ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ሐረር በሚገኘው የመምህራን ማሰልጠኛ ገብተውም በመምህርነት ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በወቅቱ ናሽናል ካሽ ሪጅተር ኩባንያ (ኤኒሲአር) ይባል በነበረ የአሜሪካ ተቋም ውስጥ ተቀጥረው በበርካታ ኃላፊነቶች ላይ ለዓመታት አገልግለዋል። በዚሁ ተቋም አማካኝነት ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ አቀኑ። በአሜሪካም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ ትምህርት መስክ አገኙ። ላለፉት 35 ዓመታት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች እየተዘዋወሩ የራሳቸውን የንግድ ሥራ የሠሩት እኚሁ ሰው ነዳጅ ማደያና የንግድ ሱቅ በመክፈት በስደት ላይ ለሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሥራ እድል መፍጠር ቻሉ።
የዛሬው ‹‹የዘመን እንግዳችን›› ምንም እንኳን ለረጅም ዓመታት በንግዱ ዘርፍ የተሠማሩ ቢሆንም ከስደት በፊት ‹‹ከፍቅር በስተጀርባ›› የተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፋቸውና በአዲስ ዘመን እና በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ይጽፏቸው በነበረው የተለያዩ መጣጥፎቻቸው ከፍተኛ እውቅና አግኝተውም ነበር።በቅርቡ ደግሞ ‹‹የአዕምሮ፣ የአይንና የጆሮ ምስክር›› የተሰኘ ከፊል ፍልስፍና የሆነ መጽሐፍ በማሳተም ለአንባቢዎቻቸው አድርሰዋል። በተለይም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይፅፏቸው በነበሩት ልብ ኮርኳሪ መጣጥፎች የብዙ አንባቢያንን ትኩረት መሳባቸው ይነገራል። አቶ ወርቅዬ ደምሴን አዲስ ዘመን ጋዜጣም በሕይወት ገጠመኞቻቸውና በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ዙሪያ በማነጋገር የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ለዲያስፖራው ወደ ‹‹ሀገራችሁ ግቡ፤ ሀገራችሁን አገልግሉ›› ብሎ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ እርስዎና ባለቤትዎ በአሜሪካ ያላችሁን የሞቀ ኑሮ እርግፍ አድርጋችሁ ወደ ሃገራችሁ ለመግባት ምን እንዳነሳሳችሁ ያጫውቱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ወርቅዬ፡- ልክ ነሽ፤ እዚህ የመጣነው በዋናነት መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትለን ቢሆንም በተለይ ለውጡ ከመጣ በኋላ ወደ ሃገራችን ለመግባት ከፍተኛ ጉጉትና መሻት ነበረን። እንዳልሽው ከሃገሬ ከወጣሁ በኋላ ሃገሬን ለመጎብኘት የመጣሁት በጣት በሚቆጠሩ ጊዜያት ነው። ከሠላሳ ዓመት በላይ በአሜሪካ የራሴን የንግድ ተቋም ከፍቼ ጥሩ ኑሮ እኖር ነበር። ይሁንና የፈለገውን ጥሩ ነገር ቢኖርሽ እንደሃገር የሚሆን የለም። ሁሌም ቢሆን የገዛ ሃገርሽ ባለመሆኑ ባይተዋርነት ነው የሚሰማሽ። ብዙዎቹ እንደሚሉትም እኔም ለእነዚያ ዓመታት ሙሉ ልቤ ከሃገሬና ከሃገሬ ሕዝብ ጋር ነበር። በተለይ እድሜሽ እየገፋ በመጣ ቁጥር እስከመቼ ነው በሰው ሀገር ? የሚል ጥያቄ በመጠየቅ ነው የምትኖሪው። የምታገኚውን ገንዘብም ሆነ ሃብት ከደሃው ሕዝብሽ ጋር ተቋድሰሽ ከምትበይው ጋር ፈፅሞ አይነፃፀርልሽም።
እኔ እንዳውም ይህንን ወደ ሃገር የመመለስ ሃሳብ ብዙ ካሰብኩበት በኋላ ለባለቤቴ ሳማክራት ያለምንም ማቅማማት በደስታ ነው የተቀበለችው። ብዙዎቹ ጓደኞቻችንም በውሳኔያችን ተደንቀዋል፤ጥቂት የማይባሉትም ወደ ሃገራቸው መመለስ እንደኛ እየፈለጉ በኑሮ ምክንያት ባለመቻላቸው ዘወትር እየተቆጩ ነው የሚኖሩት። እርግጥ ነው ከመጣሁ ሁለት ዓመት ቢሆነኝም አሁንም አልፎ አልፎ እየሄድኩኝ እመጣለሁ፤ ግን ቋሚ ኑሮዬን ያደረኩት እዚሁ ሃገሬ ላይ ነው። በአጠቃላይ ወደ ሃገሬ መመለስ መቻሌ ለእኔ ትልቅ እፎይታና ሰላም ነው የሰጠኝ። እርግጥ ነው ከመምጣታችን በፊት እንዴት ጦርነትና ችግር ወደአለባት ሃገር ትሄዳላችሁ ያሉን ነበሩ። ነገር ግን አሜሪካም ሆነ እዚህ ሞት ከመጣ ማምለጥ አይቻልም፤ ፈጣሪ የፈቀደው እንጂ የሚሆነው እኛ ስለሸሸን ከሞት መቅረት አንችልም። ስለዚህ ውሳኔዬ ትክክል ነው ብዬ ነው የማስበው። ደግሞም በኢትዮጵያ ያለው ሰላምናመተሳሰብ በአውሮፓናበአሜሪካ አይገኝም። እውነቴን ነው የምልሽ ይህንን ተሳስበንና ተደጋግፈን የመኖር ባህላችንን እንደቀላል ልናየው አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ብዙ እድሜዎትን በንግድ ሥራ ያሳለፉ ሰው ቢሆንም ሁለት መጽሐፎችንና የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍ ይታወቃሉ። እስቲ ስለዚህ ሥራዎች በጥቂቱ ያስታውሱን?
አቶ ወርቅዬ፡- እውነት ነው፤ በሙያዬ አካውንታትና ብዙ ዓመታትም ንግድ ሥራ ላይ ብቆይም መጻፍና ማንበብ በጣም ነው የሚያስደስተኝ ። በተለይ ራሴን ከጊዜው ጋር ማራመድና እውቀት ማግኘት እፈልግ ስለነበር ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መጽሐፍ ሳልመርጥ የማንበቡ ልምድ አለኝ። የሚሰማኝና የተገነዘብኩትን ጽፌ ለአንባቢዎች በማድረሴ ከፍተኛ ደስታ ነበር የሚፈጥርልኝ። በተለይ በእኛ ዘመን እንዲህ እንዳሁኑ የመዝናኛ አማራጮች ያልበዙበት ወቅት ስለነበር በአዲስ ዘመንና በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ላይ የማወጣቸው መጣጥፎች ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፈውልኝ ነበር። ጽሑፌን ግን በቀጥታ ለታላቁ ደራሲና በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለነበረው በዓሉ ግርማ በቀጥታ የምልክለት በመሆኑ እዛ የሚሠሩት ሠራተኞች ሳይቀር ስሜን እንጂ በመልክ አያውቁኝም ነበር። በዚህ የተነሳ ብዙዎቹ የምሠራቸውን ጽሑፎች በዓሉ ግርማ እየጻፈ በብዕር ስም የሚያወጣው ይመስላቸው ነበር።
የራሴንና የመጀመሪያውን ከፍቅር በስተጀርባ የተሰኘውን ልብወለድ መጽሐፌን ከፃፍኩኝ በኋላ ነው ብዙዎቹ ስለእኔ ትክክለኛ ማንነት ያወቁት። ይህንን መጽሐፍ አሜሪካ አሳትሜው እዚህ ለገበያ ካቀረብኩት በኋላ ተመልሼ ሄድኩኝ። መጽሐፉ በወቅቱ በጣም ተወዶ ስለነበር ወዲያውኑ ነው ተሸጦ ያለቀው። ያሳተምኩት ትንሽም ስለነበር የወደደው ሰው ሁሉ ሊያገኘው አልቻለም። ሁለተኛውና ‹‹የአይን የጆሮና የአዕምሮ ምስክር›› የተሰኘው መጽሐፌም ሃሳብ የተፀነሰው አሜሪካ ሳለሁ ነበር። ይህ መጽሐፍ በዋናነት መነሻው የሰው ልጅ ኑሮ ላይ ያተኮረ ሲሆን ይዘቱ የሚያጠነጥነው ሁሉም ሰው እንዴት ራሱን ችሎ መቆም እንዳለበት፤ በተለይ በሌሎች መሪነት ወደ ገደል ከመግባቱ በፊት በራሱ እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት፤ የተነገረውን ሁሉ ዝም ብሎ ከመቀበል ይልቅ ለምንና እንዴት? ብሎ የመጠየቅ ባህል በምን መልኩ ማዳበር እንደሚገባው የሚተነትን ዝርዝር የያዘ ፍልስፍና እና ምርምርም አዘል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው የወያኔ አስተዳደር ዲያስፖራውን ሳይቀር በማንነት እንዲከፋፈልና አንድነት እንዳይኖረው ከፍተኛ አሻጥር ሲደረግበት እንደነበር ይታወቃል። እስቲ በእርስዎ የአሜሪካ ቆይታ የነበረው ሁኔታና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ‹‹በቃ›› ወይም በ‹‹No more›› ዘመቻ ዳግም አንድ ሆኖ ለሃገሩ በኅብረት የቆመበት ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ይንገሩን?
አቶ ወርቅዬ፡-እንዳነሳሽው ሕዝቡን በጎሳ እንደከፋፈሉትና እርስ በእርስ እንዲባላ ማድረጋቸው ሳያንስ በስደት ላይ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በልዩነቱ ላይ ብቻ አተኩሮ እንዲሠራ አድርገውት ነው የኖሩት። በተለይ እንደእኔ አይነቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ለሚያምነው ዲያስፖራ ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር። የሃገራችንንም ገፅታ በማበላሸት የነበረው አሉታዊ ሚና በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ይሁንና ሕዝብም ሆነ ሃገር የመከፋፋሉ ድብቅ ሴራ በእኛ ሃገር ብቻ የተከሰተ አይደለም። መላው ዓለም ድሮም ሆነ አሁን በዚህ በመከፋፈል አጀንዳ ሲታመስ ነው የኖረው፤ አሁንም የዚሁ ችግር ሰለባ የሆኑ በርካታ ሃገራት አሉ። ለምን ይመስልሻል ኮርያ ለሁለት የተከፈለችው? የራሺያ 15 ጠቅላይ ግዛቶች ከአንድነት ወደ ትንንሽ ሃገራት የተቀየሩት? ፓኪስታንስ ከሕንድ ለምን ተገነጠለች? ኢትዮጵያም ኤርትራን እንዴት አጣች? በጠቅላላው በዓለም ውስጥ ያለው መከፋፋል ከየት መጣ ብለሽ ብትጠይቂኝ የእኔ እምነትና ምላሽ የሚሆነው ከዚሁ ሁሉ በስተጀርባ ያለውና በምዕራባውያኑ የሚመራው የአዲሱ የዓለም አስተዳደር እየተባለው የሚጠራው የክፉ መንፈስ ሥርዓት ነው።
አሁንም ትግራይን ለመገንጠል ይሞክራሉ። እንዳልኩሽ ይህ እየሆነ ያለው በትልቅ ድርጅት የተቋቋመው አዲስ የክፉ አሠራር ሲሆን በተለይ በኢኮኖሚ የበለፀጉት የአውሮፓ ሃገራትና አሜሪካ ላይ በስፋት ተንሰራፍቶ እየሠራ ይገኛል። ብዙዎቹን ሃብታም ያደረገው ይህ ድርጅት መሠረቱ ግን ሰይጣናዊ ተልዕኮ ይዞ ሰዎችን እርስ በእርስ በማጋደልና በማጫረስ ነው የሚንቀሳቀሰው። በእርግጥ አሁን ያለው ትውልድ በዚህ ክፉ ድርጅትና እየሠራ ስላለው የክፋት ሥራ ዙሪያ ጥልቅ ግንዛቤ አላቸው ብዬ አላምንም። ለዚህም ነው የዓለማችን ሃብታሞች በሥራ ብቻ ሃብታም የሆኑ የሚመስላቸው። ግን አይደለም። ለምሳሌ እነ ቢልጌትና ሮክ ፊለር የተሰኙ ሰዎች የዚሁ ክፉ አስተዳደር ተከታዮች ናቸው። ከእያንዳንዱ ድጋፋቸውና ልማታቸው በስተጀርባ ይህንኑ ድብቅ አጀንዳ ነው የሚያስፈፅሙት።
እንዳነሳሁልሽ በምዕራባውያኑ የሚመራው ይህ ክፉ አስተዳደር ሃገራትን በመከፋፈልና የአንድ ሃገር ሕዝብን በመለያየት ለራሳቸው በሚመች መልኩ ዓለም የነውጥና የጥፋት መናኸሪያ የማድረግ እቅድ ይዞ ነው እየሠራ ያለው። ምዕራባውያኑ እኛን ድሮም ቢሆን አሁንም በሃይማኖትና በጎሳ በመከፋፈል ከፍተኛ ሴራ ሲሠሩ እንደነበር ይታወቃል። ሆኖም ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ልትደፈርላቸው ባለመቻሏ እቅዳቸውን ሊያሳኩ አልቻሉም። አሸባሪው የትሕነግ ሰዎች የምዕራባውያን አጀንዳ አስፈፃሚ እንደመሆናቸው ሕዝቡን በውጊያም ሆነ በጎሳ ልዩነት በመፍጠር ለመበታተን ሞክረዋል፤ አሁንም እየሞከሩ ናቸው። አብዛኞቹ የአሜሪካ ድርጅቶች በእርዳታ ሰበብ ሕዝቡን ለመከፋፋል ጥረት ያደርጉ የነበረበት ምክንያት ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል ነው። እንዳሰቡት ኤርትራን አስገንጥለዋል፤ አሁን ደግሞ ትግራይን ለመገንጠል ዳር ዳር እያሉ ነው።
ምዕራባውያኑ በአሸባሪው ትሕነግ አማካኝነት ከፋፋይ ፖሊሲ ቀርፀው አማራን ከኦሮሞ ሲያባሉ ነው የኖሩት። አሁንም ለዓመታት በሰው አዕምሮ ላይ የተዘራው የክፋት አጀንዳ ዛሬ ላይ ከማቆጥቆጥ አልፎ እየተጫነው ነው የሚገኘው። የሁለቱም ብሔረሰብ ሕዝቦች አብሮ የተጋባ፤ አብሮ በሰላምና በፍቅር የኖረ የዋህ ሕዝብ ነው። ይሁንና አሁን ላይ ከዚህ ቀደም አይተን በማናውቀው መልኩ እርስ በእርሳችን በሰበብ በአስባቡ እየተጋደልን የምዕራባውያኑ መሳቂያና መጫወቻ ሆነናል። በመሠረቱ የአንድን ሃገር ሕዝብ መቀነስ ለዚህ ድርጅት ትልቅ ነገር ነው። ምክንያቱም ዓላማውም ይኸው ስለሆነ ነው። በነገራችን ላይ ሁለተኛው መጽሐፌ በዚሁ ጉዳይ ላይ በዝርዝር ነው የፃፍኩት።
እንደሚታወቀው አሸባሪው ትሕነግ ከምሥረታቸው ጀምሮ በዚሁ የምዕራባውያኑ የክፋት ፖሊሲ የሚታዘዙ በመሆናቸውና የመሣሪያ ድጋፍ ስላገኙ ነው ኢትዮጵያን ተቆጣጥረው እንዳሻቸው የኖሩት። እነአቦይ ስብሐትና መለስን አስተምረው እና ኮትኩተው ጫካ የላኩት እነሱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከውጭ በሚያገኙት የመሣሪያ ድጋፍ ታግዘው የኢትዮጵያን ሕዝብ በዝብዘው ባካበቱት ሃብት ነው ሲንፈላሰሱ የቆዩት እንጂ የእኔ ቢጤ ድሃ አልነበሩም እንዴ?። የኢትዮጵያ ሕዝብም የወያኔን የክፋት አጀንዳ ቀድሞ ስላልተገነዘበ ነው እርስ በእርስ ሲባላ የኖረው። አሁን የምዕራባውያኑም ሆነ የወያኔ የክፋት ዓላማ ግልጽ ሆኖ በመውጣቱ ልክ እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም ሊያተራምሱን የማይምሱት ጉድጓድ የለም። ስለዚህ ይህንን የክፋት አጀንዳ መንገንዘብና መንቃት አለብን። ልክ እንደ ቀደምቱ ጊዜ አንድነታችንንና ኅብረታችንን ልናጠናክር ይገባል። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ የዓለም ሕዝብ የሚቀናብንና ድንቅ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። ፈጣሪም በቅዱስ ቃሉ ደጋግሞ ቃል የገባላት ምድር በመሆንዋ ምዕራባውያኑም ሆነ ሌሎች ጠላቶቿ ያሰቡት አይሳካቸውም። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደነበረው ኅብረታችንና ማንነታችን መመለሳችን አይቀርም። ደግሞም ሃገር ስትረጋጋ ወደነበርንበት ሁኔታ መመለሳችን አይቀርም፤ ያሳለፍነውን መጥፎ ትውስታ በሙሉ ረስተን በአዲስ ተስፋ ሃገራችንን ቀና የምናደርገበት ,ሁኔታ እንደሚፈጠር ሙሉ እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ እያደረገ ያለውን ጫና እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ወርቅዬ፡- አሁንም ቢሆን ቀድሜ ያነሳሁልሽ ጉዳይ ነው ምክንያቱ። ይህን ድርጅት ያቋቋሙትም ሆነ የሚመሩት እነሱ ናቸው።ያቋቋሙትን የዓለም ሃገራትንበሥራቸው ለማስገዛትና የበላይነታቸውን አስቀጥለው ለመጠበቅ ነው። በእኔ እምነት ይህ ድርጅት የተቋቋመበት አጀንዳ ይህ ሆኖ ሳለ ከዚህ ድርጅት መልካም ነገር መጠበቁ በራሱ የዋህነት ነው የሚመስለኝ። ምክንያቱም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሲጠቀም የኖረው ምዕራባውያኑን ነው እንጂ እንደኛ በድህነት ውስጥ ላሉ ሃገራት ወይም ሕዝቦች አይደለም።
በሌላ በኩል ደግሞ እዚህ የሚደረገውንና አሸባሪው ቡድኑ የሚሠራውን ሴራና ጥፋት አያውቁትም ብዬ አላስብም። በተጨባጭ ያውቁታል። ይህ ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን በደል፤ ንፁሓንን በግፍ ሲገድልና ሲያሰቃይ እንደነበር አሳምረው ያውቃሉ። መረጃውም አላቸው። ሁሉንም ነገር በሳተላይት ይከታተላሉ። ሆኖም ግን እንዲሆን የተፈለገውም ሆነ የሚፈለገው እንዲህ እንድንሆን፤ መላው ሕዝብ እርስ በእርስ ተባልቶ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ ስለሆነ ከእዚህ ጋር ተደራደሩ እያሉ በሌላ በኩል መሣሪያ የሚያቀብሉትና አይዞህ የሚሉት እነሱው ራሳቸው ናቸው። ስለዚህ ለእኔ ከዚህ ድርጅት ምንም ዓይነት መልካም ነገርና ፍትሕ መጠበቁ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ከዚያ ይልቅ ለሚመጣው ነገር ራስን ማዘጋጀትና በኅብረት መቆም ነው የሚገባው።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ከዚህ አኳያ የሃገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ምን መሠራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ወርቅዬ፡- በእኔ እምነት ይህ ሥራ በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ሃገርን ለማስተዳደር በሕዝብ ኃላፊነት የተሰጠው ብቸኛ አካል እንደመሆኑ ዳር ድንበር የመጠበቅ፤ በሃገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ለሚፈተፍቱም አጥጋቢ መልስ መስጠትና ራስን ችሎ የመቆሙ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ነኝ። በዚህ ረገድ የሃገሪቱ ሕዝብ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግልፅ ማድረግና ለሚሠራው ሥራ እንዲሁም ለሚያራምደው የውጭ ፖሊሲ ስኬታማነት ኅብረተሰቡ ከጎኑ እንዲቆም የማስተባበር ሥራ መሥራት አለበት። አንድ ጊዜ ደግሞ ሁሉንም ነገር በመንግሥት የፖለቲካ ሰዎች ፍላጎት ብቻ ከመወሰን ይልቅ የሕዝቡን የልብ ትርታ ሊያደምጥ ይገባል።
እንደተባለው ግን አሁን ላይ አሜሪካም ሆነ ሌሎቹ የምዕራቡ ሃገራት በኢትዮጵያዊ ሉዓላዊነት የሚዳፈር ጫና እያደረጉ ያሉት ልክ ደርግ ላይ ያደረጉት የነበረውን ዓይነት ነው። ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም እንደዚያ ከሚወዳት ሃገሩና ሕዝቡ ጋር ድንገት ተለይቶ ጥሎ እንዲጠፋ የተደረገው በእነዚሁ የምዕራባውያኑ ተጽዕኖ ነው። አሁንም ለእነሱ የሚመች አስተዳደር እስከሌለ ድረስ በእኛ ሃገር ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ይቦዝናሉ ብዬ አላምንም። ምክንያቱም እነሱ በዚህች ሃገር ላይ የሚሹት ነገር እስኪሳካላቸው ድረስ የቱንም ያህል ሕዝብ ቢያልቅ ግድ የላቸውም። አሁንም ደጋግሜ ማንሳት የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ኅብረቱን አጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ የአሜሪካውያንም ሆነ ሌሎች ምዕራባውያን የቱንም ያህል ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉ ሊያሸንፉንም ሆነ ሊበታትኑን አይቻላቸውም። ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ፈጣሪ ቃል የገባላት ሃገር እንደመሆንዋ ፍርዱን ይሰጣል ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለው የሰላም ንግግር እንዳው ከአሸባሪው ትሕነግ ባህሪ አንፃር ለውጤት ይደርሳል ብለው ያስባሉ?
አቶ ወርቅዬ፡-በመሠረቱ የሰላም ንግግር የሚደረገው ምን ለማግኘት እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም። እንደእኔ እምነት ምዕራባውያኑ በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር እንዲነጋገር ጫና እየፈጠሩ ያሉት ትግራይን ለመገንጠል ብቻ ነው። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ይህንን አጀንዳ ቀድሞ የተገነዘበው በመሆኑ እንደማይቀበለው ፅኑ እምነት አለኝ። የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ቀድሞ ወያኔን ባለማወቅ ሲደግፍ ቢኖርም አሁን በዚህ ጦርነት ምክንያት ልጆቹን ካጣ በኋላ ፊቱን አዙሮባቸዋል። እንዳውም የሚተነፍስበት እድል ስላላገኘ እንጂ መልሶ ‹‹ሆ›› ብሎ የሚነሳባቸው የትግራይ ሕዝብ እንደሆነ ነው የማስበው።
አሁን ላይ ከአንዳንድ የትግራይ ተወላጆች እንደምንሰማው ፈጽሞ እንኳን የመገንጠሉን ሃሳብ ሊቀበል ቀርቶ ለዚህ የዳረገን ይህ ክፉ ድርጅት ነው ብለው በታቃራኒ ነው ተሰልፈው የሚገኙት። በፊት ክደው የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ሳይቀሩ አሁን ‹‹ኢትዮጵያ ሃገራችን ናት›› ብለው ተነስተዋል። በትሕነግ ሰዎች በየእለቱ የሚነገራቸውንም የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ፈፅሞ አይቀበሉትም። ምክንያቱም አሁን ሕዝቡ ስለነቃና እውነታውን ስለተገነዘበ ነው። ስለዚህ ንግግሩ በምንም መልኩ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብዬ አላስብም።
አዲስ ዘመን፡- ምንአልባት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በንግግሩ በሚቀርቡት ሃሳቦች ባይስማማ አሁን ከሚደረገው በላይ ሃገሪቱ ላይ የሚደረገው ተፅዕኖ ይበረታል ብለው አይሰጉም?
አቶ ወርቅዬ፡- በነገራችን ላይ ይህ የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ቀደምም ቢሆን በእኛ ላይ ተፅዕኖ ሲያደርጉ ነው የኖሩት፤ አሁንም ቢሆን እንድንበረከክላቸው ሲሉ ጫና መፍጠራቸው አይቀርም። የምዕራባውያኑ ተፅዕኖ የቱንም ያህል ቢበረታ ተቋቁመን የሃገራችን ሉዓላዊነት ማስከበር ይገባናል። የኢትዮጵያ መንግሥት በፍፁም እጅ ሊሰጥ አይገባም። በአቋሙ መፅናትና የሃገሩን ዳርድንበር ማስከበር አለበት ብዬ ነው የማምነው። ግን ደግሞ ጫናው ጊዜያዊ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል እንጂ ፈርተን ከአቋማችን ወደኋላ ማፈግፈግ የለብንም። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እያራመዱት ያለው አቋም ትክክለኛና የኢትዮጵያውያን ያልደፈር ባይነት ወኔ በትክክል የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ነው የምገነዘበው። በተለያየ መልኩ ሊያስማሙትና ሊያታልሉት ጥረት ቢያደርጉም ቀድሞ ስለነቃባቸው አሻፈረኝ ነው ያላቸው። በመሆኑ በዚህ በኩል በወሰደው እርምጃና ውሳኔ እኔ ላመሰግነው እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራው ሃገርን በማሳደግ ረገድ በምን መልኩ ነው ሚናውን ሊወጣ የሚገባው?
አቶ ወርቅዬ፡- ይቅርታ አድርጊልኝና ከዲያስፖራው ብዙ መጠበቅ የዋህነት ነው ብዬ ነው የማስበው። ውጭ ስለኖረ ብቻ የተሻለ ገቢ አለው ማለት አይደለም። እኔ በኖርኩበት ሃገር እንኳን ብዙ ዲያስፖራ የእለት ጉርሱን ከመሸፈን ያለፈ ሃብት ያፈራው በጣት የሚቆጠረው ነው። እንዳውም በከፋ ችግር ውስጥም ያሉ አሉ። አሁንም ቢሆን ዲያስፖራው ድጋፍ እያደረገ ያለው ሃገር ስትጎዳ ዝም ብሎ ማየት ስላላስቻለው እንጂ ያንን ያህል የሚያወላዳ ሃብት ስላለው አይደለም።
በመሆኑም ለእኔ ዲያስፖራው መጥቶ ሃገር እንዲያሳድግ ከመጠበቅ ይልቅ እዚሁ ያለው ሕዝብ አንድነቱን አጠናክሮ ቢሠራ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብዬ ነው የማምነው። በተለይ መንግሥት ከሁለት ዓመታት በላይ በጦርነት የላሸቀውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ትልቁን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ባይ ነኝ። ለዚህ ደግሞ ሕዝቡን መደገፍና ሥራ ፈጣሪ የሚሆንበትን ሥርዓት ማበጀት ይገባዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ከማንም በላይ ደግሞ አርሶአደሩን በመደገፍ የምግብ ዋስትናችንን የምናረጋግጥበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። ደግሞም ተደጋግሞ እንደሚባለውም አብዛኛው ሕዝብ በግብርና ሥራ ላይ የሚተዳደር እንደመሆኑ ይህንን የኅብረተሰብ ክፍል መደገፍና ራሱን ችሎ እንዲቆም ማድረግ ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ወርቅዬ፡-እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም