የነፍሴ ራቁት ሴትነቷን ለብሷል..ሀሳቤ ጀምሮ የሚያበቃው እሷ ጋ ነው። እሷን ሳስብ ባልሞት እላለው፣ ለዝንታለም ብኖር እላለው፣ ደጋግሜ ብፈጠር እላለው። እሷን ሳስብ..ሀሳብ ይጠፋኛል..ጥበብ ይርቀኛል..ደግሞም ሀሳብ ይሞላኛል..ጥበብ ይወረኛል።
እሷን ሳስብ..ለብቻዬ እስቃለው..አፌ ውስጥ ሞልቶ የሚፈስ የምስጋና መዐት ይፈጠራል። እሷን ሳስብ እንደ እስቅያስ፣ እንደ ሙሴ፣ እንደ አብረሀም፣ እንደ ሰለሞን፣ እንደ ኤሊያስ ሀይል ይጎበኘኛል። እሷን ሳስብ ደስ የሚል ደስታ ደስ ይለኛል።
እሷን ሳስብ ከምድር ወደ ሰማይ በተዘረጋ የወርቅ መሰላል ላይ እመላለሳለው። በእግዜር ታቅፌ፣ በእየሱስ ተስሜ..እሳታማ መንበሩን ነክቼ ሰው እሆናለው። ነፍሴ ማረፊያ ታጣለች..እዛም ልሂድ እዚም ልርገጥ በብኩርና ፊት ነኝ..እሷን ሳስብ ምድር ሁሉ መንገዴ ናት።
እሷን ሳስብ ብዙ ነኝ። እልፍ መዐት። ከዚህ እስከዛ ጥግ የሌለኝ። አለም ምድር የማትበቃኝ..አድማስ ጠረፍ የጠበበኝ። እሷን ሳስብ ከዋክብታማ ሰማይ ነኝ..በብርሀን የሚያበራ፣ በጨለማ የደመቀ ጸደያማ ቀለማት። ሳቅ ያረበበት፣ ፈገግታ የተዋበበት ነፍስና ስጋ።
ፈንጥዤ ተኝቼ ፈንጥዤ እነቃለው..ከንጋት መልስ ህይወቴ ውስጥ እሷ እንዳለች ሳስብ በራሴ ውስጥ ሌላ እሆናለው። ፈንጥዞ ተኝቶ ፈንጥዞ መንቃት ምን እንደሚመስል በእሷ ነው ያየሁት..በነፍሴ አለላ።
እያደርኩ አዲስ ነኝ..እየከረምኩም ሌላ። እሷ ጋ እስክደርስ ቅርቤ ሩቅ ነቅ..ሩቄ ላመል ነው። እሷጋ እስክደርስ ሀሳቤ እንዥርግ ነው..ዝንተ አለምን መሳይ። ተራምጄ እስክደርሳት፣ ተንጠራርቼ እስክነካት የፊት ለፊቴ ገጽዋ የምጻትን ያክል ይርቀኛል። አቤት ስወዳት! አለም የእሷን ያክል መደሰቻ አልሰጠችኝም። አለም በኩስተራው የምታውቀው ፊቴ እሷ ፊት ነው የሚፈገው። ሳቄ እሷ ፊት ነው የሚጀምረው። የምንም ነገር መጀመሪያዬ ናት..እሷን አልፌ፣ እሷን ተሻግሬ የምጀምረው ምንም የለኝም። ፊተኝነትና ኋለኝነት ሳያሸብሩኝ በመኖሯ ውስጥ አለሁ። በነፍሴ እርሻ ላይ አቆጥቁጣ ደስታና መከራዬ ሆና ትጠዘጥዘኛለች..እጠዘጠዝላታለሁም። በእሷ ያወኩት..ከእሷ የተማርኩት ብዙ እውነት አለኝ..ከእውነቴ አንዱ ምድር ላይ ደጋግሜ ብፈጠር የእሷን ያክል መደሰቻ አላገኝም የሚለው ነው።
እስካያት..ዛጎል መሳይ አይኖቿን እስክሳለማቸው ተቅበዝባዥ ነኝ። እስክነካት..የገላዋን አንድ ቦታ እስክስመው ረፍት የለሽ ነኝ። በውበቷ ገዳም..በነፍሷ አጥቢያ ውስጥ የተሸሸኩ ባህታዊ ነኝ። ከጽድቅ ሌላ..ከአኮቴት ሌላ አመል የሌለኝ። ባለሁበት የትም ቦታ ላይ አለች። እንደ መልከ ማርያም እየደገምኳት..የነፍሷን ሰዐታት እያነበነብኩት ካለሁበት ወዳለችበት እተማለው። አተማመሜ ያስደንቀኛል..ወዴትም ባልተራመድኩት የችኮላ ርምጃ ነበር የምፈጥነው። ወደ እሷ ስሄድ ዝግ ብዬ አላውቅም..ከእግሮቼ የሚፈጥኑ ብዙ ሀሳቦች አሉኝ..ከሀሳቤ የሚፈጥኑ ብዙ ህልሞችም።
ሳያት ለፈንጠዝያዬ ምድር አትበቃኝም..ለሳቄ..ለፍንደቃዬ አለም ትጠበኛለች። ሳያት ቀለያት አይበቃኝም..በጋቴ እሰነዝረዋለው። በክንዴ እመትረዋለው። ሳያት ሰማይ የጸደይ መልክ ይጸንሳል። ሳያት ጀምበር ብርሀን ታረግዛለች፣ ጨረቃ ጸዳል ትለብሳለች። ሳያት ሌላ ነኝ…እንደዚህ ቀደሙ ደማቅ። ሳያት በእኔ ውስጥ የማይሆን የለም..ተፈጥሮ እውነት ስታ በእኔና በእሷ ውስጥ ልክ ትሆናለች። አለም ያላየችው ብዙ ተዐምር እሷን በማየቴ ውስጥ ይስተናግዳል።
እየሳኩ ሄጄ እየሳኩ እነካታለው። እያሰብኳት ሄጄ እያሰብኳት አቅፋታለው..እዋሀዳታለው። የክረምት ጠል እንደጠጣች የጸበል ዳር በለስ ልጃገረድ ፊቷ በፈገግታና በውበት ተዥጎድጉዶ ክንዴ ላይ ሲያርፍ ያን ነው ህይወት የምለው። ያን ነው መኖር የምለው። ያ ነው ማመስገኛዬ። ያ ነው በህይወቴ እንዳላጣው የምሰጋው አምሮቴ። ያን ከሺ ብርቅ ልቆ፣ ከሚሊዮን እድል ልቆ ወደ እኔ የሚቦርቅ..ወደ እኔ የሚንጠራራ ፊቷን ሳየው ህይወት ባልሰጠኝ፣ መኖር ባልቸረኝ ክብርና ማዕረግ ውስጥ እንደቆምኩ አስባለው።
አልጋው መሀል ላይ እንደተጋደመች የሚስቅ ፊቷን በሚስቅ ከንፈሬ እስመዋለው። ሊያቅፈኝ የሚንጠራራ እጇን ሊያቅፋት በተዘረጋ እጄ እቀበለዋለው። ስታየኝ የምትሆነው መሆን ሳያት ከምሆነው መሆን ጋር ይዛመድብኛል። እኔ ብቻ እንደማልወዳት፣ እኔ ብቻ እንደማላፈቅራት፣ እኔ ብቻ እንደማልሳሳላት፣ እኔ ብቻ እንደማልናፍቃት፣ እኔ ብቻ እንደማላስባት፣ እኔ ብቻ እንደማልጨነቅላት በምትሆነው መሆን እደርስበታለው። የማልስመው የሰውነት ክፍል የላትም..ከእሷ ጋር ስሆን እንደሳምኳት ነው። እሷም የምትሰስተኝ አንዳች የላትም..ሁኚ እንዳልኳት ትሆንልኛለች።
ነፍሴ መረጋጊያዋ ናት። ፊቷ ላይ እልፍ አእላፍ የዝምታ ቅኔን ትቀኛለች። የእሷን ፊት እንደማየት፣ የእሷን ገላ እንደመንካት በምድር ደስታ የላትም። እግዜርንም በእሷ ያመሰገነችውን ያክል በምንም አላመሰገነችውም። ነፍሴ ለብዙ ነገር አሜን ብላ ታውቃለች፣ ለብዙ ነገር እጅ ነስታ ታውቃለች፣ ለብዙ ነገር ወደ ሰማይ አይታ ታውቃለች እንደ እሷ የሆነችበት ግን የላትም።
እጄን በጀርበዋ ውስጥ ሸቅሽቄ አነሳኋትና ክንዴ ላይ አሳርፋታለው..ደረቴ ላይ እጥላታለው። ጠረኗ ከአለም ይሰውረኛል። ከወንድነቴ ዘልቆ በነፍሴ እንጦሮጦስ ውስጥ ያርፋል። አለም የሌላት..ጸጋን ያስከነዳ የአንገት ስር ሽታ አላት። ከእሷ ውጪ የትም የማይሸት፣ የትም የማይጠርን መዐዛ። ከእሷ አንገት ውጪ፣ ከእሷ ገላ ውጪ፣ ከእሷ ቀሚስ ውጪ በየትም ቅዱስ ቦታ ላይ የማይገኝ ሽታ። ያን የገላዋን ጠረን ተዋሀድኩት። ደረቴ ላይ አስተኝቼ አስተዋልኳት..ንጹህ ናት..ንጹህ ያልሆነ ምንም የላትም። አይኗን፣ ቅንድቧን፣ አፍንጫዋን፣ ጉንጩዋን ሁሉ ነገሯን እየነካካሁ እስማታለው። የምሆነው መሆን ያስቃታል። ፊቴ ላይ ትፈነድቃለች። ሳቋ ሳያስቀኝ ቀርቶ አያውቅም። አብሬአት እስቃለው..አብሬአት እፈነድቃለው። ንጹህ ያልሆነ ምንም የላትም ብያችሁ የለ? ሳቃም እንደ ገላዋ ንጹህ ነው። ደረቴ ላይ አስደግፌአት ንጹህ ሴትነቷን እንደፈለኩ እሆንበታለው። በንጽህናዋ ውስጥ ንጹህ ሆኜ እፈጠራለው። ያኔ ነፍሴ ክንፍ ያላት ይመስለኛል..በደስታ የማትበርበት የለም።
ክንዴ ላይ ታቅፌ፣ ደረቴ ላይ ለጥፌ ሁሉ ነገሯን ሳምኩት። ስስማት ነፍሴ ውስጥ ጣይ ትወጣለች፣ ጀምበር ትፈነጥቃለች፣ በ ልቤ አደይ ያቆጠቁጣል..መስከረምን እሆናለው። ግን ስሜአት አልጠግብም። ከንጹህ ሳቋ፣ ከንጹህ ፍንደቃዋ ተዋህጄ አረካም። ከአጠገቤ ሸሸት ስትል በረሀ ነኝ..።
በነፍሴ ሁሉም ቦታ ላይ ጽፌአታለው። በመንገዴ ሁሉም ቦታ ላይ አትሜአታለው። የሌለችበት ወንድነት የለኝም። ጉንጩዋ የቤተክሲያን ያክል፣ የካህን እጅ ያክል፣ የመስቀልን ያክል ያምረኛል። ፊቷ እንደ ብር ወለባ፣ እንደ አመልማሎ፣ እንደ ዘበናይ ፈርጥ ያምረኛል። ሳቋ የምስራቅ ደፌ ነው..የተስፋዬ መውጫ። እግዜርን አሜን እለዋለው..እግዜርን ተመስጌን እለዋለው..ክብርህ ይስፋ እለዋለው..በእሷ በስድስት ወር ህጻን ልጄ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015