ዕለተ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ተሰማ። የማህበራዊ ገጾች በዚህ መረጃ ተጥለቀለቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቅ ብለው መርዶውን ተናገሩ።
ሕዝቡም ከሌሊት የቀጠለ አግራሞቱን ይዞ ጠዋት ‹‹አሁንስ ምን ይፈጠር ይሆን?›› እያለ የማለዳ ዜና ለመስማት አይኑን ቴሌቭዥን ላይ ተከለ። አንዳንዱ ደግሞ ‹‹አገር አማን›› ብሎ ተኝቶ አድሮ ጠዋት ጥቅምት 25 ቀን አዲስ አስደንጋጭ ዜና የሰማበት ዕለት ነው። የሰማውን ማመን አቅቶት ከጎኑ ያለውን ሰው የጠየቀበት ዕለት ነው። ብዙ ሰዎች ግን ዘመኑ ባመቻቸው የማህበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት ክስተቱን ሌሊት ሰምተዋል።
ጥቅምት 24 ሌሊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን መግለጫ ብዙ ሰው ሰምቷል። የዚያን ቀን ሌሊት የማህበራዊ ገጾች፣ ቀን ከሚታየው በላይ እንቅስቃሴያቸው ጨመረ። ሌሊት የሰማው ሰምቶ ያልሰማውም ተኝቶ ነጋና ጥቅምት 25 ቀን ጠዋት ግን የሁሉም ቀልብ ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሆነ። ‹‹ምን ይፈጠር ይሆን?›› በሚል ስጋት ብዙዎች በያሉበት መጨነቅ ጀመሩ። የሁሉም ዓይንና ጆሮ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ሆነ። ለመሆኑ በዚህ ቀን ምን ተባለ? ምን ተከሰተ?
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት የተሰማበት የመጀመሪያው ቀን ነው። ስለዝርዝር ሁኔታው ብዙ ሰው አያውቅም። ዝርዝር ጉዳዮች የተሰሙት ከቀናት በኋላ ነው። እየቆየ ግን አሳዛኝ የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቶችም መሰማት ጀመሩ። የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችም ቀኑን ሙሉ ድርጊቱን አወገዙ።
የሰሜን ዕዝ መጠቃት ዜና ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የጦር መኮንኖች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች፣ የተለያዩ ዘርፎች ባለሙያዎች እና በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በዕለቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚከተለውን መግለጫ ሰጠ።
‹‹…ከሀገራዊ ለውጡ በፊት እንደ ሀገር መቀጠል የማንችልበት ደረጃ ላይ ስለመድረሳችን ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት እንችላለን።
ህዝብን በጸረ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ለመምራት የሚደረግ አይን ያወጣ ተጽዕኖ፣ አድርግ ወይም አታድርግ በሚሉ ቃሎች ብቻ የተገደበ እና ህዝብን ለማሸማቀቅ በርካታ ድርጊቶች ሲፈፀሙ እንደነበር ይታወቃል።
ህዝብን ከፋፍሎ የመግዛት አባዜ የተጸናወተው ጥቂት የሕወሓት ቡድኖች በርካቶች ተገፍተው ከሀገር እንዲወጡም ምክንያት ነበሩ።
ለሀገራቸው ፖለቲካ ያገባናል ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች ሀሳባቸውን አውጥተው መግለጽ እንዳይችሉ ሲደረግባቸው የነበረውን አፈና፣ እስር፣ ግርፋት እና አሰቃቂ ድርጊቶች ለፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ እንደምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው።
የመሰረተ ልማት እጥረት ባልተቀረፈበት እና የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን መፍታት አዳጋች በሆነባት ሀገር እነዚሁ ቡድኖች በርካታ የህዝብና የመንግስት ተቋማትን በመዝረፍና የዘረፉትን ወደ ውጭ ሀገራት በማሸሽ በህዝብ ላይ ክህደት በሀገር ላይ የኢኮኖሚ ውድቀት አስከትለዋል።
እወክለዋለሁ ላለው የትግራይ ህዝብ በተጨባጭ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የተሳነው ይህ ቡድን ከሀገራዊ ለውጡ እኩል መራመድ ባለመቻሉና ሲፈፅማቸው የነበሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች ከህዝብ ፊት መቆም እንዳይችል ስላደረገው ውህደቱን ከመቀላቀል ይልቅ መግፋትን አማራጩ አድርጓል።
ለህገ መንግስታዊ ስርዓት ጠበቃ ነኝ ሲል የነበረው የሕወሓት ቡድን የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ለመነጣጠልና ለህገ መንግስቱ ያለውን ንቀት ያረጋገጠበትን ህገ ወጥ ክልላዊ ምርጫ ሲያደርግና ህጋዊ ያልሆነ መንግስት ሲመሰርት በሆደ ሰፊነት የተመለከተው የፌደራል መንግስት ይህ ቡድን እየተከተለው ያለው ኢ-ህገ መንግስታዊ አካሄድ ከዛሬ ነገ ሊለወጥ ይችላል በሚል ጊዜ ሰጥቶ ቆይቷል።
ዳሩ አምባገነናዊ ባህሪው እያደገ ቢመጣም። የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሀገራዊ ለውጡ በጋራ ለመቆም ፍላጎት ቢኖረውም ጥቂት የሕወሓት ቡድን አመራሮች ግን የህዝቡን ፍላጎት ወደ ጎን በመግፋት ህዝቡ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖረው ጭቆና ሲያደርስበት ቆይቷል።
ብልጽግናና የለውጡ መሪዎች ሕወሓት ውህደቱን እንዲፈጽምና ለጋራ ሀገራችን በጋራ እንቁም መርህ በተደጋጋሚ ጊዜ የድርጀቱን መሪዎች በማግኘት ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ማወያየት ቢቻልም ወትሮውንም ሀገርንና ህዝብን የማገልገል ጽኑ ፍላጎት ሳይሆን ጥያቄያቸው በስልጣን የሚገኝ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ለውህደቱ እምቢታቸውን አሳይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተስፋ ያልቆረጡት የለውጡ መሪዎች በህዝብ የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ በርካታ ጥረቶችን በማድረግ የትግራይን ህዝብ ከለውጡ ጋር አብሮ ለማስቀጠል ያላሰለሰ ግፊት ቢደረግም በጸረ ለውጥ ቡድኖች ሰንኮፍነት እንደታሰበው ውህደቱን ለማቀላቀል የተደረገው ጥረት ያለ ውጤት ተጠናቋል።
መቀሌ የመሸገው ቡድኑ ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ ጠዋት ማታ የአማራ ክልልና የፌደራል መንግስት ጦርነት በህዝባችን ላይ ሊከፍቱብን ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ ህዝቡን በማደናገር እረፍት አሳጥቶት ከርሟል።
የትግራይ ህዝብ ጦርነት እንዳንገሸገሸው የኢትዮጵያ ህዝብ ከልብ ይረዳዋል።
ጦርነት የመጨረሻ እንጂ የመጀመሪያ አማራጭ እንዳልሆነ ብልጽግና ይገነዘባል።
የመከላከያ ሰራዊቱን ከክልሉ ፈቃድ ውጭ ማደራጀት አትችሉም የሚል አቋም እየተከተለ ያለው ሴረኛውና ጥቂቱ የሕወሓት ቡድን የፌደራል መንግስትን ውሳኔዎችና የሚሰጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ እንዳይሆኑ ግትር አቋሙን ሲያሳይ ቆይቷል።
ከህዝብ አብራክ ወጥቶ ህዝብንና ሀገርን ከጥቃት እየተከላከለ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊቱን የቆየ ክብርና ዝና ለማጠልሸት ሲሞክር ሆደ ሰፊው ሰራዊት ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ለጥፋት ሁሌም የማይተኛው ጥቂት የሕወሓት ቡድን አማካኝነት በተሰጠው ትዕዛዝ በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕና ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ላይ ሌሊት በተኛበት ጥቃት ከማድረሳቸው ባሻገር ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርገዋል።
ነገሩን በሆደ ሰፊነት ሲመለከተው የቆየው መንግስት እየተፈፀሙ ያሉ ድርጊቶች ገደብ በማለፋቸውና ግልጽ ትንኮሳ በመፈጠሩ ምክንያት ይህንኑ ድርጊት ሊመክት የሚችል አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል።
በዚህ መሀል ምንም የማያውቀው የትግራይ ህዝብ ተጎጂ እንዳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እየተወሰደ ይገኛል።
በአጠቃላይ ከዚህ በፊት እንደምናደርገው ሁሉ ብልጽግና ፓርቲ ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን የሚሰራና የህዝብንና ሀገርን ሰላም አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ማናቸውንም ነገሮች ለመታገስ እንደማይችል ታውቆ በተሣሣተ መረጃ ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ ላይ ያልተገባ ስጋት በመፍጠር ተጠራጣሪ ለማድረግ የሚደርገው ተከታታይ ቅስቀሳ የትግራይ ህዝብ ሊያወግዘው የሚገባ መሆኑን በፅኑ በማመን የሚከተሉትን የአብሮነትና የአጋርነት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
1. ለተከበርከው የትግራይ ህዝብ
የትግራይ ህዝብ ከሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ጠንካራ ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጋሩ፣ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ በፀረ-ጭቆና ትግል ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆነው በአንድ ጉድጓድ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አሁን ላለንበት የሀገረ መንግስት ምስረታ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ህዝቦች ናቸው። ሆኖም የሕወሓት ቡድን የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ የትግራይን ህዝብ የሚያለያዩ ሙከራዎችን በፅናት እንድትታገሉ የከበረ ጥሪያችንን እያቀረብን በዚህ ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገው ትግል ውስጥ ከጎናችን እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
2. ለመላው የትግራይ ምሁራን
ሀገርን በሚፈለገው ደረጃ መለወጥ ካስፈለገ ምሁራን የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍ ያለውን ቦታ መያዙ ግልጽ ነው።
ሆኖም ግን ሕወሓት በክልሉ የሚገኙ ምሁራንን ለሀገራቸው ሁለንተናዊ አበርክቶ እንዳያደርጉ በጥቅም የተሳሰረው ቡድን እንቅፋት እንደሆነባችሁ መረዳት ተችሏል።
ስለሆነም ምሁራን በነጻነት ተንቀሳቅሰው ያላቸውን አቅምና ዕውቀት ለሀገራችን ህዝቦች እንዲያበረክቱ ካስፈለገ ጨቋኙንና ጸረ ለውጡን የሕወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ያስፈልጋል።
ስለሆነም የተከበራችሁ በትግራይ የምትገኙ ምሁራን ሁላችሁም የፌደራል መንግስት በክልሉ እያደረገ ያለው ህገ መንግስቱን ማስከበር ስራ በውጤታማነት ለመፈፀም እንዲቻል የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ የአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋልን።
3. ለመላው የትግራይ ወጣቶች
በክልሉ የምትገኙ ወጣቶች ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ሳትችሉ ነገር ግን በስማችሁ እየተነገደ ለበርካታ ዓመታት ቆይታችኋል።
ይህንን አይን ያወጣ ዘረፋና ሌብነት በሕወሓት ቡድን አማካኝነት ሲካሄድ እንደነበርም የአደባባይ ሀቅ ነው።
በስሙ ሲነገድበት ለቆየው የትግራይ ወጣት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ ዘንድ በዚህ ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷልና መላው የትግራይ ወጣቶች በፌደራል መንግስት በኩል እየተወሰደ ያለውን ህግን የማስከበር እርምጃ በመደገፍ ለክልሉና ለሀገር ሰላም አጋር እንድትሆኑ የትግራይ ወጣቶች ከመላው የሀገራችን ወጣቶች ጋር በመሆን የጀመርነውን አገራዊ ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
4. በትግራይ ክልል ለምትገኙ የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች
የትግራይ ክልል የፀጥታ ሀይሎች በሀገሪቱ ከሚገኙ የፀጥታ ሃይሎች ጋር በጋራ በመሆን ህዝባዊነታችሁን ጠብቃችሁ ለአንዲት ሉአላዊት አገር መከበርና ቀጣይነት ክቡር መስዋዕትነት በመክፈል ላይ መሆናችሁን ብልጽግና ፓርቲ ከልብ ይገነዘባል።
ምንም እንኳ በክልሉ አምባገነን የሆነው የሕወሓት ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን እንግልትና ስቃይ የታዘባችሁ ቢሆንም ባለው ጸረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ምክንያት ለውጡን ከህዝባችሁ ጋር ሆናችሁ ማጣጣም ሳትችሉ ቀርታችኋል።
ሆኖም ለረዥም ዓመታት የክልሉን ህዝብ ሰላም ደህንነት በሀላፊነት መንፈስ ወስዳችሁ ስትጠብቁ የቆያችሁ የክልሉ ፖሊስ፣ ልዩ ሀይል አባላትና ሌሎችም በህዝብ ትክሻ ላይ ሆኖ እየቀለደ ባለው ዘራፊና አጥፊ የሕወሓት ቡድን ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለውን ትግል በመቀላቀል ህዝባዊነታችሁን እንድታረጋግጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ…››
ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ። ከምክር ቤቱ የዕለቱ አጀንዳዎች መካከልም፤ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ከአደጋ ለመከላከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለማፅደቅ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አባላትን ለመሰየም የሚቀርብለትን የውሳኔ ሀሳብም ለማጽደቅ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርምሮ በስድስት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። ጠቅላይ ዓቃቤ ህግም በዕለቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ሳምንቱ በሙሉ የመግለጫዎችና የውግዘት ዜና ሆኖ ሰነበተ። እነሆ የዚያን ጊዜ የተጀመረው ጦርነት ጦሱ ለሁለት ዓመታት ያህል ቀጥሎ፤ ልክ በሁለተኛ ዓመቱ ዋዜማ ግን ሌላ አስደሳች ዜና ተሰማ። የፌዴራሉ መንግሥትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ ለ10 ቀናት ያህል ያደረጉት የሰላም ድርድር ተጠናቆ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም መግለጫ ተሰጠ። ይህም የታሪክ አካል ሆኖ ይቀመጣል። በአኩሪ ታሪኮቻችን እንኩራ፤ ከስህተቶቻችን እንማር!
የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ፤ ጥቅምት 24 የሚታወሰው የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ለመፍጠር ሳይሆን ተመሳሳይ ታሪክ እንዳይደገም ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም