ኢትዮጵያ የአያሌ ቱሪስት መስህቦች ባለቤት ናት። የሰው ዘር መገኛ ይህች ሀገር፣ ከ3 ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረችው “የሉሲ” ወይም ድንቅነሽ ቅሬተ አካል፣ የአረቢካ ቡና ዝርያ ፣ የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይ ፣ የኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ፣ የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎል መገኛዎች መሆኗ በእጅጉ ይታወቃል።
በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ የአያሌ የዱር እንስሳት ፓርኮችና መጠበቂያዎች ይገኙባታል። በርካታ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና የተለያዩ እምነቶች ሀገርም ናት። በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔሰኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች።
የእነዚህ ሁሉ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም ፣ በውጭ ሀገሮች ቱሪስቶች ካልሆነ በስተቀር በሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ብዙም ያልተጎበኘች እና በዜጎቿ ዘንድ የመጎብኘትና የማወቅ ባህል በሚፈለገው ልክ ያልዳበረባት ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሰሞኑ የቱሪዝም ሚኒስቴር “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የተሰኘ እና የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማነቃቃት እና ማበረታታትን ያለመ ንቅናቄ መጀመሩን አስታውቋል። ንቅናቄው በዋናነት ትውልዱ ስለ ሀገሩ ባህልና ታሪክ በአጠቃላይ ቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲያውቅ የሚያስችል መሆኑም ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ የበርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ባለቤት መሆኗን ለትውልዱ በማስተዋወቅ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ንቅናቄው ማስፈለጉ ተነግሯል። ይህንን ጉዳይ በማስመልከት የዝግጅት ክፍላችን ከቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ጋር ያደረገውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፦ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ንቅናቄ በይፋ አስጀምራችኋል። ለመሆኑ የዚህ ንቅናቄ ዋና አላማና መዳረሻ ግብ ምንድን ነው?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፡- ‹‹የልወቅሽ ኢትዮጵያ›› ዋና አላማ የአገር ወስጥ ቱሪዝምን ማነቃቃትና ማንቀሳቀስ ነው። የአገር ውስጥ ቱሪዝሙ ማለትም በአገራችን ያለውን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ተዘዋውሮ በጋራም ሆነ በተናጠል የመጎብኘት ባህል አሁን ካለው በተሻለ መልኩ ማደግ አለበት። አካባቢያችንንም ሆነ ራቅ ብለው የሚገኙትን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦችን ማወቅ ያስፈልገናል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ነች። በጣም ብዙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ ቅርሶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶች አሏት። ህዝቦቿ ከአንድ ቦታ ወደሌላኛው ተንቀሳቅሰው ይህን ሀብት የሚያዩበት በዚህ ሀብት የሚዝናኑበት፣ ልምድ የሚወስዱበት በዚያው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚገኝበት መሆን ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው ቱሪዝም በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ በቅርቡ ነው የተካተተው፤ አሁን እንደ ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተወስዷል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይበልጥ ሳቢ በማድረግ ኅብረተሰቡ ሀገሩን የማወቅ ጉጉት እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ ነው። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም የእርስ በርስ የባህል ትውውቅን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ሚናው የጎላ ይሆናል።
ንቅናቄው በዋናነት በትምህርት ቤቶች በሚመሠረቱ የቱሪዝም ክበባት እና በተቋማት አማካኝነት ይተገበራል። በተለይ ታዳጊዎች ነባሮቹን እና አዳዲሶቹን የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጎበኙ እና እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥራል፤ በተጨማሪም የሆቴል እና ቱሪዝም ኢኮኖሚን በማነቃቃት ረገድም ከፍተኛ አበርክቶ እንዲኖረው ተፈልጎ ነው ንቅናቄው የተጀመረው።
አዲስ ዘመን፦ ትውልዱ አገሩን እንዲያውቅ ከማስቻል ባለፈ ኢኮኖሚውን ያነቃቃል ብለዋል። ይሄ በምን መልኩ ይፈጸማል?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ በዋናነት የቱሪዝሙ ዘርፍ ባለፉት ሁለት አመታት በኮቪድ፣ በአገር ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጣም ተጎድቶ እና ተፋዝዞ ቆይቷል። ወረርሽኙ በዓለም ደረጃ ከባድ ቀውስ አስከትሏል። እኛ ከዚህ ለማንሰራራት በዋናነት በአንደኛ ደረጃ እንደ መነሻ አድርገን እየተጠቀምን ያለነው የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማነቃቃትን ነው። ይህንን እንደ ስትራቴጂ አስቀምጠናል።
ሁለተኛው ደግሞ ከጎረቤት አገራት ያለውን ግንኙነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ግንኙነቱን በማጠናከር እንዲሁም ዲጂታል ፕሮሞሽኑን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ ነው። በዋናነት ግን የአገር ውስጥ ቱሪዝም በማጠናከር በዜጎች ዘንድ የመጎብኘትና የመንቀሳቀስ ባህል እንዲሰርፅ ብናደርግ የበለጠ ከቱሪዝም የሚገኘውን ጥቅም ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይችላል።
በዚህ ምክንያት ነው በልወቅሽ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የአገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማንቀሳቀስና ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ በማለት ንቅናቄው ይፋ የተደረገው። ህዝባችን ብዙ ነው። በርካታ የሚጎበኙ መስህቦች አሉን። በዚህ ላይ ከሰራን ኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ጥቅም እናገኝበታለን” የሚል እሳቤ የያዘ ንቅናቄ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ንቅናቄ መቼ ይጀመራል? ምን አይነት ተግባራቶችስ ይካተቱበታል?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ አሁን ንቅናቄው ተጀምሯል። በውስጡ በርካታ ተግባራት አሉት። ከዚህ ውስጥ በዲጂታል ቅስቀሳ፣ ልዩ ልዩ ሁነቶችን በማካሄድ አላማውን የማስተዋወቅና ዜጎች ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራን ነው።
ከዚህ ውስጥ “የአገርህን እወቅ” የቱሪዝም ክለቦች ማለትም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ያሉትን ተጠቅሞ ፅንሰ ሃሳቡን የማስተዋወቅ ስራዎች ይካሄዳሉ። በዚህም ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ያሉት ይካተታሉ። ሁሉም ወጣቶችና ታዳጊዎች አገራቸውን ማወቅ እንዲችሉ ይህንን መዋቅር ለመጠቀም አስበናል።
በዚህ ሂደት ውስጥ በርካታ የጉብኝት መርሃ ግብሮችን በማቀናጀት ተማሪዎች የሚመለከቷቸውንና ሊያውቁ የሚገባቸውን የመስህብ ስፍራዎች የመለየት ስራ ጎን ለጎን ይሰራል። ክልሎች የከተማ አስተዳደሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በዚህ ንቅናቄ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ እቅዶችን ነድፈን ወደ ስራ ገብተናል።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ ንቅናቄ ውስጣዊ አንድነትን የማጠናከር፣ የዜጎችን ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድነት የማጉላት ግብ አስቀምጣችኋል። ይህንንስ በምን መልኩ ልታሳኩት አሰባችሁ?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ ልወቅሽ ኢትዮጵያ በዋናነት ሊያስገነዝበን የሚፈልገው አገራችንን እንድናውቅ ነው። ከጫፍ ጫፍ ያለውን ህብረተሰባችንን ብናውቅ አንዳችን የአንዳችንን ስሜት የመረዳት ነገር ይፈጠራል።
ይህ ይዞት ከሚመጣው የመደጋገፍና የመረዳዳት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባሻገር ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳም አለው። ታሪካችን የሚያስገነዝበው ሁሉም ዜጎች ተዋደው፣ ተከባብረው የኖሩ ህዝቦች መኖራቸውን ነው። በመሃል ለጥቂት ጊዜ በተፈጠረው ሁኔታና ችግር ምክንያት ልዩነቶቻችንን መዘን የማውጣትና ሌሎች አመለካከቶች ሲንፀባረቁ ይታያል።
የልወቅሽ ኢትዮጵያ ንቅናቄም እነዚህን ችግሮች የመቅረፍ አላማንም በማንገብ ጭምር ነው የተነሳው። ከአንድ አካባቢ የሚነሳ ማህበረሰብ በሌላ ጥግ ያለውን የአገሩን ክፍል በሚጎበኝበት ጊዜ ባህሉም ሆነ የአኗኗር ሁኔታው ምን ያህል የተመሳሰለ እንደሆነ የማየት እድል ይኖረዋል። ምን ያህል የኢትዮጵያ ህዝብ አንዱ ጫፍ ከአንዱ ጫፍ ተመሳሳይ ነገር እንዳለው በደንብ መረዳት ይችላል።
ብዙ ነገሮቻችንን ስናይ አንድ አይነት ናቸው። በጣም የሚወደዱና የሚስቡ ባህሎች አሉን። ስለዚህ ይህ ሃብት አንዳችን በአንዳችን ማጌጥ እንድንችል ያደርገናል። ልወቅሽ ኢትዮጵያም እነዚህን አንድ የሚያደርጉንንና የሚያስተሳስሩንን ሃብቶች ልንጠቀምባቸው የምንችለው በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰን መመልከትና ለማወቅ መጓጓት ስንችል እንደሆነ ያስገነዝበናል።
አስተሳሰባችን ቀና የሚሆነው ካለንበት ሰፈር ለመውጣት ፍቃደኛ ስንሆን ነው። ይህን ስናደርግ ልምድ ማግኘት እንችላለን። ይህ አካሄድ በሁሉም የዓለም ክፍል ያለና የሚሰራበት ነው። አስተሳሰባችን እንዲሰፋ መንቀሳቀስ ይኖርብናል። በዚህ ጊዜ የራሳችንን ሰጥተን የሌላውን ባህል፣ ማንነት እንዲሁም የኑሮ ብሂል መቀበልና መለዋወጥ ያስችለናል። ይህን ማድረግ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ጉልህ ሚና አለው በሚል እንደ አንድ ዋና ጉዳይ ተወስዶ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱም ሆነ መንግስት እንደ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራበት ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ ምን ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? ተቋማዊ ቅርፅ ይዞ እንዲቀጥል፣ ዜጎች አገራቸውን የመጎብኘት ባህል እንዲኖራቸውና ዘላቂ ውጤት ለማምጣትስ ምን እየተሰራ ነው?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የማነቃቃት ግቡ በስትራቴጂ ላይ ተቀምጧል። ለረጅም አመት የሚቆይና በስፋት የሚሰራበት ነው። ይህ ዘርፍ በአገራችን እንደ ባህል ተደርጎ እስኪወሰድ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።
አሁን የቱሪዝም ዘርፉ ከገባበት ድብቴ እንዲላቀቅ ይህ ንቅናቄ በዋናነት ቢያስፈልግም ዜጎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ስፍራ ነባርና አዳዲስ መስህቦችን ለመመልከት የሚያደርጉትን ጉዞ እንደ ባህል መውሰድ እስከሚችሉ ድረስ ይህን እንሰራበታለን።
ልወቅሽ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እንደመሆኑ ፕሮጀክቱን ለእዚህ አመት እንጠቀምበታለን። ለቀጣይ ዓመት ደግሞ ሌላ ተመሳሳይ እና የተሻለ ሃሳብ በመፍጠርም ተከታታይ ስራዎችን እንሰራለን። “ልወቅሽ ኢትዮጵያ” ለዚህ አመት ብቻ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማነቃቃት አንፃር ልንጠቀምበት ያሰብነው መሪ ሃሳብ (ሞቶ) ነው።
በውስጡም በርካታ ሁነቶች፣ ሃሳቦች፣ በተግባር ላይ የሚውሉ ድርጊቶችና ግቦችን ያነገበ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች የሚገኙ መስህቦች፣ የመዳረሻ ስፍራዎች እንዲሁም አዳዲስ የተሰሩ የቱሪዝም ሃብቶችን በአንድ ላይ በማካተት ተግባራዊ የሚሆን ነው።
ወጣቶች አሁን ላይ በቡድን በመሆን አዳዲስ መዳረሻዎችን የመመልከት ባህል እያዳበሩ ነው። በተለይ መልክአ ምድሮችን (ሃይኪንግ) መጎብኘት፣ በወንዞች ላይ መንሸራሸር (ራፍቲንግ) እና ሌሎች ልዩ ልዩ አዳዲስ ሃሳቦችን እየፈጠሩ የጉብኝት ባህል እንዲዳብር የሚያደርጉ ወጣቶች አሉ። ይህ ልምድ እየሆነ እየመጣ ነው። ሚኒስትር መስሪያ ቤቱም አነዚህን ወጣቶችና ቡድኖች እንደ አንድ ባለድርሻ በመውሰድ ለመስራት እየተዘጋጀ ይገኛል። የንቅናቄው አንድ አካልም ናቸው።
የቱሪዝም ሚኒስቴር መስከረምን የቱሪዝም ወር በማለት ሰይሞ ሰፊፊ ስራዎችን አከናውኗል። ለምሳሌ ያህል ለመስቀል ዜጎች ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ባህሉን ለቀናት ቆይታ አድርገው ሲያከብሩ እግረ መንገዳቸውን በተራራ መውጣት (ሃይኪንግ) በብስክሌት ግልቢያ (ባይኪንግና) መሰል መዝናኛዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተሰርቷል። ወደ ጉራጌ ዞን ሶዶ የተደረገው ጉዞ ለእዚህ በአብነት ሊወሰድ ይቻላል። ይህንን ልምድ በየቦታው የማድረግ ሰፊ እቅድ አለ። አጋጣሚውም ዜጎች የኢትዮጵያን መልክአ ምድር በሚገባ እንዲያውቁት ከማድረጉም ባሻገር ባህልና የአኗኗር ዘይቤ እንዲገነዘቡ ያስችላል።
አዲስ ዘመን፦ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንፃር በርካታ ክፍተቶች እንደነበሩ ይታወቃል።ለመሆኑ እነዚህ ክፍተቶች ምንድናቸው? የተቀመጠ የመፍትሄ ሃሳብስ አለን?
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ የቱሪዝም ዘርፍ በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንፃር በርካታ ክፍተቶች ነበሩ። ለዚህ ምክንያቱ በልዩ ልዩ የአገሪቱ የመዳረሻ ስፍራዎች ላይ የሚገኙ መስህቦች ለጎብኚዎች ምቹና የለሙ አለመሆናቸው ነው። ይህ እንደ ትልቅ ክፍተት ሊወሰድ የሚችል ነበር።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ መስህቦችና መዳረሻዎችን በቅጡ አለማወቅም ሌላኛው ችግር ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ የሚያሳየው ሰፊ የፕሮሞሽን ወይም የማስተዋወቅ ክፍተት እንደነበር ነው። እነዚህን አንኳር አንኳር የምንላቸውን ችግሮች ለይተን መፍትሄ ለመስጠት እየሰራን ነው። በተለይ ተወዳዳሪ የሚሆን የሰው ሃይል ችግር አለ። እሱን ለማሟላት እንሰራለን። ነቅሰን ያወጣናቸው ችግሮች በቶሎ መፍትሄ እንዲያገኙም እቅድ በመንደፍ ወደ ተግባር እየገባን ነው። እስካሁን ድረስም ጥሩ ውጤት እያመጣን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ሆነው ጊዜዎትን ስለሰጡን እናመሰግናለን!!
ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት፦ እኔም አመሰግናለሁ!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም