ነዋሪነቷ በብራዚል የሆነ ቫሌሪያ የተሰኘች እናት በፍርድ ቤት ክስ ትመሰርታለች። ክሷም ለጥቂት ጊዜ በፍቅር አብሯት ከቆየው ሰው መውለዷን ተከትሎ የአባትነት ድርሻውን እንዲወጣ ማድረግን የሚመለከት ነው። ፍርድ ቤትም «አባት ነው» በሚል የተጠረጠረውን ፈርናንዶ የተባለ ግለሰብ ወላጅነት ለማጣራት የዲኤንኤ ምርመራ እንዲያደርግ ያዛል(ለሳይንስ ምስጋና ይግባውና)።
በትዕዛዙ መሰረት የተደረገው ምርመራ ውጤትም ህጻኗ የፈርናንዶ ልጅ ስለመሆኗ 99 ነጥብ 9 በመቶ ያረጋገጠ ሆነ። ይህንን ተከትሎም አባት ይግባኝ አቀረበ፤ ለፍርድ ቤቱ። ይኸውም እርሱን የመሰለ መንታ ወንድም ያለው በመሆኑ ህጻኗ የእርሱ ልትሆን ትችላለች የሚል ነው። ፍርድ ቤትም ፋብሪሲዮ የተባለው ሌላኛው መንታም ምርመራ እንዲያደርግ ይወስናል። ይሄኛው ምርመራ ውጤትም የልጅቷ አባት ስለመሆኑ የሚያሳይ ሆነ።
መንትዮች አንድም የተለያየ ጾታ እና መልክ ይዘው አሊያም ከአንድ ቅርንጫፍ እንደተቀጠፉ ሁሉ ምናቸውም ሳይለያይ ተመሳስለው ሊወለዱ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ምስስሎሽ ደግሞ ቤተሰብን ጨምሮ በመንትዮቹ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሊያደናግር ይችላል። ከወደ ብራዚል እንዳገኘው ጠቅሶ ኦዲቲ ሴንትራል ባሰራጨው ዘገባውም ላይ፤ በህክምናም ጭምር ሊለይ ያልቻለ ምስስሎሽ ማጋጠሙን ነው ያስነበበው። የሚያስገርመው ደግሞ ከሳይንሳዊው ማረጋገጫ ባሻገር የህጻኗን አባት ማንነት ከሁለቱ ደፍሮ ይፋ ያደረገ አለመኖሩ ነው።
በዚህ የተነሳም ፍርድ ቤቱ ከውሳኔ ሳይደርስ ለሶስት ዓመታት (እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ) ቆይቶ በቅርቡ አስደናቂ ፍርድ ሰጥቷል። ውሳኔውም ሁለቱም አባቶች በመሆናቸው ከደመወዛቸው 30 በመቶ የሚሆነውን ለልጃቸው ተቆራጭ እንዲያደርጉ የሚያዝ ነው። ጉዳዩን የያዙት ዳኛ ፊሊፕ ሉዊስ ፔሩካ እንደገለጹት ከሆነም መንትዮቹ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ፍቅር ጀምረዋል። የጀመሩትን ከግብ አለማድረሳቸው እንዳለ ሆኖም አንዳቸው ከሌላኛቸው የፍቅር ጓደኞች ጋር በድብቅ ይገናኙ ነበር። ይህም ሁለቱም ላይ ለመወሰን እንዳበቃቸው ይጠቁማሉ።
ዳኛው ጉዳዩን ሲያብራሩም «የህጻኗ አባት ከ ሁለት አንዳቸው ናቸው። ነገር ግን ተግባራቸው በሃገሪቷ ህግ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው። በእነርሱ ምክንያትም ሌላው ተጎጂ መሆን የለበትም፤ ይህ የክብር ጉዳይም ነው» ብለዋል። ለምርመራው የወጣውን 15 ሺህ 500 ዶላርም መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
ግራ አጋቢውን ክስ የመሰረተችው ቭላሪያ፤ ከመንትዮቹ አንዱን በእርሷ አባባል ፈርናንዶን (ይህንን ስም ስለነገራት)የተዋወቀችው በአንድ ድግስ መሆኑን ታስታውሳለች። በወቅቱ ይዞት የነበረው ቢጫ ቀለም ያለው ሞተር ሳይክል የፋብሪሲዮ መሆኑንም ነበር የነገራት። ከዚህ ባሻገር የበዛ ምስስሎሻቸው በፍቅር ግንኙነት ከየትኛው ጋር እንደነበረች የምታውቅበት መንገድ አልነበረም።
ስለ ጉዳዩ በሰጠችው አስተያየትም «የሚያሳዝን ነገር ነው፤ ይህንን ማድረግ አልነበረባቸውም። እውነቱን ያውቃሉ፤ ነገር ግን ከኃላፊነት ለመሸሽ ሲሉ ነው እንዲህ የሚያደርጉት» ብላለች።
ዳኛው ፊሊፕ ሉዊስ ፔሩካ የቭላሪያ ልጅ ባለመንታ አባት በመሆኗ፤ አባቶቿ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ የሚል ውሳኔያቸውን ያስተላለፉ ቢሆንም፤ የመንትዮቹ ጠበቃ ግን አሁንም ተቃውሞ በማቅረብ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
ብ ርሃን ፈይሳ