ተቋርጦ የቆየው የ30 ኪሎ ሜትር ጎዳና ላይ ሩጫ ከነገ በስቲያ በቢሾፍቱ ከተማ ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ላይም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ መሆን የቻሉ ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአዲሱ የውድድር ዓመት የመጀመሪያውን ውድድር ለማካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል። በዚህም መሰረት ከሁለት ዓመታት በላይ ተቋርጦ የቆየውን የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ ያካሂዳል። በ2012 ዓ.ም ይህንን ውድድር ለማካሄድ ዝግጅት ሲደረግ ቢቆይም በወቅቱ በመላው ዓለም በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሊሰረዝ ችሏል። ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦም ፌዴሬሽኑ በገጠመው የስራ መደራረብ ምክንያት ሊሰረዝ ችሏል።
ውድድሩን ከነገ በስቲያ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቢሾፍቱ ከተማ የሚያካሄድ ሲሆን፣ ሁለት ክልሎች፣ 12 ክለቦች፣ የግል ተወዳዳሪዎች እንዲሁም አንጋፋ አትሌቶች ተካፋይ ይሆኑበታል። ከእነዚህም መካከል በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የውድድሩ ተካፋዮች ናቸው። በወንዶች በኩል ሙሌ ዋሲሁን፣ ፋንታሁን ሁነኛ፣ ጠበሉ ዘውዴ፣ ብርሃኑ በቀለ፣ ልመንህ ጌታቸው፣ ኃይለማርያም ኪሮስ እና ባየልኝ ተሻገርን የመሳሰሉ አትሌቶች የውድድሩ ተካፋይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በሴቶች በኩል ደግሞ ህይወት ገብረኪዳን፣ ሶፊያ ሸምሱ፣ አጸደ ባይሳ፣ ትዕግስት በቀለ፣ ታዱ ተሾመ፣ ባሻንቄ እሙሴ፣ መገርቱ ገመቹ፣ ብሩክ ታምሬ እና ሃገሬ በላቸውም በውድድሩ የሚሳተፉ ታዋቂ አትሌቶች መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ ትናንት በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
ዓላማውን ለክልልና ከተማ አስተዳደር ክለብ ተቋማት የግል ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል መፍጠር ያደረገው ውድድሩ፤ አትሌቶች ከውድድሩ በሚያገኙት ሽልማት እንዲበረታቱ የሚያስችልም ነው። በዚህ ውድድር በአጠቃላይ 404 አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 100 የሚሆኑት ሴቶች 304ቱ ደግሞ ወንዶች ናቸው። በዚህም መሰረት የ30 ኪሎ ሜትር ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ሲደረግ፤ በአንጋፋ አትሌቶች መካከል የሚካሄደው ውድድር ግን 15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው። የረጅም ርቀት የጎዳና ላይ ውድድር እንደመሆኑ መካፈል የሚችሉት አትሌቶች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ መሆን እንዳለበትም ተጠቁሟል።
ውድድሩ በታሰበው መልክ እንዲካሄድ የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችም ዝግጅታቸውን አጠናቀው ውድድሩ የሚካሄድበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ለአጠቃላይ ለዚህ ውድድርም ፌዴሬሽኑ ከ700ሺ ብር በላይ ወጪ ሲያደርግ ከዚህ ውስጥ ከ318ሺ ብር ለሽልማት የሚውል መሆኑ ታውቋል። በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ አትሌቶች እንደየደረጃቸው ከሚያገኙት የሜዳሊያ ሽልማት ባለፈ እስከ ስምንት ባለው ደረጃ ሩጫውን ለሚያጠናቅቁ ደግሞ የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል። በዚህም በሁለቱም ጾታ አሸናፊ የሚሆኑት አትሌቶች የ40ሺ ብር ተሸላሚ ሲሆኑ፤ ሁለተኛ የሚሆኑት 20ሺ እንዲሁም ሶስተኛዎቹ 18ሺ ብር የሚያገኙ ይሆናል።
በተመሳሳይ በአንጋፋ አትሌቶች መካከል በሚካሄደው የ15 ኪሎ ሜትር ሩጫ ከአንድ እስከ ስድስት ባሉት ደረጃ ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል። አሸናፊ የሚሆነው 6ሺ ብር፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ የሚሆኑት ደግሞ 3ሺ እና3ሺ ብር ተሸላሚዎች ናቸው።
ይህ የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በ2001 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ነበር የተካሄደው። ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ከተካሄደ በኋላም ውድድሩ እስከ 2010 ዓ.ም ተቋርጦ ቆይቷል። ከዓመታት በኋላም አራተኛውንና አምስተኛውን ውድድር በቢሾፍቱ ከተማ መካሄዱን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም