
‹‹ሌባ ላመሉ ዳቡ ይልሳል›› እንዲሉ ሌብነት አመል የሆነባቸው ሰዎች የሚሰርቁት ቢያጡ ውዳቂና የማይረባ ነገር ማንሳታቸው አይቀርም፡፡ ‹‹ሌብነት አመል የሆነባቸው ሰዎች ምንም ነገር ይስረቁ የሰረቁትን ዕቃ በሚገርም አይነት መንገድ ሸሽገው መውሰዳቸው ግን ትንሽ ያስገርማል›› ሲል ከሰሞኑ ዩ.ፒ.አይ ከወደ አሜሪካ ይዞት የወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
ነገሩ እንዲሀ ነው፡፡ በአሜሪካ ኒውዮርክ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ወደ አንድ የህንፃ መሣሪያ መደብር ያመራል፡፡ ወዲያውም የተዘጋውን የመደብሩን በር ከፍቶ ወደ ውስጥ ጥልቅ ይላል፡፡ በመቀጠልም ቀልቡ የሳበውን አንድ በኤሌክትሪክ የሚሠራ የእንጨት መጋዝ አፈፍ አድርጎ ያነሳል፡፡ ከዛም መጋዙን በግልገል ሱሪው ውስጥ ይደብቅና በጃኬቱ ሸፍኖ ከመደብሩ ውልቅ ብሎ ይወጣል፡፡ ይዞት በመጣው ፒካፕ መኪና መጋዙን ይዞ ይሰወራል፡፡
በማግሥቱ የመደብሩ ባለቤት አገር ሠላም ነው ብሎ ወደ መደብሩ ሰተት ብሎ ይገባና የመደብሩን የደህንነት ካሜራ መመልከት ይጀምራል፡፡ በደህንነቱ ካሜራ አማካኝነት ከመደብሩ የኤሌክትሪክ መጋዝ በአንድ ግለሰብ መሰረቁን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ይመለከታል፡፡ ወዲያውም ለፖሊስ ስልክ ይደውላል፡፡ ፖሊስም ከደህንነት ካሜራው የተገኘውን ተንቀሳቃሽ ምስል መነሻ በማድረግ ግለሰቡን ማፈላለግ ይጀምራል፡፡
ፖሊስ በክትትሉ ሂደት ከተጠርጣሪው ጋር ቅርበት አለው ያለውን አንድ ግለሰብ ይዞ ምርመራ ቢያካሄድም የመጋዙን ቀበኛ ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ተጠርጣሪ ነው ተብሎ የተያዘውም ግለሰብ ሰዎች ሌባ ነው ብለው በመክሰሳቸው በማህበራዊ ትስስር ገፆች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ‹‹ከሁሉ በላይ ግን ሰውየው መጋዙን በግልገል ሱሪው ደብቆ የወሰደበት መንገድ ግን ብዙዎችን አስገርሟል›› ሲል ዘገባው አስፍሯል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በአስናቀ ፀጋዬ