በእግር ኳስ ወዳጆች ዘንድ የሚናፈቀው የዓለም ዋንጫ በኳታር ሊካሄድ 14 ቀናት ብቻ ይቀሩታል። በትልቋ አህጉር እስያ ለሁለተኛ ጊዜ በአረብ ምድር ደግሞ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን ይህንን የዓለም ዋንጫም ትንሿ ከበርቴ አገር ኳታር ልታስተናግደው ዝግጅትን ጨርሳለች። በመካከለኛው ምስራቅ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱ ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኳታር ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። የስፖርት ቤተሰቡም የዓለም ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች ለዋንጫ የሚያደርጉትን ፍልሚያ ለመመልከት በጉጉት እየተጠባበቀ ነው።
ይህንን ተከትሎም በዓለም ዋንጫ ታሪክ የማይረሱ ክስተቶችን በዛሬው ስፖርት ማህደር አምዳችን የምንዳስሰው ይሆናል። የዓለም ዋንጫ ሲነሳ ብራዚል ቀዳሚዋ የእግር ኳስ ሀገር ስለመሆኗ፤ የእግር ኳስ ተጫዋች ሲታወስም የምንጊዜም ኮከቡ ፔሌ ቀድሞ መጠራቱ አያጠራጥርም። በእግር ኳስ ስፖርት የምትታወቀው የደቡብ አሜሪካዋ ሀገር በታላቁ የውድድር መድረክ አምስት ዋንጫዎችን በማንሳት በድል የተንቆጠቆጠ ታሪክ ያላት ብቸኛዋ ሀገር ናት። ዓለም ዋንጫ እና ብራዚል የተገናኙት ደግሞ ስዊድን አዘጋጅ የሆነችበት እአአ የ1958ቱ ውድድር ነበር። ታዲያ ይህ ወቅት በልዩነት የሚታወሰው ብራዚል የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫውን በማንሳቷ ብቻም ሳይሆን ታላቁ የእግር ኳስ ሊቅ ከዓለም የተዋወቀበት በመሆኑም ጭምር ነው።
እአአ 1957 የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ከአርጀንቲና ጋር ለነበረበት ዓለም አቀፍ ጨዋታ አንድን ታዳጊ አካተተ። ብራዚል በሜዳዋ (በማራካኛ ስታዲየም) ባካሄደችው በዚህ ጨዋታም 2 ለ 1 በሆነ ውጤት መርታት ችላ ነበር። ያኔ ታዲያ የደጋፊዎች ትኩረት በድሉ ላይ ብቻ ሳይሆን በጨዋታው አንድ ግብ ባስቆጠረው የ16 ዓመት ታዳጊ ላይ ነበር። ይህ ታዳጊ በብራዚል ብሄራዊ ቡድን በትንሽ እድሜው ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ሆኖም ዛሬም ድረስ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ለተነሳው ‹‹ይህ ተጫዋች ማነው?›› የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ምላሹ ኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሚንቶ ወይም ፔሌ የሚል ነበር። ይህ አስገራሚ ተጫዋችም ተስፋው ቀድሞ የሚተነበይ የእግር ኳስ ክስተት ነበረና በቀጣዩ ዓመት ስዊድን አዘጋጅ በሆነችበት የዓለም ዋንጫ በሚካፈለው ብሄራዊ ቡድን አባል ለመሆን ቻለ።
በዓለም ዋንጫው ብራዚል በቡድን አራት ከሩሲያ፣ እንግሊዝ እና አውስትራሊያ ጋር ነበር የተደለደለችው። ከቡድኑ አባላት መካከል አንዱ የሆነው የ17 ዓመቱ ፔሌ ግን በጉልበት ጉዳት ምክንያት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሊሰለፍ አልቻለም። ከጉዳቱ አገግሞ በተካፈለበትና ከሩሲያ ጋር በነበረው የምድቡ ሶስተኛ ጨዋታ ላይም ግብ ከሆኑት ሁለት ኳሶች መካከል አንዱን በማቀበል ብቃቱን ሊያሳይ ቻለ። ከምድቧ ቀዳሚ በመሆን ወደ ሩብ ፍጻሜው ያለፈችው ብራዚል ከዌልስ ጋር በነበራት ጨዋታ ደግሞ ወጣቱ ፔሌ ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቡድኑን ወደ ግማሽ ፍጻሜው ሊያሸጋግር ችሏል።
የግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ በብራዚልና ፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ሲካሄድም፤ ባልተጠበቀ ሁኔታ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን እና ፔሌ አስደናቂ ብቃታቸውን አሳዩ። ቡድኑ አውሮፓዊቷን ተጋጣሚውን ከረታበት 5 ግቦች መካከል ተዓምረኛው ተጫዋች ፔሌ ሶስቱን በማስቆጠር በዓለም ዋንጫ ታሪክ ሶስታ(ሐትሪክ) የሰራ ትንሹ ተጫዋች በሚልም ተመዘገበ። ይህም የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት ሙሉ ለሙሉ ሲወስድ የስፖርት መገናኛ ብዙሃን አርዕስቶችም በወጣቱ ተጫዋች ላይ የተቃኙ ሆኑ።
በፍጻሜው ጨዋታም ብራዚል ከአዘጋጇ ስዊድን ጋር ተገናኘች። አስደናቂ በነበረው በዚህ ጨዋታ ላይም አረንጓዴና ቢጫ ለባሾቹ በተመሳሳይ ለግማሽ ደርዘን አንድ የቀረው ግብ አስቆጠሩ። ብራዚልም 5ለ2 በሆነ ሰፊ የግብ ብልጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን የግሏ በማድረግ ከእግር ኳስ ባለታሪኮች ተርታ ለመሰለፍ በቃች። ከተቆጠሩት ግቦች መካከል ሁለቱን ኳሶች በ55ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ከመረብ ያዋሃደው ደግሞ በታላቁ የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ወጣቱ ኮከብ ፔሌ ነበር። በዚህም ተጫዋቹ በአጠቃላይ ያስመዘገባቸው ግቦች ቁጥር ስድስት በመድረሱ፤ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በሚል ሊመረጥ ቻለ።
ከጨዋታው በኋላ የስዊድኑ ተጫዋች ሲግቫርድ ፓርሊንግ ፔሌን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት አድናቆቱን ሳይሸሽግ ‹‹እውነት ለመናገር ፔሌ አምስተኛውን ግብ ሲያስቆጥር፤ ላጨበጭብለት ፈልጌ ነበር›› ብላል። ባርኔ ሮናይ የተሰኘው ጸሐፊ ደግሞ ‹‹ምንም ሳይሆን ችሎታው ነበር የሚመራው፤ ይህ የመጀመሪያው ጥቁር የዓለም ምርጥ ተጫዋች ነው›› በማለት ገልጾታል ፔሌን።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም