‹‹ በአዲስ ዓመት ምርጥ ምርጥ ምግቦችን እና መጠጦችን በአዲስ መልክ ጀምረናል። ›› የሚለው የመጠጥ ቤቱ ማስታወቂያ ዘውዴን አስገርሞታል። ዘውዴ መታፈሪያ ወደ መጠጥ ቤቱ ሲገባ ለራሱ ‹‹ ኑሮ የተወደደው እኔ ላይ ብቻ ይሆን እንዴ ?›› ሲል ጠየቀ። ደገመና ‹‹ እንዴት እንዲህ ኑሮ እየተወደደ በአዲስ መልክ ምግብና መጠጥ መነገድ ይጀመራል? ›› በማለት አጉረመረመ።
ተሰማ መንግስቴና ገብረየስ ገብረማሪያም ግን ዘውዴን ያሳሰበው ጉዳይ እነርሱን አላሳሰባቸውም። እንደውም የኑሮ መወደድ ጉዳይ ሃሳባቸው ላይ አልመጣም። ሰው የሚያየውም ሆነ የሚያዳምጠው የሚፈልገውን ብቻ በመሆኑ ‹‹ በአዲስ ዓመት ምርጥ ምርጥ ምግቦችን እና መጠጦችን በአዲስ መልክ ጀምረናል። ›› የሚለው የመጠጥ ቤቱ ማስታወቂያን ጭራሽ አላዩትም። ስለዚህ እነተሰማ የዘውዴ ዓብይ ጉዳይ ለእነርሱ ተራ ነው። ከኑሮ መወደድ ይልቅ እነርሱ ‹‹የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በሁሉም ግንባር እጅ እየሰጡ፤ እየተበተኑ ነው። ፈርጠጠው በረሀ እየገቡ ነው›› የሚለው ዜና አስደንቋቸዋል፤ እንዲሁም አስደስቷቸዋል። ምክንያቱም ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ከሆነ ቡድን ይህ አይጠበቅማ!
ገብረየስ ከትህነግ ሽንፈት ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት እና ትህነግ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙበት የሰላም ንግግር ደቡብ አፍሪካ ላይ መጀመሩ አስፈንጥዞታል። ገብረየስ እርሱ በደስታ ሰምጦ ዘውዴ አኩሩፎ ሲያየው በጥቂቱ ገረመው። ለዘውዴ ጥያቄ አቀረበ። ‹‹ ምነው ብቻህን ስብሰባ ገባህ ? ›› አለው። መተከዙ ፣ዝምታን መምረጡ ስላላስደሰተው። ዘውዴም ‹‹ ያልተነካ ግልግል ያውቃል፤ እናንተማ ምንም የሚያስጨንቃችሁ ነገር …። ›› ብሎ ንግግሩን እንኳን ሳይቋጭ ። ለምን አንጨነቅም ሁሉም እኮ የሀገር ጉዳይ ነው ! ብሎ ገብረየስ በስጨት ሲል ተሰማ በመሃል ገብቶ ‹‹ ምን ማለትህ ነው? እያለቀ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ነው። ›› ሲል ዘውዴን ለመገሰፅ ሞከረ።
‹‹እናንተ! እናንተም አለቅን ትላላችሁ? እኔ እና እንደኔ አይነቱ ይለቅ እንጂ እናንተማ በደህና ጊዜ አጭዳችሁ ጎተራችሁን ሞልታችኋል። ኪሳችሁ አያጣም። ›› ሲል ዘውዴ መለሰ። በዚህ ጊዜ ገብረየስ ተበሳጨ ‹‹ምን ማለት ነው? ወዶ አይደለም ሰውየው ‹ ባልፈጨሁ በንኖብኝ ባላደረግኩት ተመካኘብኝ› ያለው፤ ምንም ባልፈፀምኩት ነገር ትወቅሰኛለህ። በግልፅ ስትዘርፍ ኖረሃል ለምን አትልም? ብዘርፍማ ኖሮ ቤት ተከራይቼ አልኖርም ነበር። ህንፃ ገንብቼ የፎቅ አከራይ እሆን ነበር። አሁንም የምኖረው ደልቶኝ ሳይሆን ብዙ ነገር ጎድሎብኝ ለፍቼ ሰርቼ ነው። ሌላው ቀርቶ ሰላም በሆነና ጎተራዬ በነጠፈ፤ ›› እያለ ዘውዴ እርሱና ተሰማ ላይ የሰጠው አስተያየት ትክክል አለመሆኑን ቃላቶቹን እየደጋገመ ተናገረ።ከፊቱ አንዴ ጎንበስ ሌላጊዜ ደግሞ ቀና እያለ።
ዘውዴ፤ ገብረየስ መበሳጨቱን አይቶ ወደኋላ አላለም፤ የእርሱም ስሜት ቀላል አልነበረም፤ ግለቱን ጨምሯል፤ ‹‹ ነገሩ ‹ሳይርበው የሚበላ ርሃብን አያውቅም› ይባል አይደል? ችግር የማያውቅ ሰው ለተቸገረ አያዝንም፤ ርቧችሁ ስለማታውቁ ለተራበ አታዝኑም። ደግነቱ እኛም አይከፋንም። ጥጋባችሁን በሙሉ ችለን ተሸክመናችሁ እንኖራለን፤›› ሲል ተሰማ ደሙ ፈላ እየተንቀጠቀጠ መናገር ጀመረ።
ተሰማ ‹‹ እኛ ላይ የሚያስቆጣህ ምንድን ነው? የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ የትህነግ ታጣቂዎች ተበትነዋል፤ የታደሉት እጅ ሰጥተዋል። ሌሎች ደግሞ በተሳሳተ መረጃ ተደናግረው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል? ሲባል ከፋህ እንዴ? መቼም እስከ አሁን በተከታታይ ከአንተ ጋር ስናወራ ያለኝ መረጃ የጦርነት ዘመንን ማየት እንደሰለቸህ፤ ሕዝቡ ከጦርነት አረፍ የሚልበትን ጊዜ እንደናፈቅክ ስትገልፅ ነበር። አሁን ደግሞ ሰላም እንዲሰፍን ሊነጋገሩ ነው፤ ይሔንን አንተም ስትፈልገው የኖርከው ጉዳይ ነው። አሁን ምን አዲስ ነገር መጣ? ›› ብሎ ዘውዴ ላይ ሲያፈጥ ዘውዴ መታፈሪያ ተሸማቀቀ። እነርሱ የሚያስቡት እና እርሱ እያሰበ የሚናገርበት ርዕሰ ጉዳይ ራሱ የተለያየ መሆኑን ተረዳ።
ዘውዴ ቀጠል አደረገና ላለመረታት ‹‹በእርግጥ እኔ እየተብሰከሰኩ ያለሁት በኑሮ ውድነት ነው። እኛ ስለምንጎርሰው እየተጨነቅን መጠጥ ቤቱ ‹በአዲስ መልክ ምግብና መጠጥ ጀምረናል› ማለቱ አናዶኛል። እንኳን አዲስ የመጣ መጠጥና በተለየ መልኩ የተሰራ ምግብ ገዝቶ መብላት ቀርቶ መንገድ ላይ የሚሸጥ ሙዝ ገዝቶ መብላት አቅቶናል። በሌላ በኩል ጦርነትና የኑሮ ውድነት ደግሞ ይገናኛል። ጦርነት አውዳሚ ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚው ላይ ችግር ከፈጠሩ እና የዋጋ ግሽበት እንዲመጣ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ጦርነት መኖሩ ነው።
ከጦርነት ውስጥ ዋናው መውጫ መንገድ ሰላም መሆኑ አይካድም፣ አሁን ደግሞ ጦርነቱ ሲያበቃ ሕዝብን ካማረሩ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የኑሮ ውድነት በአስቸኳይ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል። የኑሮ ውድነት ጉዳይ መፍትሔ ካልተበጀለት እና በጊዜ እርሱ ላይ ማተኮር ካልተቻለ፤ የሰሜኑ ጦርነት ቢያበቃም የመሃል አገሩ ጥያቄ፣ የኑሮ ውድነት ይሻሻል፤ መልካም አስተዳደር ይስፈን፣ ሙስና… የሚለው ያሰጋል።
አፍነዋለሁ ቢባል ደግሞ የሚቻል አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ በነፃነቱና በእኩልነቱ ላይ ድርድር አያውቅም፤ አስተዋይ፣ ጨዋ፣ ታጋሽ፣ አገሩን ከልቡ የሚያፈቅርና ኩሩ ሕዝብ ነው። ነገር ግን የኑሮ ውድነቱ በዚሁ ከቀጠለ፤ ማጉረምረሙ አይቀርም፤ ገፍቶ ከወጣ ጥያቄ አታንሳ ተብሎ ከታፈነ አላስፈላጊ መስዋዕትነት እስከመክፈል እንደሚደርስ ከገብረየስ ዘመዶች መማር ይገባል። ›› ብሎ ፈገግ በማለት ውጥረቱን አረገበው።
ገብረየስ ‹‹ ዛሬ በደንብ ግራ ተጋብተህ ግራ እያጋባኸን ነው። ›› ብሎ በረዥሙ ተነፈሰ። ቀጠለና ‹‹ የኑሮ ውድነት፣ ጦርነት፣ ዕልቂት፣ መፈናቀልና ውድመት የሚያሳቅቀን እኛንም ጭምር ነው። ግለሰብ ባለሥልጣናት በሥልጣን ላይ እየባለጉ በሕዝብ ስም ሊነግዱ ይችላሉ። ይህ ቢያማርርህ ቢያሳዝንህ ተገቢ ነው። ነገር ግን እኛን ከእነርሱ ጋር ጨፍልቀህ እንደዘራፊ መግለፅህ ደስ አያሰኝም። አንዳንዴ ብትበሳጭም ንግግርህ ምን ያህል የሰዎች ስሜትን እንደሚጎዳ መገንዘብ አለብህ። በሌላ በኩል ከትህነግ ነን ባዮቹ ጋር የትግራይ ተወላጆች ተሰልፈው የተዋጉት አንዳንዶቹ በስርዓቱ ተጠቃሚ ስለነበሩ፤ አንዳንዶቹ ተታለው ሲሆን ብዙዎቹ ግን ተገደው ነው። ዘመዶችህ ላልከው ደግሞ እነርሱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ዘመዶች ናቸው›› አለው።
ዘውዴ ገብረየስ ማምረሩ ገባው። የበለጠ ማብራራት ፈለገና ‹‹ በአንድ መልኩ ጦርነት አለ ብሎ መሰለፍ የሚዋጉትን ማወቅና ማሸነፍ በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን የሕዝብ ምሬትና ለቅሶ ሲጥል እንጂ ሲቆርጥ አይታይም፤ የሚገዘግዘው ሳይታይ በድብቅ ነው። መጨረሻ ላይ ቆርጦ ሲጥል ለሁላችንም አደጋ አለው። ሳይርቅ በቅርብ ሳይደርቅ በርጥብ ብዬ ነው። አንድ ችግር ከማደጉ በፊት ወይም መጥፎ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በቅርብ ማስተካከል ካልተቻለ አደጋው የከፋ ይሆናል። ለኔ የታየኝ ለእናንተ አልታያችሁም። የተበሳጨሁት ለዛ ነው። ሰው የሚያየው መቼም የቸገረውን ነው። ያው በገቢ ከእኔ መሻላችሁ የሚታይ ሃቅ በመሆኑ እንደኔ የኑሮ መወደድ ላያሳስባችሁ ይችላል። ›› ብሎ ፈገግ አለ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ ያልዘሩት አይበቅልም፤ ማንኛውም ነገር የአንድ የተፈፀመ ነገር ውጤት ነው። ከጣርክ ከለፋህ እንደኛ ብቻ ሳይሆን ከእኛም በላይ ገቢ ማግኘትህ አይቀርም። የራስህን ድክመትና ስህተት ሁሉንም ነገር ወደ መንግስት እና ወዳለውና ወደነበረው ስርዓት ካላከከው ችግሩ የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የአንተም ጭምር ነው። ችግርን ወደ ውስጥም ማየት ጥሩ ነው። ሰው ከስህተቱ ይማራል አይደል የሚባለው፤ ደግሞ አንድ አባባል አለ ብልጥ ልጅ ከሰው ሞኝ ደግሞ ከራሱ ይማራል። አሁን ሁላችንም ከራሳችን የምንማረው ብዙ ነገር አለ ። ስለነርሱ ማሰብህን ትተህ ስለራስህና ስለቤተሰብህ ከጀርባህ ስላሉት ዘመዶችህ አስበህ ብትንቀሳቀስ አሁንም ቢሆን ገቢህ ያድጋል ብዬ አምናለሁ። ችግሩ አንተ እኔ ዘውዴ ስለሆንክ የፈለገውን ያህል ብጥርም ምንም ነገር ማግኘት አልችልም ብለህ ራስህ ላይ ቆልፈሃል። ›› ብሎ ለመገሰፅ ሞከረ።
ዘውዴ ከት ብሎ ሳቀ፤ ቀጠለና ‹‹ ብልህን ሰው ለማሞኘት መሞከር ትዝብት ማትረፍ ነው። በእውነት እናንተ ከኔ የተሻለ ገቢ ያገኛችሁት ከእኔ በላይ ሰርታችሁ ነው? ይሔ በእውነት ያስቃል። እኔንስ ተዉኝ! በምግብና በነዳጅ ዋጋ ላይ የታየው ከፍተኛ ጭማሪ፣ እንደእናንተ አይነት አንዳንዱ ካልሆነ በቀር በመላው ኢትዮጵያውያን ኑሮ ላይ ያደረሰውን መቃወስ ለመረዳት መንገደኛ ጠይቆ ለማወቅ አያዳግትም፤ ወጣ ብሎ ማንንም መንገደኛን መጠየቅ ብቻ በቂ ነው። ትክክል ነው! ሰላም እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። ነገር ግን ሰላም ብቻውን ዳቦ አይሆንም። በአሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚስተዋለው ችግር በደንብ ታስቦበት ካልተሔደ አደጋው ከሰላም መደፍረስ በላይ መሆኑን አትዘንጉ ለማለት ነው። ›› የተሰማውን ሀሳበ ሰነዘረ ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ ሳይቸግር ጤፍ ብድር እንደሚባለው በዚህ ሰዓት የሚያስፈልግ ነገር ቢሆንም እንኳን ሁሉንም ነገር አጥብቆ መሻት አይጠቅምም። ለጊዜው የሚያስፈልገን የሰላም ጉዳይ ነው። ሌላው ከዛ በኋላ ይደረስበታል። ሰላም ከሌላ ዳቦ ቢሞላ ማን የት ቦታ ሆኖ ሊበላው ብለህ ፤ኢኮኖሚውም ሆነ ሌላ ሌላው ሁሉ በቀደም ተከተል ይደረስበታል። ይህን አጠናቀን ፊታችንን ወደቀጣዩ ችግራችን ›› ሲል ዘውዴ ከተሰማ ከተል አድርጎ ‹‹ አንድ ችግር ከመድረሱ በፊት መጠንቀቅ፤ ከደረሰም ሳይባባስ ቀድሞ መከላከል እንጂ መዘናጋት ተገቢ አይመስለኝም። የምግብ ምርቶች፣ የግንባታ ቁሳቁሶች፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎችም አቅርቦቶች በተወሰኑ የተደራጁ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። መንግሥት ገበያውን ለመቆጣጠር ዋጋ መወሰን ባይኖርበትም፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን መቆጣጠርና በየዘርፉ የትርፍ ህዳግ ምጣኔ ማውጣት አለበት። ምክንያቱም በእያንዳንዱ ጉዳያችን እጁን የሚሰድ ነጋዴ አለ።
አየር አመጣሽ ትርፍ ብለው በዚህ ሰሞን እንኳነ አታይመ ከውጪ በሚገቡ የቅንጦት ሸቀጦች ላይ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገባ እገዳ ተደረገ ሲባ ምድረ ነጋዴ በመደርደሪያው የሞላውን በየመጋዘኑ ያከማቸውን ሁሉ ከእጥፍ በላይ አናረው እኮ። ስለዚህ ነጋዴው ላይ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ይገባል። ይህ አንደኛው መፍትሔ መሆኑን መስሪያ ቤት ውስጥ አንድ የኢኮኖሚክስ ምሩቅ የተናገረው ነው። በእርግጥ ሌሎችም የተለያዩ መፍትሔዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ድንገት እየተነሱ መደብር ማሸግ፣ መጋዘን ውስጥ ያሉ ሕጋዊ ዕቃዎችን እንደ ሕገወጥ ክምችት መውረስና በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ዕርምጃዎችን መውሰድ አያዋጣም። ስለዚህ አስቀድሞ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ ተመስርቶ ለዚህ የዋጋ ግሽበት መላ ማዘጋጀት ዛሬ ነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
አንዳችም የገቢ ጭማሪ ሳይኖራቸው እንደ ሰደድ እሳት የሚንቀለቀለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። የምግብ፣ የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የልጆች ትምህርትና ልብስ፣ እንዲሁም ሌሎች ተደራራቢ ወጪዎች ኑሮን እያከፉት ነው። የኢኮኖሚ ጠቢባንም ሆኑ የሌሎች ባለሙያዎች ዕገዛ ታክሎበት፣ ኢኮኖሚው ከገባበት ማጥ ውስጥ መውጣት ካልቻለ መጪው ጊዜ ከባድ ነው። ›› ብሎ ራሱን ነቀነቀ ።
ተሰማ በበኩሉ ‹‹ ትክክል ነው፤ ሳይቃጠል በቅጠል ማለትህን ማንም አይቃወምም፤ ነገር ግን የማያውቁትን ነገር አውቃለሁ ማለት ያስገምታል። መቸኮልም አይገባም። እኛ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች አይደለንም። ስለኑሮ ውድነትም ሆነ ስለዋጋ ግሽበት እንዲሁም ስለኢኮኖሚው መቃወስ ምንም ማለት አንችልም። ምክንያቱም ሳይማሩ መተርጎም ዕባጭን ሳይበጡ እንደማከም ነው። ሃሳብ ለመስጠትም ትንሽም ቢሆን ማወቅን ይጠይቃል። ማማረርም፤ መቸኮልም አይገባም። ›› በማለት ምላሽ ሰጠ።
‹‹አሁን እንኳን ሰው ቤተሰቡን አጥቶ ያለዘር እየቀረ ባለበት በዚህ ጊዜ ስለኑሮ ውድነት ለመነጋገር ሌላ ሞራል ያስፈልጋል። በኑሮ ውድነት ተጎዳሁ ማለት ከባዱን ጉዳቱ ካለማየት የሚመነጭ ነው። ›› በማለት ገብረየስ ሲናገር ዘውዴ ተናደደ። ‹‹ ምንድን ነው? ‹በጦርነቱ የተጎዳሁት እኔ ብቻ ነኝ› አልክ እኮ! በጦርነቱ የተጎዳው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ሰላሙም ሆነ የኢኮኖሚው ጉዳይ በአገር ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ተመሳሳይ ነው። በሰላም መደፍረስ ምክንያት ከሚደርሰው ዕልቂትና ውድመት በተጨማሪ፣ ሳይቀጠል በቅጠል ተብሎ ተከታታይነት ያላቸው ፈጣን እርምጃዎች ካልተወሰዱና ዘላቂ መፍትሔ ካልመጣ ወደፊትም ሰላም ይኖራል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። እኔ የኑሮ ውድነት የጠጣሁበትን ሂሳብ መክፈል እንዳልችል የገደበኝ በመሆኑ ክፈሉልኝ›› ብሎ ሲወጣ፤ ተሰማ እየሳቀ ‹‹ በቀን በቀን እየጠጣህ የሚልሰው ዳቦ እንዳጣ ድሃ ታለቃቅሳለህ። ›› ብሎ የጠጡበትን ሂሳብ ከፍሎ እጁን ኪሱ ከቶ ወደ ውጪ ወጣ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2015