ዩኒየኑ ከአስራ አምስት አገራት ያላነሱ ደንበኞች አሉት። በተለይ በማርና ቡና ታዋቂነትን ያተረፈ እና በአገር ውስጥም ቡናው የተለመደና የታወቀ ነው፤ የቤንች ማጂ ጫካ ቡና ህብረት ሥራ ዩኒየን። የዩኒየኑ የምርት ዝግጅት ሥራ ክፍል ዳይሬክተር አቶ አብዮት ዳዲ፤ ዩኒየኑ በውጪ ገበያው ላይ ተገቢውን ተሳትፎ እንዳያደርግ የተገደበበት ሁኔታ እንዳለ ይጠቁማሉ። ለእዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል አርሶ አደሩ ምርት በጥራት እንዲያቀርብ የሚያግዘውን ግብዓት ማግኘት አለመቻል አንዱ ነው ይላሉ።
በቅርቡ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ሸካ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የገበያ ተሳትፎ ላይ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች እና የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች በመከሩበት ሲምፖዚየም ላይ የተሳተፉት አቶ አብዮት፣ በምርት ላይ የሚታየውን የጥራት ችግር ለማቃለል በ2014 ዓ.ም ዩኒየኑ የጥራት ማስጠበቂያ ግብዓት ከውጪ ማስገባት መጀመሩን ይጠቅሳሉ።
የምርት ጥራት ግብአቱን በማስገባቱ ወቅት ትልልቅ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን አቶ አብዮት ይናገራሉ። የጥራት ማስጠበቂያው በሚፈለግበት ጊዜ መጥቶ ለአርሶ አደሩ እንዲዳረስ ማድረግ እንዳልተቻለም ጠቅሰው፣ ይህም አርሶ አደሩና ዩኒየኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ይላሉ። ይህ ችግር ተቃሎ የቡና ማድረቂያ እና ጥራት ማስጠበቂያ ሽቦዎች እና ሸራዎች ቀጥታ ከውጪ እንዲያስገቡ እና በጊዜ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር እና ድጋፍ ቢደረግ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያመላክታሉ።
እንደ አቶ አብዮት ገለፃ፤ አካባቢው በጣም ትልቅ የማምረት አቅም አለው። አሁንም ለሀገሪቱ በርካታ ዶላር እያስገባ ይገኛል። በ2013 ዓ.ም አካባቢው ከአንድ ሚሊየን ዶላር ያላነሰ የውጭ ምንዛሬ ማስገባት ችሏል። በዩኒየኑ በወቅቱ ከ150 ኮኒቴነር በላይ ቡና ወደ ውጪ መላክ ተችሏል፤ በ2014 ዓ.ም በተከሰተው አገራዊ ችግር እና ዩኒየኑም ባጋጠመው መሰናክል ሳቢያ ወደ ውጪ የሚላከው ምርት መጠን ቀንሷል። አሁን የሚላከውን መጠን ወደ ነበረበት ለመመለስ ታቅዷል። በዚህም ወደ 30 ኮንቴነር የታጠበ፣ 70 ኮንቴነር ደረቅ ቡና ለማቅረብ እየተሰራ ነው።
በዩኒየኑ ውስጥም አለመግባባት ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፣ በገቢዎች በኩል ‹‹የተጠራቀመ ያልተከፈለ ግብር አለ›› በሚል የዩኒየኑን የባንክ ሂሳብ ገቢዎች ማሳገዱ በ2014 ዓ.ም ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት ከሆኑት መካከል እንደሚጠቀስ ያመለክታሉ።
‹‹ ከግብር ጋር ተያይዞ መጥራት ያለባቸው ነገሮች መጥራት አለባቸው። በተለይም ለጥያቄዎች በሰዓቱ ተገቢው ምላሽ ሊሰጥ ይገባል።›› የሚሉት አቶ አብዮት፤ ‹‹የአስራ አምስት እና የአስራ ሶስት ዓመት ግብር አለብህ።›› ብሎ ዩኒየኑ ያልሰበሰበውን ግብር መጠየቁ ዩኒየኑን ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩንም መጉዳቱን ያስረዳሉ።
ይህን ችግር ለመፍታት የተደረገውን ጥረት ተከትሎም ህብረት ሥራ ኮሚሽን እና ግብርና ባለበት ከግብር አስከፋዩ ጋር ድርድር በማድረግ ተጠራቀመ የተባለው የግብር ዕዳ መሰረዙን ጠቅሰው፣ እነዚህን ጥረቶች ተከትሎም የአርሶ አደሩም ሆነ የዩኒየኑ የሥራ ፍላጎት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፤ አሁንም መጥራት ያለበት ነገር መጥራት አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ ተመሳሳይ ነገሮች እንዳይኖሩ ከስር ከስር መከናወን ያለባቸው ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ነው ያመለከቱት።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ዩኒየኑ ምርቱን መጀመሪያ ከአርሶ አደር ማህበራት ይሰበስብና ይሸጣል፤ ሽያጭ ፈጽሞ ካተረፈው 30 በመቶውን ለመሰረታዊ ማህበራት ይሰጣል፤ መሰረታዊ ማህበራት ደግሞ ለአርሶ አደር ያከፋፍላሉ። በዚህ መልኩ ሲከፋፈል አርሶ አደሩ ከሚደርሰው ገንዘብ ላይ አስር በመቶውን ግብር ይከፍላል። አርሶ አደሩ ራሱ ግብር እየከፈለ፤ አሁን በድጋሚ ዩኒየኑ ይክፈል እየተባለ መሆኑን በመጠቆም፤ ጉዳዩ ተገቢነት የጎደለው ስለመሆኑ ያብራራሉ።
ዩኒየኑ ግብር መክፈል ካለበት በወቅቱ ተነግሮት መስተካከል ያለበት ጉዳይ ባለመስተካከሉ የተነሳ ዩኒየኑ በ2014 ዓ.ም ምርት መሰብሰብ አልቻለም ነበር ያሉት አቶ አብዮት፣ አሁንም ገቢዎች አካባቢ ጥርት ያለ ስራ ቢሰራ ለውጥ እያመጣ ከሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ ቤት እየተሸጋገረ ያለው አርሶ አደር የበለጠ የዕለት ገቢው ሊያድግ ይችላል ሲሉ ያብራራሉ።
አሁን እያንዳንዱ አርሶ አደር ያቀደውን በደንብ ተረድቶ እየሠራ ነው ያሉት አቶ አብዮት፣ ዩኒየኑ በ2013 ዓ.ም 150 ኮንቴነር ቡና ወደ ውጪ ልኳል ይላሉ። በ2014 ዓ.ም ግን ብዙ እንዳልተሳካለት ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት ግን 12 ሚሊየን ኩንታል እሸት ቡና ለመሰብሰብ ማቀዱን ተናግረዋል። አሁን የቡና መሰብሰቢያው ወቅት ገና መሆኑን ገልጸው፣ እስከ አሁን ብዙ ባይሰበሰብም እስከ ታህሳስ ሁሉንም መሰብሰብ ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።
ሌላው የሲምፖዚየሙ ተሳታፊ የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ነው። በዩኒየኑ የዋንኮ ቡና የማርኬቲንግ ባለሞያ አቶ ኩመራ አሸናፊ እንደሚናገሩት፤ ዩኒየኑ በኦሮሚያ ክልል የሚመረቱ ቡናዎችን ‹‹ዋን ኮ ቡና›› የሚል መለያ (ብራንድ) በመያዝ የተቆላ፣ የተፈጨ እና ጥሬ ቡና ወደ ውጪ ይልካል። ለአገር ውስጥ ገበያም ያቀርባል። በዩኒየኑ የይርጋጨፌ፣ የጉጂ፣ የሊሙ፣ የጅማ፣ የሐረር እና የነቀምት ቡናዎች ለገበያ ይቀርባሉ። ለውጪ ለመላክ የማይመጥኑትን ደግሞ ቆልቶና ፈጭቶ ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል።
ድርጅቱን ለየት የሚያደርገው ጥራት መሆኑን በማመላከት፤ የቡናን ጥራት ለማስጠበቅ ከገበሬው ጀምሮ የሙያ ድጋፍ በመስጠት እስከ መጨረሻው ሒደት የሙያ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም ይገልፃሉ። ዩኒየኑ ይህንን ጠብቆ ምርት ስለሚሰበስብ በብዛት ምርጥ ቡና ያቀርባል ሲሉ ያብራራሉ።
አቶ ኩመራ እንደሚገልፁት፤ የኦሮሚያ ቡና በትላልቅ ገበያዎች ላይ በጥራቱ ይታወቃል። በውጪ ገበያም ምንም ሳይቀላቀልበት በላከው ናሙና መሰረት እንደሚሸጥ ይታወቃል። ይህ ዩኒየን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታወቀው በላይ በውጪው አለም በደንብ የታወቀ ነው። ትልልቅ የቡና አቅራቢ ድርጅቶች ስታር ባክስን ጨምሮ የሚመርጡት ትልቅ ኩባንያም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በዋንኮ ቡና ታዋቂነትን እያተረፈ ይገኛል።
በአገር ውስጥ ቡና ተቆልቶ የተፈጨ ቡና ይቀርባል ሲባል ከገብስ ጋር የሚተሳሰርበት ሁኔታ ነበር የሚሉት አቶ ኩመራ፣ ዋንኮ ግን ንፁህ ያልተቀላቀለ ቡና በማቅረብ ተለይቷል ነው የሚሉት። ጥራትን ትኩረት አድርጎ የሚሰራ እና አንዱ ቡና ከሌላው ቡና እንደሚለይ ማሳየቱን ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ዩኒየን ጥራትን አስጠብቆ ምርት ሲያቀርብ በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አይደለም፤ በቡና ላይ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ የቡና ንግዱን እየረበሸበት ይገኛል። በአጠቃላይ በወጪ ንግድ ላይ በህጋዊ መንገድ ከሚወጣው ይልቅ በኮንትሮባንድ የሚወጣው ቡና እየበዛ ነው። ይህ በመንግስት ክትትል መቆም ይኖርበታል፤ ያለበለዚያ አርሶ አደሩ እና ዩኒየኖች ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም።
የተለያዩ ሌሎች ሴራዎችም መኖራቸውን የሚገልፁት አቶ ኩመራ፤ ለገበሬውም ሆነ ለአገር የማያስቡ ለውጭ ምንዛሬ ፍለጋ ብቻ ብለው ቡና የሚልኩ መኖራቸውንም ይጠቁማሉ። ወደ ውጪ የሚላከው ቡና ከአገር ውስጥ ባነሰ ዋጋ ለገበያ የሚቀርብ ሲሆን፤ ግለሰብ ቡና ላኪዎች በዚህ የሚያጡትን በተለያየ መንገድ የሚያካክሱበት ሁኔታ እንዳለ ይጠቁማሉ። አገር ውስጥ በውድ ገዝተው በውጪ ሀገር ሸጠው በሚያገኙት ዶላር ብዙ የሚያተርፉበትና ህዝቡን መልሰው የሚጎዱበት ሁኔታ ስለመኖሩ ያብራራሉ። የቡና ዋጋ በአገር ውስጥ ገበያ ጨመረ ሲባል ለገበሬው ትልቅ ጥቅም ሊመስል እንደሚችልም አመልክተው፣ ይህ ችግር የኢትዮጵያን የቡና የወጪ ንግድ እየረበሸው መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ አቶ ኩመራ ገለጻ፤ ለግለሰብ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለአገርም ማሰብ ያስፈልጋል። ቡናውን በውድ ገዝተው በውጪ ገበያ አራክሰው ሽጠው፤ ጥራቱን ያልጠበቀ ዘይትና ብረት አስገብተው ህብረተሰቡ ላይ መልሰው ዋጋውን ይጭናሉ። በዚህ ሳቢያ በጥቂት ግለሰቦች አገር ብዙ ታጣለች። ከግል ጥቅም ይልቅ የአገር ጥቅም ላይ ቢታሰብበት መልካም ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የቤንች ሸካ ዞን የቤንች ማጂ አንድነት የገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ሥራ ዩኒየን የቡና እና የቅመማ ቅመም የምርት ጥራት ባለሙያ ወይዘሮ ራዲያ ጀማል በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ መሰረታዊ ማህበሩ ከአርሶ አደሩ የሰበሰበውን ምርት ዩኒየኑ ሰብስቦ ገበያ አፈላልጎ ይሸጣል። ቡና በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጪ ገበያም ይሸጣል። ዩኒየኑ ቡና ላይ ብዙም የገበያ ችግር የለበትም።
እሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒየኑ ኮረሪማ ላይ ከፍተኛ ችግር አጋጥሞት ነበር። መሰረታዊ ማህበሩ ከአርሶ አደሩ ከሰበሰበ በኋላ ዩኒየኑ ተረክቦ ገበያ ሲያፈላልግ የኮረሪማ ገበያ ጠፋ። በዚህ ምክንያት በአንድ ዓመት ውስጥ ዩኒየኑ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር ከስሯል።
በሌላ በኩል ለዩኒየኑ አባላት ስልጠና በመስጠት የማድረቂያ ሽቦ መቅረቡን ወይዘሮ ራዲያ ጠቅሰው፣ የቡና ማድረቂያ ሽቦ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ። አሁን አርሶ አደሩ ስለጥራት ብዙ ችግር የለበትም፤ በተሻለ ጥራት ሲያቀርብ የተሻለ ገንዘብ እንደሚገኝ ተረድቷል የሚሉት ባለሙያዋ፣ ፈተና እያጋጠመ ያለው ከቡና ውጪ ባሉት ምርቶች ገበያ ማጣት ነው ይላሉ።
የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ዑመር እንደተናገሩት፤ የቡና አምራች ህብረት ሥራ ማህበራት ወደ ውጪ የሚልኩት የቡና ምርት አነስተኛ ነው፤ አሁን ደግሞ የበለጠ እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህ ችግር መንስኤ የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የአገር ውስጥ ገበያ በውጪ ገበያው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ፤ ህብረት ሥራ ማህበራት ጥራት ያለው ምርት ይዘው አለመገኘታቸው፤ ምርቱን በሚሰበስቡበት ወቅት የሚያስፈልጋቸው በቂ ፋይናንስ ማግኘት አለመቻላቸው ከምክንያቶቹ መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ማህበራት፣ ዩኒየኖች፣ ባንኮች እና ከሚሽኑ በትኩረት መስራት አለባቸው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ተገኝ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በክልሉ 2ሺ 369 የህብረት ሥራ ማህበራት እና 20 ዩኒየኖች ይገኛሉ። ዩኒየኞቹ የሚጠበቀውን ያህል ወደ ውጪ በሚላኩ ምርቶች ላይ ስኬታማ አይደሉም፤ የዚህ ምክንያቶቹ ደግሞ የውስጥና የውጪ ተብለው የሚታዩ ናቸው።
በተለይ በቡና ንግድ ሥራ ላይ የተመሰረቱ ማህበራት ዋነኛ ችግራቸው የፋይናንስ ችግር ነው። ዩኒየኖች አብዛኛውን ከአባላት የሚቀበሏቸውን ምርቶች ለመሰብሰብ ግለሰቦች ገንዘብ ይፈልጋሉ። ዩኒየኖች ደግሞ ለግለሰቦቹ ገንዘብ ማቅረብ አይችሉም። ከባንክ በብድር መልክ የሚገኘው አብዛኛው የግብይት ገንዘብ የሚለቀቀው መጨረሻ ላይ ምርቱ ተሰብስቦ ለገበያ ቀርቦ ግብይቱ ሊያልቅ ሲል ነው። ስለዚህ በተለይ የፋይናንስ ተግዳሮት የዩኒየኞቹ ከፍተኛ ችግር ነው።
ማህበራት እና ዩኒየኖቹ ያላቸውንም ገንዘብ የሚያስተዳድሩበት መንገድም የራሱ ተግዳሮት ያለበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ የሚያገኙትን ፋይናንስ ለዋናው ተልዕኳቸው ከማዋል ይልቅ ወጣ ያለ ተግባር ላይ ሲያውሉ መታየቱንም ያመለክታሉ።
ይህን ችግር ለማቃለል ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አቶ አክሊሉ ይገልጻሉ። የሕብረት ሥራ ማህበራትን በተለይ ከቡና አንፃር እየፈተናቸው ያለው የተጋነነ ዋጋ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ አሁን በሸካ አንድ ኪሎ እሸት ቡና እስከ ሃምሳ ብር እየተሸጠ ነው። ይህም በዓለም አቀፍ ግብይት ደረጃ በዶላር ሲሰላ አሁን ላይ አንድ ኪሎ እሸት ቡና በዓለም ገበያ ላይ አራት ዶላር ነው። አሁን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሸካ አካባቢ አንድ ኪሎ ቡና እየተሸጠ ያለው በ6 ዶላር ነው። የአስተዳደር ወጪ፣ የትራንስፖርት ወጪ ሳይጨመር ይህ ዋጋ እጅግ የተጋነነ ነው።
ይህ ሁኔታ ሲታይ የሕብረት ሥራ ማህበራት በግለሰብ ነጋዴዎች ምክንያት ከወጪ ንግድ አቅራቢነት ሊወጡ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው። በዛ ላይ ማህበራቱ ግብይቱን ለመፈፀም የፋይናንስ ችግራቸውን ለማቃለል ቅድመ ብድር ይዘጋጅ ቢባልም፤ ብድሩ የሚለቀቀው ግብይቱ ካለቀ በኋላ መሆኑ ግለሰብ ላኪዎች ተፎካክረው ቀድመው የሚወስዱበትን ሁኔታ በስፋት ፈጥሯል። ስለዚህ ጉዳዩ አገራዊ መፍትሔ፤ በተለይ የፖሊሲ አቅጣጫ ይፈልጋል ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።
ከግብር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጥያቄ በሚመለከት በሰጡት ምላሽም፤ ግብር ላይ መጣረሶች መኖራቸው እንደማይካድ ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በህብረት ሥራ አዋጅ የሚወጣው የሚፀድቀውም በግብር መስሪያ ቤት የሚወጣውም የሚፀድቀውም ተመሳሳይ በሆነ አካል ነው። ህጉ ተናቦ መውጣት አለበት። ተናቦ ባይወጣ እንኳ ተናቦ ከመስራት አንፃር ሰፊ ክፍተት አለ ሲሉ ያብራራሉ።
ግብር እንዴት እና መቼ መከፈል አለበት? የሚለውን ለማህበራት የማሳወቅ ሥራ አልተሠራም። ግብር መክፈል ካለባቸው ግብር መክፈል አለባቸው ብለን እናምናለን ያሉት አቶ አክሊሉ፣ ለበርካታ አመታት የተጠራቀመ ብሎ መጠየቅ የለበትም ይላሉ። ለአስር እና ለአስራ ሶስት ዓመታት ቆይቶ መጠየቅ ተገቢ እንዳልሆነም አመልክተዋል። እዚህ ላይ መነጋገር ይገባል ይላሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ አምና የተፈጠረውን ችግር ለጊዜው መፍታት እንደታቸለም አስታውሰው፣ በቀጣይ ነገሮችን ማስተካከል እንደሚገባ አያጠያይቅም፤ ለዚህም ከግብር አስከፋዩ ጋር እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/ 2015 ዓ.ም