- ከኢትዮጵያ 39 አምራቾች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፦ 8ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና የፋሽን ሳምንት (ASFW) በሚል ከጥቅምት 25 እስከ 28 ቀን 2015 በአዲስ አበባ አውደርዕይ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። በአውደ ርዕዩ ከኢትዮጵያ 39 የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ባዛሩን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት ከጥቅምት 25 እስከ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው 8ተኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንት አውደ ርዕይ ከ30 አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ አምራቾችና ላኪዎች ይሳተፋሉ፡፡
አውደ ርዕዩ ከመሴ ፍራንክፈርት ኢግዚቢሽን (GmbH)፣ ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ልብስ ስፌት ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአውደርዕዩ ከኢትዮጵያ 39 ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች የሚሳተፉ መሆኑንም ጠቁመው አንጋፋ የአፍሪካ የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች የሚገኙበት በመሆኑ ለኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። ከ6000 በላይ የንግድ ባለሙያዎች፣ ግብዓት አቅራቢዎችና ገዢዎች ይጎበኙታል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይል ያላት የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በትኩረት እየተገነቡ እና የአፍሪካ የአምራቾች ማዕከል ለመሆን አቅዳ እየሰራች መሆኑን ያስታወሱት አቶ ታረቀኝ በዛሩም በኢትዮጵያ መካሄዱ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን የራሱ እገዛ አለው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ100 ሺህ በላይ የስራ እድል መፍጠር ችሏል ያሉት አቶ ታረቀኝ ለወደፊትም መስፋፋት የሚገባው መሆኑን አመላከተዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካን የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አመላክተው የአፍሪካ የነጻ የንግድ ቀጠናን ማጽደቅ አፍሪካውያን እርስ በርስ ያለንን የንግድ ድርሻ ለማሳደግ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የንግድ ደረጃ ለማሻሻል ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ በመባል የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ውስጥ የሚመረተውን ምርት ለመላው ዓለም በማሰራጨት ላይ የተለየ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻ የንግድ ቀጠና ማዕከል በድሬዳዋ መመረቁ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድል መሆኑን አስታውሰዋል። ከኢትዮጵያ ታምርት ጋር ተያይዞ በነበረው መነሳሳት በሀገር ውስጥ ምርት ለመጠቀም መንግሥት በያዘው ቁርጠኝነት ሙሉ ለሙሉ መሳካቱን ጠቁመው በ2014 ሁሉም ዓይነት የሚሊተሪ ዩኒፎርም በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ብለዋል።
የጥጥ ምርትን በተመለከተም ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከውጭ የምታስገባ እንደነበር አስታውሰው በ2014 ዓ.ም 100 በመቶ ኢንዱስትሪዎች የአገር ውስጥ ጥጥ ተጠቅመዋል። ነገር ግን የሀገር ውስጥ የጥጥ ምርት ጥራት ጋር ተያይዞ ቀጣይ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት፣ የስራ እድል ከመፍጠር እና ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ከማምጣት አኳያ ሰፊ ተሞክሮ እና ልምድ የተገኘበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና ጋርመንት አምራቾች ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ አገኣዚ ገብረየሱስ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው በዓለም አቀፍ አውደርዕዩ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት፣ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ፣ የፋሽን ትዕይንትና የፋብሪካ ጉብኝቶችን ያካተተ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የንግድ ትርኢቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ የንግድ ግንኙነቶችን ለማጠናከርና የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠር የጎላ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል።
በዘርፉ የሚሳተፉ አምራቾችም የጨርቃጨርቅ፣ የአልባሳትና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያቀርቡ በመሆኑም አምራቾች በሚያገኙት የልምድ ልውውጡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ይጠበቃል። በዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢቱ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ለማስተዋወቅ ያግዛልም ብለዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም