የደርግን ሥርዓት ለመጣል 1978 ዓ.ም ነበር የሕወሓት ታጋይ ሆነው ትግል የጀመሩት። ከዚያ በእግረኛ ምድብ ተራ ወታደር ሆነው ሞርታር ተኳሽ ነበሩ። አዲስ አበባ እስከገቡበት ድረስ የሞርታር ሻምበል አዛዥ ነበሩ። አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች ሠርተዋል። በመሐንዲስ ትምህርት ቤት አስተዳደርና ፋይናንስ፣ የመከላከያ መሐንዲስ ዋና መምሪያ የሎጂስቲክስ ኃላፊ፣ የቤቶችና መሬት ክትትል አስተዳደርና ፋይናንስ እንዲሁም በመከላከያ ኮንስትራክሽን የኢንዶክትሬሽን የኮሙኒኬሽን ዋና ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ይሁንና በ2007 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ አባል ነህ በሚል ወደ እስር ቤት ተወረወሩ፤ የአራት ዓመት ደመወዝም ተከለከሉ።
በሂደት የትዴፓ አባል ሆነዋል። ከለውጡ ወዲህ ደግሞ የጡረታ መብታቸው ተከብሯል። የዛሬው ‹‹የወቅታዊ አምድ›› እንግዳችን ኮሎኔል ፍሰሐ ገብረመድህን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የፓርቲው ፀጥታና ደህንነት ኃላፊ ናቸው። በዛሬው ዕትማችን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን አካፍለውናል።
አዲስ ዘመን፡- በሰሜኑ አገራችን በነበረው ጦርነት በአማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች እንደ አገርም የደረሰው ጉዳት ከባድ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የጦርነትን አስከፊነት እንዴት ይገልጹታል ?
ኮለኔል ፍሰሐ፡- እንድነገርኩህ እኔ ጦርነትን በፊልም ሳይሆን የማውቀው በውስጡ ብዙ ዓመታትን ያሳለፍኩ ሰው ነኝ። ጦርነት ማለት የሰው ሕይወት የሚበላ፣ አካል የሚያጎድል፤ ንብረት የሚያወድም ነው። እያንዳንዱ ተተኳሽ የአገር ሀብት ነው። የወደሙት ተሽከርካሪዎችም በተመሳሳይ ብዙ ብር የወጣባቸው ናቸው። ይህ እጅግ ብዙ ንብረት የወጣበት በመሆኑ የአገር ዕድገትን በጣም ጎትቷል። በዚህ ማንም የሚስማማበት ሃሳብ ነው። በሌላው የትግራይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ወጣት ጉልበትን ልማት ላይ ከማዋል ጦርነት ላይ ውሏል። ይህም ከፍተኛ ኪሳራ ሲሆን አገሪቱን በጣም ነው የጎዳው።
ጦርነቱ አፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎችን የጦርነት አውድማ አድርጓል። በርካታ የንብረት ውድመት፤ የሰው ሕይወት መጥፋትና ብዙ መፈናቀሎችን አስከትሏል። እንደ አገር የደረሰው ውድመት በገለልተኛ አካል ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም ከፍተኛ ጥፋት መሆኑን መካድ የለብንም። ጦርነት አውዳሚ በመሆኑ ፈጽሞ መካሄድ ያልነበረበት ነው። የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ቀላል ማየት አይገባም። ሆኖም ከችግሩ ለመውጣት የጠፋው ጠፍቶም ወደ ሰላም መንገድ መጓዝ ትልቅነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን የሰላም ስምምነት እንዴት ያዩታል?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- ብዙ የንብረት ውድመትና የሰው ሕይወት መስዋት ቢሆንም ቅሬታውን ለመፍታት ግን አሁንም ይቻላል የሚለው ነገር አበረታች ነው። በመጀመሪያ ጦርነቱን የትግራይ ሕዝብ አይፈልገውም ነበር። ነገር ግን በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ የተጀመረ እና ያልተጠበቀ ነው። ሁለተኛው የትግራይ ሕዝብ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሲነካ ለምን ብሎ የሕወሓትን ቡድኖች ሲቃወም ነበር። በሌላ በኩል፤ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ከአማራ እና አፋር ሕዝቦች ጋር በባህል፣ በዕምነት፣ በታሪክ የተጋመዳቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ።
የሰሜኑን ሕዝብ የጋራ የሚያደርገው እና የሚያመሳስላቸው ነገር ይበዛል። እርስ በእርስ በደም የተሳሰሩም ናቸው። ጦርነቱ ያስከተለው ችግር እንዳለ ሆኖ ሰላም ለመፍጠርና እርቅ እውን እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ይሳካል የሚል እምነት አለኝ። የቀድሞ አንድነትና ፍቅር ስለሚበልጥ ያለፈውን መተው ይኖራል። ማወቅ ያለብን ነገር ይህ ጦርነት በሁሉም አካባቢ ያሉ ዜጎቻችን ፈልገው የገቡበት አለመሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ጦርነቱ በሁሉም አካባቢዎች ያስከተለው ጠባሳ በጣም የከፋ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ሕዝብ ያመጣው አይደለም።
ሁሉንም ነገር ሰከን ብሎ ማየት ይቻላል። በእኔ አረዳድ የአማራ፣ የአፋርና የትግራይ ሕዝቦች ቅሬታውን በቀላሉ ይፈቱታል የሚል እምነት አለኝ። ሕዝብን ለፖለቲካ ትርፍ ብለው ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ማወቅ አለብን። የአማራ እና ትግራይ ሕዝብን ለመነጣጠል የተሄደበት ርቀትም አልተሳካም ማለት ይቻላል። አንዱን ከሌላው መነጠል አይቻልም። ቀድሞ የነበረው የሥነ- ልቦናዊ ትስስሩ በተፈጠረው ቅራኔ ተራርቆ ይቆያል ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ችግሮቹ ጎልተው በታዩባቸው ክልሎች የሰላም ስምምነቱ እውን እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ባለድርሻ አካላት ብዙ ናቸው። ሰላምና አንድነት እንዲመጣ የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው። በሁሉም አካባቢ ያሉ የእምነት መሪዎች ለተከታዮቻቸው ሰላምንና ፍቅርን መስበክ አለባቸው። ተከታዮቻቸውም የእምነታቸውን ሕግ ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ተጽእኖ ፈጣሪ ታዋቂ ሰዎች ትርፍ ያለው ከሰላምና አንድነት እንጂ ከጦርነት አለመሆኑን ማሳወቅ ይገባቸዋል። መሪዎች የፈጣሪን ቃል በማስተጋባት የእርቁን ጉዳይ ማሳወቅ ዋና ሥራቸው ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው በሰላም ላይ የሚሠሩ ማህበራትም ትልቅ ድርሻ አላቸው። እነዚህ ሕዝቦች ዕጣ ፈንታቸው አንድ መሆኑንና በጋራ ሲኖሩ የሚያተርፉት ነገር የበዛ እንደሆነ መሥራት ነው። የትግራይ፣ አፋርና አማራ ሕዝቦች አንድ ናቸው። ጥፋቱ ሁሉም ዘንድ የደረሰ ነው። አሁን ያንን ወደኋላ ማሰብ፤ ቂምና ቁርሾ መቁጠር፣ ቁስል ማከክ ሳይሆን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር ነው። ካለፈው መጥፎ ጊዜ ይልቅ መጪውን መልካም ጊዜ ማሰብና ማለም ያተርፋል። ሁሉም ሊረዳ የሚገበው የአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልል ሕዝቦች ቅንጣት ጥፋት የላቸውም።
በወቅቱ በትግራይ ጊዜያዊ መስተዳድር በተመሠረተበት ወቅት ትግራይ ክልል ነበርኩ። በትግራይ ክልል የወደሙ መሠረተ ልማቶችንና አንድነቱን ለመመለስ የአማራ ሕዝብ የከፈለው ዋጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለአንድነቱ ብለው ብዙ ነገር ሠርተዋል። ከአማራ ክልል ከፍተኛ እርዳታ ሲመጣ ነበር። በወቅቱ የአማራ ሕዝብና አማራ ክልል መንግሥት ሲያደርጉት የነበረው ተሳትፎ በጣም የላቀ ነው። የአፋር ክልልም የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት ትልቅ ድርሻ ነው የተወጣው። አሁንም ቢሆንም የተፈጠረው ጊዜያዊ ቅራኔ መሆኑን ማወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ሕዝብ የሰላም ስምምነቱን እንዳይቀበል እየቀሰቀሱ ያሉት አካላት ምን አስልተው ነው?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- ወደ ኋላ ሄደን አንድ ነገር ላስታውስ። የቀድሞ መንግሥት ወይንም የደርግ ሥርዓትን ለመጣል የተሄደበትን መንገድ ማስታወስ ጥሩ ነው። በፍጹም የሌለ ቅስቀሳ ይደረግ ነበር። ይህ የሆነው የሕዝብን ወገንተኝት ለማግኘት ሲባል የሚነዛ ፕሮፓጋንዳ ነው። በዚህ ሂደት በ1983 ዓ.ም የደርግ ሥርዓት ወድቆ በሌላ ተተካ። በዚህ ሁኔታ ግን ሕዝብ ለሕዝብ ቅራኔ አልነበረም። ይልቁንም እጅና ጓንት ሆነው ነው ሲሠሩ የነበሩት። አሁን ያለው ሁኔታም ያው ነው።
በእርግጥ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በተለያየ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን ከሕዝብ የማናከስ ሥራዎች በስፋት ሲሠራ ነበር። እኛ ይህ ነገር ተገቢ አይደለም ብንል ሰሚ አላገኘንም። በአማራ በኩልም የተጋነነ ባይሆንም በተመሳሳይ ሁኔታ ተገቢ ያልሆኑ የቃላት መወራወር ነበር። ይህ ሁሉ ሆኖም ጉዳዩ የሕዝብ መሆን አልቻለም። አሁንም የሰላም ስምምነቱን ወደ መሬት ለማውረድ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራውን ማጠናከር ይገባል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባህርዳር አንድ ስብሰባ ላይ ነበርኩ። አንድ የሃይማኖት አባት ያሉትን ማስታወስ እፈልጋለሁ። ‹‹የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው የጦርነት ጉሰማና ጥይት ማቀበል ሳይሆን የሚበላው ዳቦ፣ የሚማርበት ትምህርት ቤት፣ ንጹህ አየርና ሰላማዊ ሕይወት ነው›› ብለው ሲከራከሩና ለሕዝብ የወገነ ንግግር ሲያደርጉ ሰምቼ ነበር። ይህ አስተሳሰብ በርካቶችም ዘንድ ያለ ሲሆን በትግራይ በኩልም በተመሳሳይ ያለው ይኸው ነው። ኅብረተሰቡ የሚፈልገው ሰላም ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው በሁለቱም ወገን ያለው ሰላም ፈላጊ ሕዝብ መሆኑን ነው።
ሌላ ትልቅ ማሳያ መጥቀስ ይገባል። በጦርነቱ ወቅት ሆነ በአሁኑ ሰዓት በርካታ የአማራ፣ አፋርና፣ ትግራይ ሕዝቦች በጋራ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖራሉ። ይጋባሉ፣ አብረው ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ማህበራዊ ሕይወት ይጋራሉ። ቀድሞ ከነበረው የተለየ ነገር የለም። ይህ የሆነው ግጭቱ የሕዝብ ባለመሆኑ ነው። በየጨዋታው መሃል ሲነሳ ይህ ጦርነት ጥቂቶች ያመጡት እንጂ የአንድ አገር ሕዝቦች እንዴት ይጣላሉ ብለው በቁጭት ሲያወሩ ነው የምንሰማው።
ሦስቱም ሕዝቦች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸውና ዳር ድንበር በመጠበቅ አንድነቷን ያስቀጠሉ ናቸው። ከትግራይ የመጡ ሰዎች ሲያወሩ የምንሰማው የግለሰቦች የግል ጥቅም፤ ማስከበርና የስልጣን መደላደል ለማስከበር የተደረገ ጦርነት እንጂ የውጭ ወራሪ አልመጣብንም፣ ይህ ፈጽሞ መሆን የሌለበት ነው ብለው ሲኮንኑ ነው የምንሰማው። በዚህም አጠቃላይ መረዳት የሚቻለው በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ሕዝቡ ጦርነቱ መጀመር የሌለበት ጥፋት እንዲሁም ሕዝባዊ ቅርፅ የሌለው መሆኑ ነው።
ከሃያ ዓመት በፊት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ጦርነት ተካሂዶም ሕዝብ ለሕዝብ ይገናኝ ነበር። ሌላው ቀርቶ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ። ሌሊት ጭምር እየተገናኙ የጋብቻ ሁኔታ ይፈጸም ነበር በወሰን አካባቢ። ከ20 ዓመት በላይ በሁለቱም አገራት መካከል ድንበር ተዘግቶም ቢሆን ሕዝብ ከሕዝብ ይገናኝ የነበረው ግጭቱ ሕዝባዊ ሳይሆን የፖለቲከኞች ፍላጎት በመሆኑ ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኤርትራ አቅንተው ሰላም ከወረደ በኋላ ድንበር አካባቢ ያሉ ሰዎች በተለይም ዛላምበሳ ግንባር ላይ ሕዝብ ለሕዝብ ሲገናኝ የነበረውን ስሜት ማስታወስ ብቻ በቂ ነው። ይህ መቼም የማንረሳው ነው። ያ ሁሉ ጦርነት ተካሂዶ ቁርሾ ቀርቶ ሰላም የወረደበት ነው። ከዚህም በግልጽ መረዳት የሚቻለው ጦርነቱ ሕዝብ ለሕዝብ አለመሆኑን ነው።
ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ያለውንም ከፍተኛ መሥዕዋነት ተከፍሎ ነው አገር የፀናቸው። እኔ በቦታው ስለነበርኩ በደንብ አውቀዋለሁ። በኢትዮጵያ በኩል 70ሺ ሰዎች ሞተዋል። በኤርትራ በኩል ከዚህ በላይ ነው ዋጋ የተከፈለው። ግን በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም ሕዝብን ከሕዝብ መነጠል አልተቻለም።
ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያም ወደ ኤርትራ ሲጎርፉ ነበር። ስለዚህ አሁንም መረዳት የሚገባን ሕዝብ ከሕዝብ አለመጣላቱን ነው። በመሆኑም ከአማራ ወደ ትግራይ፤ ከትግራይ ወደ አማራ መሄድ ይቀጥላል። ወደ አፋርም ያለው በተመሳሳይ ሁኔታ። ብዙ ጥረት ቢደረግም ግጭቱን ሕዝባዊ ማድረግ ያልተቻለውም ለዚህ ነው። ነገር ግን በጦርነት ወቅት ችግሮች ተፈጥረዋል። ይህ ድሮም የነበረ አሁንም ያለ ነው።
ሌላው መረዳት የሚገባን የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ከሌላው ክልል ወታደሮች ወይንም የፀጥታ አካላት አንዱ ለሌላው ጠላት አይደሉም። አንዱ ከሌላው በደም የተሳሰረ ነው። ስለዚህ የትግራይ ወጣት ከማንም አይጣላም። ከእናቱ፣ ከአባቱ፣ ከወንድምና እህቱ ሊጣላ ነው? አይጣሉም። ይልቁንም በኢትዮ ኤርትራ እንዳየነወ ሁሉ በሕዝቡ መካከል ሰላምና ይቅርታ ይሰፍናል።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የምናስተውለው ነገር አለ። በውጭ ያሉ ፅንፈኛ ዳያስፖራዎች በሰላም ስምምነቱ ላይ ተቃውሞ እያነሱ ነው። ይህ ለትግራይ ሕዝብ አስበው ነው?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- በመገናኘ ብዙኃን የምከታተለው ብዙ ጉዳይ አለ። በመጀመሪያ በትግራይ ክልል የተካሄደው ጦርነት በርካቶችን ለሕይወት መስዕዋት የዳረገ ነው። ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበትን ንብረትም አውድሟል። በአካል ጉዳት ደረጃም እጅግ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ መሆኑ ይታወቃል። በሥነ- ልቦናም የፈጠረው ጫና እጅግ የከፋ ነው። በርካታ ዜጎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በጦርነቱ የተነሳ የምግብ እጥረት የተከሰተባቸው አካባቢዎች አሉ። በመሠረተ ልማቶችም ላይ የደረሰው ጉዳት የመሠረታዊ ሁኔታዎችን አዛብቷል። ይህ ችግር በትግራይ ብቻ ሳይሆን የጦርነት ቀጣና በነበሩ አማራ እና አፋር ክልሎችም የተስተዋለ ነው። በእሳት ላይ እሳት የሆነ ነገር ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ የመድኃኒት አቅርቦት የለም። ስለዚህ እነዚህ አካላት የሠላም ሂደቱን የተቃወሙበት የራሳቸው ምክንያት አላቸው። ዋናው ምክንያታቸው በአገር ላይ ሰላም እንዳይሰፍን ነው። ሁለተኛ የሚያተርፉት ከሰላም ሳይሆን ከግጭት በመሆኑ ነው። እነሱ የእነሱ ልጆች አይሞቱም ፣ አይቸገሩም እነሱ ሰላም በሚነፍስበት አየር ላይ ሆነው ነው እሳት የሚያቀጣጥሉት። ይሄንን የትግራይ ሕዝብ ሊያውቅና ሊነቃ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ሰላም አያስፈልግም፤ ጦርነቱ ይቀጥል ብለው ሰልፍ ማድረጋቸውና መቃወማቸው ምክንያቱ ምንድን ነው ?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- እንዳልኩህ ነው፤ እነዚህ አካላት ይህ ጦርነት ከቆመ ቢዝነሳቸው ይቆማል። ጠዋትና ማታ ያልተፈጠረውን እየጻፉ እና ሰልፍ እየወጡ በሕዝብ ይነግዱበታል። በርቀት ሆነው በጦርነት በሚማቅቅ ሕዝብ ላይ ቢዝነስ ይሠራሉ። እነርሱ እያሰቡ ያሉት በዩቱብ እና በመሰል መንገድ የሚያገኙትን ገንዘብ ብቻ ነው። ይህም በመሆኑ የሰላም ሂደቱ ምንድን ነው ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ ትክክል አይደለም ብሎ መቃወም ይጠቅማቸዋል። በአጠቃላይ ይህን የሚያደርጉት ለጥቅማቸው ብቻ ነው። ከዚህ በተረፈ ሕዝብን ያማከለ ሥራ የመሠራት ፍላጎት የላቸውም። ለሕዝብ ሰላም ለአገር አንድነት የሚያስቡም አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- ለወለዳቸውና ላሳደጋቸው የትግራይ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ለምን አይገዳቸውም?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- አሁንም ትንሽ ወደ ኋላ መለስ ብለን በታሪክ የሆነው እንመለከት። የደርግ ሥርዓትን ለመጣል ተብሎ እና ለትጥቅ ትግሉ ብዙ ወጣት መሥዕዋት ሆኗል። በትንሹ ከትግራይ 60ሺ ሰዎችን ገብሯል። 100ሺ የሚሆኑት አካል ጉዳተኛ ሆነው ቀርተዋል። ይህ የተለመደ ሆኖ ቀጥሏል።
በዚህ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ምንም የተጠቀመው ነገር የለም። በዚህም የተነሳ በየጊዜው ሲጠይቅ ቆይቷል። ጥቂት አመራሮች ብቻ ሲጠቀሙ፣ ሕዝቡ የበይ ተመልካች ሆኖ ነው የኖረው፤ ግን ጥያቄውን አላቋረጠም። በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የነበረው ማስታወስ ጥሩ ነው። በዚያ ወቅትም እነዚህ ውጭ ያሉት አካላት ዳንኪራ ሲመቱ ነበር። ታዲያ አሁንም ያለው ይህ ነው። ይህን በማስተባበርና በመምራት ደግሞ የሚሠሩ አሉ። የሚያገኙት ጥቅም ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ሥም የተመሠረቱ የልማት ድርጅቶችና ከመሳሰሉት እየተደጎሙ ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ በዚህ ሁሉ ፅንፈኛ ዳያስፖራ ፍላጎትና የውጭ ጣልቃገብነት እያለ ግን ሕወሓት ሰላም መንገድ ይሻል ማለቱ ከምን የመነጨ ነው?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡– አሁን ያለውን ሰላም ለመቀበል ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ተገዶ ነው የሚል እምነት አለኝ። በተግባርም እየታየ ያለው ይህ ነው። በጦርነቱ ያልተፈለገ መሥዕዋት ተከፍሏል። በዚህም የተነሳ የሕወሓት አመራሮች እታች ድረስ ወርደው ሕዝብ ሲያወያዩ ነበር። ልጆቻችን ሕክምና አጥተው በጨው እያጠብን ነው ብሏል ሕዝቡ። ሕክምና የለም፣ ምግብ የለም፣ መሠረተ ልማት የለም፣ ብለው ጥያቄ እያበዙበት ነው። የዚህ ጦርነት መጨረሻው የት ነው ብለው አመራሩን በየቦታው ሲጠይቁት ነበር። የሕዝቡ የመረረ ጥያቄ ለሰላሙ መንገድ አስተዋጽኦ አድርጓል።
አሁን ደግሞ ሌላ ፋሽን ይዘው ብቅ ብለዋል። እየተደራደረ ያለው ሕወሓት እንጂ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት አይደለም በማለት እነዚህ ጽፈኞች ሌለ ሴራ ጀምረዋል። በዚህ ላይ መንግሠት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ባለድርሻ አካላት መረባረብ አለባቸው። ስለጉዳዩ በሚገባ ለሕዝቡ ማስረፅ ተገቢ ነው። ሰራዊት እንደ ሰራዊት ወደ ትግራይ ሲሄድ በተጠና እና በኃላፊነት የተሳካ ሥራ መሥራት አለበት። በዚህ መንገድ ከተሄደ ጦርነት የመረረው የትግራይ ሕዝብ ደስተኛ ሆኖ ነው የሚቀበለው። በተደጋጋሚ ጦርነቶች የትግራይ ወጣት ረግፏል። ወጣት ብቻ ሳይሆን ለአቅመ ጦርነት ያልደረሱ ሕፃናትና ዕድሜያቸው የገፋ አዛውንቶችም ለዚህ የከፋ ችግር ተጋልጠዋል። በዚህም ብዙ አካል መጉደልም ደርሷል፤ ሕዝቡም መሮታል። ሆኖም በዚህ ላይ ውዥብር እንዳይፈጠር ከፍተኛ ትጋት የሚጠይቅ ሥራ መኖሩን ማወቅ ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ ወታደር ልጠይቆዎት። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም የጦር መሳሪያ ቢፈቱ ችግር አለው?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- በሥምምነቱ አንድ ያስደሰተኝ ነገር ቢኖር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መተግበር አለበት የሚለው መግባቱ ትክክለኛ መርህ ነው። በኢትዮጵያ አንድ መከላከያ ሰራዊት ብቻ መኖር አለበት ይላል። ይህን ሕግ ሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 87 በዝርዝር አስቀምጦታል። ስለዚህ ሕግ የማስከበር ሥራው አንዱ መሆን አለበት። ሌላው ዳር ድንበር ማስከበርና መጠበቅ ኃላፊነት ያለበት የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት መሆኑን አስቀምጧል። ይህም በሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ላይ በዝርዝር የተቀመጠ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ሌላ መከላከያ ሰራዊት መኖር የለበትም። ከዚህ በመነሳት የምንረዳው በክልሎች የመከላከያ ሰራዊት መገንባት መብትና ስልጣን የላቸውም።
ክልሎች የሚፈቀድላቸው መደበኛ ወይንም ሕዝባዊ ፖሊስ ነው። የትግራይ ክልልም ከሌሎች ክልሎች የተለየ መሆን አይችልም፤ ሕጉም የሚለው ይህንን ነው። ሰላምም እንዲሰፍን ከተፈለገ ሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊ መሆን አለበት። ብዙ ሕይወት የተገበረበት፣ በርሃብ ሕዝብ የተቀጣበት፣ መሠረት ልማት የተቋረጠበት፣ ንብረት የወደመበት፤ አካል መጉደል የደረሰበት ሕገ መንግሥቱ ባለመከበሩ ነው። በሥምምነቱም የአገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ ይግባ የተባለው ሕገ መንግሥታዊ ስለሆነም ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ በሌሎች ክልሎችም መሰል ድርጊት እንዳይከሰት ምን መደረግ አለበት?
ኮሎኔል ፍሰሐ፡- ወታደር ስለነበርኩ፤ አሁን ደግሞ ወደ ፖለቲካው ስለገባሁ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሕገ መንግሥት የሚፃረር ሁኔታና አደረጃጀት መኖር የለበትም። የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው። ተግባራዊ አናደርግም የሚሉ ከሆነ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት። ፓርቲዎች በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት እና በምርጫ ብቻ አሸንፈው ወደ ስልጣን መምጣት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን ደስ ሲላቸው በሰላማዊ መንገድ ሲሻቸው ደግሞ በጥይት እንፋለምና ስልጣን እንያዝ ማለት አያስኬድም።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለት እግር ስላላቸው አንዴ ሰላማዊ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተጻራሪ መቆም አይገባም። መንግሥት ሕግን የማስከበር ኃላፊነት አለበት። ለአገር ሰላምና ዕድገት ሕዝብም የሚጠበቅበትን መወጣት አለበት። መንግሥት ምን አደረገልን ብቻ ሳይሆን እኛ ምን አደረግን ብሎ ራስን መጠየቅ ይገባል። ለመንግሥት ብቻ የሚወረወር ነገር መቆም አለበት። ስለዚህ በቀጣይ እንደ አገር መሰል ድርጊቶች እንዳይከሰቱ በጋራ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ኮሎኔልፍሰሐ፡- እኔም ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ኀዳር 1/ 2015 ዓ.ም