የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደረጉትን የፊፋ ዋና ጸሃፊ ፋትማ ሳሙራን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ዋና ጸሃፊዋ ፋትማም ስምንት መቶ የእግር ኳስ ትጥቆችን እንዳበረከቱ ተገልጿል።
የአለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ተቋም ፊፋ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ፋትማ ሳሙራ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶችን እንዳደረጉ ተጠቁሟል።
ዋና ጸሐፊዋ በስራ ጉብኝታቸው ወቅት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ተገኝተው ምልከታዎችን ያደረጉ ሲሆን፤ በመጨረሻም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጸሃፊዋን ተቀብለው እንዳነጋገሩ ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ፕሬዘዳንቷና ዋና ጸሐፊዋ በመከሩበት ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዲሁም የጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁንም ተገኝተዋል፡፡
በፕሬዘዳንቷ ጽህፈት ቤት በነበረው ውይይት ላይ ዋና ጸሃፊዋ ፋትማ ሳሙራ፣ ድርጅቱ (ፊፋ) በ90ዎቹ በተከሰተው የዓለም መንግስታት የአደረጃጀት ማስተካከያ ወቅት ለስፖርትና ለስነዜጋ የትምህርት አይነቶች የተሰጠውን አነስተኛ ግምት ለማስተካከል በትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ስፖርትን ለማስፋፋት እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያና በፊፋ መካከል ጠንካራ ግንኙነት ያለ መሆኑን ገልጸው የእግር ኳስ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ጨምሮ ለሴትና ወንድ ታዳጊ ህጻናት እየተደረገ ላለው ድጋፍ ፊፋን አመስግነዋል፡፡
ዋና ጸሃፊዋ ፋትማ በኳታር ከቀናት በኋላ በሚጀመረው የዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ የሚጠቀምበትና ስማቸው ያረፈበትን ኳስ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ማበርከታቸው ታውቋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ዋና ጸሀፊዋ ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ ከ800 በላይ የሚሆኑ ዓለም በዚህ ወቅት እየተጠቀመባቸው ያሉ የመጨረሻ ደረጃ የተለያዩ የእግር ኳስ ትጥቆችን ለኢትዮጵያ አበርክተዋል። ዋና ጸሐፊዋ ያበረከቱት የስፖርት ትጥቅ የእግር ኳስ መጫወቻ ኳስ፣ ጫማ እንዲሁም ማሊያ ያካተተ መሆኑም ታውቋል።
ሴኔጋላዊቷ የፊፋ ዋና ጸሃፊ ባለፈው ዓመትም በፊፋ ስም ለ600 ታዳጊዎች የሚሆን የእግር ኳስ ስፖርት ትጥቅ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቷም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተለያዩ ቀናት በተካሄዱ መርሃ ግብሮች በፊፋ ስም በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ ኑሮ ለሚገኙና እግር ኳስን ለሚያዘወትሩ ታዳጊ ወጣቶች ማበርከታቸው የሚታወስ ነው።
ዋና ጸሐፊዋ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜዎች በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ከአመታት በፊትም ከፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር በመሆን በካፍ የምስረታ በዓልና በጠቅላላ ጉባኤው ላይ በእንግድነት ለመገኘት አዲስ አበባ ተገኝተው ነበር።
በተለይም በዚያን ወቅት ዋና ጸሐፊዋ የፊፋ ክፍለ አህጉራዊ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ በሚቋቋምበት አግባብ ዙሪያ በወቅቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ጋር በመወያየት ጥረት አድርገዋል። በወቅቱም ፊፋ በአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ከመክፈት በተጨማሪ ተከታታይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማካሄድ ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸው አይዘነጋም።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም