የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አንደኛ ዙር ውድድር በባህርዳር ስቴድየም ተከናውኖ ባለፈው ሳምንት በስኬት ተጠናቋል። ሁለተኛውን ዙር ውድድር የተረከበችው ድሬዳዋ ከተማም ከትናንት ጀምሮ ጨዋታዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።
ካለፈው የውድድር አመት በተለየ በግቦች ተንበሽብሾ የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ዙር ውድድር በአምስቱ ሳምንታት የጨዋታ መርሃ ግብሮች በርካታ ግቦችን ማስተናገድ ቢችሉም የተመልካች ድርቅ አሳሳቢው ጉዳይ ነበር። ያም ሆኖ ጨዋታዎች በርካታ ግቦችን ማስተናገዳቸው ስቴድየም ተገኝቶም ይሁን በቴሌቪዥን መስኮት ለተከታተለ ተመልካች አዝናኝ ነበሩ ማለት ይቻላል።
ከአምስቱ ሳምንታት ጨዋታዎች ሁለቱ ሳምንታት ሃያ አንድ ሃያ አንድ ግቦች ከመረብ ያረፉበት ሲሆን ሁለት ሳምንታት አስራ ስምንት አስራ ስምንት፣ አንደኛው ሳምንት ደግሞ ሃያ ግብ ያስተናገደ ነበር። አንደኛውና ሶስተኛው ሳምንት ጨዋታዎች ከፍተኛው ሃያ አንድ ግብ የተቆጠረባቸው ሲሆኑ አራተኛና አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እያንዳንዳቸው አስራ ስምንት ግቦች ተስተናግደውባቸዋል። ሃያ ግቦች ከመረብ ያረፉበት ቀሪው የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ነው። በአጠቃላይ በአምስቱ ሳምንታት ጨዋታዎች አርባ ጨዋታዎች ዘጠና ስምንት ግቦች ከመረብ አርፈዋል። ሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላለፈ እንጂ የግቦች ቁጥር የበለጠ ሊሆን ይችል ነበር።
በመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስና ከስምንት አመታት በኋላ ወደ ሊጉ ተመልሶ እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ፍልሚያ በአምስቱ ሳምንታት ጨዋታዎች ከፍተኛ ግብ ያስተናገደ ነው። ፈረሰኞቹ አዲስ አዳጊውን መድን ሰባት ለአንድ መርታታቸው ይታወሳል። ይህም አዲስ አዳጊውን መድን ገና ከጅምሩ ሊጉ የከበደው አስመስሎት ነበር። ይሁን እንጂ መድን በቀጣይ ሳምንታት ጨዋታዎች አገግሞ በርካታ ግብ ከማስተናገድ ወደ ብዙ ግብ አስቆጣሪነት ተሸጋግሮ በሊጉ የባህር ዳር ቆይታ ክስተት ሊሆን ችሏል። በዚህም መድን በፈረሰኞቹ ከደረሰበት የሰባት ለአንድ ሽንፈት በኋላ በሁለተኛው ሳምንት መርሃ ግብር አርባ ምንጭ ከተማን አራት ለሶስት በመርታት ሊያገግም ችሏል። በሶስተኛው ሳምንትም አዲስ አዳጊውን ለገጣፎ ለገዳዲን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት መርታት ችሏል። በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት ደግሞ ድቻን አንድ ለዜሮ መቻልን ደግሞ ሁለት ለአንድ በመርታት ከፈረሰኞቹ ጋር በእኩል አስራ ሁለት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ የደረጃ ሰንጠረዡን ሁለተኛ ሆኖ የባህርዳር ቆይታውን አጠናቋል።
በአምስቱ ሳምንታት መርሃ ግብሮች ከተካሄዱ አርባ አንድ ጨዋታዎች ሶስቱ ብቻ ካለ ግብ መጠናቀቃቸው በራሱ ሊጉ በባህር ዳር በነበረው ቆይታ ለተመልካች አዝናኝ እንደነበር ማሳያ ነው። ካለ ምንም ግብ የተጠናቀቁት እነዚህ ሶስት ጨዋታዎች በመጀመሪያው ሳምንት ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከመጀመሪያው ሳምንት ተላልፎ ጥቅምት 19 የተከናወነው ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ፣ አራተኛ ሳምንት ላይ አርባ ምንጭ ከተማ ከሃዲያ ሆሳዕና ናቸው።
ከአምስቱ ሳምንታት መርሃ ግብሮች አስራ ሁለት ነጥቦችን ሰብስቦ የባህር ዳር ቆይታውን በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሚሆን ፍንጭ የሰጠ መንገድ ላይ ይገኛል። ፈረሰኞቹ አምስተኛ ሳምንት ላይ በአምና የዋንጫ ተፎካካሪያቸው ፋሲል ከነማ ከገጠማቸው የአንድ ለምንም ሽንፈት ውጭ አራት ጨዋታዎችን በአሸናፊነት ተወጥተዋል። ባሸነፉባቸው ጨዋታዎችም በርካታ ግቦች የማስቆጠር አቅማቸው ጎልቶ የታየ ሲሆን የተቆጠሩባቸው ግቦች በአንጻሩ ጠንካራ የተከላካይ መስመር እንዳላቸው ያሳየ ነው። ፈረሰኞቹ በነዚህ ሳምንታት በአራት ጨዋታዎች አስራ አምስት ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፉ በአምስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን ብቻ አስተናግደዋል። መድን ላይ ያስቆጠሩት ሰባት ግብ ትልቁ ሲሆን ሲዳማ ቡናን አምስት ለአንድ የረቱበት ውጤት በተከታይነት ይቀመጣል። ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመጨረሻ ሰዓት ባስቆጠሩት ግብ አንድ ለዜሮ ያሸነፉበት ጨዋታም ፈረሰኞቹ የተቸገሩበት እንደነበር ታይቷል። ሌላው አዳማ ከተማን ሁለት ለአንድ ያሸነፉበት ጨዋታም ተጠቃሽ ነው።
ሌላው አምና እስከ መጨረሻው ሳምንት የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረው ፋሲል ከነማ በባህር ዳር ቆይታው በአምስቱ ሳምንታት ጨዋታዎች የተጠበቀውን ያህል ጥሩ አጀማመር አለማሳየቱ ነው። አጼዎቹ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከድቻ ጋር የሚቀራቸው ቢሆንም በሰባት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከአራቱ ጨዋታዎችም ሁለቱን ሲረቱ በአንዱ ተሸንፈው በአንዱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም