት አቶ ጠና፤ ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች በመሳተፍ ውጤታማ
ሆነዋል፡፡ ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንዲሉ እስከ አስመጪነት ደርሰዋል፡፡ የሕንጻዎችና የሆቴልና ሪዞርት ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡
ለንግድ ባላቸው ጥልቅ ፍላጎት ላይ የግል ጥረትና ትጋታቸው ታክሎበት በንግድ ሥራቸው አንቱ የተባሉት አቶ ጠና፤ የሕይወት ዘመናቸውን ሙሉ በሚባል ደረጃ ጊዜያቸውን ለንግድ ሥራ
ሰጥተዋል፡፡ በንግድ የሕይወት ጉዟቸውም እስራትን፣ ስደትን ጨምሮ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን
አሳልፈዋል፡፡ በመውጣት በመውረዳቸው ውስጥ እግዚአብሔር አብሯቸው ይመላለስ እንደነበር በጽኑ የሚያምኑት አቶ ጠና፤ ዛሬ ለደረሱበት ስኬት ምክንያቱ የእግዚአብሔር እርዳታ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ፡፡
ከዶሮ ንግድ ቀጥለው በሸቀጣ ሸቀጥ፣ በመኪና ዕቃ መለዋወጫና በመኪና ኪራይ፣ ብትን ጨርቅ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት እና በሌሎችም የንግድ ሥራዎች ተሳትፈዋል፡፡ በእነዚህና መሰል የንግድ ሥራዎች ወጥተው ወርደው ባካበቱት ጥሪትም በአዲስ አበባ ቦሌ ስካይ ላይት ሆቴል ፊትለፊት የሚገኙ እያንዳንዳቸው ስምንት ፎቅ ያላቸውን ሁለት ሕንጻዎች ገንብተዋል፡፡ በቅርቡም ቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርትን ገንብተዋል፡፡
ከአርሶ አደር እንዲሁም ፈሪሃ እግዚአብሔር ካደረበት ኃይማኖተኛ ቤተሰብ ስለመገኘታቸው የሚናገሩት አቶ ጠና፤ አባታቸው በወቅቱ የንግድ ሥራቸውን ተቃውመው እንደነበርም
ያስታውሳሉ፡፡ ገና በጠዋቱ ‹‹የወዲፊት ዕጣ ፈንታዬ ነጋዴ መሆን ነው›› ያሉት አቶ ጠና፣ የወላጅ አባታቸውን ቁጣ ቻል አድርገው ለነብሳቸው ጥሪ ምላሽ በመስጠት የዶሮ ንግድ ሲጀምሩ ዛሬ ላይ እዚህ እደርሳለሁ በሚል አልነበረም፡፡
ይሁንና በወቅቱ ከወላጅ እናታቸው በወሰዱት አንድ ጠገራ ብር በአካባቢያቸው ከሚገኝ ገበያ እያንዳንዳቸው 20 ሳንቲም ያወጡ ስምንት ዶሮዎችን በመግዛት የልጅነት ህልማቸውን ዕውን ለማድረግ ጉዟቸውን አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ በ20፤ 20 ሳንቲም የተገዙት ዶሮዎችም በእጥፍ አትርፈው እያንዳንዳቸው በ40 ሳንቲም ተሸጡ፡፡ ከወላጅ እናታቸው የተበደሩትን ገንዘብ ወዲያው ከፈሉ፡፡ በወቅቱ በእጥፍ አትርፈው አንድ ጠገራ ብር ማግኘት በመቻላቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደነበርም አጫውተውናል፡፡
በትርፋቸውም ተጨማሪ ዶሮዎችን ገዝተው በመሸጥ የንግድ ሥራቸውን ማቀላጠፍ
ቀጠሉ፡፡ የዶሮ ንግዱ ጠቀም ያለ ትርፍ ሲያመጣላቸው የንግድ ሥራቸውን ከዶሮ ንግድ ወደ ሸቀጣሸቀጥ ሱቅ አሳደጉት፡፡ የሸቀጥ ንግዱም እንዲሁ ከፍ ከፍ እያለ ሲሄድ መኪና እንዲገዙ በር
ከፈተላቸው፡፡ መንጃ ፈቃድ አውጥተው በመኪናው ሲሰሩ ቆዩና የመኪናዎቹን ቁጥር ሶስት አደረሱ፡፡ ይህን ጊዜ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የንግድ ሥራቸውን ይበልጥ ማስፋት ያሰቡት አቶ ጠና፤ መኪኖቻቸውን በሙሉ ይዘው ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው ኑሮው ብዙም አልፈተናቸውም፡፡
አዲስ አበባ ሲገቡ የመጀመሪያ እርምጃቸው የኔታ ዘንድ ፊደል ቆጥረው ዳዊት ደግመው ገታ ያደረጉትን ትምህርት መቀጠል ነበርና ካቴድራል ትምህርት ቤት በመግባት በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን
ቀጥሉ፡፡ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የመኪና ሥራቸውን በማስፋፋት አምስት ስድስት እያሉ የመኪኖቻቸውን ቁጥር አበራከቱ፡፡ ከነተሳቢዎቹ አስር የደረሱት መኪኖች አሰብ ድረስ እየሄዱ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ፈጠሩላቸው፡፡ በዚህ ጊዜም ነው ትዳር የመሰረቱት፡፡
በወቅቱ ገቢያቸው እየተበራከተ ሲመጣ የንግድ ቤት መግዛት እንዳለባቸው አሰቡ፡፡ አስበውም አልቀሩ፤ ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አቅራቢያ ሞዝቮልድ አጠገብ የሚገኘውን ህንጻ በ650 ሺ ብር መግዛት ቻሉ፡፡ በሕንጻው አንዱ ክፍል ቢሯቸውን በማድረግ ቀሪዎቹን ደግሞ በማከራየት ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ ወቅቱ ደርግ ወደ ሥልጣን የመጣበት በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ደርግ ‹‹የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት ሁሉ የመንግሥት ነው›› የሚል አዋጅ አወጣ፡፡ አዋጁም ተግባራዊ ሆነና ሙሉ ሕንጻቸው በመንግሥት ተወረሰ፡፡
አቶ አሁንም ተስፋ አልቆረጡም፡፡ ‹‹ደርግ የማይወርሰው ምንድነው›› ብለው መጠየቅ
ጀመሩ፡፡ የማይወርሰው የሸቀጥ ንግድ መሆኑንም
ተረዱ፣ መርካቶ ጣቃ ጨርቅ ቤት ከፍተው ብትን ጨርቆችን ከኮርያ በማስመጣት ማከፋፈል
ጀመሩ፡፡ ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ ደርግ የገቢ ንግዱን የሚከለክል አዋጅ አወጣ፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ጣቃ ጨርቅ ከኮርያ እንዲመጣላቸው አዘው መርከብ ላይ ነበርና አጋጣሚው ጥሩ የገበያ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ እጃቸው የገባው ከፍተኛ መጠን ያለው ጣቃ ጨርቅ ሌሎች ዘንድ ባለመኖሩ በእጥፍ ተሽጦ በብዙ ማትረፍ አስችሏቸዋል፡፡
ወቅቱ ገንዘብ ያለው ሰው የማይፈለግበት የደርግ ዘመን እንደመሆኑ አቶ ጠና ከዶሮ ንግድ ጀምረው ባካበቱት ሀብት አድሃሪ ተብለው ታስረዋል፡፡ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው በዋስ ሲፈቱ አገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዱ፡፡
ያኔ በናይሮቢ ኬንያ አድርገው አሜሪካ
ገቡ፡፡ በአሜሪካም ከነብሳቸው የተወዳጀውን የንግድ ሥራ ቀጥለው የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን
ሠርተዋል፡፡ ከአሜሪካ ስራዎቻቸው መካከልም ትልቅ ሱፐርማርኬት ከፍቶ በርካታ ሸቀጦችን መነገድ አንዱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከሥራቸው ጎን ለጎንም እዛው አሜሪካ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን የኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡
ከ 12 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ የደርግ ዘመነ መንግሥት አክትሞ የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣኑን ሲረከብ ወደ አገራቸው የተመለሱት አቶ ጠና፣ ኢትዮጵያ በገቡበት ፍጥነት የንግድ ሥራቸውን ለመቀጠል አልተቸገሩም፡፡ የጣቃ ጨርቅ ከኮርያ በማስመጣት የቀድሞ የንግድ ሥራቸውን ማስቀጠል ቻሉ፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ ማርሻል የመኪና ጎማ ከኮርያ ወኪል ሆነው በማስመጣት ያከፋፍሉም ጀመር፡፡ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችንም እንዲሁ ከውጭ አገራት ወደ አገር ውስጥ ማስገባቱን
ተያያዙት፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ቀደመው ሀብታቸው በመመለስ መደራጀት ሲጀምሩ አሜሪካ ትተዋቸው የነበሩትን ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ በማድረግ የንግድ ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡
ከስደት ወደ አገራቸው ተመልሰው በኪራይ ቦታ የንግድ ሥራቸውን ያስቀጠሉት አቶ ጠና፤ መሬት በሊዝ ገዝተው ሕንጻ መሥራት እንዳለባቸው በማሰብ መሀል ቦሌ ላይ 1009 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በመግዛት ሕንጻ ገነቡ፡፡ በድጋሚም ከጎኑ ያለውን ቦታ በሊዝ በመግዛት ተጨማሪ ሕንጻ በመሥራት ለቢሮ ማከራየት ችለዋል፡፡
አቶ ጠና ቦሌ ከስካይ ላይት ሆቴል ፊት ለፊት ጠና ቲኬ ህንጻ / ከበደና ቤተሰቦቹ በሚል የሚጠሩትን እያንዳንዳቸው ስምንት ወለል ያላቸውን ሁለት ሕንጻዎች በመገንባት አላቆሙም፡፡ ወደ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፊታቸውን በማዞር በቢሾፍቱ ሀይቅ ዳር ባለ አምስት ኮከብ ደረጃ ያለውን ቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርትን
ገነቡ፡፡
ሆቴሉ ከሌሎቹ ሆቴልና ሪዞርቶች ልዩ የሚያደርጉት በርካታ መሰረተ ልማቶች ያሉት ሲሆን፣ የሆቴል ግንባታው ከየትኛውም ሥራ በበለጠ እንዳደከማቸውም አቶ ጠና ያስታውሳሉ፡፡ ቦታውን ለማግኘት ከክልሉ አስተዳደር ጋር ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ጥረትን ጨምሮ ሆቴሉን ገንብቶ ለማጠናቀቅ አጠቃላይ 13 ዓመታት ወስዶባቸዋል፡፡
ሆቴሉ በሀይቅ ዳርቻ አቅራቢያ እንደ መገንባቱ ከሆቴሉ እስከ ሃይቁ የሚወስዱ 450 ደረጃዎች
አሉት፡፡ እጅግ አስቸጋሪና ገደላማ የሆነውን ቦታ በማልማት ሀይቁ ከሆቴሉ ሥር ረግቶ እንዲቀመጥና ለአይን እንዲማርክ ሆኗል፡፡ ሆቴልና ሪዞርቱን ለመገንባት 750 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበትም ይገልጻሉ፡፡
ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የበኩላቸውን የተወጡት አቶ ጠና፤ የቢሾፍቱ ቲኬ ሆቴልና ሪዞርት ብቻ ለ150 ሠራተኞች፤ በሕንጻዎቻቸው ሥርም እንዲሁ ለ200 ዜጎች በድምሩ ለ350 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ሰፊ አበርክቶ ያላቸው አቶ ጠና፤ በአሁኑ ወቅት ከሆቴሉም ሆነ ከሕንጻዎቻቸው የሚገኘው ገቢ ለሁለት ተከፍሎ ግማሹ ለበጎ አድራጎት ይሰጣሉ፤ ግማሹን ደግሞ ለልጆቻቸው
ያስቀምጣሉ፡፡ በተለይም ጠና ከበደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚለው መጠሪያ አቅመ ደካሞችን በመርዳት የበጎ አድራጎት ሥራ ይሠራሉ፡፡ ለአብነትም በተለያየ ቦታ የሚገኙ ተማሪዎች፣ ለቤተክርስቲያንና አቅመ ደካማ ነኝ ብለው ለሚመጡ ሁሉ መርጃ ይውላል፡፡
በዚህ የበጎ አድራጎት በቋሚነት በየወሩ እየመጡ ሶስት ሺ ብር ከሚወስዱ ግለሰቦች በተጨማሪ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ለመቄዶንያ የአረጋውያን መርጃ ድርጅት ብቻ በዓመት አንድ ሚሊዮን ብር የሚሰጡት አቶ ጠና፣ ይህ በጎ ሥራ በእጅጉ የሚያስደስታቸው እንደሆነ ነው ያጫወቱን፡፡
‹‹ከምንም ተነስቼ ድህነትን ለማሸነፍ ባደረግኩት ጥረት ዛሬ ላይ መድረሴን ሳስበው የሆነው ሁሉ በእግዚአብሔር እገዛ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እዚህ ላደረሰኝ አምላክም ምስጋና አቀርባለሁ›› የሚሉት አቶ ጠና፤ ዕድሜ ዘመናቸውን በሙሉ በንግድ ሥራ ውስጥ ወጥተዋል፤ ወርደዋል፤ ባፈሩት ሀብትና ንብረትም ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ተግባር አከናውነዋል፡፡ በቅርቡም 80 ዓመታቸውን ያከበሩ ሲሆን፣ ከእንግዲህ እረፍት ያስፈልገኛል በማለት ጡረታ ለመውጣት ተሰናድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ድርጅቶቻቸውን ለልጆቻቸው በማስረከብ ሂደት ላይ የሚገኙት አቶ ጠና፤ በቀጣይ በብዙ ድካምና ጥረት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ልጆቻቸው በአግባቡ ማስተዳደር እንዲችሉ
ይመክራሉ፡፡ በተለይም ልጆቻቸው ድርሻቸውን ከመጠቀም ባሻገር ለእግዚአብሔር የሚገባውን መባእና አስራት እንዲያወጡ፣ ድሆችን መርዳት እንዳይረሱና እርሳቸው የጀመሯቸውን ራዕዮች ጠብቀው ሥራውን እንዲያስፋፉ ምኞትና ፍላጎታቸው ነው፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም