በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሚባሉትን ነጋሽ ገብረማርያም ዛሬ በጥቂቱ ልናስታውሳቸው ወደድንና ያሰባሰብናቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አሰፈርን።
አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ተስፉ ከአባታቸው ከአቶ ገብረማርያም ተስፉና ከእናታቸው ከወይዘሮ ምንትዋብ አሊ በአርሲ ክፍለ ሀገር በአርባጉጉ አውራጃ ልዩ ስሙ ሚኒ በሚባል ስፍራ በ1918 ዓ.ም ተወለዱ።
ገና በህጻንነታቸው ዘመን ከእናታቸው ጋር ወደ ሀረርጌ ክፍለ ሀገር መጥተው በጨርጪር አውራጃ በሐብሮ ወረዳ መቻራ ከተማ አደጉ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ጂልቦ በሚባል ስፍራ አያታቸው ፊታውራሪ አሊ ቢሊ ቤት ከሌሎች ህጻናት ጋር ፊደል ቆጥረው ማንበብና መጻፍ ተማሩ።
በ1933 ዓም ከታላቁ ወንድማቸው ከአቶ አሰፋ ገብረማርያም ተስፉ ጋር ወደ አሰበ ተፈሪ ከተማ በኋላም ወደ አዲስ አበባ መጥተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምሀርታቸውን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል።
በ1936 ዓም አዲስ አበባ ውስጥ ተቋቁሞ በነበረው መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ገብተው በጊዜው ይሰጥ የነበረውን የሁለት ዓመት ኮርስ ካጠናቀቁ በኋላ፤ ለአንድ ዓመት ያህል ጅማ መምህራን ማሰልጠኛ አስ ተምረዋል።
አቶ ነጋሽ በትምህርታቸው በበለጠ ለመግፋት ይጓጉ ስለነበረ፤ በ1938 ዓ.ም ኮተቤ በሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል።
በ1950 ዓም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው ሁለት ዓመት ያህል የወደብ አስተዳደር ኮርስ አጠናቀው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተወሰነ ጊዜ ሰርተዋል።
ከዚያም ስኮላርሺፕ አግኝተው በአሜሪካ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመት ጋዜጠኝነት እንዲማሩ አስችሏቸዋል። ከመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ጡረታ ከወጡ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትርፍ ጊዜ መምህርነት የጋዜጠኝነት ኮርስን ሰጥተዋል።
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በአሜሪካ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ በኢትዮጵያን ሔራልድና በአዲስ ዘመን ጋዜጦች በአዘጋጅነት በተከታታይ መሥራታቸው፣ በተለይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሳቸው መምጣት በፊት ለሁለት አሠርት ዓመታት የቆየውን ልማዳዊ ቅርፅና አፃፃፍ እንዲለወጥ ማድረጋቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል።
የጋዜጣውን ገጽ ቅንብር (ሌይአውት) የዜናና መጣጥፍ አቀማመጥ፣ ርዕሶች ሁሉ ሳይቀሩ ከዘመናዊው አሠራር ጋር እንዳስተዋወቁም ይነገራቸዋል።
የጋዜጣው አቋም የሚንፀባረቅበትና ‹‹ኤዲቶሪያል›› ተብሎ ለዘመናት የቆየው ቃል ‹‹አማርኛ የለውም እንዴ?›› በማለት ጠይቀው በወቅቱ የጋዜጣው ባልደረባና በቤተክሀነት ትምህርት ሊቅ የነበሩት አፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረ ኪሮስ ‹‹ርእሰ አንቀጽ›› የሚለውን ስያሜ እንዲያመጡ በማደረጋቸው ይወሳሉ።
አቶ ነጋሽ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ከለቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን መምሪያ ረዳት ሥራ አስኪያጅ፣ በመቀጠልም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል። ከጋዜጠኝነት ሙያው በተጓዳኝም እንደ ወንድማቸው አሰፋ ገብረማርያም (እንደወጣች ቀረች ደራሲ) ደራሲ የነበሩት አቶ ነጋሽ፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933 ዓም) ላይ ጭብጡን ያደረገ ‹‹የድል አጥቢያ አርበኞች›› የተሰኘ ተውኔትም አቅርበዋል። ዕውቅናና ዝና ያተረፉበት ሁለተኛ የተውኔት ሥራቸው ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርቧል።
በሌላ በኩልም ከጋዜጠኝነት በተጨማሪ ደራሲም የነበሩት ነጋሽ ስለሴተኛ አዳሪነት ምክንያትና መፍትሔ የተንፀባረቀበት ‹‹ሴተኛ አዳሪ›› ልቦለድ እናኑ አጎናፍር በሚል የብዕር ስም አሳትመዋል። በ1965 ዓ.ም ‹‹የድል አጥቢያ አርበኛ›› የተሰኘ ተውኔት ጽፈው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ለህዝብ በመድረክ ቀርቧል። እንዲሁም በ1975 ዓ.ም በህዝቡ ዘንድ አድናቆትና እውቅና ያተረፉላቸውን ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› የተሰኘ ቲያትር ወይም ተውኔት በብሔራዊ ቲያትር ለህዝብ አቅርበዋል።
ከመንግሥት ለውጥ በኋላ የፕሬስ ነፃነት መታወጁን ተከትሎ በመጣ የግሉ ሚዲያ ዘርፍ የአቶ ነጋሽ አስተዋጽኦ የሚጠቀሰው፣ የአዕምሮ ጋዜጣ አሳታሚ የነበረው ማህደር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባቋቋመው የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ዋነኛ አስተማሪ ነበሩ።
የኢትዮጵያ የስነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በሚሰጠው ሽልማት አቶ ነጋሽ ገብረማርያም በጋዜጠኝነት የ1994 ዓም የህይወት ዘመን ሽልማት ተሸላሚ ነበሩ።
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ነጋሽ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም በሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በማግስቱ ተፈጽሟል።
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም