
ድህነት ጥላውን ላጠላባቸው ነፍሶች ቤት ከመጠለያም በላይ ነው። ቤት ገመናን ሸፋኝ፣ የዘመናት እንባን አባሽ፣ ሀዘንን መርሻ፣ ዞሮ መግቢያ ነው። የክረምቱን መግባት ተከትሎ በበጎ ፈቃድ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የአረጋውያንን እና የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ማደስ አንዱ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሃኒት፣ የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣንም በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የብዙዎችን ቤት ጎብኝቷል።ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ዝቅ ብሎ እጃቸው ላጠረባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቤታቸውን አድሶ ለባለቤቶቹ አስተላልፏል።
ወይዘሮ አብነት ቢሻው ይባላሉ፤ የመኖሪያ ጎጇቸውን በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አዲሱ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ቀልሰዋል። ቤታቸው ወደ ጎን ያዘመመ፣ለመውደቅ አንድ ሀሙስ የቀረው እርጅና የደቋቆሰው ነበር።
ድህነት ድሩን ያደራባቸው ወይዘሮዋ ኑሯቸው የስቃይ ነበር። ከአሁን አሁን ቤታችን ፈረሰ በሚል ስጋት እንቅልፋቸውም የሰቀቀን ነበር።“ቤታችን በተኛንበት የሚፈርስ ስለሚመስለን በቀን እንኳን ለመተኛት እምነት የምንጥልበት አልነበረም።”ይላሉ
ዝናብ ሲጥል የሚገባውን ውሃ ከጎረቤት ጋር በመተባበር በባልዲ እየቀዱ ያፈስሱ እንደነበር የሚያስታውሱት ወይዘሮ አብነት “የሚገባው ጎርፍ የልጆቼን ደብተር፣የቤት ውስጥ የፍጆታ ዕቃዎቼንና ልብሳችንን አበላሽቶብን ያውቃል” ሲሉም ያሳለፉትን ያስታውሳሉ።
የልብ ህመምተኛ ልጃቸው ለየት ያለ ጠረን ሲሸታት ስለምትታመም ልጃቸውን ከአካባቢው ለማሸሽ ግድ ብሏቸው ነበር። ቤቱ ልጆቻቸው ላይ ወድቆ አደጋ ያደርሳል በሚል ስጋት ብዙ የመከራ ቀናቶችን አሳይቷቸዋል። ለዚሁ ሲሉም ልጃቸውን ከሰው አስጠግተው ለማኖር ተገደውም ያውቃሉ።
ወይዘሮ አብነት “አሁን ቤቴ ስለታደሰልኝ ልጄን አያምብኝም፤ጎርፍ ይገባል፤ቤቱም ይወድቃል የሚል ስጋት የለብኝም፤የተደረገልኝን ለመናገር ቃላት ያንሰኛል” ይላሉ። በእንዲህ አይነት በጎ ሃሳብ በመነሳሳት ደካሞችን የሚደግፉ አካላትንም አመስግነዋል።
አቶ ይታገሱ ኃይሌም የቤት ዕድሳት ዕድል ከገጠማቸው መካከል ሌላኛው ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሃኒት፣የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ቤታቸውን አድሶላቸዋል። ክረምት በመጣ ቁጥር ወደ ቤታቸው የሚገባው ጎርፍ ኑሯቸውን ጎደሎ፣ህይወታቸውን ምስቅልቅል አድርጎባቸው ያውቃል።ዝናብ በዘነበ ቁጥር ውሃው ቤት ውስጥ ሲገባ በማስታጠቢያ እያወጡ መድፋት ዕለታዊ ስራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
አቶ ይታገሱ፤ “በጎርፉ ምክንያት የቤቴን መውጫ በር በሌላ በኩል ለማድረግ ስሞክር ዝናቡና ብርዱ በጆሮዬና በአፍንጫዬ ይገባ ነበር።” ይላሉ ትናንታቸውን ሲያወሱ፤ በጓሯቸው ውስጥ የገባው ውሃ ለጤና ችግር ዳርጓቸዋል።አሁን ያ ሁሉ መከራና ስቃይ ታሪክ ሆኖ አልፏል።ለዚህ ቀን ያደረሳቸውን ፈጣሪ ምስጋናቸውን ይቸሩታል።
“የተሰራው ቤት በጣም ቆንጆ ነው። ነገር ግን በፊት ከነበረው ስፋቱ ቀንሷል። የጎርፉ ጉዳይ ክረምት ሲመጣ የሚገባት ሁኔታ አልተቀረፈም። ይህንን ጉዳይ ቤቱን የሰሩልን እንደሚያስቡበት አልጠራጠርም” ሲሉ ተናግረዋል። አሁን የሌለን ማድቤትና መጸዳጃ ቤት ነው። ይህንንም ችግር አሰሪው አካል እንደሚፈታው እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
እድገታቸው አዲሱ ሚካኤል አካባቢ ለሆኑት አቶ ወንድሙ ገብረ እየሱስም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብና መድሃኒት፣ የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ቤት አድሶላቸዋል።
“ቤቶቹ በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን የተሰሩ በመሆናቸው እድሳት ተደርጎላቸው አያውቁም። ለመኖር በጭቃ መጠገን ያስፈልጋል ይላሉ። ከ1998 እስከ 2000ዓ.ም ባለው ጊዜ በልማት ትነሳላችሁ ተብለው በጭቃ እንዳይሰሩ ተደርገው እንደነበር ያወሳሉ። በዚህም ቤቱ ዝናብ በዘነበ ቁጥር የልጆቻቸው ደብተር፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ በጎርፍ በመበላሸቱ የወደሙትን ንብረቶች የመተካት አቅም የለኝም” ይላሉ።
የቤታቸው አሰራር ውሃ ልክ የሌለውና በጭቃ የተሰራ እንዲሁም የቆየ በመሆኑ ከፓስተር አካባቢ የሚመጣው ፍሳሽ ወደ ግቢያቸው ይገባ ነበር። በዚህም ከመፋሰሻ ቱቦው የሚመጣው ሽታ ለጤንነታችን አስጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ ለሚመለከተው አካል እንዲሰራ ከሌሎች ጋር በመሆን አመልክተን ነበር። ነገር ግን በጊዜው የነበረው አካል ወደ ቤት የሚገባውን ጎርፍ እያዩ በዝምታ አልፈውን ነበር።
አሁን ያለው የመንግስት አካል ችግራችንን ተረድቶ በአካል በመምጣትና በማየት እያሳለፍን ያለውን ስቃይ ተረድቶ ለሚመለከተው አካል አሳውቀን እንዲሰራላችሁ እናደርጋለን ብለው ቃል ገቡልን። ቃላቸውንም ጠብቀው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ እንዲሰራ የመሰረት ሥራውን አስጀመሩልን። ለዚህ ክቡር ሥራ ፈጣሪ እንደችሎታቸው የሚፈልጉትን ያሳካላቸው ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም