በዓለም ላይ ከሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች መካከል በቀዳሚነታቸው የሚጠቀሱት ስድስቱ ታላላቅ ውድድሮች የ2022 የውድድር ዘመን ባለፈው ሳምንት ተጠናቀዋል። በአትሌቲክሱ ዓለም በየዓመቱ ከሚካሄዱት እነዚህ የማራቶን ውድድሮች የቶኪዮ፣ ቦስተን፣ ለንደን፣ በርሊን፣ ቺካጎ እና ኒውዮርክ ማራቶኖች ዋና ዋናዎቹ (ሜጀር) ሩጫዎች ናቸው። ታዲያ በእነዚህ ሩጫዎች ላይ የተካፈለ አትሌትም ለዓለም አትሌቲክስና ኦሊምፒክ እንደ መለኪያ የሚቀመጡ ውድድሮችም ናቸው።
በአቦት ላቦራቶሪስ ስፖንሰርነትም በዓመቱ በሚካሄዱት በእነዚህ ውድድሮች ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶች የሚያገኙት ውጤት ተደማምሮ በዓመቱ መጨረሻ አሸናፊው አትሌት ይለያል። በዓመቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካሄድ ከሆነም በማራቶን አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከስድስቱ ውድድሮች በተጨማሪ ነጥብ የሚያዝላቸው ይሆናል። በዚህ የውድድር ዓመትም ስድስተኛው የኒውዮርክ ማራቶን መካሄዱን ተከትሎ አሸናፊዎቹ አትሌቶች ተለይተዋል። በዚህም መሠረት የ2022 የአቦት ሜጀር ማራቶን አሸናፊዎቹ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጎይትቶም ገብረስላሴ ስትሆን፤ በወንዶች በኩል ደግሞ የማራቶን ጀግናው ኬንያዊ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ማሸነፋቸውን አረጋግጠዋል።
ከረጅም ዓመታት በኋላ በሴቶች የማራቶን ውድድሮች ንግሥናን የተቀዳጀችው አትሌት ጎይትቶም ገብረስላሴ ሆናለች። አትሌቷ ከዋና ዋናዎቹ ውድድሮች መካከል በመጀመሪያው የቶኪዮ ማራቶን ሦስተኛ ደረጃን ስትይዝ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው የመጨረሻው የዓመቱ ውድድር ኒውዮርክ ማራቶንም በተመሳሳይ ሦስተኛ ነበረች። ይሁንና አትሌቷ በዓመቱ በአሜሪካኗ ኦሪጎን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር አሸናፊ መሆኗ ውጤቷን ከሌሎች አትሌቶች ይልቅ ሊያንረው ችሏል።
በወንዶች በኩል አሸናፊ የሆነው የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ነው። አትሌቱ የዓመቱን ቁጥር አንድ የማራቶን አትሌትነትን ክብር ለማግኘት የቻለው ደግሞ በቺካጎ ማራቶን በማሸነፉ እንዲሁም በለንደን ማራቶን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ነው። በተሰበሰበው ነጥብ መሠረት ከኪፕቾጌ የተሻለ አትሌት ቢኖርም የወርልድ ሜጀር ማራቶን ዳይሬክተሮች በሰበሰቡት ድምጽ መሠረት አሸናፊነቱን ሊያገኝ ችሏል። በነጥብ የሚበልጠው አትሌት የሃገሩ ልጅ ኢቫንስ ቺቤት ሲሆን፤ የቦስተን እና ኒውዮርክ ማራቶኖች አሸናፊ ነበር።
የማራቶን ንጉሡ ኪፕቾጌ በዚህ ውድድር አሸናፊ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው አይደለም። እአአ ከ2015 ጀምሮ ለተከታይ አራት ዓመታት 50 ነጥቦችን በማስመዝገብ የበላይነቱን ለብቻው ተቆጣጥሮት ቆይቷል። ያለፈው ዓመት የሃገሩ ልጅ አልበርት ኮሪየር አሸናፊ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ደግሞ በድጋሚ ኪፕቾጌ ወደ ለመደው አሸናፊነቱ ሊመለስ ችሏል።
በዊልቸር ወንዶች አሸናፊ የሆነው ስዊዘርላንዳዊው አትሌት ማርስል ሃግ ሲሆን፤ በሴቶች በኩል ደግሞ አሜሪካዊቷ ሱዛና ስካሮኒ ናት። በእርግጥ ከዊልቸር አሸናፊዎቹ በቀር አሸናፊ የሆኑት አትሌቶች እነማን እንደሆኑ በግልጽ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ አልታወቁም። ነገር ግን የወርልድ ሜጀር ማራቶን የትዊተር ገጽ ሁለቱ አሸናፊዎች በ2022 የማራቶን ቁጥር አንድ ምርጦች መሆናቸው መገለጹን ሌታስራን የተባለው ድረገጽ በዋቢነት ኣሳይቷል።
ይህ ሽልማት ለማራቶን ሯጮች የሚሰጥ እንደመሆኑ በዚህ ርቀት በተለይ የሚታወቁት የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቶች መሆናቸው ግልጽ ነው። በዚህም መሠረት እአአ ከ2006 ጀምሮ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ የቻሉት ኬንያውያንና ኢትዮጵያውያን ናቸው። በሴቶች በኩል የመጀመሪያው የአቦት አሸናፊ የነበረችው አትሌት ኢትዮጵያዊቷ ጌጤ ዋሚ መሆኗን መረጃዎች ያመላክታሉ። የወቅቱ የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ ጌጤ ምርጥ አትሌት ከተሰኘች በኋላ ለረጅም ዓመታት ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች አሸናፊ መሆን አልቻሉም ነበር። በወንዶች በኩልም አትሌት ጸጋዬ ከበደ ብቸኛው አሸናፊ በመሆን በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተቀምጧል። አትሌቱ እአአ በ2012 የቺካጎ ማራቶን አሸናፊ ሲሆን፤ በለንደን ማራቶን ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ነው አሸናፊ ሊያደርገው የቻለው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም