የዛሬው የ‹‹ፍረዱኝ አምድ›› ዘገባችን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ገርጂ እየተባለ ወደሚጠራው አካባቢ ይወስደናል ።
«ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ስንገለገልበት የቆየነውን የአረንጓዴ ስፍራ (ግሪን ኤሪያ) በቦሌ ክፍለ ከተማ እና በወረዳ 14 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተባባሪነት በሕገወጥ ወራሪዎች እንዲወሰድ ተደርጓል ። በወረዳው እና በክፍለ ከተማው የመሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ተባባሪነት የተፈጸመብንን በደል የኢትዮጵያ ሕዝብ ተመልክቶ ይፍረደን» ሲሉ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የማዕድን ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነዋሪዎች ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።
የዝግጅት ክፍሉም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ የደረሰበትን የክፍል አንድ ዘገባውን እንደሚከተለው ለንባብ አብቅቶታል።
ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ አንደበት
ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታውን ያቀረቡት የማኅበሩ ጸሐፊ አቶ ፈቃዱ በቀለ እና የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ዘውዱ ንጉሴ ናቸው ።
እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ ፤ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ገርጂ አካባቢ እየኖሩ ነው። ይሄ ቦታ በ1983 ዓ.ም በማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ስም ተደራጅተው የተሰጣቸው ነው። ቦታው እስካሁንም ማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር እየተባለ ይጠራል።
በ1983 ዓ.ም መንግሥት ለማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር የመኖሪያ ቤት ቦታ ሲሰጥ ከመኖሪያ ቤቱ በተጨማሪ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚገለገልበት የአረንጓዴ ስፍራ (ግሪን ኤርያ) ጨምሮ ነበር። ይህንን የአረንጓዴ ስፍራ (ግሪን ኤርያ) የማኅበሩ አባላት ለ32 ዓመታት እያለሙ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 2015 ዓ.ም የመስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንታት በነበሩት ቀናት ላይ ለሰፋራቸው አዲስ የሆኑ እና ማንነታቸውን የማያውቋቸው የተለያዩ ሰዎች በአረንጓዴ ስፍራነት ወደ ተከለለው ቦታ አብዝተው መመላለስ ጀመሩ ። በዚህም ግራ የተጋቡት የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ለምን ወደ ቦታው እንደሚመላለሱ ይጠይቋቸዋል። ሰዎችም ቦታውን ሊገዙ መምጣታቸውን ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎ የማኅበር ነዋሪዎች «ሻጩ ማን ነው ?» ብለው ቦታውን ለመግዛት የመጡ ሰዎችን ይጠይቃሉ። ገዥዎችም አቶ ብርሃኑ ደገፋ የሚባሉ ሰው መሆናቸውን ተናግረው በአረንጓዴ ቦታነት በተከለለው ቦታ ላይ የተሠራውን ካርታም ያሳያሉ።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ነዋሪዎችም የአዩትን ማመን ከብዷቸው ሳይውሉ ሳያድሩ ወደ ወረዳ 14 የከተማ ውበት እና የአረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት በመሄድ ስለተፈጠረው ነገር ያሳወቃሉ ። ጽሕፈት ቤቱም ስለጉዳዩ ምንም እንደማያውቅ ይነግራቸዋል።
በመሆኑም ጉዳዩን ለማሳወቅ ወደ ወረዳው አስተዳደር ያመራሉ። የወረዳው አስተዳደርም ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የለኝም ብሎ ይመልሳል። ይህ በእንዲህ እያለ ጉዳዩ መፍትሔ ማግኘት ስላለበት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ አመሩ።
የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደርና ልማት ጽሕፈት ቤት ፣ የመብት ፈጠራ እና ሌሎች የመሬትን ጉዳይ ለሚመለከቱ ቢሮዎችን በሙሉ ቅሬታቸውን በማመልከቻ አሳወቁ። ከላይ የተጠቀሱት የመሬትን ጉዳይ የሚመለከቱት ጽሕፈት ቤቶች የአቤቱታ አቅራቢዎች ማመልከቻዎች ከተመለከቱ በኋላ ጉዳዩን እንዲጣራ የመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ለተባለው ክፍል መሩት ።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር አባላት ጉዳዩን እንዲጣራ ኃላፊነት የተሰጠው የመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ የተባለው ክፍል የደረሰበት ውሳኔ ለማወቅ ወደ ቢሮው ያቀናሉ። ይሁን እንጂ የጠበቃቸው ውሳኔ አልነበረም። ስለአረንጓዴ ስፍራው (ግሪን ኤርያው) የማኅበሩ አባላት በእጃቸው ላይ ያሉ ማስረጃዎችን በሙሉ እንዲያመጡ ትዕዛዝ እንጂ። ይህን ተከትሎ የማዕድን ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነዋሪዎች አረንጓዴ ስፍራው (ግሪን ኤሪያው) የእነሱ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ከ23 በላይ የሰነድ ማስረጃዎችን መሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ጽሕፈት ቤት አቀረቡ።
ሆኖም ግን ጉዳዩን እንዲያጣራ ኃላፊነት የተሰጠው መሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ሰነዶችን እንዲያቀርቡለት ከጠየቀ በኋላ የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ማኅበር ያቀረቡለትን ሰነዶች አልቀበልም አለ።
የመሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ክፍልም የማዕድን ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ተወካዮች የወሰዷቸውን ሰነዶች ተቀበሉን አልቀበልም በሚል ክርክር ይጀመራል ።
ተወካዮች እየተከራከሩ ሳለ በተመሳሳይ ሰዓት የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ማኅበር ተወካዮች ከሚኖሩበት ቦታ ወደ እጅ ስልካቸው የስልክ ጥሪ ደረሳቸው። የስልክ ጥሪውም የወረዳው መሬት ልማት ኃላፊ የቦታውን ካርታ ለተሰራለት ሰው አስረክባለሁ ብሎ መጥቶ ከነዋሪው ጋር ጭቅጭቅ መፈጠሩን የሚያሳውቅ ነበር ።
ወዲያውኑም ተወካዮች በእጃቸው የያዟቸውን ሰነዶች ለክፍለ ከተማው መሬት ማስተላለፍ ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ሳይሰጡ ወደ ሰፈራቸው ይመለሳሉ። የወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ኃላፊ ለአረንጓዴ ስፍራ የታጠረውን ቦታ ለወራሪዎች አስረክባለሁ ብሎ ከሰፈር ሰዎች ጋር ሲጨቃጨቁ ይደርሳሉ።
ይህን ተከትሎ «በምን አግባብ ነው ቦታውን የምታስረክቡት? ከዚህ በፊት እናንተ ቢሮ መጥተን ‹ ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የለንም› ስትሉን አልነበረም ወይ? እንዴት ጉዳዩን ለክፍለ ከተማው ለማሳወቅ በሄድንበት ያለማኅበሩ አባላት እውቅና መሬቱን ለወራሪዎች ለማስረከብ መጣችሁ? »ሲሉ የወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ኃላፊ ይጠይቃሉ ።
አከታትለውም በቦታው ስለተፈጠረው ነገር የአካባቢው ማኅበረሰብ ለክፍለ ከተማው ጥያቄ አቅርቦ መልስ በሚጠባበቅበት በዚህ ሰዓት ወረዳው ለምን መሬቱን ለወራሪዎች እናስረክባለን ይላል? ለማንስ ነው የምታስረክቡት? በማለት የወረዳውን መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይጠይቃሉ። የወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊም ቦታውን የሚያስረክበውም ቦታውን ተሰጠው ለተባለው ሰው ሳይሆን በውክልና ለመጣ ሰው መሆኑን ይነግራቸዋል።
ይህን ተከትሎ የማዕድን ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነዋሪዎችም በአዲሱ መመሪያ መሠረት የመሬት ጉዳይ በውክልና እንደማይስተናገድ ያዝዛል። ስለዚህ መመሪያ ጥሳችሁ ስለምን በወኪል አማካኝነት መሬቱን ታስረክባላችሁ? ቦታው ተሰጥቶታል የምትሉት ሰው 400 ካሬ ሜትር ነው ። የማህበሩ ግሪን ኤሪያ ስፋት ደግሞ 700 ካሬ ሜትር ነው። እንዴት አድርጋችሁ ነው በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መሬቱን ልትሰጡ እና ልትሸነሽኑት የምትችሉት? መሬቱን ማስረከብ ያለበት ክፍለ ከተማው እንጂ ወረዳው ነው ወይ? ጉዳዩ መስተናገድ አለበት ሕግ እና ሥርዓቱን ጠብቆ እንጂ እንዴት ሕግና ሥርዓትን ባልተከተለ አግባብ መሬቱን ልትወስዱ ትመጣላችሁ? በማለት ጥያቄ ያነሳሉ።
መንግሥት ቦታውን ለልማት ከፈለገው እና ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ከመጣ አይደለም ግሪን ኤሪያውን መኖሪያ ቤታቸውም ቢሆን አፍርሶ መውሰድ እንደሚችል፤ ነገር ግን ሕግ እና ሥርዓትን ባልተከተለ አግባብ ሲመጣ ግን የሃገርን ሕልውና የሚጻረር በመሆኑ የትኛውንም አይነት ውሳኔ እንደማይቀበሉ ለወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ያስረዳሉ።
ይህ በእንዲህ እያለ በነዋሪዎቹ እና በወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ኃላፊ መካከል አለመግባባቱ በጣም ይሰፋና ወደ ጭቅጭቅ ያመራሉ። የተፈጠረውን ጭቅጭቅ ለማብረድም ፖሊስ ጣልቃ ይገባል።
ፖሊስ የተፈጠረውን ችግር ለማብረድ በገባበት ወቅት አቤቱታ አቅራቢዎቹ መሬቱን አዲስ ለተመራው ሰው እንድታስረክቡ የታዘዘበት ደብዳቤ አላችሁ ወይ ? አሳዩን በማለት ጥያቄ ያነሳሉ።
የወረዳው መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት
ቤት ቦታውን አስረክባለሁ የሚለው የቤት ኪራይ እና ቦታ ግብር አወሳሰን የሚል ወረቀት ይዞ መሆኑን ይነግራቸዋል። በዚህ አይነት በነዋሪዎች እና መሬቱን ለማስረከብ ከመጣው ሰው ጋር ሌላ አምባ ጓሮ ተፈጠረ። ፖሊስም ጣልቃ ገብቶ የወረዳው መሬት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊውን ቦታውን አስረክብ ስለመባሉ የሚያሳይ ደብዳቤ እንዲያመጣ ጠየቀ። ከሁለት ቀን በኋላም ከክፍለ ከተማ መሬት ልማት ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ እንዲያመጣ ነገራቸው ።
ከሁለት ቀን በኋላ ደብዳቤ አመጣለሁ ብሎ የነበረው የወረዳው መሬት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊም በተባለው ቀን ደብዳቤ ሳያመጣ ቀረ። ይልቁንም ‹‹የቦታው (ግሪን ኤሪያው) ባለቤት ነን የምትሉ ከሆነ በቦታው ላይ ያሏችሁን ማስረጃዎች ይዛችሁ በሁለት ቀን ወረዳው ጽሕፈት ቤት እንድትመጡ ›› የሚል ከግሪን ኤሪያው አጥር በር ላይ ማሳሰቢያ ለጥፎ ሄደ ። ማሳሰቢያውን ለነዋሪዎቹ በቀጥታ የተሰጠ አልነበረም ።
ይህን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎችም በአረንጓዴ ስፍራው ላይ መብራት እና ውሃ ያስገቡበትን፣ አረንጓዴ ስፍራውን ( ግሪን ኤሪያውን) ለማልማት እንቅስቃሴ ያደረጉባቸውን እና በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ሃሳብ አመንጭነት አረንጓዴ አሻራ በሃገር ደረጃ መጀመር ጋር ተያይዞ ምን ያህሉ አረንጓዴ ስፍራውን (ግሪን ኤሪያውን) ለአረንጓዴ ልማት መዋል አለበት፣ ምን ያህሉ ደግሞ ለሌሎች ተግባራት መዋል አለበት የሚል ዲዛይን በማሠራት የዲዛይኑን ኮፒ እና ሌሎች አሉ የሚባሉትን ሰነዶች ለወረዳው ያቀርባሉ።
እንደአቤቱታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፤በአጋጣሚ የሚኖሩበት አካባቢ ዙሪያውን ካባ እየተባለ የሚጠራው ድንጋይ እየወጣ የሚሸጥበት ነው። የመኖሪያ ሰፈሩ በካባ አውጭዎች እንደ ደሴት ሆኗል።
የካባ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የመኖሪያ ሰፈሩ ከስድስት በላይ መውጫ እና መግቢያ ነበሩት ። አሁን ላይ የካባ ድንጋይ በሚያወጡ ሰዎች ምክንያት መውጫ መግቢያው ተበልቶ አሁን ብቸኛ መውጫ መግቢያ የቀረው የግሪን ኤሪያው የሚገኝበት ብቻ ነው ። አሁን ይህ ግሪን ኤሪያ ቢወሰድ የሰፈሩ ሰዎች በሙሉ መውጫ አይኖራቸውም ።
በሰፈሩ ደስታ እና ኃዘን ሲያጋጥምም ድንኳን ሲተከል እንኳን ለመግባት እና ለመውጣት የሚገጥማቸው ፈተና ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ። ስለሆነም የግሪን ኤሪያው ቦታ የሰፈሩ ሰዎች መተንፈሻ መሆኗን አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።
ከአቤቱታ አቅራቢዎች የተገኙ ሰነዶች ምን ይላሉ?
ሰነድ አንድ፡- የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት የሥራ ማኅበር በቀን 6/7/1996 ዓ.ም በቁጥር ማኤቁ4ሥማ/96 ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የምስራቅ ዲስትሪክት ቁጥር አራት ጽሕፈት ቤት በተጻፈ ደብዳቤ እንደተመላከተው የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት የሥራ ማኅበር በኅብረት የሚጠቀሙበትን መናፈሻ ቦታ (ግሪን ኤሪያ) አገልግሎት ለማሳደግ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ፤ ነገር ግን ሰፈሩ አዲስ በመሆኑ የተነሳ የውስጥ ለውስጥ መብራት እና ሌሎች አገልግሎቶች ስለሌለው በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች መከሰታቸውን ፤ ስለሆነም በሰፈሩ ያለውን የጸጥታ ችግር ለማስወገድ ማኅበሩ በጋራ በሚጠቀምበት መናፈሻ ቦታ (ግሪን ኤርያ) ላይ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ እንዲገባላቸው እና በቂ የመንገድ መብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይጠይቃሉ።
ማኅበሩ ያነሳውን ጥያቄ ተከትሎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በውል ቁጥር 483447 እና በደንበኛ ስም ማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ነዋሪዎች ስም 220 ቮልት ቆጣሪ በ22/07/1996 ዓ.ም እንደተሰጣቸው ሰነዶች ያመለክታሉ ።
ሰነድ ሁለት፡- በቀን 5/13/1995 ዓ.ም ቁጥር ማኢቁ4ቤሥማ13/95 በማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት ማኅበር ስም በተጻፈ ደብዳቤ የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን የምሥራቅ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለግሪን ኤሪያው ውሃ እንዲገባላቸው መጠየቃቸውን እና በጥያቄአቸውም መሠረትም የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ምሥራቅ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በማእድን እና ኢነርጂ የመኖሪያ ቤት ስም 2821185 ቁጥር የተመዘገበ የውሃ ቆጣሪ በሚያዚያ ወር 1997 ዓ.ም እንደሰጣቸው በሰነዶቹ ላይ ያሳያሉ።
ሰነድ ሶስት፡- በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በቀን 27/03/2011 ዓ.ም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ/14/ 1/466/2011 ለማዕድን እና ኢነርጅ ቁጥር አራት ማኅበር አስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ የሚያሳውቅ ደብዳቤ ተጽፏል።
ለዚህ ደብዳቤም መነሻ ምክንያትም የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት በቀን 21/3/2011 ዓ.ም በቁጥር ቦ/ክ/ከ/በ/ባ/1572/11 ለወረዳ 14 በጻፈው ደብዳቤ በሕገወጥ መልኩ የተወረሩ የአረንጓዴ ቦታዎችን ለታለመላቸው አገልግሎት እንዲመለሱ ማስጠንቀቁን ተከትሎ ነበር።
ይህን ደብዳቤ ተከትሎ በወረዳ 14 ከሚገኙ የአረንጓዴ ቦታዎችን መካከል በማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ስር እየተዳደረ የሚገኘው የአረንጓዴ ቦታ መሆኑን ጠቅሶ ይህ ቦታ ከታለመለት አግባብ ውጭ ለእድር ቤት ፣ ለመኪና ማሳደሪያ፣ ለሸማች ማኅበር እንዲሁም፣ ለሌሎች ተግባራት እየዋለ በመሆኑ የግሪን ኤሪያው ለታለመለት ሥራ የማይውል ከሆነ እርምጃ እንደሚወሰድ የሚያስጠነቅቅ ነው።
ሰነድ አራት፡- በቦሌ ከፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ/14/0.3/795/2014 በቀን 02/10/2014 ለማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት የማኅበር በተጻፈ ደብዳቤ እንደተመላከተው በወረዳ 14 በማዕድን ቁጥር አራት ማኅበር አረንጓዴ ቦታ ውስጥ ያሉ መኪኖች ለረጅም ጊዜ የቆሙ መሆናቸው ይጠቅሳል ። በመሆኑም በማኅበሩ ግቢ ውስጥ ችግኝ ለመትከል ስለተፈለገ እና መኪኖቹም የማኅበሩን ውበት ስላበላሹ ይህ ደብዳቤ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአምስት ቀናት ውስጥ እስከ 7/10/14 ዓ.ም ድረስ በአስቸኳይ እንድታነሱ እያስጠነቀቀ የማያነሱ ከሆነ ጽሕፈት ቤቱ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስዱ መሆኑን የሚጠቁም ነው ።
ሰነድ አምስት፡- በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት በቁጥር ቦ/ክ/ከ/ወ/14/0.3/470/2013 በቀን 27 02/2013 ዓ.ም ለማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር በተጻፈ ደብዳቤ እንደተመላከተው የወረዳው አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት በማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት በሚገኘው አረንጓዴ ስፍራ የተተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከቡ የሚጠይቅ ነው ።
የወረዳው መሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ምላሽ
ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከሆኑት አቶ ፈይሳ ሙሉጌታ ጋር ተገናኝተን በማዕድንና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ስር የሚገኘውን የአረንጓዴ ስፍራ ለሦስት አስርተ ዓመታት በአረንጓዴ ስፍራነት ሲጠቀሙበት መቆየታቸውን እና ቦታው የእነሱ ስለመሆኑ የማኅበሩ አባላት ይናገራሉ ። ስለዚህ ምን ይላሉ ? የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር ።
እሳቸውም‹‹ማኅበሩ ቦታውን ለ30 ወይም 40 ዓመታት በአረንጓዴ ስፍራነት ሊጠቀሙት ይችላሉ። ነገር ግን በመመሪያው መሠረት ለበርካታ ዓመታት የአረንጓዴ ስፍራውን ተጠቀሙ ማለት በቦታው ላይ ባለመብት ይሆናሉ ማለት አይደለም›› ሲሉ ገልጸውልናል።
የክፍለ ከተማው መሬት አስተዳደር ከዚህ ቦታ ጋር ተያይዞ መረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን የሚናገሩት ኃላፊው፤ የማዕድንና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ይህንን ቦታ እንዲጠቀም የፈቀደ ማንም መንግሥታዊ ተቋም አለመኖሩን ይገልጻሉ። መንግሥትን ሳይጠይቁ ውሃ እና መብራት ስላስገቡም ቦታው የማኅበሩ ነው ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ። ቦታው በጂአይ ኤስ እንደማይታይም አመላክተዋል። በጂአይ ኤስ የማይታይ ቦታም ሕጋዊነት እንደሌለው ይናገራሉ ።
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ማኅበሩ ከከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር ተነጋግረው ለበርካታ ዓመታት በአረንጓዴ ስፍራ ቢያለሙትም ጂአይ ኤስ እስከሌለው ድረስ ሕጋዊ አይደለም ብለውኛል ። ይህን የሚል መመሪያ አለ ወይ? መመሪያውን ቁጥር ጠቅሰው ይንገሩኝ ። ጥያቄውን ተከትሎ አቶ ፈይሳ የትኛው መመሪያው እንደሆነ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ነገር ግን በከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት የሚተዳደር ካርታ እስከሌላቸው ድረስ ሕጋዊ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ከከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር ውዝግብ ያስነሳውን ቦታ እንዴት በጋራ ማልማት እንዳለባቸው ለበርካታ ዓመታት ሲጻጻፉ እና ሲያለሙ እንደነበር ይታወቃል። ሕገ ወጥ ከሆኑ የእናንተ መሥሪያ ቤት እስከዛሬ ለምን አላስቆመም ? በዚህ ዓመት(በ2015ዓ.ም) ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው መሬቱ በአረንጓዴ ስፍራ አልተካተተም ልትሉ የቻላችሁት? ሲል የዝግጅት ክፍል የጠየቃቸው ኃላፊው፤ ‹‹የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሕጋዊ እንዳልሆነ ነግሯቸው ነበር›› ሲሉ መለሱ። አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የጠየቃችሁበትን ደብዳቤ ልታሳዩን ትችላለችሁ ? ሲል ኃላፊውን ጠየቀ ። ኃላፊውም ከዚህ በፊት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዳልሰጡ ፤ ነገር ግን በቃል እንደነገሯቸው መለሱ። በቃል የሚሰጥ ትዕዛዝ ከሕግም ሆነ ከመመሪያ አኳያ ተቀባይነት የለውም ። ስለዚህ በደብዳቤ ያስጠነቀቃችሁበት ካለ ልታሳዩን ትችላችሁ? ሲል ደግሞ ጠየቀ። ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ምላሽ መስጠት ሳይችሉ ቀሩ ።
የማዕድን እና ኢነርጂ ቁጥር አራት ማኅበር ከወረዳው እና ከክፍለ ከተማው የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር ሲጻጻፉ ቆይተዋል። ማኅበሩ ሕገ ወጥ ከሆነ ማኅበሩ ከወረዳው እና ከክፍለ ከተማው የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማትን ቢሮ ጋር ሲጻጻፍ የክፍለ ከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ማኅበሩ የሚያለማው ግሪን ኤሪያ ሕገወጥ ስለመሆኑ በደብዳቤ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ አላችሁ? ሲል ጠይቆ ነበር ፡። ሆኖም ኃላፊው ‹‹የለንም። ስለዚህ የማውቀው ነገር የለም›› የሚል መልስ ሰጥተውናል። ይህ የክፍለ ከተማው መሬት ልማት እና አስተዳደር ማስጠንቀቂያ ካልሰጠ ዛሬ ላይ ማለትም በ2015 ዓ.ም ሲለማ የኖረን ግሪን ኤሪያ ሕጋዊ አይደለም ልትሉ እንዴት ቻላችሁ? ሕገ ወጥ ከሆነ ስለምን መብራት እና ውሃ ሲገባ ዝም አላችሁ? ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው የክፍለ ከተማው መሬት ልማት እና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስቁመዋል የሚል ምላሽ ሰጡ ። ካስቆመ ያስቆመበት ደብዳቤ ያሳዩን ስንል ጠየቅን ። ሆኖም ኃላፊው ደብዳቤ አለመኖሩን ነው ያረጋገጡልን።
ከአዘጋጁ፤
ውድ አንባቢያን በማዕድንና ኢነርጂ ቁጥር አራት የመኖሪያ ቤት ማኅበር እና በወረዳ 14 እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ መካከል የተከናወኑትን የደብዳቤ ልውውጦች በመመልከት ለአለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት የአረንጓዴ ስፋራው (ግሪን ኤሪያ) የማን ነበር የሚለውን፤ ከሕግና መመሪያ አንጻር ኃላፊዎች ሥራዎቻቸውን በምን መልኩ እየተወጡ ነው የሚለውን ለአንባብያን እንተወዋለን።
በቀጣይ ለሚኖረን ዘገባ በወረዳው እና በክፍለ ከተማው የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ግለሰቦችን በማነጋገርና ሰነዶችን በማካተት ቀጣዩን ክፍል ሁለት የምናቀርብ ይሆናል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም